የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሜዳሊስት አትሌት ከበደ ባልቻ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

Kebede Balcha Helsinki 1983

ኢትዮጵያ በዓለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ለመጀመሪያ ግዜ ስትሳተፍ በማራቶን ብቸኛውን የብር ሜዳልያ ያስገኘው አትሌት ከበደ ባልቻ ባጋጠመው የጤንነት እክል ላለፉት ጥቂት ወራት በካናዳ ስካርብሮው ጀነራል ሆስፒታል የሕክምና እርዳታ ሲደረግለት ቢቆይም ሐምሌ 3/2010 ዓ.ም. (ጁላይ 10/2018) በ67 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን በቅርበት ድጋፍ ሲያደርጉለት የነበሩ ወዳጆቹ አሳውቀዋል፡፡

በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማሕበር (አይ.ኤ.ኤ.ኤፍ) የበላይነት የሚመራው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የዛሬ 35 ዓመት በፊንላንድ ሔልሲንኪ አሀዱ ተብሎ ሲጀመር ኢትዮጵያም በዚህ ዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድር መድረክ የመጀመሪያ ተሳትፎዋን አድርጋለች፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ በአምስት የውድድር አይነቶች (በ5000 ሜ.፣ 10000 ሜ.፣ 3000 ሜ. መሰናክል፣ 20 ኪ.ሜ. የእርምጃ ሩጫ እና ማራቶን) በወንዶች ብቻ የተዋቀረ ቡድንን ይዛ በቀረበችበት የመጀመሪያው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ብቸኛውን የሜዳልያ ድል ማስመዝገብ የቻለውም በወንዶች ማራቶን በ2 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ከ27 ሰከንድ ሁለተኛ በመሆን ያጠናቀቀው ከበደ ባልቻ ነበር፡፡ ከበደ በወቅቱ ያስገኘው ብቸኛ የብር ሜዳልያ ኢትዮጵያ በሜዳልያ ደረጃ ሰንጠረዡ ዝርዝር ላይ እንድትሰፍርና ከኩባ፣ ኔዘርላንድስ፣ ሮማኒያ እና ስፔን እኩል የ15ኛነት ደረጃን ይዛ እንድታጠናቅቅም ያስቻላት ነው፡፡

ከበደ ባልቻ (1002) የ1983 ዓለም ሻምፒዮና የማራቶን የብር ሜዳልያ አሸናፊ በሆነበት ውድድር ላይ

አትሌት ከበደ ባልቻ ሀገሩን ወክሎ በዓለም ሻምፒዮና ላይ ከተቀዳጀው ድል በተጨማሪም እ.አ.አ. በ1979 ዓ.ም. በሴኔጋል ዳካር በተካሄደው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የማራቶን የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ፣ እ.አ.አ. በ1985 ዓ.ም. በግብፅ ካይሮ በተካሄደው የአፍሪካ ሻምፒዮና የማራቶን የብር ሜዳልያ አሸናፊ፣ እ.አ.አ በ1987 ዓ.ም. በኬንያ ናይሮቢ በተከናወነው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች የማራቶን የነሐስ ሜዳልያ ባለቤት የነበረ ሲሆን ውድድሩን አቋርጦ ለመውጣት ቢገደድም እ.አ.አ በ1980 ዓ.ም. በሶቪዬት ሕብረት በተከናወነው የኦሊምፒክ የማራቶን ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክለው ከቀረቡት ሶስት አትሌቶች አንዱ ነበር፡፡

ከበደ ባልቻ በግሉ በግሪክ አቴንስ እና በካናዳ ሞንትሪያል በተሳተፈባቸው የጎዳና ላይ ውድድሮችም ተጠቃሽ የማራቶን ድሎችን መቀዳጀት የቻለ ብርቱ አትሌት የነበረ ሲሆን በተለይ በካናዳ የሞንትሪያል ማራቶን የ1979፣ 1981፣ 1983 እና 1985 ዓ.ም. (የአራት ግዜ) አሸናፊ መሆኑ እስከቅርብ ግዜ ድረስ በውድድሩ አዘጋጆች ሚገባ የሚታወስበትን እና በክብር እንግድነት የሚጋበዝበትን ስምና ዝና እንዲያገኝ አስችሎት ነበር፡፡                

ከበደ ባልቻ ዛሬ ሕይወቱ ብታልፍም የዛሬ 35 ዓመት በሔልሲንኪ ጎዳናዎች ላይ ሀገሩን ወክሎ በማራቶን ብቸኛውን የብር ሜዳልያ በማስመዝገብ የሰራው ገድል በወቅቱ የሀገሩን ሰንደቅ ከፍ ያስደረገ እንዲሁም በታሪክ መዛግብት ላይ ሰፍሮ እስካሁን የዘለቀ ወደፊትም የሚኖር ሕያው ታሪኩ ነው፡፡ ላለፉት አስራ ስምንት ዓመታት ኑሮውን በካናዳ አድርጎ የቆየው የቀድሞው ብርቱ አትሌት የቀብር ስነስርዓት በምን አይነት መልኩ እንደሚፈፀም እስካሁን ድረስ በግልፅ የታወቀ መረጃ የሌለ ሲሆን በነገው ዕለት ቤተሰቦቹ ተማክረው አንድ ውሳኔ ላይ እንደሚደርሱ ይጠበቃል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ይህን የሀገር ባለውለታና ታሪክ ሰሪ የሆነ አትሌት በክብር በመሸኘቱ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም የበኩሉን ተሳትፎ ቢያደርግ መልካም መሆኑን እየጠቆምን ለአትሌት ከበደ ባልቻ ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶቹ እና ለአትሌቱ አድናቂዎች በሙሉ ልባዊ መፅናናትን እንመኛለን፡፡