የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ዳይመንድ ሊግ ዘጠነኛ የውድድር ዓመት ዛሬ በኳታር ዶሃ በሚካሄዱ ፉክክሮች ይጀመራል

DL 2018

በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማሕበር የበላይ ተቆጣጣሪነት ዘንድሮ ለዘጠነኛ ግዜ የሚካሄደው የዳይመንድ ሊግ ፉክክር ዛሬ ምሽት በኳታር ዶሀ ይጀመራል፡፡ በዶሀው ኳታር ስፖርትስ ክለብ ስታድየም አስተናጋጅነት በሚካሄደው የዛሬ ምሽቱ ፉክክር የዳይመንድ ሊጉ የነጥብ ፉክክር አካል ያልሆኑ 2 እንዲሁም 13 የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ፕሮግራም የተያዘላቸው ሲሆን 15 ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም የውድድሩ ተሳታፊ ናቸው፡፡

የሀገሬው ደጋፊዎች በወንዶች ከፍታ ዝላይ የዓለም ሻምፒዮን የሆነው ሙታዝ ኢሳ ባርሺም እና የ400 ሜ. ተወዳዳሪው አብደራህማን ሳምባ ውጤቶችን በሚጠበቁበት ምሽት በአጭር ርቀት የሴቶች 100 ሜ. እና 100 ሜ. መሰናክልም በጉጉት ይጠበቃሉ፡፡

በርቀቱ የኦሊምፒክ ሻምፒዮን ጃማይካዊቷ ኤላይኔ ቶምፕሰን፣ በዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮኗ አይቮሪኮስታዊ ሙሬይል አሆሬ፣ የዓለም ሻምፒዮና የብር ሜዳልያ ድርብ ድል ባለቤቷ አይቮሪኮስታዊ ማሪ ጆሴ ታሉ እና የ200 ሜ. የሁለት ግዜ የዓለም ሻምፒዮኗ ኔዘርላንዳዊቷ ዳፍኔ ሺፐርስ መካከል ብርቱ ትንቅንቅ እንደሚደረግበት በሚጠበቀው የሴቶች 100 ሜ. ፉክክር ፈጣን ሰዓት እንደሚዘገብ ይታመናል፡፡ አራት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተካፋይ በሚሆኑበት የሴቶች 1500 ሜ. ፉክክር ደቡብ አፍሪካዊቷ ካስተር ሴመንያ የአሸናፊነቱን የቅድሚያ ግምት አግኝታለች፡፡ በሴቶች 3000 ሜ. ተካፋይ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውድድሩን በበላይነት ለማጠናቀቅ የውድድር ስፍራውን የርቀቱ ሪኮርድ 8፡20.68 በሆነ ሰዓት የያዘችው ኬንያዊቷ የዓለም የ5000 ሜ. ሻምፒዮን ሔለን ኦቢሪን መቅደም ፈታኙ የቤት ስራቸው ይሆናል፡፡ በሴቶች 100 ሜ. መሰናክል አሜሪካዊቷ የኦሊምፒክ ሻምፒዮን ብሪያና ማክኒል የርቀቱ የዓለም ሪኮርድ ባለቤት ከሆነቸው የሀገሯ ልጅ ኬንድራ ሀሪሰን ጋር የምታደርገው ፉክክርም ከፍተኛ ተጠባቂነት ያለው ነው፡፡

በወንዶች 200 ሜ. ቱርካዊው ራሚል ጉሊዬቭ ከለንደን የዓለም ሻምፒዮና ድሉ በኋላ የመጀመሪያ ውድድሩን የሚያደርግ ሲሆን ትሪንዳዲያዊው የኮመንዌልዝ ሻምፒዮን ጀሪም ሪቻርድስ እና ከጉዳት ከተመለሰው ካናዳዊው የኦሊምፒክ ሜዳሊስት አንድሬ ደ ግራሰ ብርቱ ተፎካካሪዎቹ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡ በ400ሜ. ወንዶች በቅርቡ በጎልድኮስት በተካሄደው የኮመንዌልዝ ሀገራት ሻምፒዮና የርቀቱ ወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ የሆነው ቦትስዋናዊው አይሳክ ማክዋላ የዓለም ሻምፒዮና የብር ሜዳልያ ባለቤት ከሆነው የባሕማሱ ስቴቨን ጋርዲነር ጋር የሚፋለሙበት ፉክክርም የተመልካችን ትኩረት ይስባሉ ተብለው ከሚጠበቁት ተርታ የሚመደብ ነው፡፡

በምሽቱ የዶሀ ውድድር ላይ ብዛት ያላቸው ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም የሚካፈሉ ሲሆን የዳይመንድ ሊግ ነጥብ በሚመዘገብባቸው የሴቶች 1500 ሜ. በሱ ሳዶ፣ አልማዝ ተሻለ፣ ጉዳፍ ፀጋዬ እና ሀብታም አለሙ እንዲሁም በሴቶች 3000 ሜ. በየኑ ደገፋ፣ መስከረም ማሞ፣ ለተሰንበት ግደይ፣ አበራሽ ምንሰዎ እና ፎቴይን ተስፋዬ ይወዳደራሉ፡፡ የዳይመንድ ሊጉ የነጥብ ፉክክር አካል ባልሆኑት ውድድሮች ተሬሳ ቶሎሳ በወንዶች 1500 ሜ. እንዲሁም ሀይለማሪያም አማረ፣ ጫላ በዩ፣ ተስፋዬ ድሪባ፣ ተስፋዬ ግርማ እና ቶሎሳ ኑጉሪ በወንዶች 3000 ሜ. መሰናከል ይፎካከራሉ፡፡

አራት አህጉሮችን፣ አስራ ሁለት አገሮችን እና 14 ከተሞችን የሚያዳርሰው የዘንድሮው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ሜይ 4/2018 በዶሀ ተጀምሮ ኦገስት 31/2018 በቤልጅየም ብራስልስ በሚካሄደው የፍፃሜ ፉክክር የሚዘጋ ይሆናል፡፡ የአጠቃላይ አሸናፊ ለሚሆኑ አትሌቶች በአጠቃላይ 3.2 ሚሊዮን ዶላር በሽልማትነት ሊበረከት የተዘጋጀበት የ2018 የዳይመንድ ሊግ ውድድር በነጥብ አሰጣጡ ረገድ ባለፈው ዓመት የነበረውን ሕግ እንደሚከተል ታውቋል፡፡ በ32ቱም የዳይመንድ ሊግ የውድድር አይነቶች ላይ የሚሳተፉት አትሌቶች በመጀመሪያዎቹ 12 ውድድሮች ላይ በሚያስመዘግቡት ነጥብ መሰረት በዙሪክ እና ብራስልስ ለሚካሄዱት የፍፃሜ ውድድሮች የሚበቁ ሲሆን በፍፃሜው ፉክክር ከፍፃሜዎቹ ውድድሮች በፊት ያስመዘገቡት ነጥብ ተረስቶ በፍፃሜው ውጤት ብቻ የየውድድር አይነቶቹ አሸናፊዎች የዓመቱ የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ዳይመንድ ሊግ ሻምፒዮንነት ክብርን የሚቀዳጁ ይሆናል፡፡ ለፍፃሜ የሚቀርቡት አትሌቶች በሙሉ የዓመቱ የዳይመንድ ሊግ ሻምፒዮን የመሆን ዕድላቸው ዕኩል ሆኖ ፉክክራቸውን የሚጀምሩ መሆኑ በዙሪክ እና ብራስልስ የሚካሄዱትን ፉክክሮች ይበልጥ ተጠባቂ ያደርጋቸዋል፡፡

በድምሩ 17 የከዚህ ቀደም የኦሊምፒክ ሻምፒዮን አትሌቶችን በተፎካካሪነት ያካተተው የ2018 የዶሀ ዳይመንድ ሊግ ውድድር እንደተለመደው የወቅቱ የዓለም ፈጣን ሰዓቶች እና ምርጥ ውጤቶች የሚመዘገብበት እንደሚሆንም ይጠበቃል፡፡

የ2018 አስራ አራቱ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች
ሜይ 4/2018 — ዶሀ – ኳታር
ሜይ 12/2018 — ሻንግሀይ – ቻይና
ሜይ 26/2018 — ዩጂን – ዩ.ኤስ.ኤ.
ሜይ 31/2018 — ሮም – ጣልያን
ጁን 7/2018 — ኦስሎ – ኖርዌይ
ጁን 10/2018 — ስቶክሆልም – ስዊድን
ጁን 30/2018 — ፓሪስ – ፈረንሳይ
ጁላይ 5/2018 — ሎዛን – ስዊዘርላንድ
ጁላይ 13/2018 — ራባት – ሞሮኮ
ጁላይ 20/2018 — ሞናኮ – ሞናኮ
ጁላይ 21-22/2018 — ሎንደን – ግሬት ብሪቴይን
ኦገስት 18/2018 — በርሚንግሀም – ግሬት ብሪቴይን
ኦገስት 30/2018 — ዙሪክ – ስዊዘርላንድ
ኦገስት 31/2018 — ብራስልስ – ቤልጂየም