ግንቦት 7ን ድግፈዋል በሚል የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች ክስ ተመሰረተባቸው

arbegnoch-ginbot7

Ginbot-7

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለመናድ የሚንቀሳቀሰውን አሸባሪው ግንቦት ሰባት ድርጅትን ድግፈዋል በሚል የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች ዛሬ ክስ ተመሰረተባቸው።

ተከሳሾቹ ይላቅ አቸነፍ እና አዋጁ አቡሃይ የተሰኙ በሰሜን ጎንደር ዞን የላይ አርማጭሆ ነዋሪዎች ናቸው።

የፌደራል አቃቤ ህግ የ52 እና የ66 አመት እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ግለሰቦች በጸረ ሽብር አዋጁ አንቀጽ 7 (1) ስር የተደነገገውን ተላልፈዋል በሚል ነው የከሰሳቸው።

ተከሳሾቹ የኢትዮጵያን መንግስት በትጥቅ ትግል በሃይል የመለወጥ የፖለቲካ አላማ በመያዝ የሀገሪቱን ህገመንግስታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተቋማት ለመናድና ለማፈራረስ በሚንቀሳቀሰውና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ በሚል የተፈረጀውን ራሱን አርበኞች ግንቦት 7 ብሎ በሚጠራው የሽብር ድርጅት ለመሳተፍ ተንቀሳቅሰዋል በሚል ነው ሊከሰሱ የቻሉት።

1ኛው ተከሳሽ ይላቅ አቸነፍ በህዳር 2007 የዚሁ ሽብር ድርጅት አመራር ከሆነው ፍስሃ ከተባለ ግለሰብ ጋር የሽብር ቡድኑ አባል ሆኖ አብሮ መስራት እንደሚፈልግ የገለጹለት የስልክ የሃሳብ ልውውጥ ማድረጋቸው በክሱ ሰፍሯል።

ተከሳሹ በታህሳስ 2007 በ2ኛው ተከሳሽ ቤት ሆኖ መብታችን እና ጥቅማችንን ተዋግተን ማስከበር ይኖርብናል፤ ይህንን ለማሳካት ደግሞ የግድ የጦር መሳሪያ ያስፈልገናል፤ ይህን የጦር መሳሪያ ደግሞ የሽብር ቡድኑ የአርበኞች ግንባር ይረዳናል በማለት ሁለተኛውን ተከሳሽ አግባብቶት ሚያዚያ 2007 ከሽብር ቡድኑ አመራር ጋር እንዳገናኘው በክስ መዝገቡ ተጠቅሷል።

2ኛው ተከሳሽ በዚህ መልኩ በሽብር ቡድኑ አባል መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ኤርትራ ከሚገኙ የአሸባሪው አርበኞች ግንቦት 7 አመራሮች የአመጽ ተልዕኮ መቀበሉም በክሱ ተመልክቷል።

ሚያዚያ 27፣ 2007 ከጠዋቱ 3 ስዓት እንየው ከተባለው የሽብር ድርጅቱ አመራር ጋር በስልክ ተገናኝቶ “ለውጊያ የምትጠቀሙበት ጥይት ተልኮልሃል፤ ሺርቦ የተባለ አካባቢ መጥተህ ውሰድ” በማለት ያስተላለፈለት መልዕክትም በክሱ ተዘርዝሯል።

ተከሳሹ አንድ ሞተር ሳይክል ተከራይቶ ጓንጓ ወንዝ ተብሎ በሚጠራው ወንዝ የተላከለትን ጥይት ተቀብሎ ወደ መኖሪያ ቤቱ መውሰዱም በመዝገቡ ሰፍሯል። በርከት ያሉ ጥይቶችም በብርበራ ከቤቱ ተይዟል ነው የሚለው ክሱ።

በመሆኑም አቃቤ ህግ በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ በማንኛውም መልኩ መሳተፍ ወንጀል ከሷቸዋል።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 14ኛ የወንጀል ችሎት የክስ መዝገቡን ለመመልከት ለነገ ጥቅምት 3 ፣ 2008 ቀጠሮ ይዟል።

Source: FBC

1 thought on “ግንቦት 7ን ድግፈዋል በሚል የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች ክስ ተመሰረተባቸው

Leave a Reply

Your email address will not be published.