ዋልያዎቹ ኬኒያን በባህር ዳር ያስተናግዳሉ

Bahirdar Stadium

ላለፉት አስርተ ዓመታት በቋሚነት በአዲስ አበባ ጨዋታዎቹን ሲያደርግ የኖረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአንድ ሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ከመዲናይቱ ውጪ በባህር ዳር ከተማ ጨዋታ ሊያደርግ ተቃርቧል፡፡ ቀጣዩ ፅሁፍ ዋልያዎቹ በቻን ማጣሪያ የኬኒያ አቻቸውን የሚያስተናግዱበትን የእሁድ እለት ፍልሚያ ይዳስሳል፡፡

የረዥም ርቀት ሩጫ ተፎካካሪዎቹ ሀገራት በእግር ኳስ ሜዳ

ኢትዮጵያ እና ኬኒያ በኣለም የስፖርት መድረክ የሚታወቁት በረዥም ርቀት የሩጫ ውድድሮች ላይ ባላቸው የላቀ የበላይነት እና አስደናቂ የእርስ በእርስ ተፎካካሪነት ቢሆንም ቢያንስ በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ በእግር ኳሱም ረዥም ዓመታት የዘለቀ ተቀናቃኝነት አላቸው፡፡ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ1962 ጀምሮ ብሔራዊ ቡድኖቹ በፊፋ ማህደር የተመዘገቡ 27 ኦፊሴላዊ ጨዋታዎች እንዲሁም ባጠቃላይ 34 ጨዋታዎች ያደረጉ ሲሆን በሁለቱም መዝገቦች ሀራምቤዎቹ የተሻለ የማሸነፍ ሬኮርድ አላቸው፡፡ ፊፋ ከሚያውቃቸው ከ27ቱ ፍልሚያዎች 11ዱ በኬኒያ፣ ስምንቱ በኢትዮጵያ ድል ሲጠናቀቁ የተቀሩት በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው፡፡ ሀገራቱ ከዚህ ቀደም በሁሉም መድረኮች (በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ፣ በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር፣ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ፣ በሴካፋ ውድድር እና በወጣቶች ማጣሪያዎች) የተፋለሙ ሲሆን አሁን ደግሞ በቻን ማጣሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኝተዋል፡፡ በሀገር ውስጥ ሊጎች በሚጫወቱ ተጨዋቾች ብቻ በተዋቀሩ ቡድኖች የሚደረገው የቻን ቀጣዩ ውድድር ከጥቂት ወራት በኋላ በምስራቅ አፍሪካዋ ሩዋንዳ የሚካሄድ ሲሆን ውድድሩ ከዚህ ቀደም ሶስት ጊዜ ተደርጎ በዲ.ሪ.ኮንጎ፣ ቱኒዚያ እና ሊቢያ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ዋልያዎቹ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የመጨረሻው ውድድር ላይ ተሳትፈው የነበረ ሲሆን የውድድሩ አሸናፊ ሊቢያ ከነበረችበት ምድብ ማለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል፤ በውድድሩ ስኬታማ አለመሆናቸውም ለአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው መሰናበት አንዱ ምክንያት ተደርጎ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የነገ ተጋጣሚ ኬኒያ ግን በዚህ ውድድር ላይ ተሳትፋ አታውቅም፡፡ የቻንን ውድድር ከዋናው የአፍሪካ ዋንጫ የሚለየው አንዱ ነገር ማጣሪያው በየቀጠናው (በየክፍለ-አህጉሩ) መደረጉ እና በውድድሩ ላይ ሁሉም ቀጠናዎች ተሳትፎ ማግኘታቸው ነው፡፡ እናም የዚህ ጨዋታ የደርሶ-መልስ አሸናፊ ከብሩንዲ እና ጂቡቲ አሸናፊ ጋር ይጫወት እና አሸናፊው በውድድሩ ከሚሳተፉ 16 ቡድኖች አንዱ ይሆናል፡፡

የዋልያዎቹ ሰሞናዊ ሁኔታ

በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሚሰለጥነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከመመራት ተነስቶ ድል ካደረገበት ያለፈው ሳምንቱ የሌሴቶ ጨዋታ በኋላ በተለየ መነሳሳት ውስጥ ይገኛል፡፡ ዋልያዎቹ  በጨዋታ እንቅስቃሴ ተበልጠው እየተመሩ ለእረፍት ከተለያዩ በኋላ በሁለተኛው አጋማሽ በእንቅስቃሴ ተሻሽለው ሁለት ድንቅ ጎሎችን አስቆጥረው ማሸነፋቸው እና ከአስጨናቂው ድል በኋላ በተለይ በተጫወቱበት ከተማ ባህር ዳር የተመለከቱት አስደማሚ የህዝብ ስሜት የእሁዱንም ጨዋታ በጉጉት እንዲጠብቁት አድርጓቸዋል፡፡ ከእሁዱ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ወሳኝ ድሉ ማግስት አራቱን በውጪ ሀገራት ክለቦች የሚጫወቱ ተጨዋቾቹን (ሽመልስ በቀለ፣ ጌታነህ ከበደ፣ ሳልሀዲን ሰዒድ እና ኦሞድ ኦኮሪ) ያሰናበተው ብሔራዊ ቡድኑ በኦሞድ ትክክለኛ ክለብ እና ለቻን ውድድር የመሳተፍ ተገቢነት ዙሪያም ሲወዛገብ ሰንብቷል፡፡ ያለፉትን ወራት ከግብፃዊው ክለቡ አል-ኢትሀድ አሌክዛንደሪያ ጋር ሲወዛገብ የከረመው ኦሞድ ለቀድሞው ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ መፈረሙ እና ፊፋ እና ካፍም ይህን ማረጋገጣቸው ብዙዎችን ባስገረመ መንገድ በዚህ ሳምንት ቢታወቅም እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ አሁንም ከአል-ኢትሀድ ጋር በሚገኘው ተጨዋች ዙሪያ ግራመጋባት ውስጥ ስለሚገኝ ባለጠንካራ ግራ እግሩን ተጨዋች በመጪው እሁድ ጨዋታ ላይ አሰልፎ ስጋት ውስጥ መግባቱን አልፈለገም፤ በዚህም ምክንያት ከእንደ እነሳልሀዲን እና ሽመልስ ሁሉ ወደ ሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ያመራው ተጨዋች ሳይጠራ ቀርቷል፡፡ አሰልጣኝ ዮሐንስ በውጪ ሀገራት ሊጎች በመጫወታቸው ምክንያት ሊጠቀሙባቸው ከማይችሉት ከአራቱ ቋሚ ተሰላፊ ተጨዋቾቻቸው በተጨማሪ ጉዳት ላይ የነበረው ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው ሊሻለው ስላልቻለ ከቻኑ የማጣሪያ ጨዋታ ውጪ ሆኗል፡፡ በአንፃሩ ሌላኛው ጉዳት ላይ የነበረው የቡድኑ ተጨዋች ኤፍሬም አሻሞ ሙሉ ለሙሉ በመዳኑ በቦታው ለአሰልጣኙ አማራጭ ይሆናቸዋል፡፡ በልምምድ ላይ የቁርጭምጭሚት ህመም የታየበት የዋናው ብሔራዊ ቡድን ምክትል አምበል እና የቻኑ ቡድን አምበል በኃይሉ አሰፋም አሁን ጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ሲነገር የግብ ጠባቂዎች ነገር ግን አሳሳቢ ሆኗል – በሳምንቱ የልምምድ ፕሮግራሞች ላይ ሁለቱም ግብ ጠባቂዎች በተለያዩ ቀናት ጉዳት የገጠማቸው ሲሆን አሁን ሁለቱም ቡድኑ ውስጥ ቢገኙም የየትኛው ጉዳት እንደሚቀል እና የትኛው እንደሚሰለፍ መገመት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ከነዚህ ጉዳዮች ውጪ ግን በተጨዋቾች ጉዳት እና ቅጣት ዙሪያ የሚነሳ ነገር ያለ አይመስልም፤ አሰልጣኙ ቀድመው በመረጧቸው እና ባለፉት ሁለት ሳምንታት አብረዋቸው በቆዩት ተጨዋቾች ሐራምቤዎቹን እንደሚገጥሙ ይጠበቃል፡፡

የቡድኑ አለቃ ሌሴቶን ድል ባደረጉበት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ  ጨዋታ እና በዛምቢያ በተረቱበት የወዳጅነት ጨዋታ የተጠቀሟቸው ፎርሜሽኖች እና የጨዋታ አቀራረቦችም ብዙዎችን ሲያነጋግሩ እና ሲያከራክሩ ሰንበተዋል፤ በእሁዱ የቻን ማጣሪያ ምን አይነት አቀራረብ ይኖራቸዋል የሚለውም አጓጊ ሆኗል፡፡ በአዲስ አበባው የወዳጅነት ጨዋታ ዝርግ 4-4-2 የመሰለ እና በሁለተኛው የባህር ዳር  ጨዋታ 4-1-3-2 የመሰለ ፎርሜሽን የተጠቀሙት አሰልጣኝ ዮሐንስ በሁለቱም ጨዋታዎች ከቡድናቸው የሚልጉትን ዓላማ ያለው የኳስ ቁጥጥር የበላይነት፣ የአማካይ ክፍል ጥንካሬ እና የመከላከል እና ማጥቃት ሚዛን የተመለከቱ አይመስልም፡፡ በዛምቢያው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ የጋቶች ፓኖም አና ምንተስኖት አዳነ የመሀል ሜዳ ጥምረት በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ  ፍፁም ደካማ የነበረ ሲሆን የሁለተኛው አጋማሽ የብሩክ ቃልቦሬ እና ፍሬው ሰሎሞን ጥምረት በመጠኑ ተሽሎ ታይቷል፡፡ በሌሶቶው ጨዋታ ቋሚ ተሰላፊዎቹ አማካዮች ለቡድኑ ጎሎች ቁልፍ ሚና ቢጫወቱም (ጋቶች የመጀመሪያውን የአቻነት ጎል በማስቆጠር እና ሽመልስ በቀለ ለማሸነፊያው ሁለተኛ ጎል ድንቅ ኳስ በማቀበል) በእንቅስቃሴ ረገድ ግን ሁለቱም  የሚጠበቅባቸውን እንዳልተወጡ ተስተውሏል – በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ፡፡ በእሁዱ የቻን ጨዋታም የቡድን ልብ በሆነው በእዚህ ስፍራ ላይ የተሻለ ነገር እንደሚመለከቱ ብዙዎች ተስፋ አድርገዋል፡፡ ለዝርግ 4-4-2 ወሳኝ በሆኑት ክንፎች ላይም በዛምቢያው ጨዋታ ግልፅ ድክመት ታይቷል – የመስመር አማካዮቹ አስቻለው ግርማ እና በኃይሉ አሰፋም ሆኑ የመስመር ተከላካዮቹ  ዘካሪያስ ቱጂ እና ሞገስ ታደሰ እየተጋገዙ መከላከሉንም ሆነ ማጥቃቱን ለማሳመር ተስኗቸው ነበር፡፡ በሌሶቶው የ4-1-3-2 አቀራረብም የመስመር ተከላካዮቹ ዘካሪያስ እና ስዩም ተስፋዬም ሆኑ ከፊታቸው የተሰለፉት በኃይሉ እና ኦሞድ ኦኮሪ በግላቸው፣ በመስመር ጥምረታቸውም ሆነ በየዲፓርትመታቸው ውህደት ላይ ጥሩ አልነበሩም፡፡ የአጥቂ ክፍሉም እንቅስቃሴ በሁለቱም ጨዋታዎች ከሚጠበቀው በታች ነበር፡፡ የዛምቢያው ጨዋታ የባዬ ገዛኸኝ እና ቢኒያም አሰፋ (ኤፍሬም ቀሬ እና ራምኬል ሎክም ተቀይረው ገብተው ነበር) እንዲሁም የሌሶቶው ጨዋታ የሳልሀዲን ሰዒድ እና ጌታነህ ከበደ ጥምረቶች በአጭር ቃል ስኬታማ አልነበሩም፡፡ ባይሆን በሌሶቶው ጨዋታ ባዬ እና ራምኬል ተቀይረው ከገቡ በኋላ የታየው የማጥቃት እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ነበር፡፡ እነዚህ ሁለት ወጣቶች በቋሚነት እንደሚሰለፉበት በሚጠበቀው የእሁዱ የኬኒያ ጨዋታ ብዙ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ለእሁዱ ጨዋታ የተያዙ የዋልያዎቹ አባላት

ግብ ጠባቂዎች

ታሪክ ጌትነት (ደደቢት)፣  አቤል ማሞ  (ሙገር ሲሚንቶ)

ተከላካዮች

ስዩም ተስፋዬ (ደደቢት)፣ ሳልሀዲን ባርጊቾ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ አስቻለው ታመነ (ደደቢት)፣ ሙጂብ ቃሲም (ሀዋሳ ከነማ)፣

በረከት ቦጋለ (አርባምንጭ ከነማ)፣ ዘካሪያስ ቱጂ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ተካልኝ ደጀኔ (ደደቢት)

አማካዮች

ጋቶች ፓኖም (ኢትዮጵያ ቡና)፣ ብሩክ ቃልቦሬ (ወላይታ ድቻ)፣ ምንተስኖት አዳነ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ፍሬው ሰሎሞን (መከላከያ)

በኃይሉ አሰፋ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ አስቻለው ግርማ (ኢትዮጵያ ቡና)፣

አጥቂዎች

ራምኬል ሎክ (ኤሌክትሪክ)፣ ቢኒያም አሰፋ (ኢትዮጵያ ቡና)፣ ባዬ ገዛኸኝ (ወላይታ ድቻ)፣

ግምታዊ አሰላለፍ፡-

ግብ ጠባቂ፡- ታሪክ ጌትነት

ተከላካዮች፡- ስዩም ተስፋዬ፣ አስቻለው ታመነ፣ ሳልሀዲን ባርጊቾ እና ዘካሪያስ ቱጂ

አማካዮች፡- ጋቶች ፓኖም፣ ምንተስኖት አዳነ፣ በኃይሉ አሰፋ እና ራምኬል ሎክ

አጥቂዎች፡- ባዬ ገዛኸኝ እና ቢኒያም አሰፋ

 

ዋልያዎቹ ከጨዋታው በፊት ምን አሉ?

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በጎረቤታቸው ቡድን ላይ ድል ማግኘት ቀላል እንደማይሆን ተናግረዋል፡፡ “ኬኒያዊያንን እናውቃቸዋለን፡፡ ከኬኒያ የምናደርገው ጨዋታ ሁልጊዜም ከባድ ነው፡፡ ከፍልሚያው ድል እንጠብቃለን፡፡ ግን በብዙ ትግል እንደምናገኘው አስባለሁ” በማለት ሲገልፁ የቡድኑ አምበል በኃይሉ አሰፋም የአሰልጣኙን ሀሳብ የሚያጠናክር አስተያየት ሰጥቷል፡፡ “ኬኒያ ጥሩ ቡድን እንደመሆኗ ቀላል ጨዋታ እንደማይሆን እናውቃለን፡፡ ነገር ግን እኛም ለውድድሩ የመብቃት ህልም ያነገበ በጣም ጥሩ ወጣት ቡድን አለን፡፡ የመጀመሪያው ጨዋታ በሜዳችን መሆኑ ከኬኒያው የመልስ ጨዋታ በፊት ድል ማድረግን የግድ ያደርገዋል” ያለው በኃይሉ አክሎም “ከሌሶቶው ድላችን በኋላ እጅግ ተነሳስተናል፡፡ የቡድናችን ስብስብም ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው፡፡ ፍላጎታችን በተጋጣሚያችን ላይ ገደብ ያለፈ ትኩረት መስጠት ሳይሆን በራሳችን ጥንካሬዎች ላይ አትኩረን ይህን ወሳኝ ጨዋታ ለማሸነፍ መታገል ነው፡፡ ባለፈው የደቡብ አፍሪካ የቻን ውድድር ላይ ተሳትፈን ነበር፡፡ ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ በውድድሩ ላይ እንደምንገኝም ተስፋ እናደርጋለን” ብሏል፡፡

ሀራምቤዎቹስ…

ባለፈው ሳምንት በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከሜዳው ውጪ ከኮንጎ ብራዛቪል ጋር 1ለ1 አቻ በመለያየት ተስፋ ሰጪ ጅማሮ ያደረገው የኬኒያ ብሔራዊ ቡድን ደርዘን የሚጠጉ በሌሎች ሀገራት የሚጫወቱ ተሰላፊዎቹን ትቶ ተሳትፎበት በማያውቀው የቻን ውድድር ላይ የመቅረብ እድሉን ለማስፋት ከኬኒያ ተነስቶ በአዲስ አበባ አድርጎ ባህር ዳር ደርሷል፡፡ በስኮትላንዳዊው አሰልጣኝ ቦብ ዊልያምሰን የሚመሩት ሀራምቤዎቹ ወሳኞቹ ተከላካዮቻቸው ሙሳ መሀመድ (ጉዳት) እና ሀሩን ሻካቫን (በወባ ህመም) ወደ ባህር ዳር ይዘው መሄድ ባይችሉም በኮንጎ ውጤታቸው ተበረታትተው ዋልያዎቹን ለመግጠም ተዘጋጅተዋል፡፡ “ስለኢትዮጵያ ብዙ አላውቅም ግን እነሱም ስለእኛ ብዙ እንደማውቁ እረዳለሁ፡፡ ውጪ ሀገር የሚጫወቱ ብዙ ተጨዋቾች ያላቸው አይመስለኝም፡፡ እናም በሙሉ ቡድናቸው ይገጥሙን ይሆናል፡፡ ግን በእኔም ልጆች እተማመናለሁ፤ ምክንያቱም በጣም በተሠጥኦ የታደሉ ናቸው” ያሉት ዊልያምሰን ከዋልያዎቹ ጋር ያላቸው የቀደመ ሬኮርድ ተስፋ እንደሚሰጣቸውም አልደበቁም፡፡ “በኡጋንዳ ብሔራዊ ቡድን የአራት ዓመታት የአሰልጣኝነት ቆይታዬ አራት ጊዜ ኢትዮጵያን ገጥሜያለሁ፤ በአንዱም ግን አልተሸነፍኩም፡፡ ይህን ሬኮርድ በባህርዳርም እንደምቀጥልበት ተስፋ አደርጋለሁ” የሚሉት ስኮትላንዳዊው አሰልጣኝ ስለሚኖራቸው የጨዋታ አቀራረብም ሲናገሩ “ኢትዮጵያዊያን ኳሱን ሲቀባበሉ በጣም ጥሩ ናቸው፤ እቅዳችን የሚሆነው ይህ ኳስ ቁጥጥራቸው እኛ ላይ እንዳይሰራ ለማድረግ ኳስ ቁጥጥርን መከልከል ይሆናል፡፡ እሁድ እለት በጥሩ ሁኔታ መጀመር ያስፈልገናል” ብለዋል፡፡

ዊልያምሰን ከኮንጎ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ላይ በቋሚነት ካሰለፏቸው ተጨዋቾች አራቱን በእሁዱ ጨዋታ በመጀመሪያ ተሰላፊነት እንደሚጠቀሙ ይጠበቃል – ግብ ጠባቂው ቦንፌስ ኦሎች፣ ተከላካዩ አቡድ ኦማር፣ አማካዩ ኮሊንስ ኦቶክ (በቅፅል ስሙ ጋቱሶ) እና አጥቂው ማይክል ኦሉንጋ፡፡ ለክለቡ ጎርማሂያ ከመሀል ሜዳ እየተነሳ ባስቆጠራቸው ዘጠኝ ጎሎች የኬኒያ ሊግ ከፍተኛ ጎል አግቢነትን እየመራ የሚገኘው ቪክቶር አሊ አቦንዶ አይን ሊጣልበት የሚገባ ተጨዋች ሲሆን የጄሲ ዌሬ እና ማይክል ኦሉንጋ አስፈሪ የአጥቂ ክፍል ጥምረትም ይጠበቃል፡፡ ዊልያምሰን እንደ ዮሐንስ 4-4-2ን የሚመርጡ አሰልጣኝ ሲሆኑ ግምታዊ አሰላለፋቸው የሚከተለውን ይመስላል፡፡

ግብ ጠባቂ፡- ቦንፌስ ኦሎች (ጎር ማሂያ)

ተከላካዮች፡- ኤድዊን ዋፉላ (ሌዮፓርድስ)፣ ሎይድ ዋሆሜ (ታስከር)፣ አቡድ ኦማር (ክለብ የሌለው) እና ጃክሰን ሳሌሀ (ሌዮፓርድስ)

አማካዮች፡- ኮሊንስ ኦኮት (ጎር ማሂያ)፣ ሀምፍሬ ሚዬኖ (ታስከር)፣ ቪክቶር አሊ አቦንዶ (ጎር ማሂያ) እና ኬቨን ኪማኒ (ታስከር)

አጥቂዎች፡- ጄሲ ዌሬ (ታስከር) እና ማይክል ኦሉንጋ (ጎር ማሂያ)

ተጠባባቂዎች፡- ዋይክሊፍ ከሳያ (ሌዮፓርድስ)፣ ብሪያን ቢርገን (ኡሊንዚ ስታርስ)፣ ቻርለስ ኦዴቴ (ፖስታ ሬንጀርስ)፣ ኤሪክ ጆሀና (ማታሬ ዩናይትድ)፣ ቤርናርድ ማንጎሊ (ሌዮፓርድስ)፣ ቲሞናህ ዋንዮንዪ (ሌዮፓርድስ)፣ ስቴፋን ዋካንያ (ቼሜሊል ሹገር)፣ ጃኮብ ኬሊ (ሌዮፓርድስ) እና ኖህ ዋፉላ (ሌዮፓርድስ)

1 thought on “ዋልያዎቹ ኬኒያን በባህር ዳር ያስተናግዳሉ

Leave a Reply

Your email address will not be published.