የ2008 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በትልልቅ ጨዋታዎች ይቀጥላል

2008 Ethiopian Premier League - Week 1 - 1

የ2008 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከአንድ ወር ተኩል ገደማ በፊት ተጀምሮ የሁለት ሳምንታት ጨዋታዎች ከተደረጉ በኋላ በሴካፋ ዋንጫ ውድድር ምክንያት መቋረጡ ይታወሳል፡፡ አሁን ይህ የኢትዮጵያ ትልቁ የእግር ኳስ የክለቦች ውድድር ከቆመበት ሊቀጥል ተዘጋጅቷል፡፡ ቀጣዩ ፅሁፍ ውድድሩ በተቋረጠባቸው ያለፉት 40 ቀናት ገደማ የተከሰቱ ጉዳዮችን ለመቃኘት እና የተወዳዳሪ ክለቦችን አጀማመር ለማስታወስ ይሞክራል፡፡

የስያሜ ስፖንሰር እና የቴሌቪዥን ስርጭት ጉዳይ

የዘንድሮው ፕሪምየር ሊግ ከመጀመሩ በፊት እጅግ አነጋጋሪ የነበሩት የሊጉ ስያሜ መብት እና የቴሌቪዥን ስርጭት ጉዳዮች ውድድሩ ከተጀመረ በኋላም ሆነ ባለፉት ጥቂት ቀናት ማነጋገራቸው ቀጥሎ ነበር፡፡ ተሳታፊ ክለቦች ‹‹ስምምነቱ የእኛንን ይሁንታ የፈለገ እና ያሳተፈ አልነበረም›› ያሉበት የቴሌቪዥን ቀጥታ ስርጭት በኢቢሲ 3 ላይ ጀምሮ ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙም ሳይዘልቅ በትክክል ባልታወቀ ምክንያት (በገንዘብ አለመስማማት ምክንያት እንደሆነ ውስጥ አዋቂዎች ይገልፃሉ) የቀጥታ ስርጭቱ ቆሞ ነበር፡፡ አሁን ውድድሩ ዳግም ሲጀምርም ቀጥታ ስርጭቱ ይቀጥል አይቀጥል የታወቀ ነገር የለም፡፡

ፕሪምየር ሊጉ ከመጀመሩ ቀናት ቀደም ብሎ ውድድሩን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሊጉን ስያሜ ለመሸጥ ከቢራ ጠማቂው ቢጂአይ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሞ ነበር፡፡ ነገር ግን ስምምነቱ የአብዛኞቹን ክለቦች በተለይም በሌላ የቢራ ጠማቂ ባለቤትነት የተያዘው ዳሸን ቢራን እና በቢራ ጠማቂ ስፖንሰር የሚደረገው ኢትዮጵያ ቡናን ይሁንታ ማግኘት አልቻለም ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ፌዴሬሽኑ ከክለቦቹ ጋር የተለያዩ ውይይቶችን ሲያደርግ ሰንብቷል፡፡ ውይይቶቹ ፍሬ ባለማፍራታቸውም ፌዴሬሽኑ ወደ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ የበላይ አካል ፊፋ የምክር ጥያቄ ማቅረቡ ተሰምቷል፡፡ ፊፋም በጉዳዩ ላይ እውቀታቸውን የሚያካፍሉ እና ችግሩን ለመፍታት የሚሞክሩ ባለሞያዎችን ልኮ ተጨማሪ ውይይቶች ሲደረጉ ነበር፡፡ በመጨረሻም ፌዴሬሽኑ በካስቴል ቢራ ስያሜ ከቢጂአይ ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን የመግባቢያ ስምምነት ለማፍረስ መዘጋጀቱ ተሰምቷል፡፡ በዚህ መሰረት ወይ አዲስ ከክለቦች ፍላጎት ጋር የማይጋጭ ስፖንሰር ለማግኘት አልያም ያለ ስያሜ ስፖንሰር ውድድሩ እንዲቀጥል ለማድረግ መወሰኑ ታውቋል፡፡

ያልተጠበቀው የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ስንብት

አምና በፋሲል ተካልኝ እና ዘሪሁን ሸንገታ አሰልጣኝነት ያለ ብዙ ችግር ሻምፒዮን መሆን የቻለው ቅዱስ ጊዮርጊስ የዋና አሰልጣኝነት መንበሩን ለሆላንዳዊው ማርቲን ኩፕማን ሰጥቶ ውድድሩን መጀመሩ ይታወሳል፡፡ ቡድኑ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በባላንጣው ኢትዮጵያ ቡና ተረትቶ ከውድድሩ ቢወጣም እና በፕሪምየር ሊጉ መክፈቻ ጨዋታ በአዳማ ከነማ ቢሸነፍም በሁለተኛው ጨዋታ ሲዳማ ቡናን 5ለ1 የደቆሰበት እና በሌሎቹም ቀደምት ጨዋታዎች ያሳየው አቋሙ በበርካቶቹ ደጋፊዎች ተወድዶለት ነበር፡፡ የሆላንዳዊው አሰልጣኝ ውብ እግር ኳስን የመጫወት ፍልስፍና በተጨዋቾቹ የበለጠ ሲለመድም በሊጉም ሆነ በአፍሪካ መድረክ አስደናቂ ቡድን እንደሚመለከቱ ደጋፊዎችም ሆኑ ገለልተኞች ተስፋ አድርገው ነበር፡፡ ነገር ግን ፕሪምየር ሊጉ በተቋረጠበት ጊዜ ማርቲን ኩፕማን ባልተጠበቀ መንገድ ከክለቡ ጋር መለያየታቸው አስደንጋጭ ዜና ሆኗል፡፡ አሰልጣኙ ለእረፍት ወደ ሀገራቸው ባቀኑበት ጊዜ ነበር ከክለቡ አመራሮች የስንብት መልእክት የደረሳቸው፡፡ ኩፕማን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ኃላፊነታቸው የተነሱበትን ትክክለኛ ምክንያት እንዳላወቁ ሲገልፁ፣ ክለቡ ግን ‹‹አሰልጣኙ ልናሟላ የማንችለውን ጥያቄ በማቅረባቸው ልናሰናብታቸው ወስነናል›› የሚል ያልተብራራ ምክንያት ሰጥቷል፡፡ ክለቡ በክረምቱ ለአካዳሚው ዳይሬክተርነት የቀጠራቸው የሀገራቸው ሰው ሬኒ ሂዲንክም ተመሳሳይ የስንብት እጣ ገጥሟቸዋል፡፡ ከነዚህ ፍፁም ያልተጠበቁ ውሳኔዎች ጥቂት ሳምንታት በኋላም ክለቡ የቀድሞ አሰልጣኙ ማርት ኖይን በዋና አሰልጣኝነት መመለሱ ተረጋግጧል፡፡ ሆላንዳዊው አሰልጣኝ በ2006 ክለቡን ይዘው በማራኪ እንቅስቃሴ የሊጉ መሪ ካደረጉት በኋላ ዓመቱን ሳይጨርሱ በስምምነት የተሻለ ደመወዝ ወዳቀረበላቸው የታንዛኒያ ብሔራዊ ቡድን አምርተው ነበር፡፡ የክለቡ አመራሮች ትልቅ ተስፋ ያሳዩትን አሰልጣኝ አሰናብተው፣ ከዚህ ቀደም ጥሩ የሰሩትን ግን ለክለቡ ‹ታማኝ› ያልነበሩትን ሰው ማምጣታቸው በደጋፊዎች ዘንድ የሀሳብ ክፍፍል ፈጥሯል፡፡ ማርት ኖይ በመጀመሪያው የክለቡ ቆይታቸው ወቅት እጅግ በአስደናቂ አቋም የረቱትን ኤሌክትሪክን በመግጠም ሁለተኛ የኃላፊነት ጊዜያቸውን ይጀምራሉ፡፡

የረዳቶች ሹም-ሽር በኢትዮጵያ ቡና

በፕሪምየር ሊጉ እና በጥሎ ማለፉ ካሳለፈው ደካማ የውድድር ዘመን በኋላ በአዲስ የውጪ ዜጋ አሰልጣኝ እየተመራ አዲስ የውድድር ዘመኑን የጀመረው ኢትዮጵያ ቡና በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ እስከ ፍፃሜ በተጓዘበት መልካም አቋሙ ለደጋፊዎቹ ተስፋን ሰጥቶ ነበር፡፡ ነገር ግን በእረፍቱ ወቅት ለደጋፊዎች ደስታን የማይሰጡ የግጭት እና ሹም-ሽር ዜናዎች ተሰምተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በመርታት ጀምረው በሁለተኛው ጨዋታ በመከላከያ የተሸነፉት ኢትዮጵያ ቡናዎች በእረፍቱ ወቅት ከወላይታ ድቻ ጋር ያደረጉት በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የገቢ-ማሰባሰቢያ ጨዋታ ለብዙ ነገሮች መነሻ ሆኗል፡፡ በጨዋታው ላይ ግብ ጠባቂያቸው ሀሪስተን ኮአሲን በሜዳ ተጨዋችነት ቀይረው በማስገባታው ከደጋፊዎች ከፍ ያለ ተቃውሞ የገጠማቸው አሰልጣኙ ድራጋን ፖፓዲች ለተቃውሞው ረዳቶቻቸውን ምክንያት አድርገው ነበር፡፡ ጉዳዩ ተባብሶም የክለቡ ኃላፊዎች ምክትል አሰልጣኙ ዕድሉ ደረጄን ከኃላፊነት በማንሳት የተስፋ ቡድኑ አሰልጣኝ ሲያደርጉት በክረምቱ የተቀጠረው የቴክኒክ ዲሬክተሩ ደሳለኝ ግርማ ሙሉ ለሙሉ ከሃላፊነቱም ሆነ ከክለቡ እንዲሰናበት ተደርጓል፡፡ ሰርቢያዊው የቡድኑ ዋና አሰልጣኝም ቡድን በፍጥነት የዋንጫ ተፎካካሪ እንዲያደርጉት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

በሌላ በኩል ከክለቡ ጋር ግጭት ውስጥ የነበረው የቀድሞው የቡድኑ አምበል ዳዊት እስጢፋኖስ ክለቡ መልቀቂያውን ሊሰጠው ፈቃደኛ ባይሆንም ፌዴሬሽኑ ስለሰጠው ወደ ድሬዳዋ ከነማ ማቅናቱ የተሰማውም በዚህ ሊጉ በተቋረጠበት ጊዜ ነበር፡፡

የሁለቱ ሳምንታት ውጤቶች፡-

ፕሪምየር ሊጉ በሴካፋ ዋንጫ ውድድር ምክንያት ከመቋረጡ በፊት በተደረጉት የሁለት ሳምንታት ጨዋታዎች የተመዘገቡት ውጤቶች የሚከተሉት ነበሩ፡፡

የመጀመሪያ ሳምንት፡-

ኤሌክትሪክ 1-0 መከላከያ

ደደቢት 2-1 ወላይታ ድቻ

ሀዋሳ ከተማ 1-1 ሲዳማ ቡና

አርባምንጭ ከተማ 1-0 ሀዲያ ሆሳዕና

አዳማ ከተማ 2-0 ቅዱስ ጊዮርጊስ

ዳሽን ቢራ 1-0 ድሬዳዋ ከተማ

ኢትዮጵያ ቡና 1-0 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ሁለተኛ ሳምንት፡-

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 0-0 ደደቢት

መከላከያ 1-0 ኢትዮጵያ ቡና

አዳማ ከነማ 2-0 ኤሌክትሪክ

ቅዱስ ጊዮርጊስ 5-1 ሲዳማ ቡና

ሀዲያ ሆሳዕና 0-1 ዳሸን ቢራ

ድሬዳዋ ከተማ 1-1 ሀዋሳ ከተማ

ወላይታ ድቻ 1-0 አርባምንጭ ከተማ

በዚህ መሰረት ሁለቱንም ጨዋታዎቻቸውን ያሸነፉት አዳማ ከተማ እና ዳሸን ቢራ መሪ ሲሆኑ አንዱን ጨዋታውን አሸንፎ ሌላኛውን አቻ የተለያየው ደደቢት ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ አንዱን ጨዋታቸውን አሸንፈው ሌላኛውን የተረቱት ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ወላይታ ድቻ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ አርባምንጭ ከተማ፣ መከላከያ እና ኤሌክትሪክ በሶስት ነጥቦች ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡ ሁለቱንም ጨዋታዎቹን አቻ የተለያየው ሀዋሳ ከተማ በሁለት ነጥቦች፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ሲዳማ ቡና በአንድ ነጥብ እንዲሁም ባለምንም ነጥቡ ሀዲያ ሆሳዕና የመጨረሻዎቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡

በመክፈቻ ጨዋታቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ሁለት ጎሎችን ያስቆጠረው የአዳማ ከተማው ወንድወሰን ሚልክያስ እና የቡድን ጓደኛው ታፈሰ ተስፋዬ፣ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አዳነ ግርማ፣ የሀዋሳ ከተማው በረከት ይስሀቅ እና የሲዳማ ቡናው አንዱዓለም ንጉሴ በሁለት ጎሎች ከፍተኛ ጎል አግቢነቱን ይመራሉ፡፡

ሶስተኛ ሳምንት፡-

የፊታችን ቅዳሜ እና እሁድ ጥቅምት 2 እና 3 የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታዎች የሚቀጥሉ ሲሆን ቅዳሜ በ9 ሰዓት በአርባምንጭ- አርባምንጭ ከተማ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን፣ በጎንደር – ዳሸን ቢራ ወላይታ ድቻን፣ በሀዋሳ – ሀዋሳ ከተማ ሀዲያ ሆሳዕናን እንዲሁም በይርጋለም – ሲዳማ ቡና ድሬዳዋ ከተማን ያስተናግዳሉ፤ በ11 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ኤሌክትሪክ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ይፋለማሉ፡፡ እሁድ በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡና መሪው አዳማ ከነማን ሲያስተናግድ ደደቢት እና መከላከያም ይፋለማሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.