ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የልብ ቀዶ ህክምና መስጠት ሊጀምር ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በቀጣይ አራት ወራት ውስጥ የልብ ቀዶ ጥገና ህክምና መስጠት ሊጀምር ነው።
የህክምና አገልግሎቱ በሆስፒታሉ መጀመር በሀገሪቱ በአመት ከ150 እስከ 200 ብቻ ይደረግ የነበረውን የቀዶ ህክምና ከእጥፍ በላይ ያሳድገዋል ተብሏል።
አዲሱ አገልግሎት በልብ ማዕከል በአመት ለ13 ሳምንታት ብቻ ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት ወደ 52 ሳምንታትም ያሻግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከህዝብ በተሰበሰበ መዋጮና “ችልድረን ሰርቲ ፈንድ” በተባለ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት አስተባባሪነት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ የተገነባው የልብ ህክምና ማዕከል በአይነቱ በሃገሪቱ ብቸኛው ነው።
ይሁንና የተሟላ የህክምና መሳሪያዎች እና በቂ ቁጥር ያላቸው ባለሙያዎች በማዕከሉ የሉም።
በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የልብ ህክምና ቡድን መሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንደሚሉት፥ ማዕከሉ በአመት ለ13 ሳምንታት ብቻ አገልግሎት ይሰጣል።
የተሟላ የልብ ቀዶ ጥገና ህክምናውም በበጎ ፍቃድ በመጡ የውጭ ሀገር ዜጎች ነው እየተሰጠ የሚገኘው።
ይህም በሀገሪቱ ካለው አጠቃላይ ስፋት አንጻር የሆስፒታሉ አገልግሎት በእጅጉ መስፋት እንዳለበት አመላካች መሆኑን ነው ተባባሪ ፕሮፌሰሩ የገለጹት።
በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ ከ6 ሺህ በላይ የልብ ህሙማን የቀዶ ጥገና ህክምና ወረፋ እየተጠባበቁ ነው ያሉት ቡድን መሪው፥ በሆስፒታሉ በሳምንት ሰባት ቀናት በቀን ለ24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጥ የልብ ቀዶ ጥገና ህክምና መከፈቱ ችግሩን ከመፍታቱ አንጻር የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
አትዮጵያ በቀጣይ አምስት አመታት ውስጥ እገነባዋለሁ ባለችው የህክምና መንደር (ሜዲካል ሲቲ) ውስጥ የሚካተተው ግዙፍ የልብ ህክምና ማዕከል ችግሩን በበቂ ሁኔታ መፍታት የሚያስችል እንደሚሆን ይጠበቃል።
አስተያየታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ የሰጡ የዘርፉ ምሁራን ሆስፒታሉ በቀጣይ ከሚጀመረው የቀዶ ህክምና ባሻገር ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት የልብ ቀዶ ህክምና ማዕከል ሊገነባ ይገባል ብለዋል።
ምንጭ:- ፋና
first of all thanks for all to be start such like activity. but it must be real in its application.
really these tpye of planning take our country forward. Keep it up!