የአሉላ ግርማ አስደናቂ ጎል ፈረሰኞቹን አሸናፊ አድርጓቸዋል

alual

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከ40 ቀናት እረፍት በኋላ ተመልሷል፡፡ በሴካፋ ውድድር ምክንያት ከመቋረጡ በፊት የሁለት ሳምንታት ጨዋታዎችን ያደረገው ውድድር ለሶስተኛው ሳምንት የተመለሰው ለረዥም ጊዜ መቋረጡ በሚያመጣው ችግር ከተፈጠረው ውዝግብ፣ በተለይም በትልልቆቹ ክለቦች ከተደረጉ ያልተጠበቁ ለውጦች እና ከሌሎችም አነጋጋሪ ጉዳዮች በኋላ ነበር፡፡ ቀጣዩ ዘገባም የፕሪምየር ሊጉን የሶስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በተለይም በኤሌክትሪክ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ፍልሚያ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ለመቃኘት ይሞክራል፡፡

ያለፉትን ጥቂት ውድድር ዘመናት ከእነሱ በማይጠበቅ መንገድ ላለመውረድ ሲታገሉ የነበሩት ኤሌክትሪኮች በክረምቱ በዝውውሩ ገበያ ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ እና ተጨዋቾችን በማምጣት የተሻለ የውድድር ዘመን ለማሳለፍ ተስፋ አድረገው ጀምረዋል፡፡ በአሰልጣኝ ብርኃኑ ሙሉ የሚመሩት ኤሌክትሪኮች በመጨረሻው ሰዓት ያዛወሩትን የቀድሞውን የቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂ ፍፁም ገብረማሪያም ጨምሮ ብሩክ አየለ፣ አለምነህ ግርማ፣ አሸናፊ ሽብሩ፣ ዋለልን ገብሬ እና ተስፋዬ መላኩን የመሳሰሉ ተጨዋቾችን ወደቡድናቸው ሲቀላቅሉ በመጀመሪያ ጨዋታቸውም መከላከያን በመርታት ተስፋ ሰጪ አጀማመር አድርገዋል፡፡ በሁለተኛ ጨዋታቸው ግን በአዳማ ከነማ እጅ ሽንፈትን አስተናግደዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በበኩላቸው ከሌሎች ቀደምት ዓመታት በተለየ በዝውውር ገበያው እምብዛም ተሳታፊ ያልነበሩ ሲሆን የብሔራዊ ቡድኑ የወቅቱ ተመራጮች አስቻለው ታመነ እና ራምኬል ሎክ እንዲሁም ቀድሞ ተጨዋቻቸው አበባው ቡታቆን ብቻ ከሚታወቁ ስሞች መካከል አዛውረዋል፡፡ በሚታወቁበት የውጪ ሀገር ተጨዋች ዝውውር ላይም ተሳታፊ አልነበሩም፡፡ ፈረሰኞቹ በክረምቱ በቀጠሩት አሰልጣኛቸው ማርቲን ኩፕማን አመራር በመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታቸው ቢረቱም ደጋፊዎቻቸው በቡድኑ በኳስ ቁጥጥር እና በማጥቃት ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ ደስተኞች ነበሩ፡፡ በቀጣዩ ጨዋታቸውም በሲዳማ ቡና ላይ የጎል ናዳ ማዝነብ ችለው ነበር፡፡ ነገር ግን በትክክል ባልታወቀ ምክንያት ሆላንዳዊው አሰልጣኝ ለእረፍት ከሄዱበት ሀገራቸው እንዳይመለሱ ተደርገዋል፡፡ ኃላፊነቱም ለቀድሞው አሰልጣኝ ማርት ኖይ መሰጠቱ ተሰምቷል፡፡ እናም የዛሬውን አያድርገው እና በ80ቹ መጨረሻ እና በ90ቹ መጀመሪያ የላቀ ተፎካካሪ የነበሩት ሁለቱ ቡድኖች እኩል ሶስት ነጥቦችን ይዘው ይህን ጨዋታ ጀምረዋል፡፡ ኤሌክትሪኮች 3-5-2 በመሰለ እና ግን ባብዛኛው ወደ 5-3-2 ያመዝን በነበረ አሰላለፍ አሰግድ አክሊሉን በግብ ጠባቂ ስፍራ፤ ሲሴ ሀሰን፣ ተስፋዬ መላኩ፣ በረከት ተሰማ፣ አወት ገብረሚካኤል እና አሳልፈው መኮንንን በተከላካይ ስፍራ፤ አዲስ ነጋሽ፣ ብሩክ አየለ እና ማናዬ ፋንቱን በአማካይ ስፍራ እንዲሁም ፍፁም ገብረማሪያም እና ፒተር ንዋድኬን በአጥቂ ስፍራ አሰልፈዋል፡፡ የማርት ኖይ ሹመት በኦፊሴላዊ መንገድ ባለመፈፀሙ ምክንያት በምክትል አሰልጣኙ ዘሪሁን ሸንገታ መሪነት ወደ ሜዳ የገቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በበኩላቸው በሆላንዳዊው ተመራጭ የ4-3-3 አሰላለፍ ሮበርት ኦዳንካራን በግብ ጠባቂ ስፍራ፤ አለማየሁ ሙለታ፣ ደጉ ደበበ፣ አይዛክ ኢዜንዴ እና መሀሪ መናን በተከላካይ ስፍራ፤ ተስፋዬ አለባቸው፣ አሉላ ግርማ እና ምንያህል ተሾመን በአማካይ ስፍራ እንዲሁም በኃይሉ አሰፋ፣ ብሪያን ኦሞኒ እና አዳነ ግርማን በአጥቂ ስፍራ ተጠቅመዋል፡፡

በጉጉት የተጠበቀው ጨዋታ የመጀመሪያውን ሙከራ የተመለከተው በስድስተኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን ከኤሌክትሪክ ተከላካዮች በረዥም የተላከ ኳስ አይዛክ ኢዜንዴ በጭንቅላቱ ላይ አምልጦት ሄዶ ፍፁም ገብረማሪያም እግር ቢደርስም አጥቂው የቀድሞ ክለቡ ላይ ጎል ለማስቆጠር የመታው ምት ሮበርት ኦዳንካራን ለመፈተን ብዙም አቅም አልነበረውም፡፡ ከፍፁም ከዚህ የተሻለ ይጠበቅ ነበር፡፡ በ17ኛው ደቂቃ አለማየሁ ሙለታ ከቀኝ መስመር ያሻገረው ጥሩ ኳስ አዳነ ግርማ በጭንቅላቱ ላይ አምልጦታል፡፡ በ25ኛው ደቂቃ በኃይሉ አሰፋ በተመሳሳይ ከቀኝ መስመር ቢያሻግርም አዳነ ጋ ከመድረሱ በፊት የኤሌክትሪኩ ተከላካይ በረከት ተሰማ ጨርፎ አውጥቶታል፡፡ በ32ኛው ደቂቃ ኤሌክትሪኮች በጥሩ ቅብብል የፈጠሩትን እድል ማናዬ ፋንቱ ወደጎል ሞክሮት ወደ ውጪ ወጥቶበታል፡፡ በ34ኛው ደቂቃ ከግራ በኩል መሀሪ መና በአየር ላይ ያሻገረውን ኳስ አዳነ ለሶስተኛ ጊዜ ሳይደርስበት አልፎት ሄዷል፡፡ በ35ኛው ደቂቃ ተስፋዬ አለባቸው ያሻገረውን ኳስ ብሪያን ኦሞኒ በሚገባ ተቆጣጥሮ ከቅርብ ርቀት ወደ ጎል የመታው ኳስ በአግዳሚው ላይ ወጥቶበታል፡፡ ይህ ለፈረሰኞቹ የመጀመሪያው አስደንጋጭ እና አስቆጪ ሙከራቸው ነበር፡፡ በ42ኛው ደቂቃ የበኃይሉ መልካም ሙከራ ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃ ላይ በኃይሉ ወደ ጎል ያሻገረው ኳስ የኤሌክትሪክ ተከላካዮች በሚገባ ማውጣት ተስኗቸው ሲደነባበሩ ኳሱ አዳነ እግር ላይ ቢደርስም አንጋፋው አጥቂ ሶስት ሜትር ከማይሞላ ርቀት ምርጡን አጋጣሚ አምክኗል፤ ምንም ጎል ሳይታይም የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል፡፡

ቡድኖቹ ለሁለተኛው አጋማሽ ወደ ሜዳ ሲመለሱ ጊዮርጊሶች በመሀሪ መና ስፍራ አበባው ቡታቆን ቀይረው አስገብተዋል፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ኤሌክትሪኮች ብሩክ አየለን በማስወጣት በኃይሉ ተሻገርን ተክተዋል፡፡ በ57ኛው ደቂቃ ፒተር ንዋድኬ ያሻገረው ኳስ ፍፁም እግር ላይ ሳይደርስ በፊት ኦዳንካራ አውጥቶታል፡፡ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአጭሩ የጀመሩትን የማእዘን ምት ተስፋዬ ከጠበበ ማእዘን ወደጎል ሞክሮት አሰግድ አክሊሉ እንደምንም አውጥቶበታል፡፡ በዚህ ምክንያት የተገኘው የማእዘን ምት ግን ሁሉንም ላስደነቀ ክስተት ምክንያት ሆኗል፡፡ በቀኝ በኩል የተገኘውን የማእዘን ምት በኃይሉ አሰፋ ወደ ውስጥ በማሻገር ፈንታ ከጎሉ ርቀት መሀል ለመሀል ይገኝ ለነበረው አሉላ ግርማ አቀበለው፤ በእለቱ በአማካይነት የተጫወተው አሉላም ከበኃይሉ የደረሰውን ኳስ ሳያቆም በቀጥታ በመምታት የአሰግድ ጎል መረብ ውስጥ ማእዘኑ ላይ መስጎታል፡፡ የአሉላ ጎል የጊዮርጊስ ደጋፊዎችን ብቻ ሳይሆን በስታዲየሙ የታደሙትን ሁሉ በአግራሞት ከመቀመጫቸው ያስነሳ እጅግ አስደናቂ ጎል ነበር፡፡ የኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ አሰግድም ሆነ ሌሎቹ ተጨዋቾች ጎሉን ለመከላከል ምንም አቅም አልነበራቸውም፡፡ ከዚያ በኋላ ኤሌክትሪኮች የቀኝ ተከላካዩ አወት ገብረሚካኤልን አስወጥተው አጥቂው ሀብታሙ መንገሻን በማስገባት በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች ጫና ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡ በ78ኛው ደቂቃ በኃይሉ ተሻገር ያሻገረውን ኳስ ፍፁም በጭንቅላቱ ገጭቶ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበታል፡፡ በ82ኛው ደቂቃ ኤሌክትሪኮች ሌላ ተሻጋሪ ኳስ ወደ ጎል ልከው የሚነካው ጠፍቶ ወጥቷል፡፡ በ84ኛው ደቂቃ አምበሉ አዲስ ነጋሽ ከ30 ሜትር ገደማ ወደ ጎል የመታው አስደናቂ ኳስ ለጥቂት በአግዳሚው ላይ ወጥቶበታል፡፡ ኤሌክትሪኮችም ይህ የመጨረሻ ደቂቃዎች ጫናቸው ፍሬ ሳያፈራ በ1ለ0 ውጤት ተረትተዋል፡፡

በሌሎች ጨዋታዎች

  • ሁለቱንም ጨዋታዎቻቸውን በማሸነፍ የሊጉ መሪ የነበሩት አዳማ ከተማ እና ዳሸን ቢራ በድል ጉዟቸው መቀጠል አልቻሉም፡፡ አዳማዎች ወደ አዲስ አበባ አቅንተው ባደረጉት ጨዋታ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር 1ለ1 ተለያይተዋል፡፡ የቀድሞው የቡናማዎቹ ታሪካዊ አጥቂ ታፈሰ ተስፋዬ ለአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ቡድን አዳማ የመሪነት ጎል ቢያስቆጥርም ጋቶች ፓኖም ባለሜዳውን ቡድን አቻ ማድረግ ችሏል፡፡ ዳሸኖች በበኩላቸው ባልተጠበቀ መንገድ በሜዳቸው በወላይታ ድቻ የ1ለ0 ሽንፈት ደርሶባቸዋል፡፡ በዛብህ መለዮ ለድቻ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል፡፡
  • አዲስ አበባ ላይ በተደረገ ጥሩ ፉክክር ባስተናገደ ሌላ ጨዋታ ደደቢት መከላከያን 3ለ2 ረትቷል፡፡ የሳሙኤል ሳኑሚ ሁለት በጊዜ የተቆጠሩ ጎሎች ሰማያዊዎቹን መሪ ቢያደርጉም መከላከያዎች በሚካኤል ደስታ እና ምንይሉ ወንድሙ ማራኪ ጎሎች አቻ መሆን ችለው ነበር፡፡ ነገር ግን ዳዊት ፍቃዱ በሁለተኛው አጋማሽ ያስቆጠረው ጎል ለደደቢት ውዶቹን ሶስት ነጥቦች አጎናፅፏል፡፡
  • ሀዋሳ ላይ በተደረገው የደቡብ ደርቢ ጨዋታ ባለሜዳው ሀዋሳ ከተማ ከታች የመጣው ሀዲያ ሆሳዕናን 4ለ3 አሸንፏል፡፡ ጋዲሴ መብራቴ (2)፣ ፍርድአወቅ ሲሳይ እና አመለ ሚልክያስ ለሃዋሳ ከተማ እንዲሁም ዱላ ሙላቱ (2) እና አበባየሁ ዮሐንስ ለሀዲያ ሆሳዕና ጎሎቹን አስቆጥረዋል፡፡ ሌላኛው የደቡብ ክለብ ሲዳማ ቡናም በበረከት አዲሱ እና ላኪ ላበርዲን ጎሎች በሜዳው ድሬዳዋ ከተማን 2ለ1 ረትቷል፤ ይሁን እንዳሻው ለድሬዳዋ ከተማ የማስተዛዘኛዋን ጎል አስመዝግቧል፡፡ አርባምንጭ ከተማዎች በበኩላቸው በሜዳቸው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር 1ለ1 ተለያይተዋል፡፡ በረከት ወልደፃዲቅ ለአርባምንጭ እና ኤፍሬም አሻሞ ለንግድ ባንክ ጎሎቹን አስቆጥረዋል፡፡
  • ከነዚህ ውጤቶች በኋላ አሁንም አዳማ ከነማ በሰባት ነጥቦች እና አራት የጎል ክፍያ መሪ ሲሆን ደደቢት በተመሳሳይ ሰባት ነጥቦች እና ሁለት ጎሎች ይከተላል፡፡ ባለስድስት ነጥቦቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻ ሶስተኛ እና አራተኛ ናቸው፡፡ የአዳማ ከነማው ታፈሰ ተስፋዬ በሶስት ጎሎች ከፍተኛ ጎል አግቢነቱን እየመራ ይገኛል፡፡
  • የአራተኛው ሳምንት ጨዋታዎች የፊታችን ረቡዕ እና ሀሙስ ቀጥለው ሲደረጉ ረቡዕ በአዲስ አበባ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሬዳዋ ከተማን እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዳሸን ቢራን ያስተናግዳሉ፡፡ ሐሙስ በሆሳዕና – ሀዲያ ሆሳዕና ሲዳማ ቡናን፣ በቦዲቲ – ወላይታ ድቻ ሀዋሳ ከተማን፣ በአዳማ – አዳማ ከተማ ደደቢትን ሲያስተናግዱ በአዲስ አበባ መከላከያ ከአርባምንጭ ከተማ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና ከኤሌክትሪክ ይፋለማሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.