ግለ-ትዝብት – ጠላን ማን ፈጠረው?

Ethiopian Traditional Drink - Tella

ጠላን ማን ፈጠረው?
ከይርጋለም ብርሃኑ
Ethiopian Traditional Drink - Tella 2

ብዙውን ጊዜ በአለሁበት አካባቢ በኢትዮጵያውያን ድግስ ላይ ጠላ ከጓደኞቹ ከውስኪ እና ከቢራ ጋር ተሰልፎ ሳየት ይደንቀኛል:: ለመሆኑ “ጠላ” ማን ፈጠረው? የሚል ጥያቄ በአምሮዬ ይመላለሳል::

ድሮ! ድሮ! ዘመኑ በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም ጠላ በኢትዮጵያ ምድር የተፈጠረ ይመስለኛል። ቀማሚዎቹም ኢትዮጵያውያን ይመስሉኛል። ለዚሁ ማረጋገጫ ደግሞ በዚህ ዘመን ላይ የጠላን መጠጥ የሚጠቀሙት ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸውና:: ስለዚህ ጠላን የፈጠሩት ኢትዮጵያውያን ኬሚስ(chemist) ሴቶች መሆናቸው በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። እስከ ዛሬ ድረስም በኬሚስ እናቶቻችን ጠላ ለዚህ ዘመን ደርሶዋል:: ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ጠላን ቀምማ ለመጠጥነት ያበቃች ሴት ማን ትሆን?? የፈጠራ ባለቤትነት መብት የማን ይሆን??መልሱን የምታውቁ ብታሳውቁኝ ደስ ይለኛል።

በሀገረ አሜሪካን በሰርግ፣ በክርስትና፣በሰንበቴ እና በአብይ በዓላት ጠላችን ከጓደኞቹ ከሌሎች መጠጦች ጋር እኩል ለተጠቃሚው ለምርጫ ይቀርባል። ነገር ግን ከእነዚህ ጓደኞቹ ጋር ሲሰለፍ መሸማቀቁ የማይቀር ነው። ምክንያቱም ውስኪ እና ሌሎችም ዘመነኛ ሆነው አሸብርቀው በሚያማምር ሁኔታ በውስጣቸው ያለው የአልኮል መጠን ተጽፎባቸው ለራሳቸው ብቻ በተሰራላቸው እቃ ለተጠቃሚው ይቀርባሉ። የጠላ አቀራረብ ግን ለራሱ በተሰራላት እንደ ሌሎቹ የአልኮል መጠን ተጽፎለት ሳይሆን ለሌሎች መጠጦች በተሰራ በተውሶ እቃ ለተጠቃሚው ይቀርባል። ታድያ የተውሶ ልብስ መልበስ አያሸማቅቅም ትላላቹ??

ጠላ ድሮ ሲፈጠር ፈጣሪዎቹ ለእሱ ብቻ የሚሆን በሸክላ በተሰራ ገንቦ ውስጥ ይጠምቁት ነበረ። ለእሱ ብቻ የተዘጋጀ ማቅረቢያ እና መጠጫ እቃ ነበረው። የሸክላ ገንቦ ሰሪዎች ኢትዮጵያውያን እንደሆኑም ብዙ ምርምር የሚያሻው አይመስለኝም። “ሸክላ ሰሪ” እየተባሉ በሙያቸው እየተንቋሸሹም ሸክለኞቹ ከእኛ ዘመን ላይ ደርሰዋል። ጠላ በእኛ ዘመን ግን በገንቦ የመጠመቅ እድል አላገኘም ምክንያቱም ገንቦ መጠቀም ኋላ ቀርነት ነውና። ያው መቼስ የውጪ አድናቂዎች አይደለን?? ይቅይታ እኔም የውጪ አድናቂ ነኝ። ጠላ ዘንድሮ ልክ እንደ ሀገራችን ኢትዮጵያ በልጽጋ እና አድጋ ፈረጆች በሰሩለት በብረት በርሜል ለመጠመቅ በቃ። እንኳን ደስ አለሽ ጠላ! አንቺም ፈረጆች በሰሩት በአቀራረብ ለማሸብረቅ ባትበቂም ለመጠመቅ ግን በቃሽ። ፈረጆቹ በርሜል የሰሩት ነዳጅ ለማመላስ ነበረ። እኛ ደግሞ አሻሽለን በርሜሏ ጠላ መጥመቂያ አደረግናት። እድገት ይሉታል እንዲህ ነው! የራስ እውቀት እና ፈጠራ ወደ ገደል ከቶ የሌላውን እውቀት እና ፈጠራ መጠቀም። ገንቦዋ በእኛው አሰራር እና ልማድ ማሳደግ እና ማሻሻል ግን አልቻልንም።

የጠላ ፈጣሪዎች ነፍሳቸውን ይማረውና እኛን ቢያዩ እንዴት ይታዘቡን ይሆን? ኧረ! እነሱማ በስንቱ ይታዘቡናል። ለሁሉም “ሆድ ይፍጀው”። ጠላ አለመታደል ሆኖ በኢትዮጵያ ምድር ተፈጠረችና እንደነ ውስኪ እና ቢራ ለሌሎች ዓለማት ለመተዋወቅም አልበቃችም። ያው እኛ ያለንን አድንቀን የራሳችንን ማሻሻል እንደ ኋላ ቀርነት ስለምንቆጥር እነ ውስኪ እና ቢራ በሀገራችን ኢትዮጵያ ዘመናዊ ፋብሪካ እየተሰራላቸው ነው። ለመሆኑ ጠላ በዘመናዊ የሸክላ ገንቦዎች ፋብሪካ ተሰርቶላት እንደ ቢራ እና ሌሎች ለዓለም ለመሰራጨት አትበቃም ነበረን??

 

2 thoughts on “ግለ-ትዝብት – ጠላን ማን ፈጠረው?

  1. As anything was not taken shape out of the blue, Tella itself had been a chemistry that developed over generations. From this we can deduce that the credit is for the society not for a particular women or men. The issue of commercializing Tella is indeed a good point.

Leave a Reply

Your email address will not be published.