ደካማው የማጣሪያው ጉዟችን ተጠናቋል

Walias first 11 against CBE

ደካማው የማጣሪያው ጉዟችን ተጠናቋል

ከጳጉሜን ጀምሮ ላለፉት ጥቂት ወራት በጥድፊያ ሲካሄድ የከረመው የ2015 የኢኳቶሪያል ጊኒ አፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጉዞ ትናንት ምሽት ተጠናቋል፤ አላፊዎቹ እና ወዳቂዎቹም ታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከስድስት ጨዋታዎቹ አንዱን አሸንፎ፣ በአራቱ ተሸንፎ እና በአንዱ አቻ ተለያይቶ፣ ሊያገኛቸው ከሚችላቸው 18 ነጥቦች አራቱን ብቻ አግኝቶ ከምድቡ የመጨረሻውን ደረጃ ይዞ አጠናቋል፡፡ በብዙ ውዝግቦች፣ እና አነጋጋሪ ጉዳዮች የተሞላው የዋልያዎቹ የማጣሪያ ጉዞ ፍፃሜውን ያገኘው ትናንት ምሽት በሜዳቸው ከማላዊ ጋር አቻ ከተለያዩ በኋላ ነበር፡፡

የትናንቱ ጨዋታ

ከትናንቱ ጨዋታ በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እጅግ አነስተኛ የማለፍ እድል የነበረው ቢሆንም (እድሉ በማሊ እና አልጄሪያ ጨዋታ መንጠልጠሉ እንዳለ ሆኖ) በአዲስ አበባ ስታዲየም እና በዙሪያው የነበረው ድባብ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከተመለከትነው አንፃር በጣም የቀዘቀዘ ነበር፡፡ በቀደሙ ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች የሙሉ ቀን ሰልፍ የነበረው እና ሰዓታት ቀደም ብሎ ይሞላ የነበረው ስታዲየም ትናንት ባዶ ስፍራዎች ይታዩበት ነበር፡፡ ምናልባት ይህ በብሔራዊ ቡድኑ ጠባብ የማለፍ እድል ተስፋ ከመቁረጥ የተከሰተ ሊሆን ይችላል፡፡ ወደ ጨዋታው ስናመራ ሁለቱ ቡድኖች ጨዋታውን የጀመሩት በሚከተሉት አሰላለፎች ነበር፡-

ኢትዮጵያ

ግብ ጠባቂ፡- ጀማል ጣሰው

ተከላካዮች፡- አብዱልከሪም መሀመድ፣ ቢያድግልኝ ኤልያስ፣ ሳላሃዲን ባርጊቾ፣ አበባው ቡታቆ

አማካዮች፡- ናትናኤል ዘለቀ፣ ታደለ መንገሻ፣ ሽመልስ በቀለ

አጥቂዎች፡- ዩሱፍ ሳላህ፣ ዳዊት ፍቃዱ፣ ኦመድ ዑክሪ

ተጠባባቂዎች:- ታሪክ ጌትነት፣ ግርማ በቀለ፣ አንዳርጋቸው ይላቅ፣ ብርሀኑ ቦጋለ፣ጋቶች ፓኖም ፣ ፋሲካ አስፋው፣ እንዳለ ከበደ እና ራምኬል ሎክ

ማላዊ

ግብ ጠባቂ፡- ማክዶናልድ ሀራዋ

ተከላካዮች፡- ጆን ላንጄሲ፣ ፍራንሲስ ምሊምቢካ፣ ሊምቢካኒ ምዛቫ፣ ሀሪ ንዪሬንዳ

አማካዮች፡- ቺማንጎ ካይራ፣ ሮበርት ንጋምቢ፣ ፊሸር ኮንዶዊ፣ ጆሴፍ ካምዌንዶ

አጥቂዎች፡- ኤሶ ካንዬንዳ፣ ጋስቲን ሲሙኮንዳ

ጨዋታውን በዋና ዳኝነት የመሩት አርቢትር ሬዱኔ ጂዬድ እንዲሁም ረዳቶቻቸው አብድላዚዝ ኤል ሜህራጂ እና ኤሳም ቤንባፓ ሁሉም ከሞሮኮ ነበሩ፡፡ ባለሜዳዎቹ ዋልያዎቹ ጨዋታውን ያደረጉት በሙሉ ቢጫ ትጥቅ ሲሆን ነበልባሎቹ በበኩላቸው በሙሉ ቀይ ትጥቅ ጨዋታውን አድርገዋል፡፡

በርካታ ጎሎች ማስቆጠር ያስፈልጋቸው የነበሩት የማሪያኖ ባሬቶ ዋልያዎቹ ጨዋታውን የጀመሩት በማጥቃት ፍላጎት እና ተነሳሽነት ቢሆንም በማላዊ ጥብቅ መከላከል እና በራሳቸው የቅንጅት እና መረጋጋት ችግር መነሻ የጎል እድሎችን ለመፍጠር ተቸግረውም ዘግይተውም ነበር፡፡ የጨዋታው የመጀመሪያው እውነተኛ የጎል ሙከራ የተደረገው በ11ኛው ደቂቃ ሲሆን ይህም በኦመድ ኦኩሪ ከርቀት ተመቶ የማላዊው ግብ ጠባቂ ማክዶናልድ ሀራዋ እና የግቡ ቋሚ ተባብረው የመለሱት ሙከራ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ተጨዋቾቻችን የማላዊን ጎል ለማስከፈት ቢጥሩም እንደገና ኦመድ ከዳዊት ፈቃዱ ተቀብሎ ለመግባት ሲሞክር ግብ ጠባቂው ከጎሉ ፈጥኖ ወጥቶ ካወጣበት በስተቀር የሚጠቀስ ሙከራ ሳንመለከት የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ የተለየ እና የተሻለ ነገር እንደሚታይ ተስፋ ቢደረግም እንዲያውም የባሰ ሆኖ የማላዊን ጥብቅ መከላከል፣ የኢትዮጵያን ቡድንን ደካማ ቅንጅት እና ተስፋ ሰጪ ነገር ለመስራት አለመቻል ብቻ ተመልክተናል፡፡ አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ በ63ኛው እና በ70ኛው ደቂቃዎች ሁለት የተጨዋቾች ቅያሬዎች (እንዳለ ከበደን እና ራምኬል ሎክን በዩሱፍ ሳሌህ እና ዳዊት ፍቃዱ ቦታ) ቢያደርጉም ተቀይረው የገቡት ተጨዋቾችም የተለየ ነገር መስራት ሳይችሉ ጨዋታው ተጠናቋል፡፡ ሁለቱ ቡድኖችም ተያይዘው ወድቀዋል፡፡ በቀድሞው የቡድኑ አምበል ያንግ ቺሞዚ የሚሰለጥኑት ማላዊዎቹ ከእኛ ቡድን በተለየ በራሳቸው ላይ የተወሰነ እድል የነበራቸው ቢሆንም ለማሸነፍ አለመጫወታቸው እና አቻ እንደሚያሳልፈው ቡድን ፍጹም መከላከል ላይ ማተኮራቸው ሁሉንም ሰው ግራ ያጋባ ነበር፡፡ ለማመን ቢከብድም አሰልጣኙ አቻ እንደሚያሳልፋቸው ተማምነው ያንን አጨዋወት እንደተገበሩ ከጨዋታው በኋላ ተናግረዋል፡፡

ባሬቶ ምን አሉ?

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አወዛጋቢው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ ለተወሰኑ ጥያቄዎች ምላሾችን ሰጥተዋል፡፡ ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ በኮንትራታቸው ዙሪያ እና በፈቃዳቸው ከስልጣናቸው ይለቁ እንደሆነ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ሲመልሱ ለ2015 የአፍሪካ ዋንጫ ማሳለፍ በኮንትራታቸው ላይ እንዳልሰፈረ እና እሳቸውም በፈቃዳቸው እንደማይለቁ ለራሳቸው እንደ ግብ ካስቀመጧቸው ነገሮች መካከልም ለወጣቶች እድል መስጠት እና የተጨዋቾችን ብቃት ማሳደግን ጨምሮ የተወሰኑትን ማሳካት እንደቻሉ ገልፀዋል፡፡ የአጭር ጊዜ (የሁለት ዓመት) ኮንትራት እያላቸው ለምን አዲስ ቡድን መገንባትን እንደፈለጉ ሲጠየቁም ኮንትራታቸው የአራት ወራት ብቻ ቢሆን እንኳን የሚያደርጉት ይህንኑ እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡ ወጣቶችን የሚጠቀሙትም ለማደግ እና ለመሻሻል በተሻለ ስለሚፈልጉ፣ በሜዳ እና በሜዳ ውጪ ባህርይም ከነባሮቹ የተለዩ እና የተሻሉ በመሆናቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ባሬቶ ለቡድናቸው ደካማ የማጣሪያ ጉዞ ምክንያቱን ሲጠየቁም ስለጊዜያዊ ውጤት በመጨነቅ ፈንታ የረዥም ጊዜውን ማሰብ እንደሚኖርብን እናም ስለ መጫወቻ ሜዳዎች እጥረት እና ስለ መንገድ ላይ እግር ኳስ አለመኖር እንዲሁም በወጣቶች እድገት እና በክለቦች ተጨዋች አያያዝ እና በተመሳሳይ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚኖርብን ገልፀዋል፡፡

እንዴት ጨረስን?

ትናንት እኛ ማላዊን ባስተናገድንበት ተመሳሳይ ሰዓት ማሊ እና አልጄሪያ በማሊ ዋና ከተማ ባማኮ፣ በማርች 26 ስታዲየም የመጨረሻ የምድብ ጨዋታቸውን አድርገው ነበር፡፡ ማለፋቸውን ቀድመው ያረጋገጡት እና እኛም እንደሚያሸንፉ ተስፋ አድርገንባቸው የነበሩት አልጄሪያዎች እንደ እነ ያሲኔ ብራሂሚ፣ ራፊክ ሀሊች፣ ሳፊር ታይደር እና ሪያድ ማህሬዝ አይነት ቁልፍ ተጨዋቾቻቸውን ሳይዙ ገብተው ከጨዋታ ብልጫ ጋር በማሊ አቻቸው 2ለ0 ተረተዋል፡፡ የሰይዱ ኬይታ ፍፁም ቅጣት ምት እና የሙስጠፋ ያታባሬ ተጨርፎ የተቆጠሩ ገሎች የሄነሪ ካስፔርዣክን ቡድን ለኢኳቶሪያል ጊኒው የአፍሪካ ዋንጫ አብቅተዋል፡፡ ከትናንትናዎቹ የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታዎች በኋላ የምድቡ ቡድኖች የመጨረሻ አቀማመጥ ይህን ይመስላል፡-

1ኛ- አልጄሪያ፡  6 ጨዋታ   15 ነጥብ እና 7 የጎል ክፍያ

2ኛ- ማሊ፡     6 ጨዋታ     9 ነጥብ እና 2 የጎል ክፍያ

3ኛ- ማላዊ፡    6 ጨዋታ     7 ነጥብ እና -4 የጎል ክፍያ

4ኛ- ኢትዮጵያ፡  6 ጨዋታ     4 ነጥብ እና -5 የጎል ክፍያ

 

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.