ጌትነት ዋለ በራባት ዳይመንድ ሊግ የኢትዮጵያ የወንዶች 3000ሜ. መሰናክል ሪኮርድ ሰበረ

Getnet Wale2

ገንዘቤ ዲባበም በሴቶች 1500ሜ. በዚህ ዓመት ለሶስተኛ ግዜ የወቅቱን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ አሸንፋለች

የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ዳይመንድ ሊግ የዘንድሮው ውድደር ዓመት ስድስተኛ መዳረሻ በሆነችው የሞሮኮዋ ራባት ከተማ ትላንት ምሽት ተከናውኗል፡፡ ‹‹ሚቲንግ ኢንተርናሽናል መሐመድ ስድስተኛ ደ አትሌቲስም ደ ራባት›› በሚል ስያሜ በተካሄደው የራባት ዳይመንድ ሊግ 11 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሶስት የዳይመንድ ሊግ እና በሁለት ነጥብ የማይያዝባቸው ውድድሮች ላይ ተፎካካሪ ነበሩ፡፡ የዳይመንድ ሊጉ አካል ከሆኑት ውድድሮች መካከል በወንዶች 3000ሜ. መሰናክል ጌትነት ዋለ በሴቶች 1500ሜ. ገንዘቤ ዲባባ በወቅቱ ፈጣን ሰዓት አሸናፊዎች ሆነዋል፡፡ 

ኢትዮጵያውያኑ ተሳታፊ ከነበሩባቸው የዕለቱ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች መካከል ገንዘቤ ዲባባ እና ሲፋን ሀሳን ብርቱ ትንቅንቅ ሊያደርጉበት እንደሚችሉ የተገመተው የሴቶች 1500ሜ. እንደተጠበቀው ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በተለይ በመጨረሻው ዙር በሁለቱ ተጠባቂ አትሌቶች መካከል ሳቢ ፉክክር በታየበት ውድድር ገንዘቤ በመጨረሻው አንድ መቶ ሜትር ባሳየችው ብርታት የወቅቱ ፈጣን በሆነ 3:55.47 ሰዓት አሸናፊ ለመሆን በቅታለች፡፡ ሲፋን ሀሳን በ3:55.93 ሁለተኛ ስትወጣ ኢትዮጵያዊቷ ጉዳፍ ፀጋዬ በ3:57.40 ሶስተኛ ሆና አጠናቃለች፡፡ በዚህ ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበሩት ኢትዮጵያዊያኖቹ አክሱማዊት እምባዬ በ3:59.02 አምስተኛ፣ ለምለም ሀይሉ በ4:02.97 አስራ አንደኛ ሆነው ጨርሰዋል፡፡

ገንዘቤ ዲባባ በራባት የዳይመንድ ሊግ ውድድር ላይ Photo © Diamond League Organizers

የሴቶች 1500ሜ. ፉክክር የወቅቱ ፈጣን እና የውድድር ስፍራው ሪኮርድ የሆነውን ሰዓት በማስመዝገብ በበላይነት ያጠናቀቀችው ገንዘቤ ዲባባ ከራባቱ ድሏ በኋላ ‹‹ዛሬ ምሽት ባሳየሁት አቋም ደስተኛ ነኝ፡፡ በአፍሪካ ምድር ሮጬ ማሸነፌም ልዩ ስሜት አለው፡፡ በዘንድሮው ውድድር ዓመት ለሶስተኛ ግዜ የወቅቱን ፈጣን ሰዓት ለማስመዝገብ በመቻሌም ኮርቻለሁ፡፡ አሁን ባለሁበት የብቃት ደረጃም ለዓለም ሻምፒዮናው ዝግጁ እንደሆንኩ ይሰማኛል፡፡›› ብላለች፡፡ በ1500ሜ. የቤት ውስጥ እና የቤት ውጭ የዓለም ሪኮርድ ባለቤት የሆነችው ገንዘቤ ዘንድሮ በርቀቱ አንድ የቤት ውስጥ እንዲሁም ሁለት የቤት ውጭ ውድድሮችን ያደረገች ሲሆን በሶስቱም አጋጣሚዎች የወቅቱን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ማሸነፍ ችላለች፡፡ በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ በስፔን ሳባዴል 3፡59.08 በሆነ ግዜ ያሸነፈችበት የወቅቱ ፈጣን ሰዓት በቤት ውስጥ ውድድር ታሪክ የምንግዜውም 8ኛው ፈጣን ሆኖ ተመግቧል፡፡ በቤት ውጭ ውድድር ከአስር ቀን በፊት በሮም ዳይመንድ ሊግ ላይ ስታሸንፍ ያስመዘገበችው 3፡58.26 የሆነ ፈጣን ሰዓት በ2015 ዓ.ም. የርቀቱን የዓለም ሪኮርድ ከሰበረች ወዲህ የሮጠችው የራሷም ፈጣን ሰዓት የነበረ ሲሆን ትላንት ምሽት በራባት ያሸነፈችበት ሰዓት ደግሞ ከአስር ቀን በበፊት በሮም ካስመዘገበችውም የተሻለ ሆኗል፡፡

የወንዶች 3000ሜ. መሰናክል የዳይመንድ ሊግ ቅድመ ውድድር የአሸናፊነት ግምት የተሰጠው በሀገሩና በደጋፊዎቹ ፊት ለሚሮጠው ሞሮኳዊው ሱፊያኔ ኤል ባካሊ የነበረ ቢሆንም በኢትዮጵያውያን አትሌቶች የበላይነት ተጠናቋል፡፡ የመጨረሻው ዙር ፉክክር በኢትዮጵያውያኑ ጌትነት ዋለ እና ጫላ በዮ መካከል የተደረገ ሲሆን ጌትነት የመጨረሻውን መሰናከል ካለፈ በኋላ በጨመረው ፍጥነት በ8 ደቂቃ ከ06.01 ሰከንድ ቀዳሚ ሆኖ ጨርሷል፡፡ ጌትነት ውድድሩን በአሸናፊነት የጨረሰበት ሰዓት የወቅቱ ፈጣን፣ የራሱ ምርጥ እንዲሁም ላለፉት ሰባት ዓመታት በሮባ ጋሪ ተይዞ የቆየውን የኢትዮጵያ ሪኮርድ የሰበረበት ሆኖም ተመዝግቧል፡፡ በርቀቱ የከዚህ ቀደሙ የኢትዮጵያ ሪኮርድ ሮባ ጋሪ እ.አ.አ ሜይ 11/2012 ዓ.ም. በዶሀ ዳይመንድ ሊግ ላይ አስመዝግቦት የነበረው 8:06.16 ነበር፡፡ በራባቱ ውድድር ኢትዮጵያዊ ጫላ በዮ ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀበት 8:06.48 ሰዓትም የራሱን ምርጥ ያሻሻለበት ሲሆን ኬንያዊው ቤንጃሚን ኪገን በ8:07.25 ሶስተኛ ወጥቷል፡፡ የቅድመ ውድድር የአሸናፊነቱ ግምት ተሰጥቶት የነበረው ሞሮኳዊው ኤል ባካሊ በ8:27.56 አስራ አንደኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡  

ጌትነት ዋለ በራባት የዳይመንድ ሊግ ውድድር ላይ Photo © Diamond League Organizers

በራባት የወንዶች 3000ሜ. መሰናክል አሸናፊ የሆነው ጌትነት ዋለ ከድሉ በኋላ በሰጠው አስተያት ‹‹ውድድሩ በጣም ጥሩ ነበር፡፡ በውድድሩ ላይ ባሳየሁት አቋም የረካሁ ሲሆን በአሸናፊነት ለመጨረስ በመብቃቴም በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ከዚህ ውድድር በፊትም 8:06 በሆነ ሰዓት መግባት ችዬ ስለነበር በዛሬው ውድድር ላይም ጥሩ ውጤት ጠብቄ ነበር፡፡ የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን ስለምፈልግም ከውድድሩ በፊት ልምምዴን ጠንክሬ እሰራለሁ፡፡›› ብሏል፡፡

የዳይመንድ ሊጉ የነጥብ ፉክክር አካል የነበረው የሴቶች 800ሜ. ውድድርም ኢትዮጵያዊቷ ሀብታም አለሙ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ግዜ ከሁለት ደቂቃ በታች መጨረስ የቻለችበት ሆኗል፡፡ ሀብታም ውድድሩን በ1:59.90 በሆነ ሰዓት በሁለተኛነት ስታጠናቅቅ ኬንያዊቷ ኔሊ ጄፕኮስጌይ በ1:59.50 በአሸናፊነት ጨርሳለች፡፡

በራባት የዳይመንድ ሊጉ የነጥብ ፉክክር አካል ባልነበሩት የወንዶች 1500ሜ. እና 5000ሜ. ውድድሮች ላይም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን ኬንያዊው ቪንሰንት ኪቤት በ3:35.80 ቀዳሚ ሆኖ ባጠናቀቀበት የወንዶች 1500ሜ. ኢትዮጵያዊው ታደሰ ለሚ በ3:37.40 አስረኛ ሆኖ ጨርሷል፡፡ አብዛኛውን ዙር ኢትዮጵያዊው ሶሎሞን በሪሁ ከኬንያዊው ኤድዋርድ ዛካዮ ጋር ለቀዳሚነት በተፎካከሩበት የወንዶች 5000ሜ. ዛካዮ በ13:11.49 አንደኛ፣ ሶሎሞን በሪሁ በ13:16.08 ሁለተኛ፣ ሞሮኳዊው ሱፊያን ቡካንታር በ13:17.26 ሶስተኛ ሆነው ጨርሰዋል፡፡ የዚህ ውድድር አካል የነበሩት ኢትዮጵያውያኑ አቤ ጋሻሁን (13:29.49) እና መለሰ ብርሀን (13:44.08) በቅደም ተከተላቸው መሰረት ዘጠነኛ እና አስራ አንደኛ ሆነው አጠናቀዋል፡፡

እስካሁን ባስመዘገቡት ውጤት መሰረት ከወዲሁ በዙሪክ እና ብራስልስ ለሚደረጉት የዳይመንድ ሊግ ፍፃሜ ውድድር ማለፋቸውን ካረጋገጡት መካከል ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም ይገኙበታል፡፡ በወንዶች 5000ሜ. ከሚደረጉት አራት የማጣሪያ ውድድሮች ሶስቱ የተካሄዱ ሲሆን ሰለሞን ባረጋ በ22 ነጠብ 1ኛ፣ ጥላሁን ሀይሌ በ12 ነጥብ 3ኛ፣ ሀጎስ ገ/ሕይወት በ12 ነጥብ 4ኛ በመሆን ኦገስት 29 በዙሪክ ለሚካሄደው የፍፃሜ ውድድር ማለፋቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በ3000ሜ. ወንዶች ከሚደረጉት አራት የማጣሪያ ውድድሮች ሁለቱ የተካሄዱ ሲሆን ጫላ በዮ በ12 ነጥብ ለብራስልሱ ፍፃሜ ማለፉን አረጋግጧል፡፡ በሴቶች 1500ሜ. ከሚደረጉት ስድስት የማጣሪያ ውድድሮች ሶስቱ የተካሄዱ ሲሆን ጉዳፍ ፀጋዬ በ19 ነጥብ በዙሪክ ለሚካሄደው የፍፃሜ ውድድር ማለፏን አረጋግጣለች፡፡ የዳይመንድ ሊጉ ሰባተኛ ውድድር ፕሪፎንቴይን ክላሲክ (ዩጂን ዳይመንድ ሊግ) ለ2021 የዓለም ሻምፒዮና ዝግጅት እተካሄደ ካለ የመሰረተ ልማት ግንባታ ጋር በተያያዘ ምክንያት ጁን 30 ቀን 2019 በካሊፎርኒያ ስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ የሚካሄድ ሲሆን ገንዘቤ ዲባባ፣ አልማዝ አያና፣ ሄለን ኦቢሪ፣ ሲፋን ሀሳን እና ካስተር ሴሜኒያን የሚገናኘው የሴቶች 3000ሜ. ፉክክር በተለየ ጉጉት ይጠበቃል፡፡