‹‹የተሻለ ውጤት እያመጣሁ ለምን ራሴን ከኃላፊነት አነሳለሁ?!››

Yohaness Sahle

‹‹የተሻለ ውጤት እያመጣሁ ለምን ራሴን ከኃላፊነት አነሳለሁ?!››

የኢትዮጵያ ወንዶች እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን በርዋንዳው የቻን ውድድር ላይ ተሳትፎ አድርጎ ተመልሷል፡፡ ዋልያዎቹ ካደረጓቸው ሶስት የምድብ ጨዋታዎች በሁለቱ ተሸንፈው እና በአንዱ አቻ ተለያይተው ከምድባቸው የመጨረሻውን ደረጃ ይዘው አጠናቅቀዋል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ ዋና አሰልጣኙ ዮሐንስ ሳህሌ በቻኑ ውድድር ዙሪያ ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ አሰልጣኝ ዮሐንስ በጋዜጣዊ መግለጫው ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጧቸውን ምላሾች እንደሚከተለው በርዕስ በርዕስ ከፋፍለን አቅርበናቸዋል፡፡

‹‹በቂ ዝግጅት አላደረግንም››

አሰልጣኝ ዮሐንስ ከጥያቄዎችም በፊት እንዲሁም ከጥያቄዎች በኋላ ቡድናቸው ለውድድሩ በቂ ዝግጅት እንዳላደረገ ተናግረዋል፤ ለቡድኑ ውጤታማ አለመሆንም አንዱ ምክንያት ይህ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ‹‹ህክምና እና የአካል ብቃት ቴስትን ጨምሮ ለዝግጅት የነበሩን 10 ቀናት ብቻ ነበሩ፡፡ ያገኘነውም አንድ የወዳጅነት ጨዋታ ብቻ ነበር፡፡ የወዳጅነት ጨዋታ ማጣት ከ13 ወይም 14 ተጨዋቾች በላይ እንዳናይ አድርጎናል፡፡ ዲ.ሪ.ኮንጎዎች ርዋንዳ በመመላለስ ተዘጋጅተዋል፤ ካሜሩኖች ሁለት ሳምንት ቀደም ብለው ርዋንዳ በመግባት አየሩንም ሆነ ሌላውን ነገር ሊለምዱ ችለዋል፤ አንጎላዎችም ከርዋንዳ ጋር ሳይቀር ተጫውተዋል፡፡ እኛ በርዋንዳ ሶስት ቀናት ብቻ ነበረን፡፡ የተሻለ ዝግጅት መኖር የተሻለ ስራ እንደሚያሰራ የታወቀ ነው›› በማለት አሰልጣኙ ስለዝግጅታቸው ማነስ ካብራሩ በኋላ ወደርዋንዳ ከማምራታቸው በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ግን በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረው እንደነበር ሲጠየቁ ‹‹አዎ እንደዚያ ብዬ ይሆናል፡፡ ዝግጅታችን በቂ እንዳልነበር የተረዳነው እዚያ ደርሰን ሌሎችን ቡድኖች ስንመለከት ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ለሰበብ ብዬ የተናገርኩት አይደለም›› በማለት መልሰዋል፡፡

‹‹ከጨዋታ፣ ጨዋታ ተሻሽለናል››

ዋልያዎቹ በሰፊ ብልጫ ከተሸነፉበት የዲ.ሪ.ኮንጎ ጨዋታ በኋላ በሁለተኛው የካሜሩን ጨዋታ መሻሻላቸው በእንቅስቃሴም ሆነ በውጤት ቢታይም በሶስተኛው ጨዋታ ሽንፈቱ ተመልሷል፡፡ አሰልጣኝ ዮሐንስ ግን ውጤቱን ወደጎን ብለው ቡድናቸው ከጨዋታ ወደ ጨዋታ መሻሻሉን ተናግረዋል፡፡ ‹‹በኮንጎ ተበልጠን ተሸንፈናል፡፡ በአካል ብቃት ልንቋቋማቸው አልቻልንም፡፡ ጨዋታውን በቪዲዮ ተመልክተን ድክመቶቻችንን ልናውቅ እና ልናስተካክል ሞክረናል፡፡ ተጨማሪ ጥረት ማድረግ እንደሚገባን ተስማምተናል፡፡ ካሜሩኖች አንድም ሙከራ አላደረጉብንም፡፡ እኛ አንድ ሙከራ አድርገናል፡፡ ኳስ በመቆጣጠር ቢበልጡንም ኢላማውን በጠበቀ ሙከራ አልበለጡንም፡፡ በህብረት ስራ፣ በጥረት፣ ስህተቶችን በመቀነስ እና በራሳችን ሜዳ ኳስ ባለማበላሸት ረገዶች ተሻሽለን ነበር፡፡ እኛ ላይ ማግባት ባለመቻላቸውም እርስበእርሳቸው ሲጣሉ ነበር፡፡ በአንጎላው ጨዋታ ወደ ሜዳ የገባነው ሁለት አጥቂ ይዘን፣ በኃይሉ አሰፋ እና ራምኬል ሎክ ከመስመሮች እንዲሁም አስራት መገርሳ ከመሀል ተነስተው እንዲያጠቁ ነግረናቸው ነው፡፡ በአምስት ሰው ልናጠቃ ሞክረናል፡፡ በተለይ በሁለተኛው ግማሽ የተሻልን ነበርን፡፡ ብዙ ያጠቃንበት፣ ብዙ የማእዘን ምቶች ያገኘንበት እና ጎል ያገኘንበት ነበር፡፡ ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻላችንን ካፍ የሚልክን የጨዋታው ስታቶችም ይመሰክራሉ›› ሲሉ መሻሻላቸውን ያብራሩት ዮሐንስ አጥቂ አብዝተው በመግባታቸው ብቻ ማጥቃቱ ተሻሽሏል ብለው መናገር ይችሉ እንደሆነ ሲጠየቁ ‹‹ከኮንጎ ጋር ምንም ሙከራ አላደረግንም፤ በካሜሩን ጨዋታ አንድ ሞከርን፤ በአንጎላ ጨዋታ ደግሞ አንድ ሞክረን እሱም ጎል ሆነ፡፡ እናም ማጥቃታችን ተሻሽሏል ልንል እንችላለን፡፡ የሁሉም ተጨዋቾች የግል ብቃት መሻሻሉንም የካፍ ስታቶች አሳይተዋል›› በማለት መልሰዋል፡፡

‹‹የተሻለ ውጤት እያመጣሁ ለምን ራሴን ከኃላፊነት አነሳለሁ?!››

በምስራቅ አፍሪካ እግር ኳስ ላይ ለሚሰራ Soka25east.com  ለተሰኘ ድረ-ገፅ ራሳቸውን ከኃላፊነት ለማንሳት መዘጋጀታቸው እንደተዘገበ የተጠየቁት አሰልጣኙ፣ ርዋንዳ እያሉ ለካፍ የሚዲያ ቻናል እንዲሁም ኢትዮጵያም እያሉ ከሀገሪቱ ጋዜጠኞች ጋር ይፋዊ ፕሬስ-ኮንፈረንሶችን ብቻ እንደሰጡ በመግለፅ ይህን ነገር እንዳልተናገሩ አረጋግጠዋል፡፡ አያይዘውም ግን ራሳቸውን ከኃላፊነት ስለማንሳት ለተጠየቋቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ከነበረው ውጤት የተሻለ ማምጣት ካልቻልኩ ራሴ እንደምለቅ ተናግሬ እንደነበር አልክድም፡፡ ግን ከቀድሞው ያነሰ ውጤት እያስመዘግብኩ አይደለም፡፡ በሴካፋ የተሻለ ውጤት አምጥቻለሁ፡፡ በሴካፋ ሁለት ግቦች ነበሩኝ – ለወጣቶች እና ለተተኪዎች እድል መስጠት እና የተሻለ ውጤት ማምጣት፡፡ ሁለቱንም አሳክቻለሁ፡፡ ወጣቶቹን ተጠቅሜ ካለፈው ውድድር የተሻለ ውጤት አስመዝግቤያለሁ፡፡ ለቻን ውድድር የተስማማሁትም ለማሳለፍ ነበር፡፡ ይህንንም አድርጌዋለሁ፡፡ የምረካበት ባይሆንም ካለፈው ቻን የተሻለ ውጤትም አስመዝግቤያለሁ – አንድ ነጥብ አግኝተናል፤ ጎልም አስቆጥረናል፡፡ ታዲያ ለምን ብዬ ራሴን ከኃላፊነት አነሳለሁ?!›› ሲሉ በፈቃዳቸው እንደማይለቁ አረጋግጠዋል፡፡

‹‹እኛ ማን ነን ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል››

አሰልጣኝ ዮሐንስ ቡድናቸው እየሰራ ያለው ተግባር ክብር እንደሚሻም ተናግረዋል፡፡ ‹‹በውድድሩ ዝቅተኛ የፊፋ ደረጃ የነበረን እኛ ብንሆንም የምንችለውን ሁሉ አድርገናል፡፡ ከማንም ያነሰ አልሰራንም፡፡ 16 ውስጥ መግባትም ትልቅ ነገር ነው፡፡ እግር ኳስ ተለውጧል፡፡ የአፍሪካ አንደኛዋ አልጄሪያ እና የአፍሪካ ዋንጫ የምንግዜም ኃያሏ ግብፅ እንዲሁም የመጨረሻው ቻን የፍፃሜ ተፋላሚዎች ጋና እና ሊብያ በዚህ ውድድር መሳተፍ አልቻሉም፡፡ እነሱ በሌሉበት ውድድር እኛ መገኘት መቻላችን ትልቅ ነገር ነው፡፡ እነ ናይጄሪያ እና ሞሮኮም ከምድብ ተሰናብተዋል፡፡ በውጤታችን ባልደሰትም አላዘንኩም፡፡ በሚበልጡን ሀገራት በመሸነፋችን አላዝንም፡፡ ለስራችን ክብር መሰጠት አለበት፡፡ ኬኒያን በማሸነፋችን፣ በእነሱ ጎል ባለማስተናገዳችን መመስገን አለብን፡፡ የእግር ኳስ ደረጃችን የት ነው? ወጣቶች ላይ ተሰርቷል ወይ? የምንፈልገው እና ያለው አብሮ ይሄዳል ወይ? እኛ ማን ነን? ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ወደ ልማታዊው ነገር ብናተኩርም ጥሩ ነው›› ብለዋል፡፡

‹‹የቡድኔ ዲሲፕሊን ሬኮርድ የሚሆን ነው››

የቡድናቸው ጠንካራ ጎን ምን እንደሆነ የተጠየቁት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳያመነቱ የተጨዋቻቸውን የሜዳ ዲሲፕሊን አንስተዋል፡፡ ‹‹የቡድኑ ትልቁ ጥንካሬ ዲሲፕሊን ነው፡፡ ከ20 በላይ ጨዋታዎች አድርገን የተመለከትነው አንድ ቀይ ካርድ ብቻ ነው፡፡ ይህ በሀገራችን ሬኮርድ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በተጨማሪም ወጣቶቹ ተጨዋቾቼ በተደራራቢ ጨዋታ አለመፍረክረካቸው፣ የማሸነፍ ፍላጎት እና ተስፋ አለመቁረጥም ጥንካሬዎቻችን ናቸው›› ሲሉ ገልፀዋል፡፡

‹‹107.000 ህዝብ ሜዳ ገብቶ ደግፎኛል››

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሲጫወት በስታዲየም የሚገኘው ህዝብ እየቀነሰ መሆኑ እና በየቤቱ፣ በየመንገዱ እና በማህበራዊ ድረ-ገፆች የሚሰጡ አስተያየቶች አዎንታዊ እንዳልሆኑ ተጠቅሶ እሳቸው ስለ ህዝቡ ስሜት ምን ይሉ እንደሆኑ የተጠየቁት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሲመልሱ ‹‹ስለ ህዝቡ ስሜት አላውቅም፡፡ የእኔ ስራ ኳስ ሜዳ ላይ ነው እንጂ የህዝብን ሀሳብ ለማወቅ መጣር አይደለም፡፡ ነገር ግን በባህር ዳር ስታዲየም 107.000 ህዝብ ስታዲየም ገብቶ እንደደገፈን አውቃለሁ፡፡ ይህ ቁጥር በአፍሪካ ሬኮርድ ይመስለኛል፡፡ በሀዋሳም 60.000 ህዝብ ስታዲየም ታድሟል›› በማለት የህዝብ ድጋፍ አብሯቸው እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

(ከላይ የሰፈሩት የአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ምላሾች ለፅሁፉ አመቺነት ሲባል ቃል በቃል የተወሰዱ አይደሉም)

1 thought on “‹‹የተሻለ ውጤት እያመጣሁ ለምን ራሴን ከኃላፊነት አነሳለሁ?!››

  1. He is a good coach. Please give him the time he needs. It is the Federation that’s the problem, not the Coach. To repeat what Sewnet achieved by qualifying the Walyas for the CHAN Tournament for the 2nd time in a row should be celebrated. Yes, the results at the Tournament may have been disappointing but getting to the Tournament to begin with is a big accomplishment.

Leave a Reply

Your email address will not be published.