የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 23ኛው ሳምንት ዘገባ፦ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ዋንጫው ሲቃረብ፣ ወልዲያ መውረዱን አረጋግጧል፤ የሙገር እና ኤሌክትሪክ ግብግብ አጓጊ ሆኗል

10960037_812024938891654_777049548444374040_o
ፎቶ ምንጭ፦ የቅድስ ጊዮርጊስ ቡድን የፌስቡክ ገጽ።

 

23ኛ ሳምንቱን ባካሄደው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የራሱን ድል እና የሰሞኑን የተለመደ የሲዳማ ቡና ነጥብ መጣል ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ዋንጫው ሲቃረብ ሲዳማ ቡና ከዋንጫ ፉክክሩ ውጪ መሆኑ ተረጋግጧል፤ የሰሞኑ ባለምርጥ አቋም እና ከሀዋሳ ከነማ ጋር ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ደደቢት ብቻ ለዋንጫው ጊዮርጊስን የሚፎካከርበት አነስተኛ እድል አለው፡፡ ከታች ወልዲያ ከነማ መውረዱን ሲያረጋግጥ ሙገር ሲሚንቶ እና ኤሌክትሪክ ቀሪውን ቦታ ይዞ ላለመውረድ ፍልሚያቸውን ቀጥለዋል፡፡ ቀጣዩ ዘገባ የሳምንቱን ምርጥ ጨዋታ ሰፋ አድርጎ ቃኝቶ ሌሎች የሳምንቱ ክስተቶችንም ይዳስሳል፡፡

የኦሮሚያ ደርቢ

የካቻምናው (2005) የውድድር ዘመን ሲጠናቀቅ አዳማ ከነማ ወደ ብሔራዊ ሊጉ በመውረዱ ምክንያት ባለፈው የውድድር ዘመን የኦሮሚያን ደርቢ መመልከት አልተቻለም ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን አዳማ ከነማ ተመልሶ በመምጣቱ እና ሙገር ሲሚንቶም ከብዙ ትግል በኋላ ከመውረድ በመትረፉ ይህ ደርቢ ዳግም ህያው ሆኗል፤ በሚቀጥለው ዓመት ስለመኖሩ ግን ያጠራጥራል፡፡ ካልኖረ ግን ላለመኖሩ የአሁኑ ተጠያቂ አዳማ ሳይሆን ሙገር ይሆናል፡፡ አጓጊው የሁለቱ ክለቦች የኦሮሚያ ደርቢ አርብ ከቀትር በኋላ በአሰላ ስታዲየም የተጀመረው ከስር ያደጉት አዳማዎች በአሸናፊ በቀለ ድንቅ አመራር ታግዘው ፍፁም ያልተጠበቀ ጉዞ በማድረግ አሁን የሜዳልያ ደረጃ ይዘው ለማግኘት እየታገሉ በአንፃሩ ባለሜዳዎቹ ሙገሮች ባለመውረድ ትግል ጭንቅ ውስጥ ሆነው ነበር፡፡ ሙገር ሲሚንቶዎች አቤል ማሞን በግብ ጠባቂ ስፍራ፤ ተክለፃዲቅ አበበ፣ ሚፍታህ አወል፣ ደስታ ደሙ እና እንግዳወርቅ አየለን በተከላካይ ስፍራ፤ አዲሱ አላሮ፣ አስጨናቂ ገብረስላሴ፣ መርዋን ራያ እና ሄኖክ ፍሰሀን በአማይካ ስፍራ እንዲሁም ኤፍሬም ቀሬ እና በረከት ሳሙኤልን በአጥቂነት አስጀምረዋል፡፡ አዳማዎች በበኩላቸው ኤማኑኤል ፌቮን በግብ ጠባቂነት፤ አንተነህ ገብረክርስቶስ፣ ወንድወሰን ሚልክያስ፣ ዳንኤል ስለሺ እና ሱሌይማን መሀመድን በተከላካይ ስፍራ፤ ደሳለኝ ደበሽ፣ አመሀ በለጠ፣ ወንድሜነህ ዘሪሁን፣ እና ታከለ አለማየሁን በአማካይ ስፍራ እንዲሁም ዮናታን ከበደ እና በረከት አዲሱን በአጥቂ ስፍራ እንዲጀምሩ አድርገዋል፡፡ የጨዋታው የመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች የተመጣጠኑ ነበሩ፡፡ የኳስ ቁጥጥሩን ለመያዝ ትግል የታየበት እና ባብዛኛው ከሩቅ የተመቱ ሙከራዎች የታዩበት ነበር፡፡ ምናልባት የሚጠቀስ አስቆጪ የጎል ሙከራ ቢኖር በ11ኛው ደቂቃ በአዳማው ተከላካይ ዳንኤል ስለሺ ስህተት ያገኘውን ኳስ የሙገሩ አማካይ አስጨናቂ ገብረስላሴ ሳይረጋጋ መትቶ ወደ ውጪ የወጣበት ነበር፡፡ በ20ኛው ደቂቃ ግን ባለሜዳዎቹን ያስደነገጠ በበርካታ ደጋፊዎች የሚደገፉትን እንግዶቹን ያስደሰተ ክስተት ሆነ፡፡ የአዳማው አምበል ሱሌይማን መሀመድ ከቡድን ጓደኞቹ ጋር አንድ ሁለት ተጫውቶ (double pass) ወደ ሙገር ጎል ክልል እንደገባ በሙገር ተጨዋች ማልያው ተጎትቶ በመውደቁ አርቢትሩ ይርጋለም ወልደጊዮርጊስ ያለምንም ማመንታት ፍፁም ቅጣት ምት ሰጡ (ለነገሩ ማመንታት የማይፈልግ ግልፅ ድርጊት ነበር)፡፡ ፍፁም ቅጣት ምቱን ለመምታት በአምሀ በለጠ እና ዮናታን ከበደ መካከል ትንሽ ክርክር ከተደረገ በኋላም ከአሰልጣኙ በመጣ ትዕዛዝ ዮናታን መትቶ ወደ ጎል በመቀየር አዳማን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ከዳሸን ቢራ አዳማን የተቀላቀለው ዮናታን ለአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ቡድን ጎሎችን ማምረቱን ቀጥሎበታል፤ ለእሱም ተቸግሮበት ከነበረው ዳሸን አንፃር አዲሱ ቡድኑ ፍፁም የተመቸው መስሏል፡፡ ከዚህ ጎል በኋላ ግን የጨዋታው እና የጎል ሙከራዎች የበላይነት ሙሉ ለሙሉ ወደ ባለሜዳው ሙገር አዘንብሎ ታይቷል፡፡ የግርማ ወልደዮሀንስ ቡድን በሁለት አጥቂዎች (አንድ ረዥም እና ሌላኛው ፈጣን)፣ እና ታጋይ አማካዮች ከመጠቀሙ ውጪ ይህ ነው ብሎ ለመግለፅ የሚያበቃ የማጥቃት ስትራቴጂ ባይታይበትም ቋሚ ተሰላፊ የመሀል ተከላካዮቹን በጉዳት ምክንያት በማጣቱ ደክሞ የዋለው የአዳማ የተከላካይ ክፍል በሰራቸው ስህተቶች መነሻ የሚያስቆጩ የጎል እድሎችን መፍጠር ችሎ ነበር፡፡ በ26ኛው ደቂቃ ከመሀል ሜዳ አካባቢ የተመታ የቅጣት ምት በሙገር ተጨዋቾች ተገጭቶ ጎል ከመሆን የተረፈው በአግዳሚው ሲሆን፣ በ32ኛው ደቂቃም በእለቱ ድንቅ እንቅስቃሴ ያደረገው ሄኖክ ፍሰሀ ከራሱ ሜዳ ጀምሮ ኳሱን እየገፋ መጥቶ ለኤፍሬም ቀሬ ያቀበለውን ወጣቱ አጥቂ በጉጉት መትቶ በአግዳሚው ተመልሶበታል፡፡ የሙገር ደጋፊዎችን እጅግ ያስቆጨ ሙከራ ነበር፡፡ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ራሱ ሄኖክ በረዥሙ ለበረከት ሳሙኤል የጣለለትን ኳስ ከግብ ጠባቂው ፊት ይገኝ የነበረው ግዙፉ አጥቂ (በተለምዶ ተከላካይ ነው፤ በአጥቂዎች በተለይም አካካፓ ጌዲዮን ጉዳት በተፈጠረ እጥረት ምክንያት ወደ አጥቂነት ተቀይሮ ነው) መቆጣጠር ሳይችል ቀርቷል፡፡ ወጣቱ አማካይ ሄኖክ ግን ሁለቱንም ኳሶች ያቀበለባቸው መንገዶች ድንቅ ነበሩ፡፡ በ39ኛው እና 41ኛው ደቂቃዎችም ሙገሮች ከማዕዘን ምት እና ከተሻገረ ኳስ ያገኟቸው እድሎች የመጀመሪያው በእንግዳወርቅ አየለ እና ሁለተኛውን በበረከት አማካይነት በጭንቅላት ቢሞከሩም አንዱ ሲወጣ ሌላኛው በኤማኑኤል ፌቮ ተይዟል፡፡ በ44ኛ ደቂቃ ደግሞ ወደ አዳማ ጎል በመሬት የተሻገረን ኳስ የመሀል ተከላካዩ ዳንኤል ራሱ ጎል ላይ ሊያስቆጥር ተቃርቦ ነበር፡፡ በዚህ ሁሉ የሙገር ጫና መካከል አዳማዎችም እድሎች ሊፈጥሩ ሞክረዋል፡፡ በ31ኛው ደቂቃ በረከት አዲሱ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ዮናታን በተካነበት የጭንቅላት መግጨት ሊያገባ ሲል ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ ደርሶ ለጥቂት ሞጭልፎ ሲያወጣበት፣ በ43ኛው ደቂቃ ሌላኛው በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ከኤሌክትሪክ የወሰዱት ወንድሜነህ ዘሪሁን ኳሱን በሚገባ ተቆጣጥሮ ለበረከት አዲሱ እጅግ ያማረ ኳስ ቢሰነጥቅለትም በረከት ከጨዋታ ውጪ ተብሏል፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ የተጀመረው ሙገሮች አማካይ ክፍላቸው ላይ ቅያሬ አድርገው ነበር፡፡ ከጨዋታው በኋላ አሰልጣኝ ግርማ ያሰቡትን ፈጠራ ሊያበረክት እንደተቸገረ የገለፁለት መርዋን ራያ ወጥቶ አዲስዓለም ደሳለኝ ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡ ባለሜዳዎቹ ይህን አጋማሽ የጀመሩት ከመጀመሪያው አጋማሽ ካቆሙበት በመቀጠል ነበር – በማጥቃት እና ጫና በመፍጠር፡፡ በ47ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተመታን ኳስ ኤፍሬም በጭንቅላቱ ሞክሮ አንተነህ ገብረክርስቶስ ከመስመር ላይ አውጥቶበታል፡፡ ነገር ግን የሙገር ጫና ፈፅሞ ፍሬ-አልባ አልነበረም፡፡ በ49ኛው ደቂቃ ከአዳማ ጎል በግራ በኩል ከ30 ሜትር ገደማ የተገኘውን የቅጣት ምት የሙገሩ አምበል ተክለፃዲቅ አበበ በድንቅ ሁኔታ በግራ እግሩ መትቶ በማስቆጠር ሙገርን አቻ አድርጓል፡፡ የአዳማው ግብ ጠባቂ ፌቮ እንደቆመ ነበር ጎሉ የተቆጠረው፡፡ ጎሉ ሲቆጠር የሙገር ተጨዋቾች እና ደጋፊው ላይ የታየው የደስታ ስሜት የተለየ ነበር፡፡ ጎሉ እንደተቆጠረ ከ20ኛው ደቂቃ ጎላቸው በኋላ በተጋጣሚያቸው በሚገባ እንደተበለጡ የተረዱት የአዳማው አሰልጣኝ አሸናፊ ለብዙ ደቂቃዎች ሲያሟሙቅ የነበረው ዳኛቸው በቀለን (በአስገራሚ ቅፅል ስሙ ኤቦላ) በአምሀ በለጠ ቦታ ሲተኩ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላም በረከት አዲሱን አስወጥተው ቢኒያም አየለን አስገብተዋል፡፡ ዘንድሮ ተቀይሮ እየገባ ልዩነት ሲፈጥር የነበረው ቢኒያም በዚህ ጨዋታም ይህንን ለመድገም ለመቃረብ ከደቂቃ በላይ አልወሰደበትም፤ በዚህ ክስተትም አጥቂው ለክለቡ ልዩነት ባይፈጥርም ለጨዋታው አወዛጋቢ ሁነት ምክንያት ሆኗል፡፡ በዚህ የ64ኛው ደቂቃ ክስተት ቢኒያም በረዥሙ በተላከለት ኳስ ከሙገሩ ግብ ጠባቂ ጋር ቢገናኝም ወደ ጎል ሳይሞክር በተከላካይ ተገፍቼያለሁ ብሎ ወድቋል፡፡ አርቢትር ይርጋለም ግን በዝምታ አልፈውታል፡፡ ከጥቂት እንቅስቃሴዎች በኋላ ግን የአዳማው አምበል ሱሌይማን አርቢትሩ ጨዋታውን እንዲያስቆሙለት አድርጎ ለአራተኛው ዳኛ የክስ ሪዘርቭ አስይዟል፡፡ ከጨዋታው በኋላ አሰልጣኝ አሸናፊ እንደገለፁት አምበላቸው ይህን ያደረገው የቢኒያምን የፍፁም ቅጣት ምት ቅሬታ ጨምሮ በአንዳንድ ውሳኔዎች ደስተኛ ባለመሆናቸው ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ጨዋታው በተወሰነ መጠን የተመጣጠነ የመሰለ ሲሆን በሁለቱም በኩል የሚያስቆጩ እና የሚማርኩም ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ በአዳማ በኩል ዳኛቸው እና ቢኒያም ባልተሳካ ቮሊ ሲሞክሩ፣ ወንድወሰን ሚልክያስ ከማዕዘን የተሻገረን ኳስ ለግብ ጠባቂው አሳቅፎታል፡፡ ሱሌይማን እየገፋ መጥቶ ለቢኒያም ያቀበለውን እና ቢኒያም ያዘጋጀለትን ወንድሜነህ ከፍፁም ቅጣት ክልል ውጪ መትቶ አቤል ጨርፎ ያወጣበትም የሚማርክ እንቅስቃሴ እና ሙከራ የታየበት ነበር፡፡ አዲሱ አላሮን አስወጥተው መቆያ አልታዬን ባስገቡት ሙገር በኩል ተቀይሮ የወጣው አዲሱ፣ እንግዳወርቅ አየለ እና በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በረከት ሳሙኤል ሙከራዎች አድርገዋል፡፡ ነገር ግን ተጨማሪ ጎል ሳይገኝ በ1ለ1 ውጤት ተጠናቋል፡፡ ጨዋታው እንደተጠናቀቀ ከሙገር አጥቂዎቹ በረከት ሳሙኤል እና ኤፍሬምን ከአዳማ ወንድወሰን፣ ወንድሜነህ እና በረከት አዲሱን ያሳተፈ ግጭት የተከሰተ ሲሆን ይህንን ተከትሎም በተለይ ከአዳማ ደጋፊዎች በኩል ድንጋዮችን ጨምሮ ቁሳቁሶች ወደ ሙገር ተጨዋቾች ተወርውረዋል፡፡

ከጨዋታው በኋላ የሙገሩ አሰልጣኝ ግርማ ልጆቻቸው ባሳዩት ታጋይነት እንደተደሰቱ በፈጠራው በኩል ግን በተለይ ከአማካዮቻቸው የሚጠብቁትን እንዳላገኙ  ገልፀዋል፡፡ የተጨዋቾች ጉዳትንም (የአጥቂ አማካያቸው እስክንድር አብዱልሀሚድን ለይተው ጠቅሰዋል) ለፈጠራ ማነስ እና ለአጥቂዎቹ በሚገባ አለመቀናጀት ምክንያት አድርገዋል፡፡ አሰልጣኙ ስለመውረድ እንደማያስቡ እና እስከመጨረሻው እንደሚታገሉም ጨምረዋል፡፡ የአዳማ ከነማው አሰልጣኝ አሸናፊ በበኩላቸው በጨዋታው ቡድናቸው ደክሞ እንደተመለከቱት አምነዋል፡፡ የተከላካዮቻቸውን ጉዳትም በምክንያትነት አንስተዋል፡፡

ሌሎች ነጥቦች    

  • መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ጎንደር አቅንቶ በመሀል ለ13 ደቂቃዎች በተቋረጠ ጨዋታ ዳሸን ቢራን 2ለ1 ረትቷል፡፡ ኤዶም ሆሶሮቪ ባለሜዳዎቹን መሪ ቢያደርግም ፈረሰኞቹ በአዳነ ግርማ ሁለት ጎሎች አሸናፊ ሆነዋል፡፡ የአዳነ ግርማ አንዱ ጎል ጨዋታው ለብዙ ደቂቃዎች ለመቋረጡ ምክንያት ነበር፡፡
  • ተከታዩ ሲዳማ ቡና በሜዳው ከመከላከያ ያለግብ አቻ በመለያየቱ የዋንጫ እድሉ ሲያከትም ሁለተኛነቱንም አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ሁለተኛነቱን የቀማው ደደቢት ኤሌክትሪክን 4ለ0 ከደቆሰ በኋላ ነበር፡፡ በዳንኤል ፀሐዬ የሚመሩት ደደቢቶች በሳሙኤል ሳኑሚ ሀት-ትሪክ እና በታደለ መንገሻ ተጨማሪ ጎል ድሉን አግኝተዋል፡፡ ይህ ጨዋታ ለኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ አጥናፉ አለሙ ስንብት ምክንያት መሆኑም እየተነገረ ነው፡፡
  • ወልዲያ ከነማ በሜዳው በአርባምንጭ ከነማ 1ለ0 መረታቱን ተከትሎ በቀጥታ ወደ መጣበት ብሔራዊ ሊግ መመለሱን አረጋግጧል፡፡ በሌሎች የአዲስ አበባ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሀዋሳ ከነማ 1ለ1 እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና ከወላይታ ድቻ 0ለ0 ተለያይተዋል፡፡
  • በዚህ መሰረት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ23 ጨዋታዎች በሰበሰባቸው 48 ነጥቦች መሪነቱን ሲያጠናክር 22 ጨዋታዎች ያደረገው ደደቢት በ40 ይከተላል፡፡ ሲዳማ ቡና በ39 እና አዳማ ከነማ በ38 ነጥቦች ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡ ከታች ሀዋሳ ከነማ ተስተካካይ ጨዋታ እያለው በ27 ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፣ ኤሌክትሪክ በ24፣ እና ሙገር በ20 ላለመውረድ ይፋለማሉ፡፡ ባለ12 ነጥቡ ወልዲያ ከነማ መውረዱ ተረጋግጧል፡፡ በከፍተኛ ጎል አግቢነት የሳምንቱ ባለሀት-ትሪክ ሳሙኤል ሳኑሚ ከደደቢት በ18 ጎሎች ሲመራ፣ የንግድ ባንኩ ፊሊፕ ዳውዝ በ15 ይከተላል፤ የኢትዮጵያ ቡናው ቢኒያም አሰፋ 13 ላይ እንደቆመ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.