የሴካፋ ቻሌንጅ ዋንጫ ዛሬ ይጀመራል

CECAFA 2015

CECAFA 2015

  • ኡጋንዳ የውድድሩ ምንጊዜም ኃያል ናት
  • ውድድሩ በሶስት ከተሞች ይካሄዳል
  • በሱፐር ስፖርት ይተላለፋል
  • ኤርትራ አትሳተፍም
  • የሁለቱ ሱዳኖች ፍልሚያ ይጠበቃል

የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሀገራት ዓመታዊ የእግር ኳስ ውድድር (ሴካፋ ቻሌንጅ ካፕ) የፊታችን ቅዳሜ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጀመራል፡፡ ቀጣዩ ፅሁፍ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት የሚካሄደውን ውድድር ለመዳሰስ ይሞክራል፡፡

ታሪክ

የሴካፋ ዋንጫ በአፍሪካ በእድሜ አንጋፋው የእግር ኳስ ውድድር ሲሆን በፈረንጆች አቆጣጠር በ1926 በኬኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ዛንዚባር እና ታንጋኒካ መካከል ጎዛጅ ዋንጫ በሚል ስያሜ የተጀመረ ነበር፡፡ ከዚያም ከ1965-1971  ድረስ የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ በሚል ስያሜ ከተካሄደ በኋላ በ1973 ሴካፋ ሲመሰረት ሴካፋ ዋንጫ መባል ጀምሯል፡፡ የክፍለ-አህጉሩ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ከተመሰረተ እና ውድድሩም በማህበሩ ከተሰየመ በኋላ ከተደረጉት ውድድሮች መካከል ኡጋንዳ 13ቱን በሻምፒዮንነት በማጠናቀቅ የውድድሩ ንጉስ ሲሆኑ ኬኒያ ስድስት ጊዜ እንዲሁም ኢትዮጵያ አራት ጊዜ ውድድሩን በማሸነፍ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡

2015 ሴካፋ

የሴካፋ ውድድር በየዓመቱ የሚካሄድ ቢሆንም አምና በ2014 ልታዘጋጅ ቃል ገብታ የነበረችው ኢትዮጵያ ዘግይታ ማዘጋጀት እንደማትችል በመግለፅዋ ውድድሩ ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡ የ2015ቱን ውድድር እንድታዘጋጅ ተመርጣ የነበረችው ርዋንዳ ብትሆንም የ2016ቱን የቻን ውድድር የማዘጋጀት ጫና ስላለባት ለኢትዮጵያ የማዘጋጀቱ እድል ተሰጥቷል፡፡ ኢትዮጵያም ዝግጅቷን ሁሉ አጠናቃ በሶስት ከተሞች (አዲስ አበባ፣ ሀዋሳ እና ባህርዳር) ውድድሩን ልታካሂድ እየተጠባበቀች ትገኛለች፡፡ በውድድሩ ላይ አዘጋጇ ኢትዮጵያን እና ተጋባዧ ማላዊን ጨምሮ 12 ሀገራት ይሳተፋሉ (ዛንዚባር የታንዛኒያ አካል ብትሆንም በሴካፋ ላይ ራሷን ወክላ ትጫወታለች)፡፡ በሌሎች የሴካፋ ውድድሮች ላይ የምትሳተፈው ጎረቤት ኤርትራ ከአዘጋጇ ኢትዮጵያ ጋር ባላት የፖለቲካ ውጥረት ምክንያት ለመሳተፍ ፍቃደኛ አልሆነችም፡፡ ውድድሩ በደቡብ አፍሪካው ግዙፍ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሱፐር ስፖርት የቀጥታ ስርጭት ሽፋን እንደሚሰጠውም ይጠበቃል፡፡

 

  • ምድብ 1፡- ኢትዮጵያ፣ ርዋንዳ፣ ታንዛኒያ እና ሶማሊያ

 

አዘጋጇ ኢትዮጵያ በመጀመሪያው ምድብ ከርዋንዳ፣ ታንዛያ እና ሶማሊያ ጋር ተደልድላለች፡፡ የአራት ጊዜ የውድድሩ ሻምፒዮን (ሁለቴ በሀገሯ ምድር እና ሁለቴ በርዋንዳ) በኮንጎ ብራዛቪል ተረትታ ከዓለም ዋንጫው ማጣሪያ ከተሰናበተችበት አሳዛኝ ክስተት አገግማ በውድድሩ ጥሩ ጉዞ እንደምታደርግ ይጠበቃል፡፡ የቡድኑ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በውጪ ሀገር ከሚጫወቱ ተጨዋቾቻቸው በቀር የተቀሩትን ሁሉ ይዘው ይህን ውድድር ያደርጋሉ፡፡ ርዋንዳዊያኑ ከሳምንታት በኋላ በሀገራቸው ለሚያዘጋጁት የቻን ውድድር ሴካፋውን ለመዘጋጃነት እንደሚጠቀሙበት ሲገልፁ ሰንብተዋል፡፡ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው በአልጄሪያ  እጅ አሰቃቂ የ7ለ0 ሽንፈት ያስተናገዱት ታንዛኒያዊያኑ በበኩላቸው ይህን ሽንፈት ለመርሳት ቢያንስ ከምድባቸው ማለፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የዓለም ዋንጫ ቅድመ-ማጣሪያቸውን በመረጧት አዲስ አበባ ባደረጉበት ወቅት ከፍተኛ ድጋፍ ያገኙት ሶማሊያዊያኑም ዝቅተኛ ግምት ሊሰጣቸው አይገባም፡፡

 

  • ምድብ 2፡- ኬኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ቡሩንዲ እና ዛንዚባር

 

ይህ ምድብ የምስራቅ አፍሪካ ኃያላኑን ኡጋንዳ እና ኬኒያን ያገናኛል፡፡ ሁለቱ ሀገራት ድንበርተኛ ከመሆናቸው ባሻገር በውድድሩ ታሪክ ብዙ ዋንጫ ያገኙ መሆናቸው በእግር ኳሱ ሜዳ የላቀ ተፎካካሪ አድርጓቸዋል፡፡ ኡጋንዳ በርቀት የውድድሩ ኃያል ስትሆን ኬኒያ በበኩሏ የውድድሩ ባለ-ክብር (የመጨረሻው ውድድር ባለድል) ናት፡፡ የፊታችን እሁድ ሁለቱ የሚገናኙበት የአዲስ አበባ ስታዲየሙ ፍልሚያም በጉጉት ይጠበቃል፡፡ በሴራዲዬቪች ሚሉቲን ‹ሚቾ› የሚሰለጥኑት እና ቶጎን ከረቱ በኋላ በዓለም ዋንጫው የምድብ ማጣሪያ የገቡ ብቸኛ የዞኑ ሀገር የሆኑት ኡጋንዳዊያኑ ለውድድሩ ባለድልነት ከአዘጋጇ ኢትዮጵያ ጋር ቀዳሚ ተገማች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በቻን ማጣሪያ በአዲስ አበባ ስታዲየም በኢትዮጵያ አቻቸው የተደቆሱት ቡሩንዲያዊያኑ እና የአንድ ጊዜ የውድድሩ አሸናፊዎች ዛንዚባርም በምድባቸው ጥሩ ተፎካካሪ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

 

  • ምድብ 3፡- ሱዳን፣ ማላዊ፣ ደቡብ ሱዳን እና ጂቡቲ

 

ይህ ምድብ በአንፃራዊነት ቀለል ያለ ምድብ ተደርጎ ሊወስድ ይችላል፡፡ ነገር ግን የሁለቱ ሱዳኖች ፍልሚያ እጅግ በጉጉት ይጠበቃል፡፡ ደቡብ ሱዳን በቅርቡ የተመሰረተች፣ የዓለማችን አዲሷ ሀገር መሆኗ እና በእርስ በርስ ጦርነት ላይ መገኘቷ ለቀድሞ እናቷ ሱዳን በቀላሉ ጨዋታውን የማሸነፍን ግምት እንድንሰጥ ሊያደርገን ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ደቡብ ሱዳናዊያኑ በብሔራዊ ቡድንም ሆነ በክለብ ደረጃ እያሳዩ ያሉት አስደናቂ መሻሻል ይህን እንዳናደርግ ሊያግደን ይችላል፡፡ የማላዊ ብሔራዊ ቡድንም ከዓመት በፊት በሜዳው ኢትዮጵያን የረታ እና በአዲስ አበባ ስታዲየም ያለጎል አቻ ተለያይቶ የተመለሰ ጥሩ ቡድን መሆኑም መረሳት የለበትም፡፡ ስለጂቡቲ ግን ምንም ለማለት ያስቸግራል፡፡

የተሳታፊ ሀገራት የኖቬምበር ወር የፊፋ ደረጃ

ቡሩንዲ 107፣ ጂቡቲ 207፣ ኢትዮጵያ 114፣ ኬኒያ 125፣ ማላዊ 97፣ ርዋንዳ 96

ሶማሊያ 203፣ ደቡብ ሱዳን 134፣ ሱዳን 128፣ ታንዛኒያ 135፣ ኡጋንዳ 68

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.