ዋልያዎቹ በ100 ሺህ ደጋፊዎቻቸው ፊት አስጨናቂውን ጨዋታ በድል ተወጥተዋል

Ethiopia vs Zambia - 06072015-2በጋቦን ለሚዘጋጀው 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የአህጉሪቱ ሀገራት በ13 ምድቦች ተከፍለው የሚያደርጉት የማጣሪያ ዘመቻ በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ተጀምሯል፡፡ በዚህ ሳምንት ከተደረጉት ጨዋታዎች መካከልም በምድብ አስር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሌሶቶ አቻውን አስተናግዶ ድል ያደረገበት ጨዋታ አንዱ ነበር፡፡ ቀጣዩ ዘገባ ከጨዋታው በፊት፣ በጨዋታው ላይ እና ከጨዋታው በኋላ የተከሰቱ ነገሮችን እና የተሰጡ አስተያየቶችን ለመዳሰስ ይሞክራል፡፡

ከጨዋታው በፊት

ጥቂት የማይባሉ አነጋጋሪ ጉዳዮች የቅድመ-ጨዋታውን ከባቢ ተቆጣጥረውት ነበር፡፡ ከአስርት ዓመታት በኋላ የዋናው ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ከመዲናዋ አዲስ አበባ ውጪ ሊደረግ መሆኑ፣ የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ከተሾሙ ጀምሮ ከጥቂት ጋዜጠኞች ጋር በፕሬስ ኮንፈረንሶችም ሆነ በቃለ-መጠይቆች ላይ የቃላት ጦርነቶች መግጠማቸው፣ የተጋጣሚው ሌሶቶ ቡድን ደካማ ነው፤ አይደለም ክርክር (የሌሶቶው አሰልጣኝ ሴፊፊ ማቴቴ በጨዋታው ዋዜማ በርካታ ተማሪዎች እና በሌላ ሙያ ላይ የተሰማሩ አማተር ተጨዋቾችን እንደያዙ ገልፀውም ነበር)፣ ዮሐንስ ሳህሌ የሚመርጡት ፎርሜሽን እና የጨዋታ አቀራረብ… እና ሌሎችም ነገሮች የጨዋታው መድረስ በከፍተኛ ጉጉት እንዲጠበቅ አድርገው ነበር፡፡ በጨዋታው እለትም የውቧ ባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች እና ከሌሎች አጎራባችም ሆኑ ሩቅ ከተሞች የመጡ በርካታ ሺህዎች አዲሱ ግዙፍ ስታዲየም ወደ ተሰራበት አካባቢ በማለዳ ሲተሙ ነበር፡፡ በከተማዋ፣ በስታዲየሙ ዙሪያ እና ስታዲየሙ ውስጥ የነበረው ስሜትም እጅግ የተለየ ነበር፡፡ ጨዋታውም ሊጀመር ሲቃረብ ከ70 ሺህ እስከ 120 ሺህ የሚገመት ህዝብ በስታዲየሙ እንደታደመ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና ከአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ተነግሯል (እንዴት ይህን ያህል የቁጥር ልዩነት እንደኖረ እና የታደመውን ተመልካች በግምት ሳይሆን በትክክል ማወቅ እንዳልተቻለ ግን ያጠያይቃል)፡፡

እጅግ የተጓጓበት ጨዋታ

ባለሜዳው የዮሐንስ ሳህሌ ቡድን ጨዋታውን ሲጀምር አሰላለፉ እንደሚከተለው ነበር፡-

አሰላለፍ (4-1-3-2 አሰልጣኙ ከጨዋታው በኋላ እንዳሉት)

ግብ ጠባቂ፡- አቤል ማሞ

ተከላካዮች፡- ስዩም ተስፋዬ ፣ ሳልሀዲን ባርጊቾ፣ አስቻለው ታመነ እና ዘካሪያስ ቱጂ

አማካዮች፡- ጋቶች ፓኖም

ሽመልስ በቀለ፣ በኃይሉ አሰፋ እና ኦሞድ ኦኮሪ

አጥቂዎች፡- ጌታነህ ከበደ እና ሳልሀዲን ሰዒድ

ተጠባባቂዎች፡- ታሪክ ጌትነት፣ ተካልኝ ደጀኔ፣ ሙጂብ ቃሲም፣ ብሩክ ቃልቦሬ፣ ምንተስኖት አዳነ፣ ራምኬል ሎክ እና ባዬ ገዛኸኝ

 

ሴኔጋላዊው የጨዋታው የመሀል አርቢትር ማላንግ ዲዬድሂዮ ጨዋታውን እንዳስጀመሩ ነበር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማጥቃት የጀመረው፡፡ ገና በሁለተኛው ደቂቃም ጌታነህ ከበደ በተከላካዮች መሀል የተሰነጠቀለትን ኳስ ተቆጣጥሮ ግብ ጠባቂውን ቢያልፈውም ወደ ጎል ከመሞከሩ በፊት ከጨዋታ ውጪ ተብሏል፡፡ ነገር ግን ይህ የጋለ ስሜት እና የማጥቃት እንቅስቃሴ ከጥቂት ደቂቃዎች አልዘለቀም፡፡ ዋልያዎቹ ቀጣዩ የማጥቃት ስጋታቸውን የፈጠሩት በ16ኛው ደቂቃ ላይ ሽመልስ በቀለ ከቀኝ መስመር አሻግሮት ለማንም ሳይደርስ ግብ ጠባቂው ያወጣበት ነበር፡፡ ከዚያም ለሌላ ሙከራ፣ ተጨማሪ 10 ደቂቃዎች አስፈልጓቸዋል፡፡ ይህም ሳልሀዲን ሰዒድ ከሩቅ መሬት ለመሬት መትቶ በሌሶቶው ግብ ጠባቂ የተመለሰበት ነበር፡፡ በእነዚህ ሙከራዎች መካከል እና ሙከራውን ተከትሎ ግን በጎላቸው አቅራቢያ ተከማችተው ይከላከሉ የነበሩት ሌሶቶዎች ቀስ በቀስ ከጎላቸው መውጣት፣ አማካይ ክፍሉን መቆጣጠር፣ በግራ እና ቀኝ መስመሮች ችግሮች መፍጠር እና የዋልያዎቹን በር መፈተሽ ጀምረው ነበር፡፡ አዞዎቹ ሁለት ወይም ሶስት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ጎል ቀርበው በግብ ጠባቂው አቤል ማሞ የተመለሱ እና ለጥቂት ወደ ውጪ የወጡ ሙከራዎች ከማድረጋቸው ባሻገር በተለይ በእነሱ የቀኝ በዋልያዎቹ የግራ ክንፍ በኩል እንደፈለጋቸው ይመላለሱ ነበር፡፡ በዚያ የጨዋታው ክፍል ሌሶቶዎቹ የዮሐንስን ቡድን የማጥቃት እንቅስቃሴ በሚገባ ከማዳፈናቸው፣ መሀሉን ከመቆጣጠራቸው እና በፈጣን እና የተደራጀ የማጥቃት ሽግግር መሀል ለመሀል ሆነ በክንፎች ሽፋን የሌለው የመሰለውን የኢትዮጵያን ተከላካይ ክፍል ጫና ውስጥ ከመክተታቸው አንፃር ጎል የሚያኙበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን መገመት እና ዋልያዎቹ ከተጠበቀው እጅግ የላቀ ተጋጣሚ ከፊታቸው እንደቆመ መረዳት ይቻል ነበር፡፡ እናም ግምቱ እውን ሆኖ በ41ኛው ደቂቃ ላይ ሌሶቷዊያኑ መሪ ያደረገቻቸውን ጎል ማስቆጠር ችለዋል፡፡ ለዚህች ጎል አግቢውን እስከመጨረሻው ያልተከተለውን የተከላካይ አማካዩ ጋቶች ፓኖምን፣ ግብ ጠባቂው አቤልን አልያም ኳሱን ባልተለመደ ሁኔታ ያነጠረውን ሜዳ ተጠያቂ ልናደርግ፣ ወይም የማይገባ ጎል እንደገባ ልናስብ እንችል ይሆናል ግን የጨዋታውን ፍሰት በሚገባ የተቆጣጠሩት ሌሶቶዊያኑ መሪ መሆን አይገባቸውም ልንል ፈፅሞ አይቻለንም፡፡ በዚህም ጎል ቡድኖቹ ለእረፍት ወጥተዋል፡፡ ከታክቲክ አቀራረብ እና ከጨዋታ ስትራቴጂ አንፃር የመጀመሪያውን አጋማሽ ከተመለከትነው ከዋልያዎቹ በኩል እጅግ ጥቂት በጎ እና ተስፋ-ሰጪ እንዲሁም በጣም በርካታ ደካማ ነገሮች አይተናል፡፡ በአንዳንድ አጋጣሚዎች በመሀል ተከላካዮቹ መካከል የነበረው ሰፊ ክፍተት፣ የመስመር ተከላካዮቹ ማጥቃቱን ማገዝ አለመቻል እና በመከላከሉም ረገድ አስተማማኝ መሆን አለመቻል፣ የአማካይ ክፍሉ ተከላካዮቹን አለማገዝ (በተለይም የሽመልስ በቀለ ጋቶችን አለመርዳት)፣ ያለፉት ሁለት ዓመታት የፕሪምየር ሊጉ ኮከቦች ኦሞድ ኦኮሪ እና በኃይሉ አሰፋ የመስመር አማካይቱን ሚና በሚገባ አለመወጣት እንዲሁም በዓመቱ ውስጥ በርካታ ጨዋታዎችን ማድረግ ያልቻሉት አጥቂዎቹ አለመናበብ እና በአካል ብቃት ለጨዋታው ዝግጁ አለመሆን ሁሉ በጉልህ የታዩ የቡድኑ ችግሮች ነበሩ፡፡

እነዚህ ችግሮች በሁለተኛው አጋማሽ ተቀርፈው እንደሚመለሱ የዋልያዎቹ ደጋፊዎች ተስፋ ቢያደርጉም ጅማሮው ላይ ለውጦች አልታዩም፡፡ የሌሶቶ የበላይነት ኃይሉ ቢቀንስም እንዳለ ነበር፡፡ 10 ደቂቃዎች ያህል እንደዚህ ከተጓዙ በኋላ ግን የአሰልጣኝ ሴፊፊ ማቴቴ ቡድን ለድሉ ጓጉቶ ይሁን አልያም ተዳክሞ ወደ ራሱ ጎል ማፈግፈግ ጀመረ፡፡ ያልተጠበቀው ኃይለኛ ዝናብ መዝነብ ሲጀምርም ቀድሞ ዝናብ አይመቻቸው የነበሩት ዋልያዎቹ ጨዋታውን መቆጣጠር፣ ፍፁም የበላይ መሆን እና ተደጋጋሚ ጥቃቶችን መፈፀም ጀመሩ፡፡ በነዚህ ደቂቃዎች ሳልሀዲን ከግብ ጠባቂው ጋር ብቻ ለብቻ ተገናኝቶ ሲስት፣ የኦሞድ ጠንካራ የቅጣት ምትም በግብ ጠባቂው ተመልሶበታል፡፡ የቢድ ቬትሱ አጥቂ ጌታነህ ከበደ ወጥቶ የወላይታ ድቻው ባዬ ገዛኸኝ መተካት ደግሞ ለዋልያዎቹ ኃያልነት መፋፋም የበለጠ ነዳጅ ጨምሯል፡፡ በሌሶቶ ግብ ክልል ከአጥቂዎቹ ሳይርቅ ከሚንቀሳቀሰው ጌታነህ በበለጠ ወደኋላ እየተመለሰ ክፍተቶች የሚፈጥረው እና አማካይ ክፍሉን የሚያግዘው ባዬ ለሌሶቶ ተከላካዮች ለመያዝ የሚያስቸግር ሆነባቸው፡፡ የባዬ ስጋት ፈጣሪነት ወደ ጎልነት ለመቀየርም ብዙ ጊዜ አልወሰደም፡፡ በባለፈው ሳምንቱ የዛምቢያ የወዳጅነት ጨዋታ ሽንፈት ላይ በደካማ አቋም የተተቸው የወላይታ ድቻው አጥቂ በ66ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀል ድሪብል እያደረገ የመጣውን ኳስ የሌሶቶ ተከላካዮች እንደምንም ሲያወጡት ከጎሉ በግምት 25 ሜትር ርቀት ላይ ይገኝ ለነበረው ጋቶች ደርሶ የኢትዮጵያ ቡናው አማካይ በአስደናቂ ሁኔታ በመሬት በመምታት ዋልያዎቹን አቻ ማድረግ እና በስታዲየሙ የታደመውን ተመልካች በደስታ ማቆም ችሏል፡፡ ከደጋፊው መሀል ደስታቸውን ለመግለፅ ወደ ሜዳ የገቡ ተመልካቾችም ነበሩ፡፡ ከጎሉ ጥቂት ደቂቃዎች በኋላም ኦሞድ ኦኮሪ ወጥቶ ራምኬል ሎክ የገባ ሲሆን ዋልያዎቹ ተቀይረው በገቡት ተጨዋቾች ዋና ተዋናይነት የማሸነፊያ ጎል ለማስቆጠር ጥቃታቸውን ቀጥለውበታል፡፡ ጥረታቸውም ሰምሮ በ80ኛው ደቂቃ ገደማ የቀድሞዎቹ የሀዋሳ ከነማ አጋሮች በኃይሉ እና ሽመልስ ተቀባብለው ሽመልስ በድንቅ ሁኔታ የሰነጠቀውን ኳስ ሳልሀዲን አግኝቶ በአስደናቂ አጨራረስ ወደ ጎልነት ቀይሯታል፡፡ ከዚህ በኋላ ሁኔታው ተገልብጦ ዋልያዎቹ ድላቸውን አስጠባቂ ሆነው ሲከላከሉ (በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሽመልስን አስወጥተው ተፈጥሯዊ የተከላካይ አማካዩ ብሩክ ቃልቦሬን አስገብተዋል)፣ አዞዎቹ በበኩላቸው የአቻነት ጎል ፈላጊ ሆነው ሲያጠቁ የመጨረሻዎቹን ደቂቃዎች አሳልፈዋል፡፡ ሌሶቷዊያኑ ሳይቀናቸውም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የ2ለ1 ድል ጨዋታው ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው በኋላ

የዋልያዎቹ አለቃ ዮሐንስ ሳህሌ ከጨዋታው በኋላ በሰጡት ፕሬስ ኮንፈረንስ በከፍተኛ ትግል ለተገኘው ድል በባህር ዳር ስታዲየም የታደሙ ደጋፊዎችን ተፅዕኖ አወድሰው የሌሶቶ ቡድን እንደተባለው ‘እጅግ ደካማ’ እንዳልነበር ጨዋታው እንደመሰከረ በመጠቆም ይህን እንዳሉ ስም ጠርተው ያልጠቀሷቸውን ሚዲያዎች ወይም ጋዜጠኞች በነገር ሸንቆጥ አድርገዋል፡፡ አሰልጣኙ የአንድንድ ተጨዋቾች በግል ጥሩ አለመሆን እንጂ ይዘውት የገቡት የ4-1-3-2 ፎርሜሽን ለመጀመሪያው ግማሽ የቡድኑ ድክመትም ሆነ ለተቆጠረባቸው ጎል ምክንያት እንዳልነበረም አስረግጠዋል፡፡ የቡድኑ ምክትል አምበል በኃይሉ አሰፋ በበኩሉ ስለ ሌሶቶ ደካማነት ብዙ ቢባልም እነሱ ተጋጣሚያቸውን ንቀው ወደሜዳ እንዳልገቡ ተናግሯል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊሱ የመስመር አማካይ ያልተጠበቀው ኃይለኛ ዝናብ እንደጠቀማቸውም አልደበቀም፡፡

ዋልያዎቹ ሲመዘኑ፡-

አቤል ማሞ፡- በተወሰኑ የጨዋታው ክፍሎች ሌሶቷዊያኑ ጨዋታውን ቢቆጣጠሩም እና ቢያጠቁም እምብዛም የጎል አጋጣሚዎች ባለመፍጠራቸው የሙገሩን ግብ ጠባቂ አቋም ለመመዘን ያስቸግራል፡፡ አቋቋሙ እና ቦታ አያያዙ ግን መልካም ነበር፡፡

ስዩም ተስፋዬ፡- የደደቢቱ ተከላካይ በመከላከሉ ረገድ ብዙ ባይታማም ማጥቃቱን በማገዝ ረገድ ጥሩ አልነበረም፡፡

አስቻለው ታመነ፡- ኳስ ከቀጠናው ይዞ በመውጣትም በዚህ ጨዋታ ሌላ ኳሊቲውን ያሳየን ተስፈኛው የደደቢት ተከላካይ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ግን (ጎሉ እንደተቆጠረበት አይነት) ከመሀል ተከላካይ አጣማሪው ጋር የነበረው ርቀት ለተጋጣሚ አጥቂዎች በሚመች መልኩ ሰፍቶ ይታይ ነበር፡፡

ሳልሀዲን ባርጊቾ፡- የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተከላካይ እንደ አስቻለው በግሉ መልካም ጨዋታ አሳልፏል፡፡ የጥምረቱ ድክመት ግን ከላይ እንደተጠቀሰው ነበር፡

ዘካሪያስ ቱጂ፡- ድንቅ ዓመት ያሳለፈው ወጣቱ የግራ ተከላካይ ምናልባትም በአጭሩ የዋና ቡድን የእግር ኳስ ህይወቱ ከባዱን 45 ደቂቃ ያሳለፈው በዚህ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ ነበር፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተጨዋች በመከላከሉ ረገድ ደክሞ ሲታይ በማጥቃቱም እንደሌላው ጊዜ አልነበረም፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽሏል፡፡

ጋቶች ፓኖም፡- የኢትዮጵያ ቡናው አማካይ ተቃራኒ ግማሾች አስተናግዷል፡፡ ተከላካዮቹን ከጥቃት መጋረድ ያልቻለበት (እሱም እርዳታ ማጣቱ እንዳለ ሆኖ)፣ በማጥቃቱም ያልተሳተፈበት የመጀመሪያ ግማሽ እና በመከላከሉ ተሻሽሎ የታየበት እና ወሳኟን የአቻነት ጎል ያስቆጠረበት ሁለተኛ ግማሽ፡፡

ሽመልስ በቀለ፡- ተቀይሮ ሲወጣ ከተመልካቾች የተለየ አድናቆት የተቸረው የፔትሮ ጄቱ አማካይ ለሁለተኛው ጎል ጥሩ ሚና ከመጫወቱ በቀር በሚታወቅበት ፈጠራ እና በማጥቃቱም ሆነ ጋቶችን በማገዙ በኩል ጥሩ አልነበረም፡፡ ኳሶቹም በቀላሉ ይበላሹ ነበር፡፡

በኃይሉ አሰፋ፡- የፕሪምየር ሊጉ የዓመቱ ኮከብ ለሁለተኛ ተከታታይ ሳምንት በብሔራዊ ቡድን ማልያ ደካማ አቋም አሳይቷል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አማካይ የመስመር ተከላካዮቹን በማገዝ የቀድሞ ታታሪነቱን ማሳየት ያልቻለ ሲሆን የታወቀ የተስተካከሉ ኳሶች የማሻገር ብቃቱም አብሮት አልነበረም፡፡

ኦሞድ ኦኮሪ፡- የአል-ኢትሀድ አሌክዛንደሪያው አጥቂ ብዙም ባልለመደው ከአጥቂዎቹ ጀርባ የመጫወት ሚና ከአንድ የቅጣት ምት ሙከራ ውጪ ቀዝቀዝ ያለ ጨዋታ አሳልፏል፡፡

ጌታነህ ከበደ፡- አብዛኛውን የዓመቱን ክፍል በክለቡ ቢድ ቬትስ በተጠባባቂነት ያሳለፈው ጨራሹ አጥቂ በግሉ ሊያስታውሰው የማይፈልግ አይነት መጥፎ ቀትር አሳልፏል፡፡

ሳልሀዲን ሰዒድ፡- የአል-አህሊው አጥቂ ከእሱ ባልተለመደ መልኩ ቀዝቅዞ ቢውልም እና አቻ ሊያደርጋቸው የሚችል መልካም አጋጣሚ ቢያመክንም የማሸነፊያውን ጎል ማስቆጠር ችሏል፡፡ አጠቃላይ አቋሙ ግን ጥሩ አልነበረም፡፡

ተቀይረው የገቡ፡-

ባዬ ገዛኸኝ፡- የወላይታ ድቻው አጥቂ ሊኮራበት የሚችል አቋም አሳይቷል፡፡ ጌታነህን ተክቶ ከገባ በኋላ ጥቃቱን ማፍጠን፣ የማይተነበይ ማድረግ እና አማካዮቹንም ማገዝ ችሏል፡፡

ራምኬል ሎክ፡- የኤሌክትሪኩ አጥቂ ከሩብ ሰዓት ያልበለጠ ጊዜ ሜዳ ውስጥ ቢቆይም ዋልያዎቹ ከአቻነቱ ጎል በኋላ ለፈጠሩት ከፍተኛ ጫና ቁልፍ ሚና ነበረው፡፡

ብሩክ ቃልቦሬ፡- ለምዘና የሚያበቃ የጨዋታ ጊዜ አልነበረውም፡፡

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ፡- የቀድሞው የደደቢት አለቃ በመጀመሪያው አጋማሽ ለታየው የቅንጅት፣ የቦታ አያያዝ እና አለመተጋገዝ ችግሮች ተጠያቂ ቢሆኑም በሁለተኛው አጋማሽ እነዚህን ድክመቶች በተወሰነ መጠን ለማሻሻላቸው እና በቅያሬዎቻቸው ለፈጠሩት አዎንታዊ ተፅዕኖ አድናቆት ይገባቸዋል፡፡

2 thoughts on “ዋልያዎቹ በ100 ሺህ ደጋፊዎቻቸው ፊት አስጨናቂውን ጨዋታ በድል ተወጥተዋል

  1. Thank you for the excellent analysis. If I may share my observation, it would be great if you can speak to all Amharic words when writing in Amharic. It’s quite unprofessional to insert non-Amharic words in what is a professional posting. That said, I always look forward to your analysis

Leave a Reply

Your email address will not be published.