የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ዕድሉን ለመሞከር ባማኮ ደርሷል

 

2015 አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጉዞውን በሽንፈት ያጋመሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ዕድሉን የሚወሰንበትን ጨዋታ ለማድረግ ወደ ምዕራብ አፍሪካዋ ሀገር ማሊ ተጉዟል፡፡ በሜዳቸው በአዲስ አበባ በኃያላኑ አልጄሪያ እና ማሊ ከሜዳቸው ውጭ በብላንታየር በትንሿ ማላዊ ሶስት ተከታታይ ሽንፈቶችን ያስተናገዱት፣ ምንም ነጥብ የሌላቸው እና አራት የግብ ዕዳ የተመዘገበባቸው ዋልያዎቹ ከዚህ በኋላ የሞሮኮ 2015ን ትኬት ለመቁረጥ ቀሪ ሶስት ጨዋታዎቻቸውን ማሸነፍ አልያም ቢያንስ ሁለቱን አሸንፈው በአንዱ አቻ መለያየት የግድ ይሆንባቸዋል (ሁለተኛው አማራጭም አስተማማኝ አይደለም፤ በሌሎች ምድቦች ሶስተኞች ውጤት ላይ የሚመሰረት ነው)፡፡ ከቀሪ ሶስት ጨዋታዎቻቸው ሁለቱን የሚያደርጉት ከሜዳቸው ውጭ ከታላላቆቹ እና በሜዳችን ከረቱን ማሊ እና አልጄሪያ ጋር መሆኑ ፈተናውን ተራራን የመግፋት ያህል የከበደ ያደርገዋል፡፡ ከእነዚህ አስቸጋሪ ፈተናዎች አንዱ ዛሬ ምሽት በሞቃታማዋ ማሊ ዋና ከተማ ባማኮ ስታድ 26 ማርስ (ማርች 26 ስታድየም) ያደርጋሉ፡፡
የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ከቅዳሜው የማሊ ሽንፈታቸው በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነታቸው ቅድሚያ የሚሰጡት ቡድኑን ለመገንባት፣ ለረጅም ዓመታት ቡድኑን ለሚያገለግሉ ወጣቶች ዕድሉን በመስጠት ልምድ እንዲያካብቱ ለማድረግ እንደሆነ እና ውጤቶች በግዜ ሂደት እንደሚመጡ ገልፀው ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ሀሳባቸው በተወሰኑ የእግር ኳስ ተከታታዮች፣ ደጋፊዎች እና ጋዜጠኞች ያልተወደደላቸው ሲሆን በየማህበራዊ ድረገፆች፣ በብሮድካስት ሚድያዎች የስፖርት ፕሮግራሞች እና በሌሎችም መድረኮች ብዙ ተቃውሞዎች ሲሰሙባቸው ሰንብተዋል፡፡ ተቺዎቹ በባሬቶ ላይ የሚያነሷቸው ቅሬታዎች ከታክቲክ እና ፎርሜሽን አንስቶ እስከ አንጋፋ ተጫዋቾችን ከቡድኑ ማስወጣት እና ለወጣቶች ዕድል መስጠት እንዲሁም የአምባገነናዊ የቡድን አመራር ድረስ የሰፋ ናቸው፡፡ በተቃራኒው ፖርቹጋላዊውን አሰልጣኝ የሚደግፉ ደጋፊዎች፣ ጋዜጠኞች እና ተንታኞችም ድምፃቸውን ከማሰማት አልቦዘኑም፡፡ ከዚህኛው ወገን ባሬቶ ለወጣቶች ዕድል መስጠታቸው፣ ቡድኑን በአዲስ መልክ ለመገንባት መጣራቸው፣ አዲስ ዘመናዊ አሰራሮችን እና አመራር ወደ ቡድኑ ማምጣታቸው ሊወደስ እንደሚገባው እና የሀገራችን እግር ኳስ ችግር መሰረታዊ እንጂ አሁን ላይ ባሬቶ ያመጡት እንዳልሆነ ይገልፃሉ፡፡ ይህ የማያልቅ የሚመስል ክርክር ከዛሬው ጨዋታ በኋላም በሰፊው እንደሚቀጥል ይጠበቃል፡፡

ባሬቶ እና አዲሱ ቡድናቸው የዛሬ ምሽቱን ጨዋታ የሚያከናውኑት በነዚህ ውዝግቦች እና ክርክሮች መሀል ሆነው ሲሆን ማሊዎችም በበኩላቸው የዛሬውን ጨዋታ አሸንፈው የማለፍ ዕድላቸውን ለማስፋት ይተጋሉ፡፡ የቡድኑ አሰልጣኝ ሄንሪ ካስፔርዣክ የቅዳሜው ድላቸው ሊያዝናናቸው እና ከመጠን ያለፈ በራስ የመተማመን ስሜት ሊፈጥርባቸው እንደማይገባ ይገልፃሉ፡፡ ‹‹ቅዳሜ በኢትዮጵያ ካገኘነው ድል በኋላ የበለጠ ውጤትን ልንራብ እና በጉዟችን ሁለተኛ የሜዳ ድላችንን ልናገኝ ይገባል›› ብለዋል፡፡

የማሪያኖ ባሬቶ ቡድን ለዛሬው ፍልሚያ ወደማሊ ይዟቸው የሄደው ተጫዋቾች

ግብ ጠባቂዎች፡ሲሳይ ባንጫ እና ጀማል ጣሰው

ተከላካዮች፡ቢያድግልኝ ኤሊያስ፣ ሳላህዲን ባርጌቾ፣ ዋሊድ አታ፣ አበባው ቡታቆ፣ ብርሀኑ ቦጋለ፣ ግርማ በቀለ፣ ዴቪድ በሻህ

አማካዮች፡ናትናኤል ዘለቀ፣ አንዳርጋቸው ይላቅ፣ ታደለ መንገሻ፣ ኤልያስ ማሞ፣ ኤፍሬም አሻሞ፣ ሄኖክ ካሳሁን

አጥቂዎች፡ኦሞድ ኡኩሪ፣ ጌታነህ ከበደ፣ ዩሱፍ ሳሌህ፣ ዳዋ ሆቴሳ

ግምታዊ አሰላለፍን በተመለከተ አሰልጣኙ በሚወዱት የ4-3-3 አሰላለፍ
ከግብ ጠባቂዎች ማንን እንደሚመርጡ ለመገመት ቢያስቸግርም ከማሊ ብሔራዊ ቡድን ባህሪ አንፃር ከመስመር የሚሻገሩ ኳሶችን በመቆጣጠሩ ረገድ የተሻለ የሆነው ሲሳይ ባንጫን ሊመርጡ ይችላሉ፡፡
በተከላካይ መስመር ምንም አይነት ለውጥ ይኖራል ተብሎ የማይጠበቅ ሲሆን ቢያድግልኝ በቀኝ፣ ሳላህዲን እና ዋሊድ በመሀል አበባው በግራ መስመር ላይ እንደሚሰለፉ ይጠበቃል፡፡

ሽመልስ በቀለ በሁለት ቢጫ ምክንያት ከቡድኑ ጋር አብሮ ስላልተጓዘ በእርሱ ቦታ ታደለ መንገሻ ከናትናኤል ዘለቀ እና አንዳርጋቸው ይላቅ ጋር የመሀል ክፍሉን እንደሚመሩ ሲጠበቅ በአጥቂ ስፍራም በቅዳሜው ጨዋታ ላይ የተሰለፉት ኦሞድ፣ ጌታነህ እና ዩሱፍ እንደሚገቡ ይገመታል፡፡

ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ወደማሊ አቅንቶ የነበረው አሚን አስካር በፊፋ በኩል መጨረስ የነበረበትን ፕሮሰስ ባለማጠናቀቁ ለቡድኑ መሰለፍ እንደማይችል እንደታወቀ በዛው ወደኖርዌይ መሄዱ ተገልጿል፡፡

ከቡድኑ ጋር ቢኖሩ መሰለፋቸው የማያጠራጥረው ሳላህዲን ሰይድ እና ቶክ ጀምስ አሁንም በጉዳት ላይ በመሆናቸው አብረው ሊጓዙ አልቻሉም፡፡

2015ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጉዞ ዋልያዎቹ ሶስቱንም ጨዋታዎቻቸውን የተሸነፉ ሲሆን በመጀመሪያ በአዲስ አበባ ስታድየም በአልጄሪያ 2-1፣ በመቀጠል ከሶስት ቀናት በኋላ ከሜዳቸው ውጭ በማላዊ 3-2 እንዲሁም ባለፈው ቅዳሜ አዲስ አበባ ላይ በማሊ 2-0 ተረተዋል፡፡ በዚሀም በዜሮ ነጥብ እና አራት የግብ ዕዳ በምድቡ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡

በዘንድሮው ማጣሪያ ከሰባቱ ምድብ አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው የሚያጠናቅቁት እና አንድ ምርጥ ሶስተኛ ሀገር ለአፍሪካ ዋንጫው ውድድር የሚያልፉ ይሆናል፡፡

ትንሽ ስለ ማሊ ብሔራዊ ቡድን

  • ቡድኑ ሊጠቀምባቸው የሚችሉ ተጨዋቾች የሚከተሉት ናቸው፡

ግብ ጠባቂዎች፡ማማዱ ሳማሳ (ገንጎ/ ፈረንሳይ)፣ ኦማር ሲሶኮ (አጃሲዮ/ ፈረንሳይ)፣ ዤርሜይ ቤርቴ (ኦንዜ ክሬቶ/ ማሊ)

ተከላካዮች፡አላሳኔ ታምቤ (ኮርትሬይ/ ቤልጅየም)፣ ኦስማን ኩሊባሊ (ፕላታኒያስ/ ግሪክ)፣ ፎውሴይኒ ዲያዋራ (ቱር/ ፈረንሳይ)፣ አዳማ ታምቡራ (ራንደርስ/ ዴንማርክ)፣ ኢድሪሳ ኩሊባሊ (ዲፋ ኤል ጀዲዳ/ ሞሮኮ)፣ ሳሊፍ ኩሊባሊ (ቲፒ ማዜምቤ/ ..ኮንጎ)፣ ሞሀመድ ኮናቴ (ቤርካኔ/ ሞሮኮ)

አማካዮች፡ባካዬ ትራኦሬ (ቡርሳስፖር/ ቱርክ)፣ ሴይዱ ኬይታ (ሮማ/ ጣሊያን)፣ ቶንጎ አህመድ ዱምቢያ (ቱሉዝ/ ፈረንሳይ)፣ ሲጋማሪ ዲያራ (ቫሎንሲዮን/ ፈረንሳይ)፣ ማሞቱ ንዲያዬ (ዙለቴ ቫሬጋም/ ቤልጂየም)፣ ያኩባ ሲላ (ኤርሲዬስፖር/ ቱርክ)፣ ሳምቡ ያታባሬ (ገንጎ/ ፈረንሳይ)፣ ባካሪ ሳኮ (ዎልቨርሀምፕተን/ እንግሊዝ)

አጥቂዎች፡ሙስታፋ ያታባሬ (ትራብዞንስፖር/ ቱርክ)፣ ሞሀመድ ትራኦሬ (ኤል ሜሪክ/ ሱዳን)፣ አብዱላዬ ዲያቢ (ሙስክሮን/ ቤልጂየም)፣ ሼክ ዲያራ ፋንታሜዲ (ኦክሴር/ ፈረንሳይ)

  • አሰልጣኝ  ሄንሪ ካስፔርዣክ   ዜግነት  ፖላንዳዊ
  • የቡድኑን አጨዋወት ስንመለከት በአካል ብቃት የዳበረ፣ በታክቲክ የተዋጣለት እና እንደየጨዋታው የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ሊጫወት የሚችል ቡድን ነው፡፡
  • በማሊ በኩል ከወሳኝ ተጨዋቾቻቸው መካከል ቅዳሜ በአዲስ አበባ ጉዳት ያስተናገደው አምበሉ ሴይዱ ኬይታ እና በጉዳት ምክንያት የማይኖረው የቦርዶው አጥቂ ሼክ ዲያባቴ መኖራቸው ያጠራጥራል፡፡
  • 2015 የሞሮኮ አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የእስካሁን ጉዞ ንስሮቹ ሁለቱን ጨዋታቸውን አሸንፈው በአንደኛው ተሸንፈዋል፡፡ በባማኮው ስታድ 26 ማርስ ስታዲየም ማላዊን 20 ድል ሲያደርጉ በአልጄርስ በአልጄሪያ 10 ተረተዋል፡፡ በአዲስአበባ ኢትዮጵያን 20 ረተዋል፡፡ በስድስት ነጥቦች እና በሶስት የጎል ክፍያ በምድቡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡

2 thoughts on “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ዕድሉን ለመሞከር ባማኮ ደርሷል

Leave a Reply

Your email address will not be published.