ዋልያዎቹ ውቅያኖስ ያቋረጡ ደጋፊዎቻቸውን አስከፍተዋል

Copyright EthioTube 2015.

ምናልባትም በኢትዮጵያ እግር ኳስ የረዥም ጊዜ ታሪክ እጅግ በርካታ ደጋፊዎች እና ጋዜጠኞችን ይዞ ከሀገሩ ውጪ የተጓዘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሚጢጢዬዋ ሀገር ሲሼልስ ጋር ፍፁም ሳይጠበቅ አቻ ተለያይቶ ተመልሷል፡፡ ቀጣዩ ዘገባ ከዚህ ወሳኝ ጨዋታ በፊት፣ በጨዋታው ላይ እና ከጨዋታው በኋላ የተፈፀሙ ክስተቶችን እና የተሰጡ አስተያየቶችን ለመዳሰስ ይሞክራል፡፡

ከጨዋታው በፊት

ከጨዋታው አስቀድሞ በርካታ አነጋጋሪ ጉዳዮች ነበሩ፡፡ በሀገራችን እግር ኳስ ባልተለመደ ሁኔታ (የናይጄሪያ ካላባር ክስተት ሳይዘነጋ) በተለያዩ ድርጅቶች በተለይም በብሔራዊ ቡድኑ ዋነኛ ስፖንሰር ዋልያ ቢራ ሙሉ ስፖንሰርነት እንዲሁም በግላቸው የተጓዙ ጥቂቶችን ጨምሮ ጨዋታውን ለመመልከት የተጓዙ ከ500 የማያንሱ ደጋፊዎች እና ብዙ ጋዜጠኞች በውቧ ሲሼልስ መገኘት ዋነኛው ነበር፡፡ ዋልያ ቢራ በድምላይነር ቦይንግ አውሮፕላን በቻርተር በረራ ብዙዎችን ሲወስድ የተቀሩት በሌሎች ድርጅቶች እገዛ እንዲሁም በጉዞ ወኪሎች የቅናሽ ፓኬጆች ወደ ቪክቶሪያ የተጓዙም ነበሩ፡፡ እነዚህ ኢትዮጵያዊያን የከተማዋን ዋነኛ የባህር ዳርቻ ሆቴሎችም ሆነ ስታዲየሙን የተቆጣጠሩ እስኪመስሉ በዝተው ይታዩ ነበር፡፡ 10.000 ተመልካች የሚያስተናግደው ሊኒቴ ስታዲየምም የሲሼልስ ሳይሆን የዋልያዎቹ እስኪመስል በርካቶቹ ታዳሚያን እነዚሁ ኢትዮጵያዊያን ነበሩ፤ ስታዲየሙ በዝማሬዎችም ደምቆ ነበር፡፡ እውነቱን ለመናገር ከአየር ፀባዩ ውጪ ሁሉ ነገር ኢትዮጵያዊ ነበር፡፡ ዋልያዎቹ ውቅያኖስ አቋርጠው ‹‹በሜዳቸው›› እንደተጫወቱ ቢገለፅ እንኳ ማጋነን አይሆንም፡፡ ጨዋታውን እንዲመሩ በቅድሚያ ተመድበው የነበሩት ኮሞሮሷዊያን አርቢትሮች በጊዜ ሲሼልስ አለመድረሳቸው እና በኋላም ግልፅ ባልሆነ ምክንያት በማዳጋስካራዊያን አርቢትሮች መተካታቸው ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ነበር፡፡ የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ለሁለት ወራት ያዘጋጁት ቡድን እንዳለ ሆኖ ሁሉንም ከውጪ ሀገራት ሊጎች የተጠሩ ተጨዋቾችን በቋሚነት ለማሰለፍ መወሰናቸው እና በቅድመ-ጨዋታ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የእነዚህ ተጨዋቾች የተሰጥኦም ሆነ የስነ-ልቦና ደረጃ በሀገር ውስጥ ከሚጫወቱ ተጨዋቾች ልቆ ስላገኙት ለመጠቀምመወሰናቸውን መግለፃቸው አነጋጋሪ ክስተት ነበር፡፡

ጨዋታው

በማራኪ ድባብ በተጀመረው ጨዋታ የዋልያዎቹ አሰላለፍ እንደሚከተለው ነበር፡-

አሰላለፍ (4-3-1-2 አሰልጣኙ ከጨዋታው በፊት እንዳሉት)

ግብ ጠባቂ፡- ታሪክ ጌትነት

ተከላካዮች፡- ስዩም ተስፋዬ፣ ዋሊድ አታ፣ አስቻለው ታመነ፣ ተካልኝ ደጀኔ

አማካዮች፡- ኤፍሬም አሻሞ፣ ጋቶች ፓኖም፣ ኦሞድ ኦኮሪ

ሽመልስ በቀለ

አጥቂዎች፡- ጌታነህ ከበደ እና ሳልሀዲን ሰዒድ

ተጠባባቂዎች፡- ለዓለም ብርሀኑ፣ ዘካሪያስ ቱጂ፣ አንተነህ ተስፋዬ፣ ብሩክ ቃልቦሬ፣ ሙሉዓለም መስፍን፣

አስቻለው ግርማ፣ ባዬ ገዛኸኝ

በሜዳቸው ባይተዋር የመሰሉት ሲሼልሶች (ሽፍቶቹ በሚል ቅፅል ይታወቃሉ) በበኩላቸው በአዲሱ አሰልጣኛቸው ብሩኖ ሳኢንዲኒ እየተመሩ በሚከተለው አሰላለፍ ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡

አሰላለፍ (4-4-2 ዝርግ)

ግብ ጠባቂ፡- ሴሲል ኪትሴው

ተከላካዮች፡- ያኒክ ማኑ፣ ቤንዋ ማሪ፣ ጆንስ ጆቤር፣ ዦን ፖል አዴላ

አማካዮች፡- ኔልሰን ሎውረንስ፣ ትሬቨር ቪዶ፣ ዠርቬ ዋዬ-ሂዩ፣ አርኪል ሄንሪዬት

አጥቂዎች፡- ሬኒክ ኤስተር እና ቤርትራንድ ላብሎሽ

ተጠባባቂዎች፡- ጄሮም ዲንግዋል፣ ዲን ሱዜት፣ አንድሪው ኦኔዚያ፣ ብሪያን ዶርቢ፣ ማርቲን ዊልያምስ፣ ሴንኪ ቪዶ እና

ቤርትራንድ ኤስተር

የኢትዮጵያ ቡድን በህዝብ ድጋፍ ሜዳው መስሎ ጨዋታውን ቢጀምርም ከመጀመሪያው ደቂቃ አንስቶ በሲሼልሶች ጥቃት ጫና ውስጥ ገብቷል፡፡ ባለሜዳዎቹ የመጀመሪያ አስደንጋጭ ሙከራቸውን ለማድረግ የወሰደባቸው ሶስት ደቂቃዎች ብቻ ነበር፡፡በአንፃራዊነት ገዘፍ ያለው 13 ቁጥር ለባሹ አጥቂ ቤርትራንድ ላብሎሽ ከመስመር ተሻግሮ ያገኘውን ግልፅ ኳስ ከአግዳሚው በላይ ለቀቀው፡፡ ከአንድ ደቂቃ ብቻ በኋላ የቀኝ መስመር አማካዩ ዠርቬ ዋዬ-ሂዩ ያሻገረውን ሌላ አደገኛ ኳስ ላብሎሽ ከቅርብ ርቀት በቮሊ ሊሞክር ሲዘጋጅ ኤፍሬም አሻሞ ቀድሞ አወጣበት፡፡ የተገኘውም የማእዘን ምት ጎል ከመሆን የተረፈው ለጥቂት ነበር፡፡ በዘጠነኛው ደቂቃ ጋቶች ፓኖም የሰራውን ስህተት የግራ መስመር አማካዩ አርኪል ሄንሪዬት ወደጎልነት ሊቀይረው ሲሞክር ከላካዮቹ ተረባርበው አወጡበት፡፡ ከአንድ ደቂቃ በኋላ አሁንም ጋቶች በአደገኛ ቀጠና በሰራው ስህተት ያገኙትን ኳሽ ሲሼልሶች አግኝተው ከሩቅ ወደ ጎል የመቱት ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጣ፡፡ ከሌላ አንድ ደቂቃ በኋላ አማካዩ ትሬቨር ቪዶ የሞከረው ወጣበት፡፡ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ሌላኛው አጥቂ ሬኒክ ኤስተር ከአስቻለው ታመነ ጋር ታግሎ ያወረደውን ኳስ ላብሎሽ ወደጎል ሲሞክር ዋሊድ እንደምንም መለሰበት፡፡ እነዚህ 13 ደቂቃዎች ለዮሐንስ ቡድን ፍፁም አስቸጋሪ ነበሩ፡፡ በአዲሱ አሰልጣኙ አመራር ለአራት ቀናት ብቻ የተዘጋጀው ቡድንአስደናቂ ጅማሮ በቦታው የነበሩ ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ ያሸበረ ነበር፤ ዋልያዎቹ በነዚህ ደቂቃዎች ቢያንስ አንድ ጎል ባለማስተናገዳቸውም እድለኛ ነበሩ፡፡ ከዚህ በኋላ የሲሼልሶች ጫና በትንሹ ከቀነሰ በኋላ በ22ኛው ደቂቃ ሄንሪዬት ለላብሎሽ ባቀበለው ኳስ አጥቂውን ከታሪክ ጌትነት ጋር አንድ ለአንድ ቢያገናኘውም ግብ ጠባቂው አውጥቶበታል፡፡ ከዚህ ክስተት 60 ሴኮንዶች ብቻ በኋላ ግን የሲሼልሶች የማያቆም ጫና ፍሬ አገኘ፡፡ ከብዙ ግልፅ የማግባት እድሎች መጠቀም ያልቻሉት ባለሜዳዎቹ ተካልኝ ደጀኔ በእጁ በነካው ኳስ የፍፁም ቅጣት ምት አገኙ፡፡ ወጣቱ የግራ ተከላካይ በእግሩ መትቶ ሊያወጣው የተዘጋጀው ኳስ በድንገት እጁ ላይ ማረፉ ነበር የፍፁም ቅጣት ምቱ መገኘት ምክንያት፡፡ ተካልኝ ሆን ብሎ በእጁ ባይነካም ከጀርባው የሲሼልስ ተጨዋች ከመኖሩ አንፃር የፍፁም ቅጣት ምቱ መሰጠት ብዙም አከራካሪ አይደለም፡፡ አማካዩ ኔልሰን ሎውረንስም ፍፁም ቅጣት ምቱን አስቆጥሮ ሀገሩን መሪ አድርጓል፡፡ ከዚህ በኋላ ጨዋታው በትንሹ የቀዘቀዘ ሲሆን ዋልያዎቹ ኢላማዎቻቸውን ያልጠበቁ ጥቂት ሙከራዎችን ከሩቅ ከማድረጋቸው ውጪ አቻ ለመሆን የተለየ ጫና አልፈጠሩም፤ የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራቸውን ለማድረግም 36 ደቂቃዎች ወስዶባቸዋል፡፡ ሽመልስ በቀለ ለጌታነህ ከበደ ያቀበለውን ኳስ ጌታነህ ከቀኝ በኩል ወደ ጎል መትቶት ግብ ጠባቂው በቀላሉ ያዘበት፤ ሳልሀዲን ሰዒድ እና ሽመልስ ጎል ለማስቆጠር እጅ የተሻለ ስፍራ ላይ እንደመኖራቸው የጌታነህ ራስ-ወዳድ ውሳኔ መልካሙን እድል አሳጥቷል፡፡ ወዲያው ግን ሲሼልሶች ወደ ፊት ሄደው በሲሼልስ ቀኝ መስመር ረዳት አልባው ተካልኝን ሲያስቸግር የዋለው ዋዬ-ሂዩ ያሻገረውን ድንቅ ኳስ ሬኒክ ኤስተር በቮሊ ሞክሮ ለጥቂት ወጥቶበታል፡፡ በ39ኛው ደቂቃ ሽመልስ በረዥሙ በመሬት ለጌታነህ ያቀበለውን የፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲው አጥቂ ወደጎል ሞክሮ ግብ ጠባቂው ያዘበት፡፡ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ይሄው የሁለቱ ቅንጅት ተደግሞ ሽመልስ በድንቅ ሁኔታ የሰነጠቀለትን ኳስ ጌታነህ አግኝቶ አሁንም በራስ ወዳድነት ወደጎል የሞከረው በግብ ጠባቂው ተመልሶበታል፡፡ የተሻለ ቦታ ላይ የነበረው ሳልሀዲን በጌታነህ ተደጋጋሚ ራስ-ወዳድ ውሳኔዎች መበሳጨቱን እዚያው ሜዳ ላይ በአካላዊ ቋንቋ ሲገልፅም ታይቷል፡፡ ይህ የዋልያዎቹ አንፃራዊ ጫና በኦመድ ተሞክሮ ግብ ጠባቂው ከመለሰው እና ዋሊድ አታ ጎል ባደረገው ኳስ ፍሬ ያገኘ መስሎ ነበር ነገር ግን ኦመድ ቅጣት ምቱን ሲመታ ዋሊድ በጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ ነበር በሚል ምክንያት ለቅፅበት ደጋፊዎችን ያስደሰተው ጎል አልፀደቀም፡፡ የሁለተኛው አጋማሽ አጀማመር ለዋልያዎቹ እጅግ ተስፋን የሰጠ ነበር፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ በአስቻለው ላይ በሰራው ጥፋት የማስጠንቀቂያ ካርድ የተመለከተው ተከላካይ አማካዩ ትሬቨር ቪዶ ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ በጋቶች ላይ በሰራው ጥፋት በማዳጋስካራዊው አርቢትር የቀይ ካርድ ተመዘዘበት፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በ53ኛው ደቂቃ ደግሞ ዋልያዎቹ አቻ ያደረጋቸውን ጎል ካልተጠበቀ ምንጭ በአወዛጋቢ መንገድ አገኙ፡፡ ጋቶች በአየር ላይ በረዥሙ የጣለለትን ኳስ በመጀመሪያው አጋማሽ በመከላከሉ ላይ ብቻ ተገድቦ የነበረው የቀኝ ተከላካዩ ስዩም ተስፋዬ ኳሷን ተቆጣጥሮ በቀላሉ ጎል አደረጋት፡፡ ስዩም ኳሱን የተቆጣጠረው በእጁ ነው በሚል የሲሼልስ ተጨዋቾችም ሆኑ ደጋፊዎች ተቃውሞ ቢያሰሙም አርቢትሩ አልተቀበሏቸውም፡፡ ከዚህ በኋላ ከጭማሪ ጊዜ ውጪ 37 ደቂቃዎች እንደመቅረታቸው የተጠበቀው በቀይ ካርዱ እና በጎሉ የተነሳሱት ዋልያዎቹ ጫና እንደሚያሳድሩ እና ተጨማሪ ጎሎች እንደሚያስቆጥሩ ነበር፡፡ ሲሼልሶች በበኩላቸው ከጎሉ በኋላ ወዲያው ከአጥቂዎቻቸው አንዱን ላብሎሽን አስወጥተው አማካዩ ሴንኪ ቪዶን በማስገባት በቀይ ካርዱ የሳሳውን መሀል ክፍላቸውን ለማጠናከር እና የተጋጣሚያቸውን ጫና ለመቀነስ ሞክረዋል፡፡ አሰልጣኝ ዮሐንስ በበኩላቸው በ70ኛው ደቂቃ ጋቶችን በማስወጣት በሙሉዓለም መስፍን ተክተውታል፡፡ ዋልያዎቹ ከጎላቸው በኋላ የተጠበቀውን ጫና ማሳደር ሳይችሉ ቀርተው ኢላማቸውን ካልጠበቁ ከሩቅ ከሚመቱ ሙከራዎች ውጪ አስደንጋጭ የጎል ሙከራዎች ያደረጉት በመጨረሻው ሩብ ሰዓት ላይ ነበር፡፡ በ76ኛው ደቂቃ ኤፍሬም ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ሳልሀዲን በጭንቅላቱ ገጭቶ ሞክሮ ለጥቂት ወጣበት፡፡ በዚሁ ደቂቃ ኦሞድ በአስቻለው ግርማ ተተክቷል፡፡ ሲሼልሶችም አጥቂያቸው ሬኒክ ኤስተርን በሌላኛው አጥቂ ዲን ሱዜት ተክተዋል፡፡ 78ኛው ደቂቃ በስታዲየሙ የታደሙ የዋልያዎቹ ደጋፊዎችን እጅግ ያስቆጨ ክስተትን ያሳየ ነበር – ሽመልስ እንደተለመደው መሀል ለመሀል የሰነጠቀውን ኳስ ሳልሀዲን አግኝቶ ከግብ ጠባቂው ጋር ብቻ ለብቻ ቢገናኝም ፍፁም ከእሱ ባልተጠበቀ መንገድ አቅጣጫም ሆነ ጥንካሬ በሌለው ምት ለግብ ጠባቂው ሴሲል ኪትሴው ሲሳይ አድርጎታል፡፡ መደበኛው ጊዜ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ብቻ ሲቀሩ ባዬ ገዛኸኝ ጌታነህን ተክቶ ወደ ሜዳ ቢገባም በባከኑ ደቂቃዎች ሲሼልሶች በአርኪል ሄንሪዬት አማካይነት ካደረጉት እጅግ አስደንጋጭ የቅጣት ምት ሙከራ ውጪ ሳናይ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው በኋላ

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ከጨዋታው በኋላ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት አጭር ቆይታ የባከኑ የጎል ማግባት እድሎችን ላልተጠበቀው የአቻ ውጤት ምክንያት አድርገዋል፤ በአንፃሩም ግን ሲሼልሶች ውጤቱ እንደሚገባቸውም አልካዱም፡፡ ከውጪ የመጡት ተጨዋቾች ባሳዩት አቋም ስለተሰማቸው ስሜት ሲጠየቁም ሀገሪቱ ያሏትን ምርጦቹን ተጨዋቾች የመጠቀም ግዴታ እንዳለባቸው የተሸፋፈነ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ 90.000 ህዝብ ባላት ሀገር ሜዳ ላይ ስለመበለጥ እና ማሸነፍ ስላለመቻል ሲጠየቁ ቻይና በህዝብ ብዛቷ በእግር ኳሱ ስኬታማ እንዳልሆነች እና ይሄ እንደ ትልቅ ነገር መነሳት እንደማይገባው ተናግረዋል፡፡ ወደአፍሪካ ዋንጫው የማለፍ እድላቸውን በመቶኛ እንዲያስቀምጡ ሲጠየቁም አሰልጣኙ ገና ሁለት ጨዋታዎች ብቻ አድርገው ግምቶችን ለማስቀመጥ እንደማይሹም ገልፀዋል፡፡ የሲሼልሱ አቻቸው ብሩኖ ሳኢንዲኒ በበኩላቸው በተጨዋቻቸው እንቅስቃሴ በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ አቋማቸው እንደተደሰቱ ገልፀዋል፡፡ በጎዶሎ ተጨዋች ባሳዩት የታጋይነት መንፈስ መርካታቸውንም አዲሱ አሰልጣኝ ጨምረዋል፡፡

Coach Sahle  inset

ዋልያዎቹ ሲመዘኑ፡-

ታሪክ ጌትነት፡- የደደቢቱ ግብ ጠባቂ ጥቂት ጎል ሙከራዎችን ከማክሸፉ ባሻገር ከተከላካዮቹ ጀርባ በረዥም የሚለቀቁ ኳሶችን ለማጨናገፍ ያሳየው ተደጋጋሚ ጊዜ አጠባበቅ አድናቆት የሚቸረው ነው፡፡

ስዩም ተስፋዬ፡- ልምድ ያካበተው ተከላካይ የአቻነቱን ጎል ያስቆጥር እንጂ በመከላከሉ ረገድም ሆነ ማጥቃቱን በማገዝ ረገድ (በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ) ጥሩ አልነበረም፡፡ በተለይ ከተቃራኒ መስመር በሚሻገሩ ኳሶች ወቅት በራሱ መስመር የሚመጣውን ተጨዋች ለመያዝ ሲቸገር ታይቷል፡፡

አስቻለው ታመነ፡- ባለፉት ጨዋታዎች ከፍ ያለ አድናቆት የተሰጠው አዲሱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካይ ከእሱ ካየናቸው አቋሞች አንፃር ደከም ያለ እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡

ዋሊድ አታ፡- ሙሉ ጤና ሳይኖረው እንደገባ ከጨዋታው በፊት በአሰልጣኙ የተነገረለት የጌልሰርቢርሊጂው ተጨዋችም በፈጣኖቹ የሲሼልስ አጥቂዎች ተቸግሮ ነበር፤ ከአስቻለው ጋር የፈጠሩት ጥምረትም ግዜ የሚፈልግ ይመስላል፡፡

ተካልኝ ደጀኔ፡- ወጣቱ የግራ ተከላካይ የመጀመሪያው አጋማሽ ከብዶት ነበር፡፡ በተለይ የዠርቬ ዋዬ-ሂዩን ፍጥነት እና ቀጥተኝነት ለብቻው መቋቋም አልቻለም፡፡ ወደፊት መሄድም አልቻለም ነበር፡፡

ጋቶች ፓኖም፡- የኢትዮጵያ ቡናው አማካይ ሊያስታውሰው የማይፈልግ ቀን አሳልፏል፡፡ ተከላካዮቹን ከጥቃት መጋረድ አልቻለም፤ ማደራጀት እና መምራት አልቻለም፤ በማጥቃቱ አልተሳተፈም፤ የሚያቀብላቸው ኳሶች (አጭሮቹም ሆኑ ረዥሞቹ) አብዛኞቹ የተበላሹ ነበሩ፡፡

ሽመልስ በቀለ፡- የፔትሮ ጄቱ አማካይ ብቸኛው የቡድኑ የፈጠራ ምንጭ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን የፈጠራቸው እውነተኛ የጎል እድሎች ሁሉ መነሻቸው ደቃቃው አማካይ ነበሩ፡፡ የመከላከሉ እና የታክቲክ ዲሲፕሊን ድክመቱ እንዳለ ሆኖ በግሉ ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡

ኤፍሬም አሻሞ፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ የመስመር አማካይ ከኦሞድ ጋር መስመሮች እየተቀያየረ ቢጫወትም ከታታሪነቱ ውጪ በፈጠራው ረገድ እምብዛም ጥሩ አልነበረም፡፡

ኦሞድ ኦኮሪ፡- ክለቡ የማይታወቀው አጥቂ በተለይ ብዙ ደቂቃዎችን ባሳለፈበት የቀኝ መስመር ምንም መፈየድ አልቻለም፡፡

ጌታነህ ከበደ፡- ለፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ መጫወት የጀመረው አጥቂ በራስ ወዳድነት በርካታ እድሎችን አምክኗል፡፡ በእንቅስቃሴውም ደካ ነበር፡፡

ሳልሀዲን ሰዒድ፡- የኤም.ሲ አልጄሩ አጥቂ ከእሱ ባልተለመደ መልኩ ቀዝቅዞ ውሏል፤ አቻ ሊያደርጋቸው የሚችል መልካም አጋጣሚ አምክኗል፡፡

ተቀይረው የገቡ፡-

ሙሉዓለም መስፍን፡- የአርባምንጭ ከነማው አማካይ 20 ደቂቃዎች ሜዳ ላይ ቢቆይም የተለየ ነገር አልሰራም፡፡

አስቻለው ግርማ፡- ለምዘና የሚያበቃ የጨዋታ ጊዜ አልነበረውም፡፡

ባዬ ገዛኸኝ፡- ለምዘና የሚያበቃ የጨዋታ ጊዜ አልነበረውም፡፡

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ፡- በሙሉ ጨዋታው ለታየው የቅንጅት፣ የቦታ አያያዝ፣ እንደ ቡድን መጫወት አለመቻል፣ የመደራጀት (organization) ችግሮች እና ሲሼልሶች አንድ ተጨዋች ካጡ በኋላ ጨዋታውን ለመለወጥ ባለመቻል ሊወቀሱ ይገባቸዋል፡፡

1 thought on “ዋልያዎቹ ውቅያኖስ ያቋረጡ ደጋፊዎቻቸውን አስከፍተዋል

  1. Mr Yohans Sahile be in mind that at list we wont to participate in AFRICAN cap of nation don’t forget!!!!!!!!!!!!!!!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published.