የመጀመሪያው የኩላሊት ንቅለ ተከላ በተሳካ መልኩ በሀገር ውስጥ ተካሄደ

kidney Transplant

kidney Transplant

የመጀመሪያው የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና ነሀገራችን በተሳካ መልኩ ተካሂዷል።

ህክምናው ባሳለፍነው ማክሰኞ መስከረም 11 2008 ዓ.ም በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ነው የተካሄደው።

ከማክሰኞ ጀምሮ በተካሄደው የንቀለ ተከላ ህክምናም እስካሁን ለሶስት ሰዎች የተሳካ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና ተደርጎላቸዋል።

ስኬቱም ህክምናውን ለማግኘት ወደ ውጭ አገራት የሚደረግ ጉዞን የሚያስቀር እና የውጭ አገራት ህክምናን ለማግኘት የገንዘብ አቅም የሌላቸው ዜጎችን ተስፋ የሚያለመልም ነው ተብሏል።

ንቅለ ተከላ የሚደረግላቸው ህመምተኞች ከኩላሊት ለጋሹ ሰው ጋር ያላቸውን የስጋ ዝምንድናን ወይም የጋብቻ ግኑኝነትን የሚያሳይ ማስረጃ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው የሆስፒታሉ የህክምና አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ብርሃኔ ረዳይ ዛሬ ስለ ጉዳዩ በሰጡት መግለጫ ላይ አመልክተዋል።

በመቀጠልም በሆስፒታሉ የተቋቋመ እና በብሄራዊ ደረጃ የሚገኙ ሁለት ኮሚቴዎች በሰነዶች ማረጋገጫ ተረጋግጠው መቅረብ ያለባቸውን እነዚሀን ማስረጃዎች እንደሚመረምሩ ተገልጿል።

በመጨረሻም ኮሚቴዎቹ የኩላሊት ለጋሹ ግለሰብ ጤንነት ብቁ መሆኑን በማረጋገጥ ንቅለ ተከላው እንዲከናወን ይፈቅዳሉ ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት የኩላሊት ንቅለ ተከላው በሆስፒታሉ እየተከናወነ ያለው ከሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ በመጡ ባለሙያዎች ድጋፍ ነው።

ባለሙያዎቹ ወደ ኢትዮጵያ እየተመላለሱ ህክምናውን የሚሰጡ ሲሆን፥ በያዝነው 2008 ዓመተ ምህረት ለ50 ሰዎች የኩላሊት ንቅለ ተከላውን ለማከናወን ታቅዷል።

ይህንንም መጠን በሚቀጥለው ዓመት በእጥፍ ለማድረስ መታቀዱን፥ የሆስፒታሉ የህክምና አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ብርሃኔ ረዳይ ገልፀዋል።

የዓለም ባንክ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት መሰረት በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ 10 ሺህ ሰዎች መካከል ሶስቱ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

Source: FBC

3 thoughts on “የመጀመሪያው የኩላሊት ንቅለ ተከላ በተሳካ መልኩ በሀገር ውስጥ ተካሄደ

Leave a Reply

Your email address will not be published.