የሴካፋ ቻሌንጅ ዋንጫ በኢትዮጵያ ይካሄዳል

CECAFA 2015

  • ‹‹ይህን ውድድር ለማዘጋጀት ከኢትዮጵያ የተሻለ ተመራጭ ስፍራ የለም››
  • ለጊዜው የስያሜ ስፖንሰር የለውም
  • በሱፐር ስፖርት ይተላለፋል
  • እንደሚሳተፉ ያረጋገጡት አምስት ሀገራት ብቻ ናቸው
  • የኤርትራ ጉዳይ አልታወቀም
  • ‹‹አሰልጣኝ ዮሐንስ ስለ ሴካፋ አላውቅም ያለው ስህተት ነው››

ኢትዮጵያ በቀጣዩ ወር የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሀገራት ዓመታዊ የእግር ኳስ ውድድርን (ሴካፋ ቻሌንጅ ካፕ) እንደምታዘጋጅ ጭምጭምታዎች የነበሩ ሲሆን ትናንት ረቡዕ ምሽት በኢሊሊ ሆቴል በተሰጠ የጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነገሩ እውነት መሆኑን የሴካፋ ባለስልጣናት እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊዎች አረጋግጠዋል፡፡ የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን (ሴካፋ) ሊቀመንበር ሌዎዴጋር ቴንጋ እና ዋና ፀሀፊ ኒኮላስ ሙሶኒዬ፣ የውድድሩን ጨዋታዎች በቴሌቪዥን የማስተላለፍ መብቱን የገዛው ሱፐር ስፖርት ተወካዮች እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም የሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች በተገኙበት ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የዘንድሮው ውድድር ከኖቬምበር 21 እስከ ዲሴምበር 6፣ 2015 (በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከህዳር 11 እስከ ህዳር 26፣ 2008) ገና ባልተወሰኑ የኢትዮጵያ ከተሞች ስታዲየሞች እንደሚካሄድ ተገልፅዋል፡፡ የሴካፋ ሊቀመንበር ሌዎዴጋር ቴንጋ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ለተደረገላቸው መልካም አቀባበል እና ከምንም በላይ ኢትዮጵያ ውድድሩን ለማዘጋጀት ፈቀደኛ በመሆኗ ምስጋናቸውን ለኢትዮጵያ ህዝብ፣ ለኢትዮጵያ መንግስት እና ለእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ አድርሰዋል፤ እንደ ሴካፋ አይነት ትልቅ ውድድር ለማዘጋጀት መወሰን ትልቅ ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅም አስታውሰዋል፡፡ የትኞቹም የአፍሪካ ቀጠናዎች ማድረግ ያልቻሉትን በየዓመቱ የክፍለ-አህጉር ውድድር የማዘጋጀትን ተግባር ሴካፋ ያለ ችግር እያደረገው በመሆኑም ደስታ እና ኩራት እንደሚሰማቸው ሊቀመንበሩ ገልፀዋል፡፡ እንደ ቴንጋ እምነት በዚህ ሰዓት ይህን ውድድር ለማዘጋጀት ከአፍሪካ ህብረት መቀመጫዋ ሀገር የተሻለ ተመራጭ ስፍራ የለም፡፡ ዋና ፀሀፊው በተደጋጋሚ ግዜ ከዚህ ቀደም ለመጨረሻ ጊዜ ኢትዮጵያ ያዘጋጀችውን የሴካፋ ውድድር እንዴት በብቃት እንደተወጣች እና ውድድሩ ያማረ እንደነበር እንደነገሯቸው ያስታወሱት ሊቀመንበሩ በቅርብ ዓመታት ሀገሪቱ በእግር ኳሱ መድረክ እያሳየችው ያለው መሻሻል፣ የሴት ብሔራዊ ቡድኑ ስኬት እና የአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ብሔራዊ ቡድን ጥሩ አቋሞች ኢትዮጵያን ውድድሩን ለማዘጋጀት በምርጡ ጊዜ ላይ የምትገኝ ምርጡ ሀገር እንደሚያደርጋት ተናግረዋል፡፡ ታንዛኒያዊው ሊቀመንበር ውድድሩ 12 ቡድኖችን እንደሚያሳትፍ እና ከኖቬምበር 21 እስከ ዲሴምበር 6 ድረስ እንደሚካሄድ ተስፋቸውን ከገለፁ በኋላ ጋዜጠኞች ውድድሩን በማስተዋወቅ ለክፍለ-አህጉሩ ውለታ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ችሎታ ያላቸው ወጣቶች በውድድሩ ላይ እንዲታዩ፣ የቀጠናው እግር ኳስ በዓለም እይታ ውስጥ እንዲገባ ውድድሩ አስፈላጊ እንደሆነ እና ለዚህም የጋዜጠኞች ሰፊ ሽፋን መስጠት፣ ቡድኖች እና ተጨዋቾች በደንብ እንዲዘጋጁ ማነሳሳት እንዲሁም ደጋፊዎች ወደ ስታዲየም እንዲጎርፉ ማድረግ እጅግ ወሳኝ እንደሆነ በመግለፅ የሚዲያ ሰዎችን አሳስበዋል፡፡ ሌሎች ተጨማሪ ውይይቶች እንደሚደረጉ እና ዝርዝር ጉዳዮች በቀጣይ ጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ እንደሚገለፁ እንዲሁም ከውድድሩ አንድ ቀን በፊት የሴካፋ ጠቅላላ ጉባኤ በአዲስ አበባ እንደሚደረግም አስታውሰው የዘንድሮውን ውድድር በይፋ አውጀዋል፡፡

የሴካፋው ሊቀመንበር ከዚህ በኋላ መድረኩን ለጥያቄዎች ክፍት ያደረጉ ሲሆን ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሾችን ሰጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ጁነይዲ ባሻም እሳቸውን የሚመለከቱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ሞክረዋል፡፡ ውድድሩ በመጀመሪያ ርዋንዳ እንድታዘጋጀው ከተወሰነ በኋላ ነበር በኋላ ላይ ለኢትዮጵያ የተሰጠው፡፡ እናም ለምን ወደ ኢትዮጵያ ሊመጣ እንደቻለ የተጠየቁት ሊቀመንበሩ ርዋንዳ ላለማዘጋጀት ወደኋላ ብላ ወይም የአቅም እጥረት አጋጥሟት ሳይሆን በጃንዋሪ ወር ከምታዘጋጀው በሀገር ውስጥ ሊጎች በሚጫወቱ ተጨዋቾች ከሚደረገው የቻን ውድድር ጋር በጣም ተቀራርቧል ብሎ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ስለገለፀላቸው እንደሆነ አብራርተዋል፤ አያይዘውም የርዋንዳ ጉዳይ ሳይሆን ከቀረ በኋላ ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቻቸው እንዲህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማዘጋጀት ፈቃደኛ በመሆናቸው ደግመው አመስግነዋል፡፡ የዛሬ አስር ዓመት ገደማ ውድድሩ በኢትዮጵያ ውስጥ በከፍተኛ ድምቀት ሲካሄድ ሼኽ መሀመድ አልአሙዲን የውድድሩ የስያሜ ስፖንሰር እንደነበሩ ይታወሳል፤ የርዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜም በተለያዩ ዓመታት ውድድሩን በስማቸው ስፖንሰር አድርገዋል፡፡ የዘንድሮውስ ውድድር የስያሜ ስፖንሰር የለውም ወይ ተብለው የተጠየቁት ሊቀመንበሩ እስካሁን የስያሜ ስፖንሰር የሚሆን ድርጅት ወይም ግለሰብ እንዳላገኙ ነገር ግን ውድድሩ በትልቁ ሱፐር ስፖርት ጣቢያ የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ስለሚያገኝ በቀሩት ሳምንታት ጥሩ ዋጋ ያለው የስያሜ ስፖንሰር እንደሚያገኙ ተስፋቸውን ገልፀዋል፡፡ በዚህ ወቅት ከኢትዮጵያ ጋር ጥሩ ወዳጅነት የሌላት እና በተለያዩ ውድድሮች ላይ ስፖርተኞቿ ጥገኝነት እየጠየቁ ሳይመለሱ የሚቀሩባት ኤርትራ በኢትዮጵያ በሚዘጋጀው ውድድር ላይ ትሳተፍ ይሆን ወይ የሚለው ለማወቅ የሚያጓጓ ጉዳይ ነው፡፡ ሊቀመንበሩ የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን ይሳተፋል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ እና እንደሚጠብቁ ነገር ግን እስከአሁን አምስት ሀገራት ብቻ በውድድሩ ላይ እንደሚኖሩ ማረጋገጫ እንደሰጧቸው ገልፀዋል፡፡ ግን ብዙ ጊዜ ሀገራት ማረጋገጫ የሚሰጧቸው ዘግይተው ውድድሩ ሲቃረብ በመሆኑ ይህ ጉዳይ በጭራሽ እንደማያሳስባቸውም አረጋግጠዋል፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ ክልሎች ትልልቅ ስታዲየሞችን እየገነባች እንደመሆኗ እና ጥቂቶቹም በከፊል ተጠናቀው ለውድድሮች ዝግጁ እንደመሆናቸው ውድድሩ በእነዚህ ስፍራዎች የመካሄድ እድል ያገኛል ወይስ በአዲስ አበባ ብቻ ይካሄዳል ለሚለው ጥያቄ የሴካፋው ሊቀመንበር ይህ ጉዳይ ገና እንዳልተወሰነ እና ከውይይቶች በኋላ ደጋፊዎችን በመሳብ፣ ለቴሌቪዥን ስርጭት በሚኖረው ተስማሚነት እና ሌሎች ነገሮችን መሰረት አድርጎ እንደሚወሰን ገልፀዋል፡፡

በዚህ ውድድር ዙሪያ ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል ብዙ አነጋጋሪ የነበረው ውድድሩ ሊካሄድ የታቀደበት ጊዜ ጉዳይ ነው፡፡ ከውድድሩ መክፈቻ ጥቂት ቀናት በፊት (በኖቬምበር 9 እና 17) የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የደርሶ መልስ ፍልሚያ የሚደረግ ሲሆን አብዛኞቹ የቀጠናው ሀገራት ይሳተፉበታል፡፡ ከውድድሩ መጠናቀቅ አንድ ወር በኋላ ደግሞ የቻን ውድድር ሲካሄድ አዘጋጇ ርዋንዳን ጨምሮ ሶስት የቀጠናው ቡድኖች ይወዳደራሉ፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ፣ አህጉራዊ የክለብ ውድድሮች እና የውስጥ ሊግ  ውድድሮችም አሉ፡፡ የጨዋታዎች መብዛት ተጨዋቾችን ከማዳከሙም በላይ የሊግ ውድድሮች በስርዓት አለመካሄድ እና መቆራረጥ ተጨዋቾቹ አቋማቸውን ጠብቀው እንዳይጓዙ እንዳያደርጋቸው ያሰጋል፡፡ የሴካፋው ሊቀመንበር ግን ጉዳዩን የሚመለከቱት በተቃራኒው ነው፡፡ እንደ ቴንጋ አስተሳሰብ ውድድሩ ከቻን አንድ ወር በፊት መደረጉ እንዲያውም የቀጠናው ተሳታፊ ሀገራት በጥሩ ሁኔታ እንዲዘጋጁ ይረዳቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ጁነይዲ ባሻ በበኩላቸው ስጋቱን እንደሚረዱት ገልፀው ነገር ግን ውድድሩን ለማካሄድ ከዚህ የተሻለ ጊዜ እንዳላገኙ አስረድተዋል፤ እንዲያውም ስጋቱን ለመቀነስ ፕሪምየር ሊጉን ቀደም ብለው መስከረም መጀመሪያ ላይ ለመጀመር አስበው የነበረ ቢሆንም ከክለቦች በመጣ ጥያቄ ወደ ጥቅምት አጋማሽ ሊወስዱት ተገደዋል፤ ውድድሩን በማዘጋጀት ዙሪያም የክለቦችን ይሁንታ እንዳገኙም አክለዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ጉዳይ የክለቦች ጉዳይ ብቻም አይደለም፡፡ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝም የተጨማሪ ውድድር መኖር በዝግጅት እቅዱ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድርበት ይችላል፡፡ እንዲያውም ዋልያዎቹ ሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔን ከረቱበት የእሁድ እለቱ ጨዋታቸው በኋላ አሰልጣኙ ዮሐንስ ሳህሌ ስለ ሴካፋ ጉዳይ ምንም እንደማያውቁ ተናግረው ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ ጁነይዲ እንዳሉት አሰልጣኙ አላውቅም ያሉት ጊዜውን እንጂ በሴካፋ መወዳደራቸውን በኮንትራታቸውም ላይ ሳይቀር የሰፈረ ነገር ነው፤ ፕሮግራም ሲወጣም በዝግጅታቸው ላይ ተፅዕኖ እንዳይፈጥር እንዲያዩት እና ሀሳብ እንዲሰጡ ተደርገው ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም ከዚህ ቀደም ብሔራዊ ቡድኑ ለአርባ ምናምን ቀናት በባህር ዳር እንዲዘጋጅ የተደረገው አሰልጣኙ ሁሉንም ውድድሮች ሴካፋንም ጨምሮ ከግምት አስገብተው ሰፊ ቡድን እንዲገነቡ ከነበረ ፍላጎት እንደሆነ ገልፀው ዮሐንስም ሆኑ የቀድሞ የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኞች ቡድኑን ከዜሮ እንደሚገነቡት የሚሰጧቸው አስተያየቶች ተገቢ እንዳልሆኑ እንደ ጎን ማስታወሻ ተናግረዋል፡፡ ሌላው ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ውድድሩን የማዘጋጁትን ወጪ የሚሸፍነው አካል ጉዳይ ነው፡፡ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ጁነይዲ መንግስት እንዲያግዛቸው ጥያቄ እንዳቀረቡ እና ከመንግስት ጋር ውይይት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረው ከቀድሞው በተለየ ግን ተሳታፊ ሀገራት የራሳቸውን የትራንስፖርት ወጪዎች እንዲሸፍኑ ስምምነት ላይ መደረሱን ይህም ብዙ ወጪ እንደሚቀንስላቸው ግልፅ አድርገዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.