የ2017 ዳይመንድ ሊግ የመጀመሪያው ፍፃሜ በዙሪክ ተካሂዶ 16 አሸናፊዎች ተለይተዋል

Photo © KEYSTONE/ENNIO LEANZA

Photo © KEYSTONE/ENNIO LEANZA

ከፍተኛ ትንቅንቅ በታየበት የወንዶች 5000ሜ. ሞ ፋራህ የመጨረሻ የትራክ ውድድሩን በአሸናፊነት ለመዝጋት በቅቷል
ሀብታም አለሙ የኢትዮጵያን የሴቶች 800 ሜትር ሪኮርድ ሰብራለች

ከ2017 የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ዳይመንድ ሊግ የፍፃሜ ውድድሮች የመጀመሪያው የሆነው የዙሪክ ውድድር በትላንትናው ዕለት ተካሂዶ ሲጠናቀቅ 16 አትሌቶች በተፎካከሩባቸው የውድድር አይነቶች የዓመቱ የዳይመንድ ሊግ ሻምፒዮንነት ክብሩን እና ሽልማቱን የግላቸው ለማድረግ በቅተዋል፡፡ በእንግሊዝ ለንደን ከሁለት ሳምንት በፊት ተካሂዶ በተጠናቀቀው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የነበሩ አብዛኞቹ ኮከብ አትሌቶች ተሳታፊ በሆኑበት የዙሪኩ የዳይመንድ ሊግ ፍፃሜም በዓለም ሻምፒዮናው ላይ የተመለከትናቸውን አይነት ያልተጠበቁ ሽንፈቶችም ተከስተዋል፡፡

በወንዶች በተደረጉት ዘጠኝ የፍፃሜ ፉክክሮች በ100ሜ. እንግሊዛዊው ቺንዱ ኡጃህ በ9.97 ሰከንድ ቀድሞ በመግባት ሳይጠበቅ የዳይመንድ ሊጉን ዋንጫ የወሰደ ሲሆን በለንደን የዓለም ሻምፒዮን መሆን የቻለው ተጠባቂው አሜሪካዊ ጀስቲን ጋትሊን በ10.04 ሰከንድ አራተኛ ወጥቷል፡፡ በ400ሜ. በለንደኑ የዓለም ሻምፒዮና ላይ በውድድሩ ወቅት በተከሰተው በሽታ ተጠቅተሀል ተብሎ እንዳይሳተፍ የተከለከለው ቦትስዋናዊው አይዛክ ማክዋላ በ43.95 ሰከንድ በማሸነፍ ዙሪክ ላይ የዳይመንድ ዋንጫውን ተቀብሏል፡፡ ኬንያውያን አትሌቶች ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ባሉት ደረጃዎች ተከታትለው በመግባት በጨረሱበት የ1500ሜ. ቲሞቲ ቼሪዮት በ3፡33.93 የዳይመንድ ሊጉ ሻምፒዮን ሆኗል፡፡ ከፍተኛ ተጠባቂነት የነበረውና አምስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተሳተፉበት የወንዶች 5000ሜ. እንደተጠበቀው እስከመጨረሻው መስመር ድረስ የዘለቀ ብርቱ ትንቅንቅ የታየበት ሲሆን በመጨረሻም ሞ ፋራህ በ13 ደቂቃ ከ06.05 ሰከንድ ከመም (የትራክ) ውድድር በድል የተሰናበተበትን ውጤት ሊያስመዘግብበት ችሏል፡፡ ሞ ፋራህን ተከትሎ ሁለተኛ ወጥቶ የነበረው አሜሪካዊው ፖል ቼሊሞ በመጨረሻዋ ቅፅበት ተፎካከሪዎቹ ላይ በፈፀመው ጥፋት ውጤቱ እንዲሰረዝ ተደርጓል፡፡ ኢትዮጵያውያው የዓለም ሻምፒዮን ሙክታር እድሪስ ውድድሩን የጨረሰው ተደነቃቅፎ በመውደቅ ጭምር ቢሆንም በ13፡06.09 ሁለተኛ ወጥቷል፡፡ ዮሚፍ ቀጄልቻ በ13:06.18 ሶስተኛ፣ ሰለሞን ባረጋ በ13:07.35 አራተኛ፣ የኔው አላምረው በ13:13.08 ስድስተኛ እንዲሁም ብርሀኑ ለገስ በ13:24.89 ዘጠነኛ ሆነው አጠናቀዋል፡፡

Photo © KEYSTONE/ENNIO LEANZA

ሞ ፋራህ የዙሪኩን ውድድር በአሸናፊነት ካጠናቀቀ በኋላ በሰጠው አስተያየት ‹‹ማሸነፉን አጥብቄ እፈልገው ነበር ማሸነፍ ችያለሁ፡፡ ለማሸነፍ መብቃቴም የሚያስደንቅ ቢሆንም የጠንካራ ስራዬ ውጤት ነው፡፡ ወደፊት የትራክ ውድድርን እና ደጋፊዎቼን እናፍቃቸዋለሁ፡፡ በስታድየም ውስጥ መሮጥን ለብዙ ዓመት ተደስቼበታለሁ፡፡ አሁን ከሁሉ ነገር በፊት ከቤተሰቤ ጋር አብሬ የምሆንበትን ግዜ በደስታ ማሳለፍ እፈልጋለሁ›› ብሏል፡፡

በለንደኑ የዓለም ሻምፒዮና ላይ በአነሳስ ስህተት ከውድድሩ ውጭ እንዲሆን ተደርጎ የነበረው የብሪቲሽ ቨርጂን አይላንዱ ኪሮን ማክማስተር በ400ሜ. መሰናክል ሶስቱንም የዓለም ሻምፒዮና ሜዳሊስቶች በማስከተል በ48.07 ሰከንድ ባልድል ሲሆን በርዝመት ዝላይ ደቡብ አፍሪካዊው ሉቮ ማንዮንጋ፣ በከፍታ ዝላይ የኳታሩ ሙታዝ ባርሺም፣ በምርኩዝ ዝላይ አሜሪካዊው ሳም ኬንድሪክስ፣ በጦር ውርወራ ያኩብ ቮድሌች ዙሪክ ላይ በማሸነፍ የዳይመንድ ሊግ ዋንጫውን ከፍ አድርገው ማንሳት የቻሉ ሌሎች አትሌቶች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያን የሴቶች 800 ሜትር ሪኮርድ በዙሪክ የሰበረችው ሀብታም አለሙ

ሰባት የፍፃሜ ውድድሮች በተስተናገዱበት የሴቶቹ ፉክክር የባህማሷ ሻውኔ ሚለር በ200ሜ. ተጠባቂዎቹን ኤላዪኒ ቶምፕሰን እና ዳፍኔ ሺፐርስ በመቅደም የዳይመንድ ዋንጫው ባለቤት ሆናለች፡፡ ደቡብ አፍሪካዊቷ ካስተር ሴመንያ በ1፡55.84 አሸናፊ በሆነችበት የ800ሜ. ፉክክር 1፡57.05 በሆነ ሰዓት አራተኛ ሆና ያጠናቀቀችው ኢትዮጵያዊቷ ሀብታም አለሙ በጁን 2012 ፋንቱ ሚጌሶ ኒው ዮርክ ላይ ያስመዘገበችውንና 1፡57.48 የነበረውን የኢትዮጵያ ሪኮርድ ለመስበር በቅታለች፡፡ በሴቶች 3000ሜ. መሰናክል የባሕሬኗ ሩት ጄቤት የርቀቱ የምንግዜውም ሁለተኛ ፈጣን፣ የውድድር ስፍራው ሪኮርድ እና የወቅቱ ፈጣን በሆነ 8፡55.29 ሰዓት በማሸነፍ የዳይመንድ ሊግ ዋንጫው ባለቤት ስትሆን ሁለተኛ የወጣችው ኬንያዊቷ ቢያትሪስ ቼፕኮኤች ያስመዘገበችው 8:59.84 የሆነ ሰዓትም በርቀቱ በተደረጉ ውድድሮች ታሪክ ከ9 ደቂቃ በታች የጨረሰች አራተኛዋ አትሌት አድርጓታል፡፡ አሜሪካዊቷ የዓለም ሻምፒዮን ኤማኮበርን በ9፡14.81 አራተኛ ሆና ባጠናቀቀችበት በዚህ ፉክክር ላይ ተሳታፊ የነበሩት ኢትዮጵያውያኑ ሶፊያ አሰፋ በ9:16.45 ሰባተኛ እቴነሽ ዲሮ በ9:20.94 ዘጠነኛ ሆነው ጨርሰዋል፡፡ በሴቶች 100ሜ. መሰናክል በለንደን የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን የበቃችው አውስትራሊያዊቷ ሳሊ ፒርሰን በዙሪኩ የዳይመንድ ሊግ የፍፃሜ ፉክክርም በ12.55 ሰከንድ አሜሪካዊቷ ሻሪካ ኔልቪስን በማይክሮ ሰከንድ ቀድማ በመጨረስ ዳግም ወደቀድሞ ድንቅ ብቃቷ መመለሷን ማስመስከር ችላለች፡፡ በስሉስ ዝላይ የካዛኪስታኗ ኦልጋ ሪፓኮቫ፣ በአሎሎ ውርወራ ቻይናዊቷ ጎንግ ሊዣኦ፣ በጦር ውርወራ የቼክ ሪፐብሊኳ ባርባራ ስፖታኮቫ ሌሎች የዳይመንድ ዋንጫ አሸናፊዎች ናቸው፡፡

የዳይመንድ ሊጉ የፍፃሜ ፉክክር እንደከዚህ በፊቱ አትሌቶች በነበራቸው ነጥብ ላይ በሚያክሉት ነጥብ መሰረት የበላይነታቸውን የሚያስጠብቁበት መሆኑ ቀርቶ ዘንድሮ በአዲስ መልክ በተተገበረው የአንድ ውድድር ፉክክር አሸናፊው እንዲለይ መደረጉም ያልተጠበቁ ውጤቶች እና አሸናፊዎች ለመታየታቸው የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዳደረገ ይታመናል፡፡ ሁለተኛውና የመጨረሻው የዳይመንድ ሊግ የፍፃሜ ፉክክር ሴፕቴምበር 1/2017 (ነሐሴ 26/2009) በቤልጅየም ብራስልስ ይካሄዳል፡፡

በዙሪኩ የፍፃሜ ውድድር ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ያሉትን ደረጃዎች ይዘው ያጠናቀቁት አትሌቶች ከዳይመንድ ሊጉ ዋንጫ በተጨማሪ ጠቀም ያለ የገንዘብ ሽልማት የሚያገኙ ሲሆን የሽልማት ገንዘቡ እስከ ስምንተኛ ያሉትን ደረጃዎች ይዘው የሚያጠናቅቁ አትሌቶችንም የሚመለከት ነው፡፡
የዳይመድን ሊግ የፍፃሜ ተፎካከሪዎች የገንዘብ ሽልማት በአሜሪካን ዶላር
ለ1ኛ. 50,000
ለ2ኛ. 20,000
ለ3ኛ. 10,000
ለ4ኛ. 6,000
ለ5ኛ. 5,000
ለ6ኛ. 4,000
ለ7ኛ. 3,000
ለ8ኛ. 2,000

1 thought on “የ2017 ዳይመንድ ሊግ የመጀመሪያው ፍፃሜ በዙሪክ ተካሂዶ 16 አሸናፊዎች ተለይተዋል

Leave a Reply

Your email address will not be published.