“የማይቻለው” ተልዕኮ አልተሳካም

FBL-AFR-2015-ALG-ETH

“የማይቻለው” ተልዕኮ አልተሳካም

ትናንት ወደ ማምሻው ገደማ ማላዊ ማሊን በሜዳዋ አስተናግዳ 2ለ0 ማሸነፏ ሲታወቅ ለብሔራዊ ቡድናችን የተሻሉ እድሎች እንደተፈጠሩ ታስቦ የምሽቱ የአልጄሪያና የዋሊያዎቹ ጨዋታ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ በከፍተኛ ተስፋ ተጠብቆ ነበር፡፡ ጨዋታው በብሔራዊ ቴሌቪዥናችን በቀጥታ ባለመተላለፉ ምክንያት በርካቶች ወደእግር ኳስ መመልከቻ ቤቶች በማምራት፣ ጥቂቶች በቤቶቻቸው በተለያዩ የውጪ ሀገራት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንዲሁም ሁለቱንም ማድረግ ያልቻሉት ደግም በቀጥታ የሬዲዮ ስርጭቶች በመታገዝ ጨዋታውን ተከታትለዋል፡፡ በእኛ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 4ከ30 ላይ ከአልጄርስ ደቡብ ምዕራብ በ45 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በምትገኘው ብሊዳ ከተማ በሙስተፋ ታከር ስታዲየም የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ ሲጀምር የቡድኖቹ አሰላለፍ የሚከተለው ነበር፡-

አልጄሪያ

ግብ ጠባቂ፡- ሞሀመድ ዜማሙሽ

ተከላካዮች፡- ፋውዚ ጎላም ፣ ራፊክ ሀሊሽ ፣ ካርል ሜጃኒ ፣ ጃሜል ሜስባህ እና ሜህዲ ዜፋኔ

አማካዮች፡- ሜህዲ ላሰን ፣ ሳፊር ታይደር፣ ያሲን ብራሂሚ፣ ሪያድ ማህረዝ እና ሶፊያኔ ፌጉሊ

አጥቂዎች፡- ኢስላም ስሊማኒ

ተጠባባቂዎች፡- ሬይስ ምቦልሂ፣ ማጂድ ቡጌራ ፣ ሊያሲን ካዳሙሮ፣ ጃሜል ሜስባህ፣ አብድልሞሜን ጃቡ፣ ባግዳድ ቡኔጃ እና ሂላል ሱዳኒ

ኢትዮጵያ

ግብ ጠባቂ፡- ጀማል ጣሰው

ተከላካዮች፡- አንዳርጋቸው ይላቅ፣ ዋሊድ አታ፣ ሳላሃዲን ባርጊቾ፣ አበባው ቡታቆ

አማካዮች፡- ናትናኤል ዘለቀ፣ ታደለ መንገሻ፣ ዩሱፍ ሳላህ

አጥቂዎች፡- ሽመልስ በቀለ፣ ዳዋ ሆቴሳ፣ ኦመድ ዑክሪ

ተጠባባቂዎች:- ታሪክ ጌትነት፣ ግርማ በቀለ፣ አብዱልከሪም መሀመድ፣ ብርሀኑ ቦጋለ፣ ፋሲካ አስፋው፣ ዳዊት ፍቃዱ እና ራምኬል ሎክ

ከተጠባባቂ ውጪ፡- ቢያድግልኝ ኤልያስ እና ጋቶች ፓኖም

ጨዋታውን በዋና ዳኝነት የመሩት አርቢትር አሊ ሌምጌፍሪ እንዲሁም ረዳቶቻቸው አብድርሀማኔ ዋር እና አብዱላዚዝ ሳል እና አራተኛው ዳኛ ሙሀመድ ሀማዳ ሁሉም ከሞሪታኒያ ሲሆኑ የጨዋታው ኮሚሽነር ሙሀመድ ሪየድ ቤን ኑር ከቱኒዚያ ነበሩ፡፡

ባለሜዳዎቹ አልጄሪያዎች ጨዋታውን ያደረጉት ጥቂት አረንጓዴ የነካካው ሙሉ ነጭ ትጥቅ ለብሰው ሲሆን ዋሊያዎች በሙሉ ቢጫ ትጥቅ ጨዋታውን ጀምረዋል፡፡ ወደ ጨዋታው ስንገባ አርቢትሩ የጨዋታውን ማስጀመሪያ ፊሽካ ካሰሙ አንስቶ የባለሜዳዎቹ አልጄሪያዊያን ወረራ እጅግ አስደናቂ ነበር፡፡ በተለይም በግራ እና በቀኝ ክንፎች በሶፊያኔ ፌጉሊ፣ ያሲኔ ብራሂሚ እና ሪያድ ማህረዝ አማካይነት የሚፈጥሯቸው ችግሮች ለመስመር ተከላካዮቻችን አበባው እና አንዳርጋቸው ከአቅማቸው በላይ ነበር፡፡ እናም በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ብቻ ለመቁጠር የሚያዳግቱ ንፁህ የጎል እድሎችን ፈጥረው በመሀል ተከላካዮቻችን እና በግብ ጠባቂው ጀማል ጥረቶች እንዲሁም በአልጄሪያዊያኑ የአጨራረስ ችግሮች ምንም ጎል ሳይቆጠርብን ቀርቷል፡፡ በእዚህ ወቅት ከእኛ ቡድን፣ በብዛት በራስ ሜዳ ተከማችቶ ያልሞት ባይ ተጋዳይነት መከላከል ከማድረግ በስተቀር ይህ ነው የሚባል መደራጀት፣ የኳስ ቅብብል አልያም አላማ ያለው የጎል ሙከራ አልነበረም፡፡ ተጨዋቾቻችን የተጋጣሚያቸውን ተጨዋቾች ጥቃት መቋቋም ከመቸገራቸው ባሻገር ኳስ በሚይዙባቸው እጅግ ጥቂት አጋጣሚዎች የአልጄሪያዊያኑን ፕሬሲንግ መቋቋም እየተሳናቸው ወዲያውኑ ኳሱን እያስረከቡ ለሌላ ጥቃት በር ይከፍቱ ነበር፡፡ ከዚያም ግን በ20ኛው ደቂቃ ገደማ በድንገት የአልጄሪያ ተጨዋቾች በራሳቸው ሜዳ ሲቀባበሉ ያበላሹትን ኳስ በመጀመሪያው አጋማሽ በሀሰተኛ ዘጠኝ ቁጥር ሚና የተጫወተው ሽመልስ በቀለ አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀረ፡፡ ሌላው የቡድናችን አጥቂ ኦመድም ተመሳሳይ እድል ለማግኘት አፍታም አልፈጀበትም፡፡ ብራሂሚ መሀል ሜዳ አካባቢ ያበላሸውን ኳስ ግን ኦመድ እንደ ሽመልስ አላመከነውም፡፡ በግራ መስመር አጥቂነት የተሰለፈው ኦመድ ኳሱን በፍጥነት ወደ ቀኝ እየገፋ ከሄደ በኋላ ለራሱ ቦታ ፈጥሮ በቀኝ እግሩ አክርሮ መሬት ለመሬት የመታው ኳስ ግብ ጠባቂው ዜማሙሽን አልፎ ጎል ሆነ፡፡ የኦመድ ኳሱን ተቆጣጥሮ ወደ ፊት የሄደበት እና ኳሱን ወደ ጎል የመታበት መንገድ አስደናቂ የነበረ ሲሆን ጎሉን ያስቆጠረው በደካማ ቀኝ እግሩ መሆኑ ደግሞ ጥረቱን የበለጠ ድንቅ አድርጎታል፡፡ በዚህ ጊዜ በአልጄሪያዊያኑ ተጨዋቾች ፊት ላይ ይታይ የነበረው መመራታቸውን ለማመን የመቸገር አይነት ስሜት ነበር፡፡ በእርግጥም ከነበራቸው የበላይነት አንፃር ይህን ስሜት ማንበብ የሚያስገርም አልነበረም፡፡ ከዚያም እንደገና የአልጄሪያ የበላይነት ቀጥሎ በክንፎቻችን ችግሮችን መፍጠራቸውን ቀጠሉ፡፡ ግን ከጥቃቶቻቸው ጎል ለማግኘት አልቻሉም፡፡ ከዚያ በ32ኛው ደቂቃ ተጨዋቾቻችን ተረጋግተው እያለ ዋሊድ አታ ወደ ፊት ሄዶ ለአማካዮቻችን ለማቀበል ሲሞክር የተበላሸበት ኳስ በአልጄሪያዊያኑ ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ጎላችን ደርሶ ማህረዝ ለፌጉሊ ያቀበለውን የቫሌንሲያው ኮከብ በቀላሉ አግብቶት ቡድኑን አቻ አደረገ፡፡ ከስጋት ከተረፍንባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አንፃር ይህ ሊፈጠር የማይገባው፣ እኛም ልንከላከለው የምንችል አጋጣሚ ነበር፡፡ ከስምንት ደቂቆዎች በኋላም ክስተቱ ተደገመ፡፡ ከተጨዋቾቻችን ስህተት የተገኘውን ኳስ አጥቂው ስሊማኒ ወደ ጎል ሞከረው ተብሎ ሲጠበቅ ወደ ኋላ መልሶ ሴንተር አድርጎት ከመሀል የመጣው ማህረዝ በቀጥታ በመምታት ሌላ ጎል አስቆጠረ፡፡ በእዚህ ጎል ላይ በጊዜው በፍጥነት በቦታቸው ካልተገኙት ተከላካዮቻችን በተጨማሪ የጀማል ጥረትም ጥያቄ የሚነሳበት ነው፡፡ በዚሁ ውጤት የመጀመሪያው ግማሽ ተጠናቀቀ ተብሎ የአርቢትሩ ፊሽካ ሲጠበቅ ከ15 ባነሱ ደቂቃዎች ውስጥ ለሶስተኛ ጊዜ ተከላካዮቻችን ራስን እንደማጥፋት የሚቆጠር ስህተት ሰሩ፡፡ የእለቱ የቀኝ ተከላካይ አንዳርጋቸው ኳሱን ሲገፋ ተቀምቶ ባለሜዳዎቹ በተመሳሳይ ፈጣን ሽግግር ጎላችን ደርሰው የወቅቱ የአፍሪካ እንቁ ብራሂሚ በአስደናቂ አጨራረስ ለቡድኑ ሶስተኛውን ጎል አስቆጠረ፡፡ 15 ደቂቆዎች፤ ሶስት ግዙፍ ስህተቶች፤ ሶስት አስደናቂ የማጥቃት ሽግግሮች፤ ሶስት ጎሎች! ይህ ከ30ኛ ደቂቃ በኋላ የታየው የጨዋታው ክስተት ነበር፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ ትንሽ የተለየ ነበር፡፡ አልጄሪያዊያኑ በበለጠ ዘና በማለት እና ጉልበታቸውን በመቆጠብ ፍላጎት ሲመለሱ ወጣቱን አጥቂ ራምኬል ሎክ በሌላው ወጣት አጥቂ ዳዋ ሆቴሳ ምትክ ያስገቡት ዋልያዎቹ በተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ሜዳ ገቡ፡፡ የማሪያኖ ባሬቶ ልጆች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ውስጥም በሽመልስ እና ኦመድ አማካይነት የጎል እድሎችን አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀሩ፡፡ ሽመልስ ከራምኬል ያገኘውን ጥሩ ኳስ በማይጠበቅ መንገድ ሲያመክን ኦመድ በግራ መስመር ያገኘውን ኳስ በተሻለ ስፍራ ለነበሩት ሽመልስ ወይም ራምኬል ማቀበል ሲገባው ራሱ መቶ አበላሸው፡፡ ቆይቶም ሌላው አጥቂ ዳዊት ፍቃዱ አማካዩ ዩሱፍ ሳሌህን ተክቶ የገባ ሲሆን በዚህ ጊዜ ሽመልስ ወደ መሀል ተመልሷል፡፡ ዳዊት መጥፎ የሚባል እንቅስቃሴ ያላደረገ ቢሆንም ሁለት ጊዜ (አንዴ ከታደለ እና በጨዋታው መጨረሻ ላይ ከሽመልስ) ያገኛቸውን ኳሶች መጠቀም ሳይችል ቀርቷል፡፡ በዚህ ግማሽ አልጄሪያዊያኑ እንደመጀመሪያው ግማሽ በከፍተኛ ፍጥነት፣ ጫና እና ፍላጎት ያልተጫወቱ ቢሆንም ወደጎልነት ያልቀየሯቸውን እድሎች ፈጥረዋል፤ እነብራሂሚ እና ፌጉሊ ድንቅ የግል ክህሎታቸውን አሳይተዋል፤ ማራኪ የህብረት እንቅስቃሴም አድርገዋል፡፡ ነገር ግን ሁለቱም ቡድኖች ሌላ ጎል ሳይጨምሩ በ3ለ1 ውጤት ጨዋታው ተጠናቋል፡፡

የቡድናችን ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች                          

ከእንደዚህ አይነት ፍፁም የበላይነት ከተወሰደብን ጨዋታ ጠንካራ ጎኖችን ማውጣት ከባድ ቢሆንም ምንም አልነበረንም ማለት ግን ስህተት ነው፡፡ በመጀመሪያው ግማሽ የመሀል ተከላካዮቻችን ዋሊድ እና ሳልሀዲን ግብ ጠባቂው ጀማል ሲወጣ ጎሉን ሲሸፍኑ የነበረበት መንገድ፣ ኦመድ በማጥቃቱ ረገድ ሲያደርግ የነበረው የግል ጥረት ሊነሱ ይችላሉ፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ አማካዩ ናትናኤል ሲያሳይ የነበረው መረጋጋት፣ ኳስ የመቀበል ፍላጎት እና ለጓደኞቹ የማቀበል ጥረትም በመልካም ጎንነት ይነሳል፡፡ የሁልጊዜ ችግራችን በሆነው የቆሙ ኳሶችን መከላከል ረገድም ጥሩ ነገር ታይቷል – በፀሀፊው አመለካከት፡፡

ከትናንቱ ጨዋታ የቡድናችን እንቅስቃሴ በርካታ የቡድንም ሆነ የግል ስህተቶችን ማንሳት እንችላለን፡፡ የቡድኑ የመከላከል አደራጀት (defensive organization) በተለይም ከማጥቃት ወደ መከላከል በምናደርገው ሽግግር ወቅት እጅግ ደካማ ነበር፡፡ ከላይ በጨዋታው ዳሰሳ ላይ እንደተጠቀሰውም ሶስቱም ጎሎች የተቆጠሩት በዚህ ችግር ነበር፡፡ በብዛት ሆነን በተከላከልንባቸውም ጊዜያት የተጨዋቾቻችን የቦታ አያያዝ (positioning) እና የታክቲክ መረዳት (tactical awareness) ጥሩ አልነበረም፡፡ የተግባቦት ችግሮችም ነበሩ – ሳልሀዲን ከቡድን አጋሮቹ ጋር ተግባብቶ የአልጄሪያን አጥቂዎች ከጨዋታ ውጪ ለማድረግ አለመቻሉ ለአብነት ይነሳል፡፡ በጫና ውስጥ የተጨዋቾቻችን ኳሶችን ለመቀበል ፍቃደኛ ያለመሆን እና ያገኙትንም ኳስ ለተገቢው ሰው አለማድረስም ታይቷል፡፡ አጥቂዎቻችን በርካታ የጎል እድሎችን ካለማግኘታቸው አንፃር ልንተቻቸው ቢከብደንም ከመረጋጋት ችግር እና ከችኮላ (የሽመልስ እና የኦመድ ይነሳሉ) ጥሩ እድሎችን እንዳበላሹ አይካድም፡፡ በተጨማሪም በእነሱ መስመር የነበሩት ተከላካዮቻችንን በሚገባ ማገዝ አልቻሉም – በተለይ ኦመድ፡፡ ጥቂት የማይባሉ ተጨዋቾቻችን ባለመዷቸው ሚናዎች መጫወታቸው (አንዳርጋቸው፣ ታደለ፣ ዩሱፍ፣ ሽመልስ… ) ጨዋታውን እንዳከበደባቸው መናገር ሲቻል ለዚህም በቀጥታ ተጠያቂ የሚሆኑት አሰልጣኙ ባሬቶ ይሆናሉ፡፡ ፖርቹጋላዊው የቡድኑ አለቃ በርካታ ወሳኝ ተሰላፊዎቻቸውን በተለያዩ ምክንያቶች ማጣታቸውን መረዳት ቢቻልም ተጨዋቾቹን በእንደዚህ አይነት ከባድ ጨዋታ ያለቦታቸው ማጫወትን እንደ መፍትሄ መጠቀማቸውን መረዳት ያስቸግራል፡፡

 

ቀጣይ ዕድላችንስ ምንድነው?    

ከትናንቶቹ የምድባችን ሁለት ጨዋታዎች በኋላ የምድባችን ቡድኖች አቀማመጥ ይህን ይመስላል፡፡

1ኛ- አልጄሪያ፡  5 ጨዋታ   15 ነጥብ እና 9 የጎል ክፍያ

2ኛ- ማሊ፡     5 ጨዋታ     6 ነጥብ እና 0 የጎል ክፍያ

3ኛ- ማላዊ፡    5 ጨዋታ     6 ነጥብ እና -4 የጎል ክፍያ

4ኛ- ኢትዮጵያ፡  5 ጨዋታ     3 ነጥብ እና -5 የጎል ክፍያ

አሁን ሁሉም ቡድኖች አንድ፣ አንድ ጨዋታዎች የሚቀራቸው ሲሆን ረቡዕ በተመሳሳይ ሰዓት (ምናልባትም ምሽት 1 ሰዓት) በማሊ ሜዳ ማሊ ከአልጄሪያ እና በአዲስ አበባ ኢትዮጵያ ከማላዊ ይጫወታሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ብሔራዊ ቡድናችን የማለፍ እድል አለው ወይስ የለውም የሚለውን በእርግጠኝነት ለመናገር አስቸጋሪ ቢሆንም ከስር የሰፈረውን የካፍ ደንብ በጥልቀት መመልከት መልስ ይሰጥ ይሆናል፡፡ ፀሀፊው ግን እጅግ የጠበበ ቢሆንም የማለፍ እድል እንዳለን ያምናል፡፡ ይህም የሚሆነው ማሊ በየትኛውም ውጤት በአልጄሪያ ከተረታች እና ዋልያዎቹ በሜዳቸው በሶስት ጎሎች በበለጠ ማላዊን ከረቱ ብቻ ይሆናል፡፡

በካፍ የአፍሪካ ዋንጫ ደንብ አንቀፅ 14 ተራ ቁጥር 2 ላይ ሁለት ወይም የበለጡ ቡድኖች እኩል ነጥቦች ካሏቸው ጉዳዩ የሚያገባቸው ቡድኖች (concerned teams) ባደረጓቸው ጨዋታዎች ያላቸው የጎል ልዩነት አላፊውን እንደሚወስን ይገልፃል፡፡ በዚህ መሰረት ኢትዮጲያ ማላዊን ከረታች እና ማሊ በአልጄሪያ ከተሸነፈች ሶስቱም ቡድኖች እኩል ስድስት ነጥቦች ይኖራቸው እና እርስ በእርሳቸው ሲጫወቱ ባስቆጠሯቸው ጎሎች እና በተቆጠሩባቸው ጎሎች ያሉት ልዩነቶች (የጎል ክፍያ) ታስበው አላፊው ይለያል ማለት ነው፡፡

Article 14

In case of equality of points between two or more teams, after all the group matches, the ranking of the teams shall be established according to the following criteria:

14.1 Greater number of points obtained in the matches between the concerned teams;

14.2. Best goal difference in the matches between the concerned teams;

14.3. Greater number of goals scored in the matches between the concerned teams;

14.4. Greater number of away goals scored in the direct matches between the concerned teams;

14.5. Goal difference in all the group matches;

14.6. Greatest number of goals scored in all the group matches;

14.7. A drawing of lots by the Organising Committee of CAF.

1 thought on ““የማይቻለው” ተልዕኮ አልተሳካም

  1. YeEthiopian chigr tchawach mereta lay new yhnin kale slew attegebachew yalewn bicha new yemimeleketut Ene gudau bota tesetot hager akef hono kewereda jemro bitases ewnet 20 sew enattalen wey.

Leave a Reply

Your email address will not be published.