የመጨረሻው እድላችንን ለመሞከር ተቃርበናል

Flames-hopes-revived-600x337

የመጨረሻው እድላችንን ለመሞከር ተቃርበናል

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ በቅርብ ዓመታት ጥቂት በጭንቀት የተሞሉ፣ እጅግ አጓጊ እና በመጨረሻ ህዝቡን ሁሉ በደስታ ያሳበዱ ቀናት ነበሩ፡፡ በሚያዝያ 1993 በአፍሪካ ወጣቶች ዋንጫ ውድድር ላይ ቡድናችን ወደ ግማሽ ፍፃሜ እና ወደ ወጣቶች ዓለም ዋንጫ ለማለፍ ደቡብ አፍሪካን ከሁለት ጎሎች ልዩነት በላይ ማሸነፍ አስፈልጎት 4ለ1 ድል አድርጎ ተስፋውን ያሳካበት፣ እንዲሁም ካቻምና በጥቅምት 4 ቀን ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለመግባት ሱዳንን በሁለት ወይም በበለጡ ጎሎች መርታት ግድ ሆኖበት በ2ለ0 ድል አላማውን ያሳካበት እና ህዝቡን በደስታ ያሰከረበት ፍፁም የማይረሱ ነበሩ፡፡ አሁንም ከሁለት ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ እድል ይዞ ግን በብዙ ጎሎች ልዩነት የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ የገባበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ምናልባት የአሁኑን የሚለየው የሌሎች ቡድኖችን ውጤት የመጠበቁ ግዴታ ነው፡፡

አከራካሪው የማለፍ እድላችን

በአልጀርስ በአልጄሪያ 3ለ1 የተረታንበት የቅዳሜ ምሽቱ ጨዋታ ከተጠናቀቀበት ቅፅበት ጀምሮ እስከ አሁንም ድረስ በዋልያዎቹ የማለፍ ዕድል ዙሪያ ከፍተኛ ክርክሮች እና ውዝግቦች ነበሩ፤ አሉም፡፡ አንዳንድ ሚዲያዎች እና የስፖርት ፕሮግራም አዘጋጆች በካፍ የእርስ በእርስ ግንኙነት ደንብ ምክንያት የማለፍ ተስፋችን እንዳከተመ ሲናገሩ የሰነበቱ ሲሆን ሌሎቹ በበኩላቸው የማለፍ የጠበበ ተስፋ እንዳለን ተስማምተው ማሊ በአልጄሪያ የምትረታ ከሆነ ቡድናችን ማላዊን መርታት በሚገባው የጎል ልዩነት ዙሪያ ክርክር ውስጥ ገብተው ነበር – አሁንም ክርክሩ አልቆመም፤ ጨዋታዎቹ ተደርገው ውሳኔዎች እስኪሰጡ ድረስም ቢያንስ ይሄኛው እሰጥ-አገባ የሚቆም አይመስልም፡፡ ለማንኛውም ግን ለአሁን የኢትዮጵያ ቡድን የማሊ መሸነፍ እና የእራሱን ከሶስት ጎል በበለጠ ልዩነት ማሸነፍ እንደሚያስፈልገው ብናስብ የተሻለ ይሆናል፡፡

የረዥሙ ጉዞ ውዝግብ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ይህን አነስተኛ ተስፋ ወደ እውነትነት ለመቀየር አልያም ቢያንስ በክብር ማጣሪያውን ለመጨረስ ከአልጄሪያ መልስ ዳግም ዝግጅቱን ጀምሯል፡፡ ቡድኑ በአልጄሪያው ጉዞ እጅግ መዳከሙ በምክንያትነት ቀርቦ ከማላዊው ጨዋታ በፊት ምንም ልምምድ ላይሰራ እንደሚችል ተሰግቶ የነበረ ቢሆንም ጠዋት እንደመድረሳቸው ቀኑን አረፍ ብለው ትናንት ምሽት ላይ ቀለል ያለ ልምምድ አድርገዋል፤ ዛሬ ምሽትም እንደዚያው፡፡ የዚህ ጉዞ ነገርም በብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ እና በፌዴሬሽኑ ሰዎች መካከል ከፍተኛ ውዝግብ ፈጥሯል፡፡ አሰልጣኙ ማሪያኖ ባሬቶ ወጪ ለመቀነስ ሲባል በኮኔክሽን በረራ እንዲሄዱ እና እንዲመለሱ መደረጋቸው በተለይ በሮም ትራንዚት ወቅት ለበርካታ ሰዓታት በማይመች ሁኔታ እንዲቀመጡ እና እንዲዳከሙ እንዳደረጋቸው እና ይህም ለአልጀርሱ ደካማ አቋም አንዱ ምክንያት እና ለነገው የማላዊ ጨዋታም በሚገባ ላለመዘጋጀታቸው ምክንያት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ በረዥም ሰዓታት በረራ እና ትራንዚት መዳከማቸው በአልጄሪያው ጨዋታ ተገቢው ትኩረት እና የአካልም ሆነ የአእምሮ ዝግጁነት እንዳይኖራቸው እንዳደረጋቸው የተናገሩት ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ልምድ ያለው እና በስህተት የማይታማው ዋሊድ አታ ግዙፍ ስህተት የመስራቱን ክስተት ይሄው ጉዳይ ከፈጠረው የአእምሮ መዳከም ጋር አያይዘውታል፡፡ ባሬቶ ጨምረውም ባለፉት ጥቂት ቀናት ተጨዋቾቹ ከገንዘብ እጥረት እና ከነበሩበት ስፍራ ጋር በተያያዘ ተገቢውን ምግብ መመገብ እንዳልቻሉም ገልፀዋል፡፡ በዛሬ ማለዳ የተለያዩ የኤፍ.ኤም ሬዲዮዎች የስፖርት ፕሮግራሞች ሀሳባቸውን የሰጡት የቡድኑ ተጨዋቾች እና ምክትል አሰልጣኙ ፋሲል ተካልኝም የባሬቶን ቅሬታዎች በተለይም የጉዞውን ድካም ተፅዕኖዎች እንደሚጋሩ አረጋግጠዋል፡፡ የቡድን መሪው ኢንጂነር ቾል ቤል በበኩላቸው የባሬቶን ሀሳቦች ያላስተባበሉ ሲሆን ችግሮቹ የተከሰቱት ግን ፌዴሬሽኑ ለቀጥታ ጉዞ ከፍ ያለ ገንዘብ ለማውጣት ካለመፈለጉ እንዲሁም ብዙ ሰዓታት ባሳለፉበት ሮም አየር ማረፊያ ከሳንዱዊቾች እና ፒዛ ባለፈ ለተጨዋቾች የሚሆን ምግብ ባለመገኘቱ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ የፌዴሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ወንድምኩን አላዩ ግን የምግብ ችግሩ የተከሰተው በገንዘብ እጥረት ሳይሆን ጥሩ ምግብ ባለመገኘቱ እንደሆነ፣ ጉዞው አድካሚ እንደሆነ ቢረዱም በሚሊየኖች የሚቆጠር ገንዘብ ለማትረፍ ውሳኔው ተገቢ እንደነበር እናም የጉዞው ድካም ለቡድኑ ሽንፈት እና ደካማ አቋም በሰበብነት ሊጠቀስ እንደማይገባ ተከራክረዋል፡፡

የምሽት ጨዋታ ጣጣዎች

ብርቅዬው የአዲስ አበባ ስታዲየም ቢያንስ ባለፉት ቅርብ ዓመታት እስከ ምሽቱ ሶስት ሰዓት ጨዋታ ያስተናገደበትን አጋጣሚ ማስታወስ ያስቸግራል፡፡ አሁን ግን ለዚያውም በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ወሳኝ ጨዋታ ይህን ሊያደርግ ተዘጋጅቷል፡፡ የነገው ወሳኝ ፍልሚያ ከምሽቱ በአንድ ሰዓት እንዲጀምር የተደረገው እንደ ሌላው ጊዜ በፌዴሬሽኑ ፍላጎት ሳይሆን የመጨረሻ ጨዋታ በመሆኑ እና ከሌላው የምድባችን ጨዋታ (ማሊ ከአልጄሪያ) ጋር በእኩል ሰዓት መደረግ ስለሚገባው፣ ካፍም ለሁለቱም ባለሜዳዎች የተሻለ አማካይ ሰዓት በመምረጡ ነው (የእኛ ሰዓት ከማሊ ከሁለት ሰዓታት በበለጠ እንደሚቀድም ልብ ይሏል)፡፡ ግን ይህ የካፍ ውሳኔ በፌዴሬሽኑ ላይ ሁለት ሸክሞችን ጥሏል – የመብራት ፓውዛዎች እና የትራንስፖርት አገልግሎት፡፡ የዚህ እድሜ ያፈጀ ምስኪን ስታዲየም እድሜ-ጠገብ ፓውዛዎች ችግር እንዳለባቸው ባለፉት ዓመታት በተጨዋቾች፣ አሰልጣኞች እና ተመልካቾች ሲነገር የቆየ ቢሆንም ሠሚ ሳያገኝ ቀርቶ አሁን በዓለም ተመልካች ፊት ለፈተና ለመቅረብ ተዘጋጅተዋል፤ የነገውን ጨዋታ በሚገባ ያስተናግዳሉ የሚለውም ብዙዎችን አሳስቧል፡፡ ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ የምሽት እንቅስቃሴ እምብዛም ባልተለመደበት አዲስ አበባ ጨዋታው ከሚፈፀምበት 3፡00 በኋላ ተመልካቾች ወደቤታቸው የሚሄዱበት ሁኔታ ሲሆን ፌዴሬሽኑ ለዚህ መፍትሄ ለማምጣት ከአንበሳ የከተማ አውቶቡስ ድርጅት እና ከሌሎች የትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶች ጋር እየተነጋገረ እንደሆነ ገልፅዋል፡፡ የስታዲየም መግቢያ ቲኬት ዋጋን በተመለከተ፣ ፌዴሬሽኑ የጥላ ፎቅን እና የከማን አንሼን መግቢያ ዋጋዎች ከ500 ወደ 300 እንዲሁም ከ100 ወደ 50 ብር እንዳወረደ በሌሎቹ ቦታዎች ግን እንደቀድሞው እንደሚቀጥል፣ የቲኬት ሽያጩም ከቀኑ በ8 ሰዓት እንደሚጀመር አረጋግጧል፡፡

የማይኖሩ ተጨዋቾች   

ባለፉት ጨዋታዎች በተለያዩ ምክንያቶች ሀገራቸውን ማገልገል ካልቻሉት ከእነ ሳላሀዲን ሰዒድ፣ ቶክ ጄምስ፣ ጌታነህ ከበደ እና ሲሳይ ባንጫ በተጨማሪ በቅዳሜው ጨዋታ ሁለተኛ ተከታታይ የቢጫ ካርዳቸውን የተመለከቱት የመሀል ተከላካዩ ዋሊድ አታ እና አጥቂው ዳዋ ሆቴሳ በነገው ጨዋታ አይኖሩም፡፡ የአሚን አስካር ጉዳይም ይህ ፅሁፍ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ መፍትሄ አላገኘም፡፡ በሌላ በኩል በአልጀርሱ ጉዞ ያልተካተቱት እንዳለ ከበደ እና ኤፍሬም አሻሞ ከቡድኑ ጋር ልምምድ እየሰሩ ናቸው፡፡

ትንሽ ስለተጋጣሚያችን ማላዊ

አሁን በምድባችን ለማለፍ ከእኛ የተሻለ እድል ያላቸው እና በወቅታዊው የፊፋ ሀገራት ደረጃ ከእኛ ሁለት ደረጃዎች ከፍ ብለው የተቀመጡት (እነሱ 109ኛ እኛ 111ኛ ነን) ማላዊዎች በቅፅል ስማቸው ነበልባሎቹ ተብለዉ ሲጠሩ በአፍሪካ ዋንጫው ታሪክ ሁለት ጊዜ (በ1984 እና 2010) የመሳተፍ እድል አግኝተዋል፡፡ ነበልባሎቹ በማጣሪያው ጉዞ በሜዳቸው ካሙዙ ኢትዮጵያን እና ማሊን በመርታት ባገኟቸው ስድስት ነጥቦች ታግዘው ሶስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሲሆን የነገውን ጨዋታም በማሸነፍ እንደሚያልፉ እየዛቱ ይገኛሉ፡፡ የቡድኑ አሰልጣኝ ያንግ ቺሞዚ አሁን አላማቸው በአዲስ አበባ ማሸነፍ እንደሆነ እና ልጆቻቸውም ለፍልሚያው እንደተነሳሱ ገልፀዋል፡፡ “ልናሸንፍ እንደምንችል አምናለሁ፤ ተጨዋቾቼም ድል እንደምናገኝ ያምናሉ፤ ለእና ዋናው ነገርም ይሄው ነው” ብለዋል፡፡ ማላዊያኑ በታላቁ የዴሞክራቲክ ኮንጎ ክለብ ቲ.ፒ ማዜምቤ እና በደቡብ አፍሪካ ክለቦች የሚጫወቱ በርካታ ተጨዋቾችን ይዘው እሁድ እለት ከእኛ ብሔራዊ ቡድን ቀድመው አዲስ አበባ የደረሱ ሲሆን በካፒታል ሆቴል አርፈው ዝግጅታቸውን እደደረጉ ይገኛሉ፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የማላዊ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በገንዘብ ችግር ምክንያት ከማጣሪያው ሊወጣ እንደሚችል ፕሬዚዳንቱ ገልጸው የነበረ ቢሆንም የሀገሪቱ ትልልቅ ድርጅቶች ባደረጉለት እርዳታ በማጣሪያው ለመቆየት ችሏል፡፡ Airtel Malawi – 10 ሚሊዮን ክዋቻ (21.000 የአሜሪካን ዶላር ገደማ) እና የሞባይል ቀፎ አምራች እህት ኩባንያው TNM – 5 ሚሊዮን ክዋቻ (10.500 የአሜሪካን ዶላር) እንዲሁም Standard Bank Of Malawi – 5 ሚሊዮን ክዋቻ (10.500 የአሜሪካን ዶላር) ለግሰዋል፡፡

የማላዊ ብሔራዊ ቡድን ቅዳሜ ማሊን ከረታበት አሰላለፉ አንድ ተጨዋች ብቻ እንደሚቀይር አሰልጣኙ ያረጋገጡ ሲሆን በዚህም መሰረት ነገ ምሽት በሚከተለው አሰላለፍ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል፡-

4-1-3-2

ግብ ጠባቂ፡- ማክዶናልድ ሀራዋ

ተከላካዮች፡- ጆን ላንጄሲ፣ ፍራንሲስ ምሊምቢካ፣ ሊምቢካኒ ምዛቫ እና ሀሪ ንዪሬንዳ

አማካዮች፡- ታታሪው ቺማንጎ ካይራ ከተከላካዮቹ ፊት ሆኖ ሽፋን ሲሰጥ ከእሱ ፊት ሮበር ንጋምቢ፣ ፊሸር ኮንዶዊ እና አምበሉ ጆሴፍ ካምዌንዶ ፈጠራውን ያበረክታሉ፡፡

አጥቂዎች፡- በምርጥ አቋም ላይ የሚገኘው ኤሶ ካንዬንዳ እና ተስፈኛው ወጣት ጋስቲን ሲሙኮንዳ የአጥቂ መስመሩን ይመራሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.