ዋልያዎቹ በቻን ለመሳተፍ አንድ ጨዋታ ቀርቷቸዋል

ETH vs Sao Tome

ከጃኑዋሪ 16 እስከ ፌብሩዋሪ 7፣ 2016 በርዋንዳ በሚካሄደው በሀገር ውስጥ በሚጫወቱ ተጨዋቾች በሚዋቀሩ

ቡድኖች የሚደረገው የቻን ውድድር ላይ ለመገኘት የሚደረጉት የማጣሪያ ፍልሚያዎች የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ

ደርሰዋል፡፡ ቀጣዩ ፅሁፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ቻን የመግቢያ ቲኬቱን ሊቆርጥበት የሚችለውን የእሁዱን

ፍልሚያ ይቃኛል፡፡

የቻን ውድድር ከሌሎች አህጉራዊ ውድድሮች የሚለየው በሀገር ውስጥ ሊጎች ብቻ የሚጫወቱ ተጨዋቾችን የሚጠቀም

ውድድር በመሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ ሀገራቱ የማጣሪያ ውድድሮቻቸውን የሚያደርጉት በየአካባቢያቸው (ቀጠናቸው)

ተከፋፍለው መሆኑም የተለየ ያደርገዋል፡፡ እናም የመካከለኛው-ምስራቅ ቀጠናን ወክሎ በውድድሩ ላይ ለመገኘት

ከሚጥሩት ቡድኖች መካከል የኬንያ አቻውን በደርሶ መልስ ጨዋታዎች የረታው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና ጂቡቲን

ጥሎ ያለፈው የቡሩንዲ ብሔራዊ ቡድን በመጨረሻው ማጣሪያ ላይ ተገናኝተው እና ከደርሶ መልሱ ፍልሚያ

የመጀመሪያውን አድርገው አሁን ማንኛቸው በሩዋንዳው ውድድር ላይ እንደሚወዳደሩ ለማወቅ የአንድ ጨዋታ እድሜ

ብቻ ቀርቷቸዋል፡፡ ቡድኖቹ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በእርስ በእርስ ጦርነት ያልተረጋጋ ድባብ ውስጥ በምትገኘው

የቡሩንዲ ዋና ከተማ ቡጁምቡራ በጦር መሳሪያ በተከበበ ስታዲየም ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታቸው ባለሜዳዎቹ

ቡሩንዲዎች በጨዋታው መጀመሪያ እና በጨዋታው መጨረሻ የባከኑ ደቂቃዎች ላይ ባስቆጠሯቸው ጎሎች 2ለ0 ድል

አድርገዋል፡፡ ለቡሩንዲ ሁለቱንም ጎሎች ያስቆጠረው ግዙፉ አጥቂ ላውዲ ማቩጎ ነበር፡፡ በዚህ ጨዋታ ላይ የዋልያዎቹ

የመስመር አማካይ ኤፍሬም አሻሞ ከአርቢትሩ በተመለከታቸው ሁለት የቢጫ ካርዶች ከሜዳ ሲወጣ፣ ከዋልያዎቹ

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ጋር ግጭት ሊፈጥሩ የሞከሩት የቡሩንዲው አሰልጣኝ አህቼን ኤት-አብደልማሌክም

ከመቀመጫቸው ተሰናብተዋል፡፡ አልጄሪያዊው አሰልጣኝ ከዮሐንስ ጋር ሊጋጩ የሞከሩት ተጨዋቻቸውን (ኤፍሬምን

ቢጫ ካርድ እንዲመለከት ያደረገው) ‹‹አዲስ አበባ ስትመጣ አርድሀለሁ›› የሚል መልዕክት ያለው አካላዊ ምልክት

እያሳዩ ሲያስፈራሩት በመመልከታቸው እንደሆነ ከጨዋታው በኋላ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ጨዋታ ላይ ከኤፍሬም ከሜዳ

መሰናበት በተጨማሪ የአጥቂው ዳዊት ፍቃዱ በጉዳት ከሜዳ መውጣትም ዋልያዎቹን ያስከፋ ክስተት ነበር፡፡ አሰልጣኝ

ዮሐንስ ከጨዋታው በኋላ ለስፖርት ዞን የሬዲዮ ፕሮግራም በሰጡት አስተያየት በትኩረት ማጣት ምክንያት

በመጀመሪያው እና በመጨረሻው ደቂቃዎች ከተቆጠሩባቸው ጎሎች በስተቀር ይህ ነው የሚባል የጎል ሙከራ

እንዳልተደረገባቸው እና የጨዋታ የበላይነት እንዳልተወሰደባቸው ገልፀዋል፡፡ የሀገሪቱ አለመረጋጋት እና በስታዲየሙ

ውስጥ የጦር መሳሪያዎችን የያዙ ወታደሮች መኖርም በተጨዋቾቻቸው ላይ የስነ-ልቦና ተፅዕኖ ማሳደሩን አስረድተዋል፡፡

ከቡሩንዲው አሰልጣኝ የተነገረውን የተጨዋች ማስፈራራት ክስም አሰልጣኝ ዮሐንስ እንዳላደረጉት በመግለፅ

አጣጥለውታል፡፡

ለቡሩንዲው ጨዋታ የተያዙ ተጨዋቾች

ግብ ጠባቂዎች

ለዓለም ብርሀኑ፡- ክለብ – ሲዳማ ቡና

ታሪክ ጌትነት፡- ክለብ – ደደቢት

አቤል ማሞ፡- ክለብ – ሙገር ሲሚንቶ

ተከላካዮች

ስዩም ተስፋዬ፡- ክለብ – ደደቢት

አስቻለው ታመነ፡- ክለብ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ሰልሀዲን ባርጊቾ፡- ክለብ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

አንተነህ ተስፋዬ፡- ክለብ – ሲዳማ ቡና

ሙጂብ ቃሲም፡- ክለብ – ሀዋሳ ከነማ

ነጂብ ሳኒ፡- ክለብ – መከላከያ

አማካዮች

ሙሉዓለም መስፍን፡- ክለብ – ሲዳማ ቡና

ብሩክ ቃልቦሬ፡- ክለብ – አዳማ ከነማ

ጋቶች ፓኖም፡- ክለብ – ኢትዮጵያ ቡና

ኤልያስ ማሞ፡- ክለብ – ኢትዮጵያ ቡና

አስቻለው ግርማ፡- ክለብ – ሀዋሳ ከነማ

ፍሬው ሰሎሞን፡- ክለብ – መከላከያ

ቢኒያም በላይ፡- ክለብ – ድሬዳዋ ከነማ

አጥቂዎች

ራምኬል ሎክ ፡- ክለብ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

በረከት ይስሀቅ፡- ክለብ – ሀዋሳ ከነማ

ምንይሉ ወንድሙ፡- ክለብ – መከላከያ

መሐመድ ናስር፡- ክለብ – መከላከያ

ዋና አሰልጣኝ፡- ዮሐንስ ሳህሌ

ግምታዊ አሰላለፍ (4-4-2)

ግብ ጠባቂ፡- ታሪክ ጌትነት

ተከላካዮች፡- ስዩም ተስፋዬ ፣ ሰልሀዲን ባርጊቾ፣ አስቻለው ታመነ፣ አንተነህ ተስፋዬ (ነጂብ ሳኒ)

አማካዮች፡- ጋቶች ፓኖም፣ ኤልያስ ማሞ፣ አስቻለው ግርማ፣ ምንይሉ ወንድሙ

አጥቂዎች፡- ራምኬል ሎክ እና በረከት ይስሀቅ (መሀመድ ናስር)

የተቀነሱ ተጨዋቾች

 የግራ ተከላካዮቹ ተካልኝ ደጀኔ እና ዘካሪያስ ቱጂ እንዲሁም የፊት አጥቂው ዳዊት ፍቃዱ በደረሱባቸው ጉዳቶች

ምክንያት ከእሁዱ ጨዋታ ውጪ ሆነዋል፡፡

 የመስመር አማካዩ ኤፍሬም አሻሞ በቡጁምቡራው የመጀመሪያ ጨዋታ በሁለት የቢጫ ካርዶች ከሜዳ

በመውጣቱ በእሁዱ ጨዋታ ላይ አይኖርም፡፡

የጨዋታው አርቢትሮች

ጨዋታውን እንዲመሩ የተሾሙት አርቢትሮች ግብፃዊያን ሲሆኑ ኮሚሽነሩ ሱዳናዊ ናቸው፡፡

ጥቂት ስለ ቡሩንዲ

ቡሩንዲ በምስራቅ አፍሪካ (አንዳንዴ የመካከለኛው አፍሪካ አካልም ተደርጋ ትታያለች) የምትገኝ ሀገር ናት፡፡ ሀገሪቱ

በ2014 ግምት የ10 ሚሊዮን ገደማ ህዝብ መኖሪያ ናት፡፡ የቡሩንዲ ዋና ከተማ ቡጁምቡራ ስትሆን የሀገሪቱ ዋነኛ

መግባቢያ ቋንቋዎች ኪሩንዲ እና ፈረንሳይኛ ናቸው፡፡ ከወራት በፊት የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ፒዬሬ ንኩሩንዚዛ ህገ-

መንግስቱን አሻሽለው ለሶስተኛ ጊዜ ሀገሪቱን ለመምራት በማቀዳቸው ምክንያት ብጥብጥ ተነስቶ ሀገሪቱ አሁን ድረስ

አለመረጋጋት ውስጥ ትገኛለች፡፡ ወደ እግር ኳሱ ስንመጣ ብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታዎቹን የሚያደርገው በዋናው ከተማ

በሚገኘው ልዑል ልዊ ርዋጋሶሬ ስታዲየም ነው፡፡ የቡሩንዲ ብሔራዊ ቡድን በመጨረሻው የቻን ውድድር ላይ

ከነበረው ተሳትፎ ውጪ በየትኛውም ዓለም-አቀፋዊም ሆነ አህጉራዊ መድረክ ተሳትፎ አያውቅም፡፡

ቡሩንዲዎች የመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎቻቸውን በሙሉ በድል የተወጡ ሲሆን ጎልም አልተቆጠረባቸውም

(በቻን ማጣሪያ ጂቡቲን ሁለት ጊዜ፣ በዓለም ዋንጫ ቅድመ-ማጣሪያ ሲሼልስን ሁለቴ፣ በአፍሪካ ዋንጫ

ማጣሪያ ኒጀርን እንዲሁም በባለፈው ሳምንቱ ጨዋታ ኢትዮጵያን ረትተዋል)፡፡ ይህን አስደናቂ የውጤት ጉዞውን

ተከትሎም ቡድኑ በመጨረሻው ወር ኦክቶበር የፊፋ ወርሀዊ የደረጃ ሰንጠረዥ ከሴፕቴምበሩ ደረጃው 21

ደረጃዎችን ከፍ ብሎ 113ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.