የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ተስፋ ስጋት ውስጥ ገብቷል

Waliya vs Congo

Waliya vs Congo

በሩሲያ ለሚካሄደው የ2018ቱ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የኮንጎ ብራዛቪል አቻውን አስተናግዶ ሽንፈት አጋጥሞታል፡፡ ቀጣዩ ዘገባ የአዲስ አበባ ስታዲየሙን ጨዋታ ለመቃኘት ይሞክራል፡፡

ባለሜዳዎቹ ዋልያዎቹ በቅድመ-ማጣሪያው ሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔን በድምር ውጤት ከረቱ በኋላ ለዚህ ፍልሚያ ሲበቁ ኮንጎዎቹ ድልድሉ ሲደረግ በነበራቸው የተሻለ ወቅታዊ የፊፋ ደረጃ ምክንያት ቅድመ-ማጣሪያ የማድረግ ግዴታ ውስጥ አልገቡም ነበር፡፡ ቡድኖቹ ወደዚህ ጨዋታ የገቡት በደርሶ-መልስ ፍልሚያው ካሸነፉ የመጨረሻውን ምድብ የመቀላቀልን ተስፋ ሰንቀው ነበር፡፡

ለአዲስ አበባው ጨዋታ ቡድኖቹ ወደ ሜዳ ሲገቡ የመጀመሪያ ተሰላፊዎቻቸው የሚከተሉት ነበሩ፡-

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን  (4-1-3-2)

ግብ ጠባቂ፡- ታሪክ ጌትነት

ተከላካዮች፡- ስዩም ተስፋዬ ፣ ሰልሀዲን ባርጊቾ፣ አስቻለው ታመነ እና ነጂብ ሳኒ

አማካዮች፡- ጋቶች ፓኖም፣

ሽመልስ በቀለ፣ አስቻለው ግርማ እና በረከት ይስሀቅ

አጥቂዎች፡- ዳዊት ፍቃዱ እና ጌታነህ ከበደ

ተጠባባቂዎች፡- አቤል ማሞ፣ ዋሊድ አታ፣ ዘካሪያስ ቱጂ፣ በኃይሉ ግርማ፣ ኤልያስ ማሞ፣ ቢኒያም በላይ እና ምንይሉ ወንድሙ

ዋና አሰልጣኝ፡- ዮሐንስ ሳህሌ       

 

IMG_2496 copy

ኮንጎ ብራዛቪል ብሔራዊ ቡድን  (4-4-2)

ግብ ጠባቂ፡- ማፎቢ ክርስቶፈር

ተከላካዮች፡- ባውድሪ፣ ንጋንጋ ፍራንሲስ፣ ባቢሌ ሳጊሴ እና ማግኖዜሌ ቢሲኪ

አማካዮች፡- አቮኖ ዱሬል፣ ንዲንጋ ዴልቪን፣ ፋብሪስ ንጉዬሲ እና ንኮንኮ

አጥቂዎች፡- ኩቤምባ ኬቨን እና ቢፎማ ቼቪ

ዋና አሰልጣኝ፡-  ክሎድ ለሯ

በቱኒዚያዊያን አርቢትሮች መሪነት የተጀመረው ጨዋታ ከመነሻው አንስቶ ማራኪ እና አይን የማያስነቅል ነበር፡፡ በተለይ እንግዶቹ ኮንጎ ብራዛቪሎች ኳሱን በመቆጣጠርም ሆነ የጎል እድሎችን በመፍጠር ረገድ ድንቅ ነበሩ፡፡ የክሎድ ለሯ ልጆች የመጀመሪያውን የጎል ሙከራ ያደረጉት በስምንተኛው ደቂቃ ኩቤምባ ኬቨን ለራሱ ክፍተት ፈጥሮ በመሬት ወደ ጎል መትቶ ግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት ሲይዝበት ነበር፡፡ በ20ኛው ደቂቃ ታሪክ ከራሱ ተከላካዮች ወደ ኋላ የተሰጠውን ኳስ በእጁ በመያዙ ከጎሉ ከሰባት ሜትሮች ርቀት ገደማ በግራ በኩል አዘንብሎ ሁለተኛ ቅጣት ምት ለኮንጎ ተሰጥቷል፡፡ ፋብሪስ ንጉዬሲ ለቢፎማ ቼቪ ያቀበለውን ኳስ የኮንጎው አጥቂ ወደ ጎል ቢመታም የዋልያዎቹ አምበል ስዩም ተስፋዬ በአስደናቂ ጀግንነት ተደርቦ አውጥቶታል፡፡ ኮንጎዎች ያገኙትን የማእዘን ምት ቼቪ አግኝቶ በእግሩ ቢሞክረውም ተደርቦ ወጥቶበታል፡፡ ባለሜዳዎቹ የመጀመሪያ ሙከራቸውን ያደረጉት በ29ኛው ደቂቃ ላይ ነበር፡፡ አስቻለው ግርማ ኳሱን እየገፋ ወደ ፊት ሄዶ ያዘጋጀለትን ሽመልስ በቀለ ወደጎል መትቶ በአግዳሚው ላይ ወጥቶበታል፡፡ በ30ኛው ደቂቃ ጋቶች ፓኖም ከሩቅ የመታው ኳስ ወደውጪ ወጥቶበታል፡፡ በ32ኛው ደቂቃ ሽመልስ ለጌታነህ የሰጠውን የፕሪቶሪያው አጥቂ ወደጎል ሞክሮ በአግዳሚው ላይ ወጥቶበታል፡፡ በ36ኛው ደቂቃ ዳዊት ፍቃዱ ከመሀል የተላከለትን እና እየገፋ ሄዶ የመታው ኳስ ጠንካራ ባለመሆኑ ግብ ጠባቂው በቀላሉ ይዞበታል፡፡ በ41ኛው ደቂቃ ፍፁም ያልተጠበቀ ክስተት ተፈፀመ፡፡ ከሽመልስ በረዥሙ የተላከን ኳስ የመሀል ተከላካዩ ባቤሌ ሳጊሴ ጌታነህ እግር እንዳይደርስ ሲሞክር እንዲሁም ግብ ጠባቂው ማፎምቢ ክርስቶፈር ኳሱን ሊያወጣ ከጎሉ ሲወጣ በመጋጨታቸው ያገኘውን ኳስ ጌታነህ ወደ ጎልነት ቀይሮት ለዋልያዎቹ ያልተጠበቀ መሪነትን አጎናፅፏል፡፡ ይህ መሪነት እና የደጋፊው ደስታ ግን ብዙም አልቆየም፡፡ ከጌታነህ ጎል ሁለት ደቂቃዎች ብቻ በኋላ በኢትዮጵያ የሜዳ ክልል በቀኝ በኩል ከፍፁም ቅጣት ክልል ውጪ ያገኙትን የቅጣት ምት ቼቪ በቀጥታ መትቶ በማስቆጠር እንግዶቹን አቻ አድርጓል፡፡ የግብ ጠባቂው ታሪክ አቋቋም እና ኳሱን ሊያወጣ የሞከረበት መንገድ ብዙ ጥያቄ ቢያስነሳም የቡድኑን አጫጭር ተጨዋቾች ሽመልስ እና አስቻለው ግርማን በግድግዳነት የመጠቀሙ ነገርም ለጎሉ አስተዋፅኦ እንደነበረው ታይቷል፡፡

ከእረፍት መልስ ዋልያዎቹ ተሻሽለው እንደሚመጡ እና በመጀመሪያው አጋማሽ የተወሰደባቸውን የእንቅስቃሴ የበላይነት እንደሚያስመልሱ ቢጠበቅም በተቃራኒው የቀይ ሰይጣኖቹ የበላይነት ልቆ ነበር፡፡ ኮንጎዎቹ በ62ኛው ደቂቃ በአስደናቂ ቅብብል ወደኢትዮጵያ ጎል ደርሰውም ፋብሪስ ንጉዬሲ በቀላሉ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል፡፡ በ70ኛው ደቂቃ ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የዋለው ንኮንኮ በግራ በኩል ነጂብ ሳኒን እና ሰልሀዲን ባርጊቾን በቀላሉ አልፎ ሄዶ ለቼቪ በመሬት ያቀበለውን የኤስፓኞል ንብረት የሆነው እና ለግራናዳ በውሰት ተሰጥቶ እየተጫወተ የሚገኘው አጥቂ ወደ ጎል ሞክሮት በታሪክ ተመልሶበታል፡፡ ወዲያውኑም ዋልያዎቹ በጌታነህ የግል ጥረት የሁለተኛው ግማሽ የመጀመሪያ ሙከራቸውን አድርገዋል፡፡ ከሴኮንዶች በኋላም ዳዊት ወደ ጎል ሞክሮ ግብ ጠባቂው ይዞበታል፡፡ በ72ኛው ደቂቃ ሳይታዩ የዋሉት የዋልያዎቹ አለቃ ዮሐንስ ሳህሌ ሁለት ቅያሬዎች አድርገዋል፡፡ የተከላካይ አማካዩ ጋቶች ፓኖም እና የግራ አማካዩ በረከት ይስሀቅ ወጥተው በኃይሉ ግርማ እና ቢኒያም በላይ ተክተዋቸዋል፡፡ በ75ኛው ደቂቃ ከግራ በኩል የተሻገረውን የማእዘን ምት አምበሉ ዴልቪን ንዲንጋ ፍፁም ነፃ ሆኖ በጭንቅላቱ በመግጨት ለቡድኑ ሶስተኛውን ጎል አስቆጥሯል፡፡ በ76ኛው ደቂቃ የሽመልስ ሙከራ በግብ ጠባቂው ተመልሷል፡፡ በ80ኛው ደቂቃ በዋልያዎቹ ተከላካዮች ስህተት የተገኘውን ኳስ ንኮንኮ ተቀይሮ ለገባው ሀርዲ ቢንጉዪላ አቀብሎት የፈረንሳዩ ሊግ 2 ክለብ ኦግዜር አጥቂ አራተኛ ጎል አድርጎታል፡፡ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ዳዊት ከሽመልስ የተቀበለውን ኳስ አስቆጥሮ የጎል ልዩነቱን ወደሁለት አጥብቧል፡፡ በ88ኛው ደቂቃ ከማእዘን የተሻገረን ኳስ በኃይሉ በጭንቅላቱ ገጭቶ ቢሞክርም በጎሉ አግዳሚ ስር የቆመው ኮንጎ ተከላካይ ጎል ከመሆን ታድጎታል፡፡ ቀይ ሰይጣኖቹ ይህን ኳስ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ይዘው ቢሄዱም ሌላኛው ተቀይሮ የገባው ፍራንሲስ ማሎንጋ ክፍት ጎል ላይ ማስቆጠር ተስኖታል፡፡ በባከኑ ደቂቃዎች ላይ ሽመልስ ልዩነቱን የበለጠ ያጠበበ ጎል አስቆጥሮ በኮንጎ ብራዛቪል የ4ለ3 ድል ጨዋታው ተጠናቋል፡፡

ዋልያዎቹ ሲመዘኑ

ግብ ጠባቂ

ታሪክ ጌትነት፡-  የብሔራዊ ቡድኑ ቋሚ ተሰላፊነቱን ያስተማመነ የመሰለው ታሪክ በዋልያዎቹ ማልያ ፈታኙን ቀን አሳልፏል፡፡ ለመጀመሪያው ጎል ቀዳሚ ተጠያቂ ከመሆኑ በተጨማሪ የቡድን መምራት ችግሩ ተጋልጧል፡፡

ተከላካዮች   

ስዩም ተስፋዬ፡- የቡድኑ አምበል በግሉ ከአብዛኞቹ የቡድን አጋሮቹ የተሻለ ቢንቀሳቀስም ቡድኑን በመምራት ረገድ ግን ብዙ ጥያቄ ሊነሳበት ይችላል፡፡

አስቻለው ታመነ፡- ወጣቱ የመሀል ተከላካይ በብሔራዊ ቡድን ህይወቱ መጥፎውን ቀን አሳልፏል ቢባል ግነት አይሆንም፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተጨዋች የቢፎማ ቼቪን ፍጥነት እና ጉልበት ለመቋቋም ከመቸገሩ ባሻገር ዴልቪን ንዲንጋ በጭንቅላቱ ላስቆጠረው ጎል ምክንያት ነበር፡፡

ሰልሀዲን ባርጊቾ፡- ሰልሀዲንም እንደ መሀል ተከላካይ አጣማሪው እጅግ ተቸግሮ ውሏል፡፡

ነጂብ ሳኒ፡- የመከላከያው የግራ ተከላካይ በመከላከሉም ሆነ ወደፊት ሄዶ ማጥቃቱን በማገዙ ረገድ ጥሩ አልነበረም፡፡

አማካዮች

ጋቶች ፓኖም፡- ታጋዩ የተከላካይ አማካይ ኳስ በመቀማት፣ በማደራጀትም ሆነ የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ ረገድ እጅግ ደካማ ነበር፡፡

ሽመልስ በቀለ፡- የፔትሮ ጄቱ አማካይ ጎል ቢያስቆጥርም እና ለሌላ ጎል መነሻ ቢሆንም አጠቃላይ እንቅስቃሴው እምብዛም በጥሩነት የሚነገርለት አልነበረም፡፡

አስቻለው ግርማ፡- የሀዋሳ ከነማው መስመር አማካይ/አጥቂ በድፍረት ኳሶችን መቀበሉ ሊያስደንቀው ቢችልም አብዛኞቹ ይበላሹበት ነበር፡፡

በረከት ይስሀቅ፡- ከክለብ አጋሩ አስቻለው ጋር ክንፍ እየተለዋወጠ የተጫወተው በረከት በሜዳ ላይ በቆየባቸው ደቂቃዎች ይህ ነው የሚባል የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርግ አልታየም፡፡

አጥቂዎች

ዳዊት ፍቃዱ፡- የደደቢቱ አጥቂ ጎል ቢያስቆጥርም የታወቀ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ተጋጣሚዎቹን ማስቸገር፣ ሌላ ፈጠራ ማበርክት አልያም ለአጥቂ አጋሩ እድሎችን መፍጠር ተስኖት ውሏል፡፡

ጌታነህ ከበደ፡- ዳግም ወደ ብሔራዊ ቡድኑ የተመለሰው የፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲው አጥቂ ከእሱ በሚጠበቅ አጨራረስ ጎል ቢያስቆጥርም እና የመጫወት እና የማሸነፍ ፍላጎቱ ልቆ ቢታይም ወደ ቀድሞ ብቃቱ ለመድረስ ገና እንደሆነ ታይቷል፡፡

ተቀይረው የገቡ

በኃይሉ ግርማ፡- ለመመዘን የሚያበቃ የጨዋታ ጊዜ አልነበረውም፡፡

ቢኒያም በላይ፡- ለመመዘን የሚያበቃ የጨዋታ ጊዜ አልነበረውም፡፡

ዋና አሰልጣኝ፡- ዮሐንስ ሳህሌ       

ቡድኑ በሁሉ ረገድ ደካማ ነበር፡፡ የግል ቴክኒክ እና አካል ብቃት ጉዳዮችን ወደ ጎን ብለን የታክቲክ እና ስነ-ልቦና ጉዳዮችን ብቻ ብናነሳ እጅጉን መበለጣችን በግልፅ የሚታይ ነበር፡፡ የአሰልጣኙ አሰላለፍ፣ ስትራቴጂ፣ ቅያሬዎች፣ ተነሳሽነትን መፍጠር፣ እርማት… ሁሉ ጥያቄዎች ይነሱባቸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.