23ኛው የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና ዛሬ ምሽት በስፔን ቫሌንሺያ ይካሄዳል

Team Ethiopia arrival in Valencia

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ቫሌንሲያ ሲደርስ የተደረገለት አቀባበል (Photo by Organizers)

በአለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማሕበር የበላይ ተቆጣጣሪነት እና በስፔኗ ምስራቃዊ የባሕር ዳርቻ ከተማ ቫሌንሲያ አስተናጋጅነት ዘንድሮ ለ23ኛ ግዜ የሚካሄደው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና የተለመደውን የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት አትሌቶች ብርቱ ፉክክር የምናይበት እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡

23ኛው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ዛሬ ምሽት 1፡05 ላይ በሴቶቹ ፉክክር ሲጀምር የኬንያ፣ ኢትዮጵያ እና ዜግነታቸውን ቀይረው ለተለያዩ ሀገራት የሚሮጡ ትውልደ ምስራቅ አፍሪካውያን አትሌቶች ትንቅንቅ የትኩረት ማዕከል እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ የርቀቱ የዓለም ሪኮርድ (1:04:51) ባለቤት የሆነችው ኬንያዊቷ ጆሴሊኔ ጄፕኮስጋይ፣ የቡድን አጋሮቿ ሩት ቼፕንጌቲች እና ፓውሊኔ ካቬኬ፣ ኢትዮጵያዊቷ ነፃነት ጉደታ እንዲሁም ባሕሬይንን ወክላ የምትወዳደረው ትውልደ ኬንያዊቷ ኢዩንስ ቼቢቺ ካላቸው የግል እና የዓመቱ ምርጥ ሰዓት አኳያ የቅድመ ውድድር የሜዳልያ አሸናፊነት ግምት የተሰጣቸው አትሌቶች ናቸው፡፡

መጀመሪያ ላይ ጠንካራ አምስት አትሌቶችን አስመዝግባ የነበረችው ኬንያ የዘንድሮው የራስ አል ካሂማህ ግማሽ ማራቶንን የራሷ ምርጥ የሆነ 1:04:52 ሰዓት በማስመዝገብ ጭምር ያሸነፈችው ፋንሲ ቼሙታይ እና የ22ኛው የዓለም ግማሽ ማራቶን የነሐስ ሜዳልያ አሸናፊዋ ማሪ ዋሴራን ባለቀ ሰዓት ያጣች ሲሆን ይህን ተከትሎም በተጠባባቂነት ይዛቸው የነበሩትን አትሌቶች በወቅቱ ለማስመዝገብ ባለመቻሏ በሶስት አትሌቶች ብቻ ለመቅረብ ተገዳለች፡፡

በቫሌንሲያው ፉክክር ላይ በተከታታይ ለሶስተኛ ግዜ ሀገሯን ወክላ የምትቀርበው ነፃነት ጉደታ እንዲሁም ብዙም እውቅና የሌላቸው መሰረት በለጠ፣ በቀለች ጉደታ፣ ዝናሽ መኮንን እና ዘይነባ ይመር በኢትዮጵያ መለያ የሚሰለፉ አትሌቶች ናቸው፡፡ ነፃነት በ2014 ኮፐንሀገን ዴንማርክ ላይ ስድስተኛ እንዲሁም ከሁለት ዓመት በፊት በዌልስ ካርዲፍ በተካሄደው ውድድር ላይ አራተኛ ሆና መጠናቀቅ የቻለች ሲሆን ዘንድሮ የሜዳልያ ደረጃ ውስጥ ይገባሉ ተብለው ከሚጠበቁት ተወዳዳሪዎች መካከል አንዷ ነች፡፡ በውድድሩ የ23 ዓመት ታሪክ በሴቶቹ የተናጠል ፉክክር በ2002 ዓ.ም. በብርሀኔ አደሬ እንዲሁም በ2012 በመሰረት ሀይሉ አማካይነት ሁለት ግዜ ብቻ የወርቅ ሜዳልያ ድልን ማግኘት የቻለችው ኢትዮጵያ በቡድን ውጤቱም ካለፉት ስምንት ውድድሮች በስድስቱ ኬንያን ተከትላ በሁለተኛነት ነው ያጠናቀቀችው፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ቫሌንሲያ ሲደርስ የተደረገለት አቀባበል (Photo by Organizers)

ሀይሌ ገብረስላሴ በ2001 ዓ.ም. ካስመዘገበው ብቸኛ የወርቅ ሜዳልያ ውጪ የተናጠል ድልን አይታ የማታውቀው ኢትዮጵያ በወንዶቹ ፉክክር ያለፉትን ስምንት ውድድሮችም የኤርትራ እና ኬንያውያንን የወርቅ ሜዳልያ ድል ፍርርቅ ከመመልከት የዘለለ ተሳትፎ አልነበራትም፡፡ በዘንድሮው የኢትዮጵያ ቡድን ውስጥ ከተካተቱት አትሌቶች ጀማል ይመር፣ ልዑል ገብረስላሴ እና ጌታነህ ሞላ ይህን ታሪክ የመቀየር አቅሙም ሆነ ልምዱ እንዳላቸው የሚታመን ሲሆን በንፅፅር ብዙም ዕውቅና የሌላቸው በተስፋ ጌታሁን እና ጂክሳ ቶሎሳም ያልተጠበቀ ውጤትን የማስመዝገብ ዕድሉ ይኖራቸዋል፡፡

የግማሽ ማራቶን ርቀቱን ከአንድ ሰዓት በታች መጨረስ በቻሉ አምስት አትሌቶች የምትወከለው ኬንያ የሻምፒዮናው ሪኮርድ ባለቤት እና ያለፉት ሁለት ውድድሮች የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ በሆነው ጂኦፍሬይ ካምዎሮር በሚመራው ቡድኗ ውድድሩን በበላይነት የማጠናቀቅ ዕድሏ ሰፊ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ኡጋንዳ፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና ባሕሬይን አትሌቶችም በቀላሉ እጃቸውን የሚሰጡ ይሆናሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡

በዚህ ውድድር ላይ አንድ ሀገር አምስት አትሌቶችን ማስገባት ቢችልም ለቡድን ውጤት ነጥብ ማስመዝገብ የሚችሉት ሶስቱ ብቻ ይሆናሉ፡፡ 23ኛው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማሕበር ዩቲዮብ ቻናል (https://www.youtube.com/channel/UCQk7fWv15ChjMJLCRVmtApw) እና የፌስቡክ ፔጅ (https://www.facebook.com/WorldAthleticsClub/) እንዲሁም በተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በቀጥታ የስርጭት ሽፋን ስለሚያገኝ የአትሌቲክስ ስፖርት አፍቃሪያን ዛሬ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ አንድ ሰዓት ጀምረው ውድድሩን በመከታተል መዝናናት ይችላሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.