Alemayehu Gemeda

መንግሥት ከሕወሓት ይልቅ ለአገሪቱ ሥጋት የሆኑ ሌሎች ችግሮች አሉብኝ አለ

ላለፉት ስምንት ወራት በትግራይ ክልል ከሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ጋር ሲደረግ የነበረውን ጦርነት በመተው ከክልሉ መውጣቱ ሲዋጋው ከነበረው ሕወሓት ይልቅ የአገሪቱ ሥጋት የሆኑ ሌሎች ችግሮች አሉና በእነሱ ለማተኮር ነው ሲል መንግሥት አስታወቀ፡፡ ሰኔ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለጋዘጠኞች መግለጫ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) እና የመከላከያ ሠራዊት፣ የሠራዊት ግንባታ አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ አሁን ኢትዮጵያ ሕወሓት ባለበት አቅም የብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት ስላልሆነና ለሌሎች ሥጋቶች ዝግጅት ለማድረግ እንዲቻል በማለም ሠራዊቱ ከትግራይ እንዲወጣ ተደርጓል ብለዋል፡፡ በተለይ መቐለ አስቀድሞ የነበራትን የስህበት ማዕከልነት አሁን ላይ አጥታለችና መቐለ መቆየትም ሆነ መልቀቅ ከወታደራዊ ጠቀሜታው አንፃር ሌሎች አካባቢዎችን ከመያዝ የተለየ አይደለም ያሉት ሌተናል ጄኔራል ባጫ፣ አስፈላጊ ከሆነ በሦስት ሳምንታት ወይም ከዚያ ባነሰ ጊዜ ተመልሰን መቐለ አንገባለን ብለዋል፡፡ ይሁንና፣ ጥፋቱና የሚወሰደው ዕርምጃ ከመጀመርያው የበለጠ ይሆናልም ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ጄኔራሉ በሰጡት ማብራሪያ የሚፈለጉት ጄኔራሎች ከ17፣ የሲቪል አመራሮች ደግ ከ12 አይበልጡም ያሉ ሲሆን፣ ለእነዚህ ደግሞ የተሰማራው ኃይል ከ50 ሺሕ በላይ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ስለዚህም ይኼ ወታደሩን ለማስወጣት የተላለፈው ፖለቲካዊ ውሳኔ ከወታደራዊ ትርፍና ኪሳራ አንፃር ዋጋው ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሥጋት እንዳይሆን ተደርጓል የተባው ሕወሓትም ከትግራይ እንደይወጣ ይደረጋል ያሉት ጄኔራሉ፣ የሠራዊቱ ትኩረት አሁን ወደ ሌላ ሥጋቶች እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ሕወሓት ኢትዮጵያን የሚያሠጋ ጉዳት አያደርስም፤›› በማለትም ተናግረዋል፡፡ አምባሳደር ሬድዋን በበኩለቸው ጦርነቱ ለስምንት ወራት ሲካሄድ 100 ቢሊዮን ብር ገደማ ወጪ እንደተደረገ በመግለጽ፣ ይኼም አገራዊ የኢኮኖሚ አቅማችን ላይ ጉዳት አድርሷል ብለዋል፡፡…