የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቻን መግቢያ በር ላይ ቆሟል

Ethiopia vs Kenya 3

ከወራት በኋላ በሩዋንዳ በሚካሄደው በሀገር ውስጥ ሊግ የሚጫወቱ ተጨዋቾችን ብቻ በሚያሳትፈው የቻን ውድድር ላይ ለመቅረብ የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታውን ከኬኒያ ብሔራዊ ቡድን ጋር እንዲያደርግ የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በደርሶ መልስ ጨዋታዎች ድል በማድረግ ከቡሩንዲ ጋር ለሚያደርገው ለቀጣዩ እና ለመጨረሻው የማጣሪያ ፍልሚያ መብቃት ችሏል፡፡ ቀጣዩ ዘገባ ዋልያዎቹ በናይሮቢ ጎላቸውን ሳያስደፍሩ የመጀመሪያ ጨዋታ ውጤታቸውን አስጠብቀው የወጡበትን የመልስ ጨዋታ በመጠኑ ይዳስሳል፡፡

ከጨዋታው በፊት

ከሁለት ሳምንታት በፊቱ የባህር ዳሩ የቡድኖቹ የመጀመሪያ ጨዋታ አንስቶ እስከ እዚህኛው ጨዋታ ጅማሮ ድረስ ለመልሱ ጨዋታ መጋጋል ምክንያት የሆኑ ሁነቶች ተከስተዋል፡፡ የዋልያዎቹ ጎል ሳያስተናግዱ በሁለት ጎሎች ልዩነት ማሸነፍ፣ የኬኒያዊያኑ በዚያ ጨዋታ ፍፁም ቅጣት ምትን ጨምሮ ንፁህ የጎል እድሎችን ማባከናቸው እና ይህ በእነሱ ዘንድ ከፍ ያለ ቁጭት ማስከተሉ፣ አሰልጣኙ ቦብ ዊልያምሰንን ጨምሮም በርካታ የቡድኑ አባላት በሜዳቸው እና በደጋፊዎቻቸው ፊት ውጤቱን እንደሚቀለብሱ ሲዝቱ መሰንበታቸው እንዲሁም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያደረጉት ደካማ አቀባበል እና ጥያቄ ያስነሳ አያያዝ የመልሱን ጨዋታ በከፍተኛ ጉጉት እንዲጠበቅ አድርገውት ነበር፡፡ የጨዋታው መጀመሪያ ሰዓት ሲደርስ በስታዲየሙ የታደመው ተመልካች ቁጥር አነስተኛ መሆን ግን የሞቀውን የሀራምቤ ከዋክብቱን ስሜት ያቀዘቀዘ፣ ጥቂት የማይባሉ ደጋፊዎችን ከሀገራቸው ውጪ ያገኙትን ዋልያዎቹን የበለጠ ያነሳሳ እና በሀገራቸውም ሆነ ከሀገራቸው ውጪ ባለ እግር ኳስ እና ሀገር ወዳድ ህዝባቸው እንዲኮሩ ያደረጋቸው ነበር፡፡

ከተጠበቀው በታች የተገኘው ጨዋታ

ኮሞሮሳዊው አርቢትር አሊ ሞሀመድ አደላይድ በሀገራቸው ዜጎች ሱሌይማን አማላዲን እና ሀማዲ ሁሴን ኢብራሂም ረዳትነት ጨዋታውን ሲያስጀምሩ ቡድኖቹ ወደ ሜዳ ይዘዋቸው የገቡት ተጨዋቾች የሚከተሉት ነበሩ፡-

ባለሜዳዎቹ ኬኒያዊያን እንደተለመደው ቦኒፌስ ኦሎችን በግብ ጠባቂነት ሲያሰልፉ፣ ኤድዊን ዋፉላ በቀኝ እና ለዚህ ጨዋታ የተመረጠው ዴኒስ ኦዲያምቦ በግራ ተከላካይ ስፍራዎች ተሰልፈዋል፡፡ ለሀገሩ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታው የሆነው ሀሩን ሻካቫ በመሀል ተከላካይ ስፍራ ከሙሳ መሀመድ ጋር ተጣምሯል፡፡ ታጋዩ ኮሊንስ ኦኮት አማካይ ክፍሉን እንዲመራ ሲደረግ ሀምፍሬ ሚዬኖ፣ ቪክቶር አሊ አቦንዶ እና ኬቨን ኪልማኒ ከጎኑ ጨዋታውን ጀምረዋል፡፡ ሜዳ ላይ የተሰለፉ የጎር ማሂያ ተወካዮችን ስድስት ያደረሰው ማይክል ኦሉንጋ በታስከሩ ጄሴ ዌሬ እየተረዳ ፊት መስመሩን እንዲመራ ተደርጓል፡፡ አሰልጣኙ ቦብ ዊልያምሰን ዋይክሊፍ ካሳያ (ግብ ጠባቂ)፣ ኖህ ዋፉላ፣ ኤሪክ ዮሀና፣ ቤርናርድ ማንጎሊ፣ ዳንሰን ካጎ፣ ብሪያን ቢርገን እና ጃክሰን ሳሌህን በተጠባባቂ ወንበር ላይ ይዘውም ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኩል በመጀመሪያው ጨዋታ በድንቅ መንገድ የፍፁም ቅጣት ምት አድኖ የቡድኑን የማለፍ እድል ያመቻቸው ታሪክ ጌትነት በቋሚዎቹ መካከል ሲሰለፍ፣ በጉዳት ምክንያት መሰለፍ ያልቻለውን ስዩም ተስፋዬን የተካው ሞገስ ታደሰ በቀኝ እና በሌሶቶው ጨዋታ ለሀገሩ የመጀመሪያ የነጥብ ጨዋታውን ካደረገ በኋላ በሳምንቱ በተካልኝ ደጀኔ ተተክቶ የነበረው ዘካሪያስ ቱጂ በግራ ተከላካይ ስፍራዎች ጀምረዋል፡፡ ከጨዋታ ጨዋታ እያመረቃ የሚገኘው የአስቻለው ታመነ እና የሳልሀዲን ባርጊቾ የመሀል ተከላካይ ጥምረትም በዚህም ጨዋታ ሌላ እድል ተሰጥቶታል፡፡ አማካይ ክፍሉ ላይ ብሩክ ቃልቦሬ እና ጋቶች ፓኖም ሲሰለፉ አምበሉ በኃይሉ አሰፋ እና ኤፍሬም አሻሞ በመስመር አማካይነት ጀምረዋል፡፡ ፊት ላይ የመጀመሪያው ጨዋታ የራምኬል ሎክ እና የቢኒያም አሰፋ ጥምረት ተደግሟል፡፡ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ አቤል ማሞ (ግብ ጠባቂ)፣ ሙጂብ ቃሲም (የመሀል ተከላካይ)፣ ተካልኝ ደጀኔ (የግራ ተከላካይ)፣ ምንተስኖት አዳነ እና ፍሬው ሰሎሞን (አማካዮች)፣ አስቻለው ግርማ (የመስመር አማካይ/አጥቂ) እና ባዬ ገዛኸኝን (አጥቂ) በተጠባባቂነት አስቀምጠውም ነበር፡፡

Ethiopia vs Kenya

ኬኒያ፡-

ግብ ጠባቂ፡- ቦኒፌስ ኦሎች

ተከላካዮች፡- ኤድዊን ዋፉላ፣ ሀሩን ሻካቫ፣ ሙሳ ሞሀመድ እና ዴኒስ ኦዲያምቦ

አማካዮች፡- ኮሊንስ ኦኮት፣ ሀምፍሬ ሚዬኖ፣ ቪክቶር አሊ አቦንዶ እና ኬቨን ኪልማኒ

አጥቂዎች፡-  ማይክል ኦሉንጋ እና ጄሴ ዌሬ

ኢትዮጵያ፡-

ግብ ጠባቂ፡- ታሪክ ጌትነት

ተከላካዮች፡- ሞገስ ታደሰ፣  አስቻለው ታመነ፣ ሳልሀዲን ባርጊቾ እና ዘካሪያስ ቱጂ

አማካዮች፡- ብሩክ ቃልቦሬ፣ ጋቶች ፓኖም፣ በኃይሉ አሰፋ እና ኤፍሬም አሻሞ

አጥቂዎች፡- ራምኬል ሎክ እና ቢኒያም አሰፋ

የሀራምቤ ከዋክብቱ በጉጉት ብቻ የተሞላ ያልተቀናጀ እና ያልተደራጀ የማጥቃት ፍላጎት እንዲሁም የዋልያዎቹ የተረጋጋ፣ በጨዋታው ጎላቸውን ሳያስደፍሩ የመውጣት ጥረት በተፋለሙበት መድረክ ከሁለቱም በኩል ያል ያህል ቀልብ የሚገዛ አልያም የሚያስደስት እንቅስቃሴ መመልከት አልተቻለም፡፡ ጎሎች የግድ ያስፈልጋቸው የነበሩት ኬኒያዊያኑ በመጀመሪያው አጋማሽ ተጋጣሚያቸውን በላቀ ጫና ውስጥ የመክተት ፍላጎታቸው በጎል ሙከራዎች የታገዘው በጥቂት አጋጣሚዎች ብቻ ሲሆን እነዚህም በ18ኛው ደቂቃ ቪክቶር አሊ አቦንዶ ወደ ጎል ሞክሮት በታሪክ ጌትነት የተመለሰው የቅጣት ምት እና የሀምፍሬ ሚዬኖ እና ማይክል ኦሉንጋ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ እንዲያውም በኤፍሬም አሻሞ ከሩቅ ተመትቶ እና በቦኒፌስ ኦሎች የተመለሰ ኳስ የመጀመሪያ ሙከራቸውን ለማድረግ 25 ደቂቃዎች ገደማ የወሰደባቸው ዋልያዎቹ በዚህ የመጀመሪያው አጋማሽ ከተጋጣሚያቸው እጅግ የተሻለ የጎል ማግባት አጋጣሚ አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል – በ43ኛው ደቂቃ ላይ የኦሉንጋን ሙከራ የያዘው ግብ ጠባቂው ታሪክ ኳሱን ይዞ ሳይጠቀምበት በመዘግየቱ የተሰጠውን ሁለተኛ ቅጣት ምት አሊ አቦንዶ ሞክሮ ግድግዳው የመለሰበትን ኳስ የዮሐንስ ልጆች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ወደፊት ይዘውት ሄደው ራምኬል ሎክ ወደ ጎል የመታ የመሰለውን ኳስ አምበሉ በኃይሉ አሰፋ ከቅርብ ርቀት ከግብ ጠባቂው ፊት ተቆጣጥሮ በቀላሉ አገባው ሲባል በጎሉ አናት ሰዷታል፤ በእውነቱ ለዋልያዎቹ እጅግ የሚያስቆጭ እድል ነበር፡፡ በዚህ ግማሽ ሌላ የሚታወስ ነገር ቢኖር የሀሩን ሻካቫ በጋቶች ፓኖም ላይ በሰራው ጥፋት፣ የታሪክ ጌትነት ኳስ እጁ ላይ በማቆየት እና የራምኬል ሎክ በአስመስሎ መውደቅ ምክንያቶች የማስጠንቀቂያ ካርዶች መመልከት ነበር፡፡

Salahadin Bergetcho

ጨዋታው ጎል ሳያስተናግድ ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምርም ኢትዮጵያዊያኑ የተጨዋች ለውጥ በማድረግ አጥቂው ቢኒያም አሰፋን አስወጥተው በሌላኛው አጥቂ ባዬ ገዛኸኝ ተክተዋል፡፡ ዋልያዎቹ የሁለተኛው አጋማሽ ጅማሯቸውን በማጥቃት አድርገው በጥሩ የቡድን ስራ የመጣውን ኳስ ራምኬል ሞክሮት ኦሎች በድንቅ ሁኔታ ጎል ከመሆን አድኖበታል፡፡ በቀጣዮቹ 10 ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል ከመጀመሪያው የተሻለ እንቅስቃሴ እና ፉክክር የታየ ሲሆን የሀራምቤ ከዋክብቱ በአቦንዶ አማካይነት ከቅርብ ርቀት የጨዋታውን ምርጥ እድላቸውን ሲያመክኑ የጄሴ ዌሬን በጭንቅላት የተገጨ ኳስ ታሪክ በእጁ ጣቶች ጨርፎ አውጥቶባቸዋል፡፡  ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በ62ኛው ደቂቃ ላይ ግን ኬኒያዊያኑ የጨዋታውን የመጨረሻ 30 ደቂቃዎች እጅግ አጓጊ እና አስጨናቂ ሊያደርግ እንዲሁም ድምር ውጤቱን ለመቀልበስ መንደርደሪያ ሊሆናቸው የሚያስችል እድል አገኙ፡፡ በዘንድሮው የኬኒያ ሊግ በእንቅስቃሴም ሆነ ጎሎችን በማስቆጠር የተሳካ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው አቦንዶ ላይ በተሰራው ጥፋት (ወይም አርቢትሩ ተሰርቷል ባሉት ጥፋት) ምክንያት የዊልያምሰን ቡድን አወዛጋቢ የፍፁም ቅጣት ምት አገኘ፡፡ በመጀመሪያው ጨዋታ በእለቱ ጥሩ በተጫወተው ኬቨን ኪልማኒ አማካይነት ወሳኝ ፍፁም ቅጣት ምቱን ላመከነው ቡድን በመልሱ ጨዋታ ሌላ ፍፁም ቅጣት ምት መሳት የሚታሰብ አልነበረም፡፡ ይህኛውን የፍፁም ቅጣት ምት የመምታት ኃላፊነት የተሰጠው ደግሞ በዚህኛው ጨዋታ በንፅፅር ጥሩ ለተንቀሳቀሰው እና ለእድሉ መገኘት ምክንያት ለነበረው አቦንዶ ነበር፡፡ በቅፅል ስሙ ‹‹አስለቃሽ ጋዝ›› ተብሎ የሚጠራው አቦንዶ ግን የማይታሰበውን አደረገ – ከኪልማኒም በባሰ ደካማ ሊባል የሚችል ፍፁም ቅጣት መቶ በታሪክ ቀኝ የሚገኘው ቋሚ መለሰበት (ቢያንስ ለትናንትም አስለቃሽነቱ ለተጋጣሚ ሳይሆን ለራሱ ቡድን ሆኗል)፡፡ አቦንዶ ወዲያውኑም በታስከሩ ዳንሰን ካጎ ተቀይሮ ወጥቷል፡፡ ከፍፁም ቅጣት ምቱ መሳት ክስተት በኋላ የሀራምቤ ከዋክብቱ ተስፋ መቁረጥ የተሞላበት፣ ደጋፊዎቻቸውንም ከስታዲየም በጊዜ እንዲለቁ ያደረገ ደካማ እንቅስቃሴ አድርገዋል፡፡ ዊልያምሰን ኤሪክ ጆሀና እና ኖህ ዋፉላን በኬቨን ኪልማኒ እና ኤድዊን ዋፉላ ምትክ ቢያስገቡም የፈጠሩት የተለየ ነገር አልነበረም፡፡ ዋልያዎቹ በበኩላቸው አስቻለው ግርማ እና ሙጂብ ቃሲምን በበኃይሉ እና ጋቶች ፓኖም ተክተው ነበር፡፡ ጨዋታውም ምንም ጎል ሳይቆጠርበት 0ለ0፣ በድምር በዋልያዎቹ የ2ለ0 ድል ተጠናቋል፡፡

አሰልጣኞቹ ምን አሉ?

የባለሜዳው እና በድምር ውጤት የተሸናፊው ቡድን አሰልጣኝ ቦብ ዊልያምሰን በሁለቱ ጨዋታዎች ላይ ያመከኗቸውን የፍፁም ቅጣት ምቶች ለሽንፈቱ ምክንያት አድርገዋል፡፡ ‹‹ሁለት ፍፁም ቅጣት ምቶችን አለመጠቀማችን የሚያሳዝን ነው፡፡ ብናስቆጥራቸው ኖሮ ቢያንስ ለመለያ ምቶች እንበቃ ነበር፡፡ ከጨዋታው በፊት ከአሊ አቦንዶ እና ዴኒስ ኦዲያምቦ ጋር በፍፁም ቅጣት ምቶች ጥበብ ዙሪያ አውርተን ነበር ግን አቦንዶ ያገኘውን ሳይጠቀምበት ቀርቷል›› በማለት ስኮትላንዳዊው አሰልጣኝ ሀሳባቸውን ገልፀዋል፡፡ የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በበኩላቸው ጎል ሳያስተናግዱ በመውጣት ማለፍ የመቻላቸውን ነገር ከስኬታማ የጨዋታ እቅድ ጋር አያይዘውታል፤ በዳኝነቱ ላይም ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ ‹‹ከመከላከል ይልቅ የበለጠ ማጥቃትን አቅደን ነበር፤ ይህ እንደሰራልንም መናገር እችላለሁ›› ያሉት አሰልጣኙ ‹‹ነገር ግን በዳኝነቱ ተከፍቼያለሁ፡፡ ዋናው አርቢትር ከእኛ በተቃራኒ በርካታ አላስፈላጊ ውሳኔዎች ሲወስኑ ነበሩ›› በማለት አክለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.