የጥሎ ማለፉ ዋንጫ የፍፃሜ ተፋላሚዎቹ ታውቀዋል

Defence 2007

 

በጊዜ ባለመጠናቀቁ ምክንያት ወደ አዲሱ ዓመት 2008 የተሻገረው የ2007 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች የጥሎ ማለፍ

ውድድር የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ማክሰኞ ከቀትር በኋላ ተካሂደዋል፡፡ ቀጣዩ ፅሁፍ ለፍፃሜ አላፊዎቹን ክለቦች ያሳወቁትን

ጨዋታዎች ለመዳሰስ ይሞክራል፡፡

መከላከያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ

ማክሰኞ በቅድሚያ የተጫወቱት የዛሬ ሁለት ዓመት በዚህ ውድድር ለፍፃሜ ደርሰው የነበሩት የኢትዮጵያ እግር ኳስ የረዥም ጊዜ

ባለታሪኮች መከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ነበሩ፡፡ ፈረሰኞቹ የፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮን እንደመሆናቸው እና በአፍሪካ ቻምፒዮንስ

ሊግ ላይ ተሳታፊ ስለሚሆኑ የተጋጣሚያቸውን ያህል ድሉ አስፈላጊያቸው ባይሆንም የጥምር ድል ባለቤት የመሆን ምኞት፣

የካቻምና ሽንፈታቸውን የመበቀል ፍላጎት እና በአዲሱ አሰልጣኝ ስር በድል የመጀመር መሻት ለጨዋታው ከፍ ያለ ትኩረት

እንዲሰጡ አድርገዋቸው ነበር፡፡ ሁለቱ ቡድኖች ወደ ሜዳ ሲገቡ አሰላለፋቸው የሚከተለው ነበር፡-

መከላከያ (4-3-3)

ግብ ጠባቂ፡- ይድነቃቸው ኪዳኔ

ተከላካዮች፡- ሙሉቀን ደሳለኝ፣ አዲሱ ተስፋዬ፣ ቴዎድሮስ በቀለ እና ነጂብ ሳኒ

አማካዮች፡- በኃይሉ ግርማ፣ ሚካኤል ደስታ እና ፍሬው ሰሎሞን

አጥቂዎች፡- ባዬ ገዛኸኝ፣ ሙሉዓለም ጥላሁን እና ምንይሉ ወንድሙ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ግብ ጠባቂ፡- ሮበርት ኦዳንካራ

ተከላካዮች፡- አለማየሁ ሙለታ፣ አስቻለው ታመነ፣ ደጉ ደበበ እና ዘካሪያስ ቱጂ

አማካዮች፡- ተስፋዬ አለባቸው፣ ምንተስኖት አዳነ እና ምንያህል ተሾመ

አጥቂዎች፡- ብሪያን ኦሞኒ፣ አዳነ ግርማ እና ራምኬል ሎክ

የጨዋታው የመጀመሪያዎቹ 15 ገደማ ደቂቃዎች የስታዲየሙን ታዳሚ ቁጭ ብድግ ያደረጉ፤ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችን በደስታ እና

በጉጉት፣ የመከላከያ ደጋፊዎችን በጭንቀት የወጠሩ፤ ገለልተኛ እግር ኳስ ወዳዶችን እኛም ሀገር እንዲህ አይነት ትንፋሽ የሚያሳጥር

እንቅስቃሴ ይታያል ወይ በሚል ግርምት ጭንቅላት ያስነቀነቁ ነበሩ፡፡ ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ በፍጥነት፣ ሀይል፣ ጀብድ እና የጎል

ሙከራዎች የታጀበው የቅዱስ ጊዮርጊስ እንቅስቃሴ ነበር፡፡ ፈረሰኞቹ ገና በሶስተኛው ደቂቃ በመሀል ተከላካዩ ደጉ ደበበ ለጥቂት

ኢላማውን የሳተ ሙከራ ጫናቸውን ሲጀምሩ በአምስተኛው ደቂቃ ከጥሩ ቅብብል በኋላ ብሪያን ኦሞኒ ከቀኝ መስመር በመሬት

ያሻገረውን ኳስ አዳነ ግርማ ደገፍ በማድረግ ጊዮርጊሶችን መሪ ያደረገች ጎል አስቆጥሯል፡፡ ወዲያውኑ መከላከያዎች ወደፊት ሄደው

ከማእዘን ምት ያገኙትን እድል ምንይሉ ወንድሙ በጭንቅላቱ ሞክሮ ሮበርት ኦዳንካራ አውጥቶበታል፡፡ በስምንተኛው ደቂቃ አዳነ

ለራምኬል ሎክ አቀብሎት በክረምቱ ከኤሌክትሪክ ፈረሰኞቹን የተቀላቀለው አጥቂ ወደ ጎል የሞከረው ወደ ውጪ ወጥቶበታል፡፡

በዚሁ ደቂቃ ላይ ምንተስኖት አዳነ መሬት አስታኮ የመታው ምትም እንዲሁ ወጥቶበታል፡፡ በዘጠነኛው ደቂቃ ኦሞኒ በቀኝ በኩል

ያገኘውን እና አንድ ተከላካይ አልፎ በግራ እግሩ አዙሮ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂውን ካለፈ በኋላ በቋሚው ተመልሶበታል፡፡

የኡጋንዳዊው ሙከራ አስደማሚ ነበር፡፡ በ10ኛው ደቂቃ ከ25 ሜትር ገደማ የተገኘን ቅጣት ምት ደጉ መትቶ በግድግዳው

የተመለሰበትን ደግሞ መትቶ ለጥቂት ወጥቶበታል፡፡ በ11ኛው ደቂቃ ዳግም በቀኝ በኩል ኦሞኒ ያሻገረውን ኳስ አዳነ

ቢያስቆጥርም ከጨዋታ ውጪ ተብሎ ተሽሮበታል፡፡ ከዚህ በኋላ የቅዱስ ጊዮርጊስ አስፈሪ ጫና (በተለይ ኦሞኒ በነበረበት ቀኝ

መስመር) ቀዝቅዞ መከላከያዎች ወደ ጨዋታው ቅኝት መግባት ችለዋል፡፡ ጫናው ቢቀዘቅዝም በ22ኛው ደቂቃ ምንያህል ተሾመ

በጥሩ ሁኔታ ያቀበለውን ኦሞኒ ቋሚ ከመለሰበት ሙከራ ጋር የሚመሳሰል ሙከራ ከቀኝ መስመር ወደ መሀል ገብቶ በመምታት

ለጥቂት ከአግዳሚው በላይ ወጥቶበታል፡፡ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ምንይሉ ከርቀት ሞክሮ ከአግዳሚው በላይ ወጥቶበታል፡፡ በ39ኛው

ደቂቃ የመከላከያን የማእዘን ምት አዲሱ ተስፋዬ በጭንቅላቱ ሞክሮ ኦዳንካራ ቢያወጣበትም ድጋሚ ገጭቶ ጎል በማድረግ አዲስ

ክለቡን አቻ ማድረግ ችሏል፡፡ የቀድሞው የወላይታ ድቻ የመሀል ተከላካይ በተለይ በአስደናቂ የመዝለል ብቃቱ በመከላከልም ሆነ

ከቆሙ ኳሶች በማጥቃቱ ረገድ የገብረመድህን ኃይሌን ቡድን እንደሚያሻሽለው ይጠበቃል፡፡ ቡድኖቹ 1ለ1 በሆነ ውጤትም

ለእረፍት ተለያይተዋል፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ እንደ ቡድኑ ሁሉ ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው የገባው የመከላከያው አማካይ ፍሬው ሰሎሞን ረዥም

ርቀት ኳስ እየገፋ እና ተጨዋቾችን እያለፈ ከመጣ በኋላ በዳካማ ውሳኔ ያቀበለው ደካማ ኳስ ለውጤት ሳይበቃ ቀርቷል፡፡

በ51ኛው ደቂቃ ምንይሉ የቅዱስ ጊዮርጊስ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ጥፋት ተሰርቶብኛል ብሎ ቢወድቅም አርቢትሩ

አልፈውታል፡፡ በ55ኛው ደቂቃ ከእረፍት መልስ ከቀኝ መስመር ወደ ግራ መስመር የተቀየረው ኦሞኒ ያሻገረውን ምንያህል

በጭንቅላቱ ሞክሮ ለጥቂት ወጥቶበታል፡፡ በ61ኛው ደቂቃ ላይ በእለቱ ከፍተኛ ሽኩቻ ሲያደርጉ የነበሩት አዲሱ የቅዱስ ጊዮርጊሱ

ተከላካይ አስቻለው ታመነ እና የመከላከያው አጥቂ ሙሉዓለም ጥላሁን ካደረጉት ትግል በኋላ አስቻለው ጥፋት በመስራቱ

የተሰጠውን የቅጣት ምት ምንይሉ አሻግሮ በኃይሉ ግርማ በጭንቅላቱ በመግጨት ጎል ማስቆጠር እና ለቡድኑ ያልተገመተ መሪነትን

መስጠት ችሏል፡፡ ለዚህች ጎል የኦዳንካራ የጊዜ አጠባበቅ ስህተትም እንደምክንያት ሊነሳ ይችላል፡፡ ከዚህ ጎል በኋላ መከላከያዎች

የመጀመሪያ ቅያሬያቸውን በማድረግ ባዬ ገዛኸኝ ወጥቶ ሳሙኤል ታዬ ተክቶታል፡፡ የቡድኑ ፎርሜሽንም ከ4-3-3 ወደ 4-4-2

ተቀይሯል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በበኩላቸው የፎርሜሽን ለውጥ ባያደርጉም በ70ኛው ደቂቃ ተስፋዬ አለባቸውን በወጣቱ ሚኪያስ

ግርማ እና በ79ኛው ደቂቃ አዳነን በፍፁም ገብረማሪያም ተክተዋል፡፡ በነዚህ ደቂቃዎች መካከልም በኦሞኒ አማካይነት

በጭንቅላት እና በመሬት ለመሬት ምት ኢላማቸውን ያላገኙ ሙከራዎችን አድርገዋል፡፡ በ83ኛው ደቂቃ ጠንከር ያለ የሚመስል

የትከሻ ጉዳት የደረሰበት የመከላከያው የመሀል ተከላካይ ቴዎድሮስ በቀለ በታፈሰ ሰርካ ሊቀየር ተገዷል፡፡ 86ኛው ደቂቃ በጨዋታው

ከታዩ አስደናቂ ክስተቶች አንዱን ያሳየን ነበር፡፡ ራምኬል ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ምንተስኖት አዳነ በአስደናቂ መንገድ

በጭንቅላቱ በመግጨት ወደ ጎል ሲመራው ሁሉም ሰው ጎል ለመሆኑ እርግጠኛ ሆኖ ነበር – ከመከላከያው ግብ ጠባቂ ይድነቃቸው

ኪዳኔ በስተቀር፡፡ ይድነቃቸው እጅግ በሚያስደንቅ መንገድ ከአግዳሚው ስር ኳሷን በማውጣት እንደስሙ ሁሉን ያስደነቀ ተግባር

ፈፅሟል፤ ቡድኑንም ታድጓል፡፡ በ88ኛው ደቂቃ በመከላከያ በኩል አዲሱ ግዙፍ አጥቂያቸው ካርሎስ ዳምጠው ምንይሉን ተክቶ

ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡ ጊዮርጊሶች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ያላቸውን ኃይል ሁሉ ለማጥቃት ሲያውሉ መከላከያዎች በፈጣን መልሶ

ማጥቃት እየሄዱ በፍሬው እና ሙሉዓለም አማካይነት እድሎችን ፈጥረው አልተጠቀሙባቸውም፡፡ ጨዋታውም በመከላከያ 2ለ1

አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ መግለጫዎች የአሸናፊው መከላከያ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የዝግጅት ጊዜ

ስላጠራቸው በደንብ የተዋሀደ ቡድን ማሳየት እንዳልቻሉ ገልፆ ባለፈው ዓመት የጀመሩትን በወጣት እና አዳዲስ ተጨዋቾች ላይ

ትኩረት ማድረግን እንደሚቀጥሉበት አረጋግጧል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሆላንዳዊ አሰልጣኝ ማርቲን ኩፐር በበኩላቸው

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተመለከትነውን አይነት ኳስ ቁጥጥር ላይ ትኩረት አድርጎ የሚጫወት ፈጣን ቡድን መገንባት

ዓላማቸው እንደሆነ እና ለፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮንነት እና ለተሻለ የቻምፒዮንስ ሊግ ጉዞ የሚታገል ቡድን ለማሳየት እንደሚሰሩ

ገልፀዋል፡፡

ሀዋሳ ከነማ ከወላይታ ድቻ

በመሀል ከዘነበው ዝናብ በኋላ በሁለቱ የደቡብ ክለቦች መካከል የተደረገው ፍልሚያ የመጀመሪያው አጋማሽ ከተጠበቀው በታች

የቀዘቀዘ፣ በሙከራዎች ያልታጀበ ቀዝቃዛ ግማሽ ነበር፡፡ ምርጡ አማካያቸው ታፈሰ ሰሎሞንን በጉዳት ማጫወት ያልቻሉት

ሀዋሳዎች ኳሱን በመቆጣጠር እና ከኋላ መስርተው በመሄድ ጥሩ የነበሩ ቢሆንም በተጋጣሚያቸው ክልል የነበራቸው ውህደት እና

ፈጠራ እምብዛም ጥሩ አልነበረም፡፡ ከቋሚ ተሰላፊዎቻቸው ከግማሽ የበለጡትን በሌሎች ክለቦች የተነጠቁት ድቻዎች

በበኩላቸው የምናውቀውን ወኔ፣ ኃይል እና የላቀ የማሸነፍ ስሜት አላሳዩንም፡፡ አላዛር ፋሲካ ለድቻ እና ሙጂብ ቃሲም ለሀዋሳ

በጭንቅላት በመግጨት ካደረጓቸው ሙከራዎች በቀር በዚህ የመጀመሪያ አጋማሽ ብዙ የጎል ሙከራዎች አልተመለከትንም፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ ግን የተሻለ ነበር፡፡ በ55ኛው ደቂቃ ዳግመኛ ሀዋሳን የተቀላቀለው በረከት ይስሀቅ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው

ሲመለስበት፣ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ የበረከት የአጥቂ አጣማሪ አመለ ሚልክያስ መሀል ለመሀል በተሰነጠቀለት ኳስ ከግብ

ጠባቂው ፊት ለፊት ቢገናኝም እድሉን አምክኖታል፡፡ በ65ኛው ደቂቃ የሀዋሳው ግብ ጠባቂ ኳስ ይዞ፣ ለቅቆ፣ ከዚያ መልሶ

በመያዙ ፍፁም ቅጣት ክልል ውስጥ ለድቻ ሁለተኛ ቅጣት ምት ቢሰጥም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡ በ72ኛው ደቂቃ አመለ ሌላ

መልካም እድል አግኝቶ በጭንቅላቱ ገጭቶ ቢሞክረውም ወጥቶበታል፡፡ በ75ኛው ደቂቃ በመጀመሪያ በረከት በመቀጠል ሌሎቹ

ጓደኞቹ ወደ ጎል ደጋግመው ቢሞክሩም ድቻዎች ተረባርበው መመለስ ችለዋል፡፡ በ77ኛው እና 81ኛው ደቂቃዎች ላይ ድቻዎች

ከግራ እና ቀኝ ክንፎች በተሻገሩ ኳሶች በጣም ጥሩ የጎል እድሎች ቢፈጥሩም ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል፡፡ ወዲያው ግን ሀዋሳዎች

ወደ ፊት ሄደው በረከት የተሰጠውን ኳስ ተቆጣጥሮ በጥሩ አጨራረስ በማስቆጠር የውበቱ አባተን ቡድን አሸናፊ ማድረግ ችሏል፡፡

አሰልጣኝ ውበቱ ከድሉ በኋላ ከጋዜጠኞች ጋር በነበረው ቆይታ የዝግጅት እጥረትን ሲያነሳ የሜዳውን አመቺ አለመሆንም

እንደፈለጉት ላለመጫወታቸው ምክንያት አድርጓል፡፡ የድቻው አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በበኩሉ የበርካታ ተጨዋቾችን መልቀቅ

ተከትሎ አዲስ ቡድን ለመገንባት እየጣረ እንደሆነ እና በጊዜ ሂደት የሚሻውን ቡድን የማየት ተስፋውን ተናግሯል፡፡

 የመከላከያ እና የሀዋሳ ከነማ የፍፃሜ ጨዋታ የፊታችን ቅዳሜ መስከረም 15 በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል፡፡

 አሸናፊው ቡድን በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ ተሳታፊ ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.