[ነፃ ሃሳብ] የአፄ ምኒልክ ሁለቱ ገፅታዎች

images_Emperor_menelik_ii_277971339

(በጃ አዳም)

የአፄው ነገር ዛሬም አልበረደም። ፖለቲካ እየተቸበቸበበት ይገኛል። ትውልዱም በተቀደደለት መንገድ ብቻ እየተመመ ነው። አፄው ውለታ ውለው ካረፉ አንድ ክፍለ ዘመን አለፈው። ነገር ግን ሞተውም በሀውልታቸው ትውልዱን ለሁለት ከፍለውታል። ይቺን አጭር ፅሁፍ እንድፅፍ ያነሳሳኝም ይሄው ነው። አንዳንዴ የማምነውን ወገን ሳጣ እና የትውልዱን በሁለት ፅንፍ መከፈል ሳይ ምነው ባይወለዱ እልና አድዋ ትዝ ስትለኝ እጄን ባፌ እጭናለሁ። አፄው የመሩት አንድ ሀገር፣ ያስተዳደሩት አንድ ሀገር ፣ የወደቁላት ለአንድ ኢትዮጵያ ለሚትባል ሀገር ሲሆን እሳቸው ግን በአንድ ሀገር ህዝቦች በሁለት ገፅታ ስለመታየታቸው ታዝቤ ነው። አንድም በጥሩ አንድም በክፉ የመታየታቸው ነገር ብዙ ተብሎለታል። ተፅፎለታልም። ትውልዱም ግራ እየገባን አለን። እኔ በበኩሌ ከየትኛው ጎራ መከፈል እንዳለብኝ አልገባኝም። ሁለቱም ጎራዎች የየራሳቸውን ምክንያት ያቀርባሉ። አንዱ “እምዬ” ሲላቸው ሌላው “ሂትለር” ይላቸዋል። የቱ ጋር ነው ስህተቱ የተፈጠረው? ታሪክ ዋሽቶናል ማለት ነው? የእውነት እንደሚባለው አፄው ብሔርን ዒላማ ያደረገ ጭፍጨፋ አድርገዋል? ካልሆነ ለምን የአንድ ሀገር ህዝቦች ስለ አፄው ሲነሳ ለሁለት ተከፈሉ? ከልጅነቴ ጀምሮ ስለ አፄው የተነገረኝን ክፉ ነገር ባላስታውስም ለሀገራቸው ያደረጉት ገድል ግን እንደ ተረት ነበር ሲነገረኝ ያደኩት። በህይወት ያለች እና ህያው ምስክር የምትሆን አድዋ ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ለዘላለም ታትሞ እንደሚኖር ግልፅ ነው። ምኒልክንና የአድዋን ድል ለያይቶ ማየት ፈፅሞ የማይሞከር ነው። እኔ በበኩሌ አይቻለኝም። ግን ምኒልክ ሂትለር ነው የሚሉትን ወገኖች ስሰማ ልቤ መከፈሉ አልቀረም። ዘፈኖቻችንም ለሁለት ጎራ ተከፍለው እናገኛቸዋለን። በአንድ ወገን “ሚኒልክ ጨፍጫፊ” ሲባል በአንዱ ወገን ደግሞ “የነፃነት ታጋይ ጥቁር ሰው” እየተባለ ይዘፈናል። አድማጩም ለሁለት ተከፍሎ ይገኛል። ለትውልድ የሚተላለፉ እነዚህ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ዘፈኖች የአፄውን ገፅታ ምን ደረጃ ላይ እንደሚያደርሱ ለመገመት አይከብድም። ጌታቸው ወንዲራድ “የህወሓት የበላይነትና የትግራዋያን ዕጣ” በሚል መፅሐፉ ላይ በ ታሪክና ፖለቲካ ርዕስ ስር ስለ አድዋ ድል እና ስለ አፄ ምኒልክ የታሪክ ምሁሮቻችንን በማጣቀስ የግሉን አተያይ ይነግረናል። ጌታቸው ወንዲራድ የምኒልክ የሁለቱ ገፅታዎች መነሻ የዘውጉን አገዛዝ እንደ ምክንያት ያቀርብልናል። “ምኒልክንና የአድዋን ድል ለፖለቲካ ጥቅም ተጠቅመውበታል” ይለናል። ” በተለየ መልኩ” ይለናል ጌታቸው “በተለየ መልኩ ባሳለፍናቸው ሃያ ስድስት ዓመታት ውስጥ በምኒልክና በአድዋ ድል ዙሪያ ጠርዝ ለጠርዝ በቆሙ ሃሳቦች ውርክብ የበዛበት የታሪክ ንትርክ ይስተዋላል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ንትርኩ አዲሱን ትውልድ ባቀፈ መልኩ በሶስት ጠርዞች፣ በሁለት ጎራ የተከፈለ ዱላ ቀረሽ ክርክር ይስተዋላል። የአድዋም ድል በዓል የልዩነታችን ቀይ መስመር አስማሪ ሆኗል”( ከገፅ 8–ገፄ 9 ልብ ይሏል)። በአንድ ወገን “ሀገርን ነፃ ያወጣ ምኒልክ” ሲባል በሌላው ወገን ደግሞ “ጡት አስቆራጩ ምኒልክ” እየተባለ ሁለት ፈፅሞ የማይጣጣሙ ገፅታዎችን ለዚህ ትውልድ ማቅረብ ትውልዱን ግራ ከማጋባትና ከመከፋፈል ውጭ ሌላ ጥቅም አለው ብዬ አላምንም። የዚህ ትርክት ዋና አላማ ጌታቸው እንደሚነግረን ትውልዱን ለመከፋፈልና ለፖለቲካ ጥቅም ከሆነ ብዙ የሚቆይና ረዥም እድሜ ያለው አይመስለኝም። ምክንያቱም ይህ ምክንያታዊ የሆነ ወርቃማ ትውልድ አንድ ቀን ነገሮችን አመዛዝኖ ይደርስባቸዋል ብዬ አምናለሁ። ለኛ የሚጠቅመን ግን ምክንያታዊ መሆን እና መሆን ብቻ ነው። የታሪክ ምሁሮቻችን በሁለቱ ገፅታዎች መስማማት ካልቻሉ ትውልዱ ለምን ብሎ ራሱን ጠይቆ በምክንያት ከተቻለ ሁለቱን ገፅታዎች በአንድ ገፅታ መጠቅለል አለበት። ካልተቻለ ግን ትውልዱ ሁለቱንም ገፅታዎች ተቀብሎ ከታሪክ መሸሽ አይቻልምና ከታሪኩም ተምሮ ልዪነቶችን አጥብቦ ለዚች ምስኪን ሀገር እድገት እጅ ለእጅ መያያዝ የውዴታ ግዴታው ብቻ ሳይሆን ጊዜውም የሚያስገድድው ነው። እንደሚባለው ምኒልክ ለሀገር ነፃነት የታገለ መሪ ከሆነ እሰየው። ለሁላችንም ነፃነት ነውና። በሌላው ወገን እንደሚባለውም ምኒልክ ሂትለር ከሆነ ይቅር ተባብለን በፍቅር ተደምረን ወደ ፊት መጓዝ እንጂ ያለን አማራጭ የታሪክን መጥፎ ጎን መተረክ ጥቅሙ ዜሮ ይሆናል። ልዩነታችንን አጥብበን ወደ ፊት በመጓዝ ለኛም ፣ ለሀገራችንም ፣ ለመጪው ትውልድም አሻራችንን አሳርፈን ማለፍ አለብን ብዬ አምናለሁ። አመሰግናለሁ። ፈጣሪ ሀገራችንን ይባርክ!!!

ጃ አዳም ፪ሺ ፲ ዓ.ም.