የዋሊያዎቹ የአጨራረስና ቅንጅት ችግር የማን?

Coach Sahle  inset

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ባለፈው ዕሁድ ወደ ሲሼልስ አቅንቶ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ አቻ ተለያይቶ መመለሱ ይታወሳል፡፡ ይህ ጨዋታ ዋሊያዎቹ በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ አመራር ያደረጉት አራተኛ የፉክክር ጨዋታ ሲሆን ከዚህ በፊት ሁለት የሜዳ ጨዋታዎችን (ሌሴቶ እና ኬንያ) አሸንፈው ከሜዳቸው ውጭ ከኬንያ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ይህ ቁጥር በግርድፉ ሲታይ ጥሩ ሊባል ይችላል፡፡ በተለይ ኬንያን በደርሶ መልስ ጨዋታ መርታት የማይናቅ ውጤት ነው፡፡ ነገር ግን ከሲሼልስ ጋር የተመዘገበው የአቻ ውጤት ብቻውን የብሔራዊ ቡድኑ ዋነኛ ዓላማ የሆነውን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ተስፋ ስጋት ውስጥ የከተተ ሆኗል፡፡ ቡድኑ በዕለቱ ያሳየው እጅግ ደካማ አቋም ጨዋታውን የተመለከቱ ሰዎችን ያላስደሰተ ሲሆን ይህ ፍፁም ያልተጠበቀ ውጤትም ብዙሀኑን ደጋፊ ማስደንገጡ እና ማስከፋቱም አልቀረም፡፡ የአሰልጣኝ ዮሐንስ ዋሊያዎች በሲሼልሱ ጨዋታ ላይ ያሳዩት እንቅስቃሴ፣ የአሰልጣኙ እና ተጫዋቾች የድህረ ጨዋታ ቃለ መጠይቆች አንዳንድ ሀሳቦችን እንድናነሳ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ከሀገር ውጭ የሚጫወቱ ተጫዋቾች፣ የተጫዋች ቅያሪ፣ ታክቲክ እና የቻይናን ጉዳይ በቀጣዩ ፅሁፍ ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡

የአጨራረስ ችግር

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኝ ዮሐንስ የተፈለገው ውጤት ላለመገኘቱ የተገኙ የጎል ማግባት አጋጣሚዎችን አለመጠቀምን ምክንያት አድርገዋል፡፡ የቡድኑ አማካይ ሽመልስ በቀለም ከስፖርት ዞን ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ያገኟቸውን ዕድሎች ያለመጠቀም እንጂ በአራት እና አምስት ጎል ልዩነት ማሸነፍ ይችሉ እንደነበር ተናግሯል፡፡ አንዳንድ የሚዲያ ሰዎችም ይህን ሀሳብ ደግፈዋል፡፡ በግልፅ እንነጋገር እና እውነት ችግሩ ይህ ብቻ ነበር? እርግጥ ነው የቡድኑ አጥቂዎች ጌታነህ ከበደ (በራስ ወዳድነት ሁለት ወይም ሶስት) እና ሳላህዲን ሰይድ (ከእርሱ በማይጠበቅ አጨራረስ አንድ) የጎል ዕድሎችን አበላሽተዋል፡፡ ነገር ግን ሲሼልሶችም ከዋልያዎቹ የበለጡ የጎል ዕድሎችን ፈጥረው ነበር፡፡ በተለይ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ያገኟቸውን ዕድሎች ቢጠቀሙ ኖሮ የዮሀንስን ቡድን ለበለጠ ውርደት ሊዳርጉት አልነበረምን? ሲሼልሶች በመጀመሪያው ግማሽ ያሳዩት የላቀ የበላይነት የሚያስገርም እና ኢትዮጵያውያን ደጋፊዎችን ቶሎ እረፍት በወጡ ብለው እስከመመኘት እንዲደርሱ ያደረገ ነበር፡፡ ታዲያ በየትኛው የገዘፈ ልዩነት ነው አጨራረስ ብቻውን እንደሰበብ የሚቀርበው?

የቡድን ቅንጅት ችግሩ የማነው?

አንድ ቡድን የመደራጀት እና የመቀናጀት እንዲሁም የሽግግር ችግሮች ከታዩበት ተቀዳሚ ተጠያቂው ማነው? ተጫዋቾች ወይስ አሰልጣኙ? የዝግጅት ግዜ ማጠር? የአቋን መለኪያ ጨዋታዎች ማነስ? እርግጥ የተጠቀሱት ጉዳዮች ሁሉ በተለያየ መጠን ለዚህ ችግር ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ምናልባትም በደረጃ ካስቀመጥናቸው እንደ እኔ አመለካከት በመጀመሪያ አሰልጣኙ በመቀጠል የዝግጅት ግዜ ከዚያ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ማነስ እና ተጫዋቾች በቅደም ተከተል መቀመጥ አለባቸው፡፡ የዮሐንስ ቡድን በሲሼልሱ ጨዋታ ላይ ለታዩበት እጅግ የገዘፉ የቅንጅት፣ መደራጀት እና ሽግግር ችግሮች ግን ተቀዳሚ ተጠያቂ እየተደረጉ ያሉት ተጫዋቾች እና የአቋም መለኪያ ጨዋታ ማነስ ናቸው፡፡ የእነርሱም ተጠያቂ መሆን ተገቢነቱ እንዳለ ሆኖ ግን ለዝግጅት ከአንድ ወር ተኩል የበለጠ ግዜ የተሰጣቸው አሰልጣኙ ኃላፊነቱን አለመውሰዳቸው እና በርካቶቹ ሚዲያዎችም ተጠያቂነቱን ከእርሳቸው ላይ ማሸሻቸው ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ነው፡፡ አሰልጣኝ ዮሐንስ ለበርካታ ሳምንታት አብረዋቸው በቆዩት ተጫዋቾች ፋንታ ለጥቂት ቀናት ያገኟቸውን ከውጭ የመጡ ተጫዋቾች መምረጣቸው ለቅንጅት ችግሩ ምክንያት ሊሆንስ አይችልምን? ለተጫዋቾች የሚጠቀሙትን ታክቲክ እንዲረዱ እና እንዲተገብሩ አለማስቻልስ ችግር አይደለም? የዝግጅት ግዜው ረዘም የማለቱ ዋነኛ ዓላማ እንደዚህ አይነቶቹን ችግሮች ለማቃለል ተብሎ የተደረገ መሰለኝ፡፡

ታክቲክ

በቪክቶሪያው ጨዋታ አሰልጣኙ ይዘውት የቀረቡትን ታክቲክ እና ስትራቴጂያቸውን ለመረዳት ይቸግራል፡፡ ዮሐንስ በቅድመ ጨዋታ መግለጫቸው ላይ 4-3-1-2 ፎርሜሽንን እንደሚጠቀሙ ሲገልፁ ምክንያታቸውም ጋቶች ፓኖም በኤፍሬም አሻሞና ዑመድ ኡኩሪ እየታገዘ ሽመልስ ነፃ ሚና እንዲኖረው ማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ጨዋታው ላይ የተመለከትነው ግን ፍፁም ከዚህ የተለየ ነገርን ነበር፡፡ ጋቶች ረዳት አጥቶ ሲቸገር የግራ እና የቀኝ ተከላካዮቹም (በተለይ ዑመድ ይጫወትበት በነበረው መስመር በኩል) ያለ አጋዥ ሲሰቃዩ አምሽተዋል፡፡ ከሽመልስ በስተቀር ይህ አሰላለፍ የተመቸው ተጫዋች ማስታወስ ያስቸግራል፡፡ ሁለቱ አጥቂዎች ጌታነህ ከበደ እና ሳላህዲን ሰይድ እንዲሁም ዑመድ ኡኩሪ በብሔራዊ ቡድኑ ማልያ በግላቸው ካሳለፏቸው መጥፎ ቀናት አንዱን አሳልፈዋል፡፡ እነዚህን ሶስት ተጫዋቾች አንድ ላይ የመጠቀም ግዴታ ውስጥ መግባት ለምን አስፈለገ የሚለው ጉዳይም ሌላ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡ እንደ አስቻለው ግርማ አይነት ተፈጥሯዊ የመስመር አማካይ እያለ ዑመድን በሚከብደው ስፍራ ማሰለፍ፣ እንደ ባዬ ገዛኸኝ አይነት የተለየ ባህሪ ያለው አጥቂ እያለ ሁለት አንድ አይነት ባህሪ ያላቸው አጥቂዎችን አንድ ላይ ማሰለፉ ለምን እንዳስፈለገም ለመረዳት ያዳግታል፡፡

የቻይና ጉዳይ

በድህር ጨዋታ ቃለ መጠይቅ ላይ ተነስተው አነጋጋሪ ከሆኑት ነጥቦች አንዱ የኢቢኤስ ቲቪ ስፖርት ጋዜጠኛ ፍስሀ ይድነቃቸው የሲሼልስ እና ኢትዮጵያን የሕዝብ ብዛት በንፅፅር በመጥቀስ እንዴት የ90 ሚሊዮን ሕዝብ ባለቤቷ ሀገር 90 ሺህ ሕዝብ ባላት ሀገር ነጥብ እንደጣለች የጠየቀበት፣ አሰልጣኝ ዮሐንስ እንደዛ ከሆነ ቻይና ለምን ውጤታማዋ የእግር ኳስ ሀገር አልሆነችም በማለት የሠጡት ምላሽ እና ይህን ምላሽ ተከትሎ ጋዜጠኛው የጥያቄውን ጭብጥ በማመላከት ደግሞ ቢጠይቅም አሰልጣኙ ለመመለስ ፈቃደኛ አለመሆናቸው ነበር፡፡ በዚህ ሁሉንም ባነጋገረ እና ባከራከረ ርዕስ ላይ (የሕዝብ ብዛት እና የእግር ኳስ ስኬት ግንኙነት) አሰልጣኙ የራሳቸውን አመለካከት የመግለፅ መብታቸውን ብንደግፍም ምላሹን የሰጡት የጋዜጠኛውን አተያይ በሚያንኳስስ መንገድ መሆኑ እና አንዳንድ ጋዜጠኞችም እዚያው ሆነውም ሆነ በኋላ ላይ በየፕሮግራሞቻቸው ጥያቄው ጭራሹንም ሊነሳ እንደማይገባ መግለፃቸው ተገቢ አልነበረም፡፡ እነ ቻይና እና ህንድን በሌላኛው ጎን እንደምሳሌ ካቀረብን ጎን ለጎን ከ10 ሚሊዮን ያነሰ ሕዝብ ያላትን ትልቅ የእግር ኳስ ሀገር ኡራጓይ መጥቀስ ተገቢ ነው፡፡ እንዲሁም ብራዚል እና አርጀንቲና፣ አውሮፓውያኑ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ፈረንሳይ እና ስፔን፣ አፍሪካውያኖቹ ናይጄሪያ፣ ግብፅ፣ ደ/አፍሪካ፣ ጋና እና ካሜሩን ባለብዙ ሚሊዮን ሕዝብ የእግር ኳስ ስኬታማዎች መሆናቸውንም መዘንጋት አይኖርብንም፡፡

አንድ ሀገር የእግር ኳስ ባህል ካለው (ቻይና እና ሕንድ የእግር ኳስ ሀገራት አይደሉም) ተጫዋቾችን የሚያገኝበት ቋት መስፋቱ የተሻለ አቅም ለሊፈጥርለት እንደሚችል አያከራክርም፡፡ እዚህ ጋር ሀገሪቱ ሰርታበታለች ወይ የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ ኢትዮጵያ ስኬታማነቷ የሚታወቀው በአትሌቲክስ ቢሆንም የእግር ኳስ ፍቅር የሚያይልባት ሀገር መሆኗ አይካድም፡፡ ከሲሼልስ 90 ሺህ ሕዝብ ውስጥ ከግማሽ በላዩ ሴቶች፣ አዛውንት እና ሕፃናት መሆናቸውን ከግምት ውስጥ ስናስገባ ተጫዋቾች የሚገኙበት ቋት እጅግ የጠበበ ይሆናል፡፡ ታዲያ በእንደዚህ አይነቱ ቡድን ተበልጦ ነጥብ መጣል ቢያንገበግብና የትኛውንም አይነት ጥያቄ ቢያሰነሳ ምን ይደንቃል? ሀገራችን ይህን ሁሉ እግር ኳስ ወዳድ ሕዝብ ይዛ ስኬታማ ላለመሆኗ ከአሰልጣኙ በላይ የሚጠየቁ ተቋማት (ስፖርት ኮሚሽን፣ ፌዴሬሽኑ፣ ክለቦች፣ የእግር ኳሱ አጠቃላይ ሲስተም…) ቢኖሩም በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ የተሳተፉ፣ በትልልቅ የአፍሪካ ክለቦች ውስጥ የሚጫወቱ፣ ብዙ ገንዘብ በሚፈስበት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውስጥ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን የመምረጥ ዕድል ያገኙት አሰልጣኝ እግር ኳስ የሙሉ ግዜ ስራቸው ያልሆነ ብዙ ተጫዋቾችን የያዘ ቡድንን ማሸነፍ ባለመቻላቸው ቢተቹ ተገቢ ነው፡፡ በእነ አልጄሪያ እና ማሊ ወይም ናይጄሪያ እና ቡርኪናፋሶ ስንሸነፍ ከስር ስለመስራት፣ ጥሩ መዋቅር ስለመዘርጋት ልናወራ እንችላለን ሲሼልስንም ለማሸነፍ ስንቸገር ይህን ካነሳን ግን…….

የተቀመጡ ተጫዋቾች – ከውጭ ከመጡ ተጫዋቾች

ባለፉት ሶስት የአሰልጣኝ ዮሐንስ ዋልያዎች ጨዋታ ጥሩ የተንቀሳቀሱት ሳላህዲን ባርጌቾ እና ራምኬል ሎክ እንዲሁም የማሪያኖ ባሬቶ ተወዳጅ ተጫዋች ናትናኤል ዘለቀ ካስፈቀዱበት ግዜ በላይ በመቆየታቸው ከቡድኑ መቀነሳቸው መገለፁ ይታወሳል፡፡ ይህ ውሳኔ የማንም ይሁን የማን ዲስፕሊን ከማስከበር አንፃር ተገቢ ቢሆንም አሰልጣኙ ግን እርሳቸው እንዳልቀነሷቸው እና ከቡድኑ ጋር ለመዋሀድ በቂ ግዜ ስላልነበራቸው ለዚህ ጨዋታ ብቻ ከምርጫ ውጭ እንዳደረጓቸው፤ የሶስቱን ተጫዋቾች ጉዳይ አስመልክቶ ከዚህ ቀደም የተላለፈው መልዕክትም የፌዴሬሽኑ እንጂ የእርሳቸው እንዳልሆነ ገልፀዋል፡፡ ይህን መረጃ የመስጠቱ ተግባር የማነው የሚለው በራሱ አከራካሪነቱ እንዳለ ሆኖ ዮሐንስ ተጫዋቾቹን ያላካተቷቸው በእውነት ለውህደት በቂ ግዜ ስላልነበረ ነው ብለው ከሆነ ይህ አስተሳሰብ ከውጭ ሀገር በመጡት ተጫዋቾች ላይ ለምን እንዳልሰራ መጠየቅም ግድ ይሆናል፡፡ ወደ ሁለት ወር ለተጠጋ ግዜ አብረዋቸው የቆዩ ተጫዋቾችን ወደ ጎን ብለው አራት ወይም አምስት ቀን ብቻ ከቡድኑ ጋር ለቆዩት ለሁሉም ከውጭ የመጡ ተጫዋቾች የቋሚ ተሰላፊነት ዕድልን መስጠታቸው ያን ያህል ግዜ የመዘጋጀታቸውን አስፈላጊነትም አጠያያቂ ያደርገዋል፡፡ አሰልጣኙ በዚህ ጉዳይ ላይ ሲጠየቁ ከውጭ የመጡት ተጫዋቾች በአካልም ሆነ በአዕምሯዊ ጉዳዮች የላቁ በመሆናቸው እንደሆነ እና በሀገሪቱ በሁሉም ክፍሎች ጥራት ያለው ተጫዋች አለመኖሩን መናገራቸውም በተጫዋቾቻቸው መንፈስ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አያሳድርም ወይ የሚል ሌላ የመነጋጋሪያ ነጥብ ሳያስነሳ አልቀረም፡፡

2 thoughts on “የዋሊያዎቹ የአጨራረስና ቅንጅት ችግር የማን?

Leave a Reply

Your email address will not be published.