የዮሐንስ ዋልያዎች በሽንፈት ጀምረዋል

Ethiopia vs Zambia - 06072015-2

Ethiopia vs Zambia - 06072015-2

በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሚመራው አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ2017ቱ የአፍሪካ ዋንጫ እና ለ2016ቱ የቻን ውድድር ላይ ለመገኘት ለሚያደርጋቸው የማጣሪያ ጨዋታዎች ዝግጅቱን ከጀመረ ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ በዋልያዎቹ አለቅነታቸው ስኬታማ መሆን ያልቻሉትን ማሪያኖ ባሬቶን ተክተው የአሰልጣኝነት ኃላፊነቱን የያዙት ዮሐንስ ሳህሌ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 44 ተጨዋቾችን መርጠው ከሁለት ቀናት የልምምድ ጨዋታዎች በኋላ ስብስባቸውን ወደ 24 የቀነሱ ሲሆን፣ ከነዚህ ተጨዋቾች ጋር ካደረጉት የጥቂት ቀናት ልምምድ በኋላ ደግሞ ከዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የአቋም መለኪያ የወዳጅነት ጨዋታ አድርገዋል፡፡ በበርካታ ወጣት እና የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ልምድ የሌላቸው ተጨዋቾች የተዋቀረው ቡድን እሁድ ከቀትር በኋላ የዛምቢያ አቻውን በሜዳው ለመግጠም ወደ ሜዳ ሲገባ ይዞት የገባው አሰላለፍ የሚከተለው ነበር፡-

ግብ ጠባቂ፡- አቤል ማሞ (ሙገር ሲሚንቶ)

ተከላካዮች፡- ሞገስ ታደሰ (ሲዳማ ቡና)፣ አስቻለው ታመነ (ደደቢት)፣ ሙጂብ ቃሲም (ሀዋሳ ከነማ)፣ ዘካሪያስ ቱጂ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

አማካዮች፡- ጋቶች ፓኖም (ኢትዮጵያ ቡና)፣ ምንተስኖት አዳነ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ በኃይሉ አሰፋ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ አስቻለው ግርማ (ኢትዮጵያ ቡና)

አጥቂዎች፡- ባዬ ገዛኸኝ (ወላይታ ድቻ) እና ቢኒያም አሰፋ (ኢትዮጵያ ቡና)

በተመሳሳይ በአዳዲስ ወጣት ተጨዋቾች የተገነባው የዛምቢያ ብሔራዊ ቡድንም የሚከተሉትን ተጨዋቾች በመጀመሪያ ተሰላፊነት ተጠቅሟል፡፡

ግብ ጠባቂ፡- ዳኒ ሙኒያኦ (ሬድ አሮውስ / ዛምቢያ)

ተከላካዮች፡- ካባሶ ቾንጎ (ቲ.ፒ ማዜምቤ / ሪ.ዲ.ኮንጎ)፣ አሮን ካቴምቤ (ፕላቲነም / ዚምባቡዌ)፣ ክርስቶፈር ሙንትሀሊ (ፓወር ዳይናሞስ / ዛምቢያ)፣ ፋክሰን ካፑምቡ (ዛናኮ / ዛምቢያ)

አማካዮች፡- ናታን ሲንካላ (ቲ.ፒ ማዜምቤ / ሪ.ዲ.ኮንጎ)፣ ኮንድዋኒ ምቶንጎ (ዜስኮ ዩናይትድ / ዛምቢያ)፣ ሉባምቦ ሙሶንዳ (ኡሊሴስ ዬሬቫን / አርሜኒያ)፣ አለን ሙኩካ (ግሪን ቡፋሎስ / ዛምቢያ)

አጥቂዎች፡- ኤቫንስ ካንግዋ (ሀፖኤል ራአናና / እስራኤል) እና ጊቭን ሲንጉሉማ (ቲ.ፒ ማዜምቤ / ሪ.ዲ.ኮንጎ)

ዝርግ 4-4-2 የመሰለ ፎርሜሽን ይዞ ወደ ሜዳ የገባው በበኃይሉ አሰፋ አምበልነት የተመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታውን ሞቅ ባለ ስሜት እና እንቅስቃሴ ቢጀምርም መልካሙ እንቅስቃሴው ከ15 ደቂቃዎች ያለፈ አልነበረም፡፡ ቡድኑ ቀስ በቀስ እየወረደ ከ20 እና 25 ደቂቃዎች በኋላ የጨዋታው የበላይነት በዛምቢያዊያኑ እጅ ገብቷል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ከባዬ ገዛኸኝ እና ምንተስኖት አዳነ ከሩቅ ተመትተው ኢላማቸውን ካልጠበቁ ሙከራዎች እና ከመስመር ተሻግረው ለጥቂት ለአጥቂዎች ሳይደርሱ ከቀሩ ኳሶች በቀር ዋልያዎቹ የተጋጣሚያቸውን ተከላካዮች ጥሰው ለመግባት እና የጎል ሙከራዎች ለማድረግ የተሳናቸው ሲሆን ተመሳሳይ 4-4-2 ፎርሜሽንን በተሻለ የተጠቀሙበት የመሰሉት ዛምቢያዊያኑ በአንጻሩ በአሮን ካቴምቤ በጭንቅላት ተገጭቶ በግብ ጠባቂው አቤል ድንቅ ጥረት ጎል ከመሆን የተረፈው፣ ሉባምቦ ሙሶንዳ መትቶት ለጥቂት የወጣበት እና ናታን ሲንካላ ከቅርብ ርቀት ሞክሮት በሙጂብ ቃሲም አስደናቂ ሸርተቴ የተመለሰበት የሚጠቀሱ ጥሩ የጎል አጋጣሚዎች መፍጠር ችለዋል፡፡ ቺፖሎፖሎ (ጥይቶቹ) ይህ ጫናቸው በሙከራዎች ብቻ ሳይገደብም በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻው ደቂቃ ከአስደናቂ የመልሶ ማጥቃት የተገኘውን እና ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ በአለን ሙኩካ አማካይነት አስቆጥረው መሪነቱን ይዘዋል፡፡ የዋልያዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ በአጠቃላይ ሲታይ የአማካይ ክፍሉ እና አጥቂ ክፍሉ ግንኙነት መሰበር፣ የሁለቱ የመስመር ተከላካዮች ወደ ፊት ሄዶ ማጥቃቱን ማገዝ አለመቻል እና የሁለቱ አጥቂዎች የቅንጅት ችግር የታየበት ነበር፡፡ ከተከላካይ ክፍሉ የተሻለ ብቃት ሌላም ከዮሐንስ ቡድን የሚጠቀስ መልካም ነገር አልነበረም፡፡

Ethiopia vs Zambia - 06072015-1

ሁለተኛው አጋማሽ የተጀመረው በዋልያዎቹ በኩል ግብ ጠባቂው አቤል በደደቢቱ ታሪክ ጌትነት፣ ጥንዶቹ አማካዮች ጋቶች ፓኖም እና ምንተስኖት አዳነ በወላይታ ድቻው ብሩክ ቃልቦሬ እና በመከላከያው ፍሬው ሰሎሞን ተተክተው ነበር፡፡ ጥይቶቹ ካረፉበት በመቀጠል ይህም አጋማሽ እንደተጀመረ ሁለት ተከታታይ አስደንጋጭ የጭንቅላት የተገጩ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል፡፡ ነገር ግን የዮሐንስ ልጆች ቀስ በቀስ ጨዋታውን በመቆጣጠር ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መንቀሳቀስም ሆነ እውነተኛ የጎል እድሎችን መፍጠር ችለው ነበር፡፡ ተቀይረው የገቡት አማካዮች ጨዋታውን በበጎ መለወጥ ሲችሉ በተለይም ፍሬው ሰሎሞን ቡድኑ አጥቶት የነበረውን ኳስ ቁጥጥር እና ፈጠራ ማበርከት ችሏል፡፡ የመከላከያው አማካይ ከቢኒያም አሰፋ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ በቀጥታ ወደ ጎል ሞክሮት በግብ ጠባቂው ዳኒ ሙኒያኦ ተጨርፎ የወጣበት ሙከራ እጅግ አስደናቂ እና ደጋፊውን በስሜት ያቆመ ነበር፡፡ ከደቂቃዎች በኋላም ራሱ ፍሬው በረዥሙ ለቢኒያም አቀብሎት የኢትዮጵያ ቡናው አጥቂ ለክለብ ጓደኛው አስቻለው ግርማ ያቀበለው እና አስቻለው ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል እየገፋ የገባውን ኳስ ሳይጠቀምበት በፊት በዛምቢያው ተከላካይ በመጠለፉ ዋልያዎቹ የፍፁም ቅጣት ምት ማግኘት ችለው ነበር፡፡ ነገር ግን ቢኒያም ወደ አየር በማንሳፍ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ እንደ ሳውዝሀምፕተኑ ኤማኑኤል ማዩካ አይነት ተጨዋቾችን ቀይረው ያስገቡት ጥይቶቹ በተሻሻለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና ምናልባትም በታወቀው የአልቲቲዩድ ተፅዕኖ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም በዚህ ግማሽ ከመጀመሪያው አንጻር ተዳክመው ቢታዩም ከላይ ከተጠቀሱት የጭንቅላት ሙከራዎች በተጨማሪ ከታሪክ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተው በግብ ጠባቂው የተመለሰባቸው አይነት ሙከራዎችን ግን አድርገዋል፡፡ ጨዋታው ወደ መጠናቀቂያው ሲቀርብ አምበሉ በኃይሉ አሰፋ እና አጥቂው ባዬ ወጥተው በኤሌክትሪኩ ራምኬል ሎክ እና በሙገር ሲሚንቶው ኤፍሬም ቀሬ ሲተኩ የመሀል ተከላካዩ ሙጂብ በሁለት የማስጠንቀቂያ ካርዶች ከሜዳ ተሰናብቷል፤ ጨዋታውም የዛምቢያ የ1ለ0 ድል ተጠናቋል፡፡

አሰልጣኞቹ ምን አሉ?

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ፡

“ዓላማችን ከህዝብ፣ ሚዲያ እና ተጋጣሚ ጫና ጋር የመጫወትን ከባድ ኃላፊነት ለወጣቶቹ ተጨዋቾቻችን ለማሳየት ነበር እናም ተሳክቶልናል፡፡እንደ እነ አቤል፣ አስቻለው፣ ዘካሪያስ እና ሙጂብ አይነቶቹ ከጠበቅነው በላይ ጥሩ ሲጫወቱ እነባዬ ትንሽ ተቸግረው ነበር፡፡ ልምድ ካላቸው ከእነበኃይሉም የጠበቅነውን አላገኘንም፡፡”

“በመጀመሪያው አጋማሽ ጋቶች እና ምንተስኖት ያዘዝናቸውን ባለማድረጋቸው አማካይ ክፍሉ ልክ አልነበረም፡፡ ጋቶች የበለጠ በመከላከሉ እና ምንተስኖት የበለጠ በማጥቃቱ እንዲሳተፉ ነግረናቸው ነበር፡፡ ግን ሁለቱም ጎል ለማግባት በመጓጓት ቦታቸውን ጠብቀው መጫወት አልቻሉም፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ የቀየርናቸው ብሩክ እና ፍሬው ይህን ችግር ፈትተዋል፤ ቡድኑም ጥሩ መሆን ችሏል፡፡”

“ዓላማዬ የተሰጠኝን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችለኝን ቡድን መገንባት እንጂ የቀጣዩን ትውልድ ቡድን መገንባት አይደለም፡፡ መቼ ከኃላፊነት እንደምነሳም አላውቅም፡፡”

አሰልጣኝ ኦነር ጃንዛ፡

“ከወሳኝ የማጣሪያ ጨዋታ በፊት እንዲህ አይነት ጠንካራ ጨዋታ በማግኘታችን ኢትዮጵያን እናመሰግናለን፡፡ ቡድናችን በአዲስ መልክ እየተገነባ በመሆኑ ስለሚመጣው ውጤት ፍርሀት አልነበረንም፡፡ ምክንያቱም ጥሩ ቡድን በአንድ ቀን መገንባት አይቻልም፡፡”

“የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሩ ጎኖች አሉት፡፡ ግን ወደፊት ሲሄድ ያለበትን የአጨራረስ እና የቴክኒክ ችግሮች መፍታት ይኖርበታል፡፡”

Ethiopia vs Zambia - 06072015-3

ዋልያዎቹ ሲመዘኑ፡

አቤል ማሞ፡ የሙገር ሲሚንቶው ግብ ጠባቂ በአየር ላይ የሚላኩ ኳሶች ላይ ጥሩ ብቃት ቢያሳይም በተቆጠረው ጎል ላይ ካደረገው የተሻለ ማድረግ ይጠበቅበት ነበር፡፡

ታሪክ ጌትነት፡ ተቀይሮ የገባው ታሪክ ከዛምቢያ አጥቂ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ መመለስ ቢችልም የኳስ ስርጭቱ ደካማ ነበር፤ ይህ ድክመቱ በተወሰኑ አጋጣሚዎችም ችግር ውስጥ ከቶት ነበር፡፡

ሞገስ ታደሰ፡ አግሬሲቩ የሲዳማ ቡና ተከላካይ ከመስመር ተከላካይ የሚፈለገው ቅልጥፍና እና ፍጥነት ሲጎድለው የሚወርዳቸው ሸርተቴዎች አደገኛ ነበሩ፤ ግልፍተኛም ነበር፡፡

አስቻለው ታመነ፡ ይህ ወጣት በአስደናቂ ፍጥነት አስተማማኝ ተከላካይ እየሆነ ነው፡፡ ከጥፋቶች የራቀው ርጉው የደደቢት ፍሬ በመጀመሪያ ኢንተርናሽናል ጨዋታው ጥሩ ጊዜን አሳልፏል፡፡

ሙጂብ ቃሲም፡ የሀዋሳው ተከላካይ በሁለት የቢጫ ካርዶች ከሜዳ ቢወጣም ከአስቻለው ጋር ጥሩ የመሀል ተከላካይ ጥምረት ፈጥሮ ታይቷል፡፡

ዘካሪያስ ቱጂ፡ የዘንድሮው የቅዱስ ጊዮርጊስ ክስተት በመከላከሉ ረገድ ሁሉንም ያስደነቀ ምርጥ እንቅስቃሴ ቢያሳይም ባልተለመደ መልኩ ወደፊት ሄዶ የመስመር አጋሩን በማገዝ ረገድ ጥሩ አልነበረም፡፡ ኳሶች ከቀማ በኋላ በትክክል የማቀበል ስኬቱም መልካም አልነበረም፡፡

ጋቶች ፓኖም፡ ዘንድሮ በሊጉ በኢትዮጰያ ቡና ማልያ በእጅጉ ተሻሽሎ የታየው አማካይ የተሰጠውን ተከላካዮቹን ከጥቃት የመከላከልም ሆነ የቡድኑ ሚዛን የመጠበቅ ኃላፊነቶች መወጣት አልቻለም፡፡

ምንተስኖት አዳነ፡ የቅዱስ ጊዮርጊሱም አማካይ እንዲሁ ሊያስታውሰው የማይወደውን ጨዋታ አሳልፏል፡፡ ምንተስኖት አማካይ እና አጥቂ ክፍሉን የማገናኘት ተግባሩን ሊወጣ አልቻለም፡፡

ብሩክ ቃልቦሬ፡ ጋቶችን ተክቶ የገባው የወላይታ ድቻው አማካይ ለተከላካይ ሽፋን በመስጠት እና የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ ረገድ ተሽሎ ታይቷል፡፡ የኳስ ስርጭቱ ፍጥነት ግን ጥያቄ የሚነሳበት ነበር፡፡

ፍሬው ሰሎሞን፡ ከእረፍት በኋላ ዋልያዎቹ የተሻለ ለመጫወታቸው የመከላከያው አማካይ ወደ ሜዳ መግባት ቀዳሚ ተጠቃሽ ምክንያት ነበር፡፡ የፍሬው ድሪብሎች፣ የሚያቀብላቸው ኳሶች እና ከአጥቂዎቹ ጋር የፈጠረው ቅንጅት በፈዘዘው ቡድን ላይ ነፍስ ዘርተውበታል፡፡

በኃይሉ አሰፋ፡ የፕሪምየር ሊጉ ኮከብ ዝም ያለ ቀትር አሳልፏል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አማካይ እንደአምበልነቱ በንግግር ቡድኑን ለመምራት ከመሞከሩ ባለፈ እንቅስቃሴው ጓደኞቹን ለመምራትም ሆነ ለማነሳሳት በቂ አልነበረም፡፡

አስቻለው ግርማ፡ ለእሱ ተፈጥሯዊ ባልሆነ የግራ አማካይ ስፍራ የተጫወተው የኢትዮጵያ ቡናው የመስመር አማካይ/አጥቂ ለፍፁም ቅጣት ምቱ መገኘት ምክንያት ቢሆንም እና የሁልጊዜ ታታሪነቱ ባይለየውም በፈጠራ እና የማጥቃት ስጋት በመፍጠር ረገድ ብዙም ጥሩ አልነበረም፡፡

ባዬ ገዛኸኝ፡ የወላይታ ድቻው አጥቂ ከአጋሩ ጋር መግባባት ሳይችል፣ የሚያገኛቸውንም ኳሶች በሚገባ ለመጠቀምም ሆነ ለማቀበል ተቸግሮ ነበር፡፡

ቢኒያም አሰፋ፡ በተጠናቀቀው የሊግ ውድድር ባለብዙ ጎል ኢትዮጵያዊ የነበረው ቢኒያም ላመከነው የፍፁም ቅጣት ምት እና ለፍሬው አስደናቂ ሙከራ ምክንያት ቢሆንም በአጠቃላይ ግን እምብዛም ጥሩ ያልነበረ ጨዋታን አሳልፏል፡፡

ራምኬል ሎክ እና ኤፍሬም ቀሬ፡ ለምዘና የሚያበቃ የጨዋታ ጊዜ አልነበራቸውም፡፡

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ፡ ኃላፊነቱን ከያዙ ገና ጥቂት ሳምንታት እንደመቆጠራቸው እና ተጨዋቾቻቸውን ካገኙ ሳምንት እንኳን እንደአለመሙላቱ ለቡድኑ የቅንጅትም ሆነ ሌሎች ችግሮች ትችት ማቅረብ ፍትሀዊ አይሆንም፡፡

ሌሎች ጉዳዮች፡

  • ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታቸውን ለማድረግ ወደ ሜዳ ሲወጡ ብሔራዊ መዝሙሮቻቸውን በተለመደው መንገድ ከሲዲ ማጫወቻ ወይም ቴፕ ሬከርደር ማሰማት ሳይቻል ቀርቶ ከኳስ አቀባይ ታዳጊ እና ከአንድ የዛምቢያ ቡድን አባል በድምፅ ማጉያ እንዲዘመር መደረጉ እጅግ አነጋጋሪ እና አሳፋሪም ክስተት ነበር፡፡
  • የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሌሶቶ ጋር የሚያደርገውን ወሳኝ የአፍሪካ ጨዋታ በቀጣዩ እሁድ፣ ሰኔ ሰባት፣ በባህር ዳር ስታዲየም ያካሂዳል፡፡ እዚያው ዝግጅቱን ለማድረግም ወደ ባህር ዳር አምርቷል፤ የሌሶቶ አቻው ሀሙስ ኢትዮጰያ እንደሚገባ ይጠበቃል፡፡
  • በውጪ ሀገራት ከሚጫወቱ እና ለብሔራዊ ቡድኑ ከተጠሩት አራት ተጨዋቾች መካከል የቢድ ቬትሱ ጌታነህ ከበደ እና የፔትሮ ጄቱ ሽመልስ በቀለ እንዲሁም የአሌክዛንድሪያው ኡመድ ኡኩሪ ከቡድኑ ጋር ወደባሕር ዳር ያቀኑ ሲሆን የአል-አህሊው ሳልሀዲን ሰዒድ በቀጣዮቹ ቀናት ቡድኑን እንደሚቀላቀል ይጠበቃል፡፡

 

 

1 thought on “የዮሐንስ ዋልያዎች በሽንፈት ጀምረዋል

  1. Stupid yohanes Sahile. Opportunist. We know you from your playing days. U do not deserve to be a coach of the national team. Aderbay.

Leave a Reply

Your email address will not be published.