የወገኔ “Amarika”

flag2

flag2

ያገሬ ሰዉ ፤ ከቀየዉ ቢሻለኝ ቀን ቢያወጣልኝ ብሎ ነፍሱን ሸጦ የፈለሰበትን ምድር ስም ተይብ ቢባል የሚያስፍራቸዉ ፊደላት ናቸዉ፤ Amarika….ብዬ ብጀምር ማጋነን ይሆንብኛል :: ወገኔ በ Amarika ድህነትን ሊያራግፍ ሀብት ሊሸምት ግዞትን አሽቀንጠሮ ነፃነትን ሊሸክፍ ተስፋን ሰንቆ ከተተ በAmarikaም ከተመ፡፡ ከወገን ኖሮ ከመራብ በሀገር ኖሮ ከመሰደብ በመሸበት አድሮ ከባየተዋር ምድር ጥጋብ እና ክብርን ሽቶ ሮጠ፤ ተሰደደ፡፡ ሆነለት፡፡ የቀን ሶስት ሩብ እየለፋ ከምን እንደተሰራ በማይታወቅ እንጀራ ሆዱን እየነፋ እነ እማማን እነ አባባን እነ ኩቺን እነጢሎን ዶላር ያስመረዝራል፤ ቀን ያወጣላቸዋል፤ ከጎረቤት በላይ ያደርጋቸዋል፡፡ እሱ የመኪና ተራ እያስጠበቀ እነ እማማን እነ ጢሎን ባለጋቢና ያደርጋቸዋል፡፡ ሳይማር አሜሪካ የላከዉን ህዝብ ሳይማር ወግ ያስተምረዋል፡፡ ለነ ኩቺም ያሜሪካ ወንድማቸዉ ከእግዜር በታች ከኦባማ ጎን ነግሶ የትንሽ ስራ መራቂያ ያሜሪካ መናፈቂያ የጎረቤት ማስፈራሪያ ሆኖ ይኖራል፡፡ ወገኔም ይህን ያዉቀዋል፤ ጎረቤታቸዉን እነ ቡለቲን አፍ ማስያዙ ያኮራዋል፡፡ ስራዉን ኑሮዉን ደብቆ የስራ ትንሽ እንደሌለ ቤተሰቡን ይመክራል፡፡ ስለወገኔ ኑሮ ዝርዝር ሁኔታ በስልክም ሆነ ባካል ከሱ ጋር መነጋገር አያስፈልግም የሴት ዕድሜ የሱ ስራ አይጠየቅማ፡፡ የቤቱ ትልቅነት የመኪናዉ ዘመናዊነት በአሜሪካዊዉ ወገኔ በዝርዝር ሊወሳ ይችላል፡፡ ይህ ማለት ግን የሱ ቤት የሱ መኪና ነዉ ማለት ላይሆን ይችላል፤ አይጠየቅም፡፡

ነገ ያቺ ሙሉ ቀን ስትመጣ ከስምንት ሻንጣ ጨርቅ እብድ ከሚያክል ስልክ እና የአሜሪካ ሰንደቅ ካለበት ካኒቴራ ጋር ቦሌ ይደርሳል እነኩቺም ካስራ አምስት ዘመድ አዝማድና ዳጎስ ካለ ብድር ጋር ይቀበሉታልእንኳን ላፈርህ አበቃህከዛማ የአንድ ወር ቆይታው በፌሽታና በአሜሪካ ኑሮ ትረካ የተሞላ ይሆናል፡፡ እንደዛ ሲሰራ ሲለፋ ለኖረው ወገኔ መዝናናት ሲያንስ ነው::

ችግር፤ ተስፋ ማጣት፤ ፖለቲካ፤ ጭቆና…ብዙ ብዙ ምክንያት ከምንወዳት ሀገራችን ያፈናቅሉናል፤፤ አሜሪካ እንዲሁም ሌሎች የሰለጠነዉ አለም የተሻለ አማራጭ ሆነዉ እናገኛቸዋለን፡፡ ለማንኛዉም ምክንያት ይሁን ሀገር ቀይሮ መኖር የግለሰብ ዉሳኔ ነዉ፡፡ ሊከበርም ይገባዋል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ግን የምንሄድበትን ቦታ፤ የምናልመዉን ኑሮ በሚገባ መረዳት ቅድሚያ ሊሰጠዉ የሚገባ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ የተሻለ ለዉጥን መፈለግ ድንቅ ነዉ፡፡ ለመለወጥ ግን ማወቅ ይቀድማል፡፡

አሜሪካን በእንግሊዝኛ ተይብ ቢባል አብዛኛዉ በትክክል እንደሚፅፍ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ነገር ግን ምን ያህሉ ሊኖርባት የመረጣትን ሀገር ቋንቋ ለመግባቢያ እንኳን በሚጠቅም ደረጃ ያዉቃል ብትሉኝ በጣም ጥቂቱ ይሆናል መልሴ፡፡ የተወሰኑ ቃላትን በአሜሪካዊያን ዘይቤ ይጠራ ይሆናል፡፡ ነገር ግን አንድ ሙሉ አረፍተ ነገር በተሟላ መልኩ ቀምኖ አያቀርብም፡፡ በዚህ አይነት ሁኔታ ታዲያ ከታክሲ ሹፌርነት እና ከመኪና ጠባቂነት ያለፈ ህልም እንዴት ይኖረዋል፡፡ ቀን ሲሞላ ተመልሶ ወይንም በስልክ ስለአሜሪካ ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች እና ህዝብ ገድል ከማዉራት ያለፈ ህልም ልንሰንቅ እንችላለን? ሁሌ ከህንፃዉ ዙሪያ ያሉትን ጥቃቅን ስራዎቸን ሰንሰራ መኖርን ከማለም፤ ለወገናችን የተሳሳተ(ያልተሟላ) መረጃን ከመስጠት፤ ራሳችንን አለአግባብ ከመኮፈስ አልፈን ህንፃዉ ዉስጥ ካሉት ሰዎች ራሳችንን እንደአንዱ የማየት፤ ህንፃዉንም ሆነ ዉስጡ ያሉትን ንግዶች (አገልግሎቶች) የራስ የማድረግ ህልም ቢኖረን ይበዛብናል? አይመስለኝም ከአንድ ድሃ የአፍሪካ ሀገር የሄደ ስደተኛ ልጅን መሪዋ አድርጋ ለመሾም የፈቀደች ሀገር እኛ ከተጋን ትምህቱንም ሆነ ሀብቱን አትከለከንም። ለዚህ ደግሞ ማሳያ የሚሆኑ ወገኖቻችን በዙሪያችን ሞልተዉናል።

ነገር ግን መጀመሪያ መማር ማወቅ ለመለወጥ መዘጋጀት ይቀድማል። አሁን ምንሰበስበው ስምንትና ዘጠኝ ዶላር ለነገው ህልማችን ግብዐት እንጂ ራሳችንን ማታለያ የሀገር ቤት ወገናችንን ማደናበሪያ መሳሪያ መሆን የለበትም።

በነገራችን ላይ ይህ ጽሑፍ በትምህቱም ሆነ በንግዱ ለራሳቸው ስኬታማ ለወገን ኩራት የሆኑትን አይመለከትም። እነሱ በተቃራኒው ለነኩቺ ወንድም ወገኔ ምሳሌዎች ናቸው። በል እንግዲህ ወገኔ ወደ Amarika ስትመለስ መዝገበ ቃላት ስንቅህ ይሁን ከዛ ለሚጥለው ደረጃ ስትበቃ እንማከራለን:: ደህና ሰንብቱ።

1 thought on “የወገኔ “Amarika”

Leave a Reply

Your email address will not be published.