ዋልያዎቹ በተሻለ እንቅስቃሴ ከካሜሩን አቻ ተለያይተዋል

Walia

Walia

ዋልያዎቹ በተሻለ እንቅስቃሴ ከካሜሩን አቻ ተለያይተዋል

በርዋንዳ እየተካሄደ በሚገኘው የ2016 ቻን ውድድር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁለተኛ የምድብ  ጨዋታውን ከካሜሩን ጋር አድርጓል፡፡ በመጀመሪያ ጨዋታቸው በደካማ አቋም በዲ.ሪ.ኮንጎ በሰፊ ውጤት የተረቱት ዋልያዎቹ በስታድ ሁዬ ከካሜሩን ጋር ያደረጉትን ወሳኝ ፍልሚያ ቀጣዩ ዘገባ ሊዳስስ ይሞክራል፡፡

የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ እሁድ በዲ.ሪ.ኮንጎ በተረቱበት ጨዋታ በመጀመሪያ ተሰላፊነት ወደሜዳ ካስገቧቸው ተጨዋቾች ሶስቱን በመቀየር ይህንን ጨዋታ ጀምረዋል፡፡ የመሀል ተከላካይ ሆኖ የጀመረው አንተነህ ተስፋዬ በያሬድ ባዬ ሲተካ፣ የተከላካይ አማካዩ ተስፋዬ አለባቸው በአስራት መገርሳ እና ብቸኛ አጥቂ የነበረው ታፈሰ ተስፋዬ በሙሉዓለም ጥላሁን ተተክተዋል፡፡ ቡድኑ 4-2-3-1 ወይም በጋቶች ፓኖም በተደጋጋሚ ወደፊት መሄድ ምክንያት 4-1-4-1 ይመስል በነበረ አሰላለፍ ጨዋታውን በነዚህ ተጨዋቾች ጀምሯል፡-

ግብ ጠባቂ፡- አቤል ማሞ

ተከላካዮች፡- ስዩም ተስፋዬ፣ አስቻለው ታመነ፣ ያሬድ ባዬ እና ተካልኝ ደጀኔ

አማካዮች፡- አስራት መገርሳ፣ ጋቶች ፓኖም፣

ኤልያስ ማሞ፣ በኃይሉ አሰፋ እና ራምኬል ሎክ

አጥቂ፡- ሙሉዓለም ጥላሁን

ዋና አሰልጣኝ፡- ዮሐንስ ሳህሌ

በመጀመሪያው የምድቡ ጨዋታቸው አንጎላን 1ለ0 የረቱት ካሜሩናዊያኑ በበኩላቸው የሚከተሉትን ተጨዋቾች ይዘው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡      

ግብ ጠባቂ፡- ፓትሪክ ንያሜ

ተከላካዮች፡- ምባህ ማንጋ፣ አሮን ምቢምቤ፣ ሞሀመድ ጄቴይ እና ማንጃንግ ኮምቢ

አማካዮች፡- ፍራንክ ቦያ፣ ጉዬ ኦም፣ ያዚድ አቱባ፣ ሶሌይማን ሙሳ እና ንጋማሌ ሞሚ

አጥቂዎች፡- ሳሙኤል ንሌንድ

ዋና አሰልጣኝ፡-  ንቶንጎ ምፒሌ ማርቲን

 

ከእሁዱ የዲ.ሪ.ኮንጎ ጨዋታ በተለየ ዋልያዎቹ በተረጋጋ መንገድ የጀመሩት ጨዋታ የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ቀዝቃዛ ነበሩ፡፡ ካሜሩናዊያኑ እንደተመኙት ጫና ማሳደር ያልቻሉ ሲሆን በመጀመሪያው ግማሽ ሰዓት የሚጠቀስ ሙከራ ያደረጉት በስምንተኛው ደቂቃ የዋልያዎቹ ተከላካዮች ኳሱን ስተው ማንጃንግ ኮምቢ የመታው እና ከአግዳሚው በላይ የወጣበት ኳስ ነበር፡፡ እንዲያውም የአሰልጣኝ ዮሐንስ ልጆች በጨዋታው ሂደት እየጎለበቱ ሄደው ጨዋታውን በሚገባ መቆጣጠር እና በርካታ የጎል ሙከራዎችንም ማድረግ ችለዋል፡፡ በ19ኛው ደቂቃ ከጋቶች የደረሰውን ጥሩ ኳስ ሙሉዓለም ጥላሁን ወደጎል መትቶት በአግዳሚው ላይ ሲወጣበት፣ በ24ኛው ደቂቃ ጋቶች ከጥሩ ስፍራ ያገኘውን ኳስ በግራ እግሩ መትቶ ኢላማውን ሳያገኝለት ቀርቷል፤ ጋቶች ከዚህ የተሻለ ማድረግ ይጠበቅበት ነበር፡፡ በ28ኛው ደቂቃ ኤልያስ ማሞ ከስዩም ተስፋዬ የተቀበለውን ኳስ ተቆጣጥሮ ከፍፁም ቅጣት ክልል ውጪ ወደጎል መትቶ ለጥቂት በአግዳሚው ላይ ወጥቶበታል፡፡ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ኤልያስ ያዘጋጀለትን ጋቶች ከፍፁም ቅጣት ክልል ውጪ መትቶ ወደውጪ ወጥቶበታል፡፡ በ30ኛው ደቂቃ ሙሉዓለም ጥሩ ኳስ ወደጎል ቢያሻግርም የካሜሩኑ ግብ ጠባቂ ቀድሞ ይዞታል፡፡ በ34ኛው ደቂቃ ከማእዘን የተሻገረውን ኳስ ጋቶች በጭንቅላቱ ሞክሮት ግብ ጠባቂው በቀላሉ ይዞበታል፡፡ ከነዚህ ሁሉ ያልተሳኩ ሙከራዎች በኋላ በ36ኛው ደቂቃ የማይበገሩት አናብስቱ በሳሙኤል ንሌንድ ሙከራ አድርገው አስቻለው ታመነ ተደርቦ አውጥቶባቸዋል፡፡ የወጣው ኳስ ከማእዘን ሊሻገር ሲል ግን የስታድ ሁዬ መብራት ሙሉ ለሙሉ በመጥፋቱ ጨዋታው ሊቋረጥ ተገዷል፡፡ መብራቱ ቀስ በቀስ በመምጣቱ ከ10 ደቂቃዎች ገደማ መቋረጥ በኋላ ጨዋታው ቀጥሏል፡፡ ጨዋታው እንደገና እንደጀመረ ከማእዘን የተሻገረውን ኳስ ፍራንክ ቦያ በጭንቅላቱ ሞክሮ አቤል ማሞ ሲይዝበት ወዲያውኑ ከሴኮንዶች በኋላ በካሜሩን ተከላካዮች መካከል የተፈጠረውን ስህተት ሙሉዓለም ከመጠቀሙ በፊት ግብ ጠባቂው ፓትሪክ ንያሜ ደርሶ ከስጋት አድኖታል፡፡ የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በዋልያዎቹ የተሻለ እንቅስቃሴ እና የጎል ሙከራዎች ታጅቦ ከካሜሩን በኩል ብዙ ነገር ሳይታይ ያለምንም ጎል ተጠናቋል፡፡

የዋልያዎቹ ደጋፊዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ የቡድናቸው ጥሩ እንቅስቃሴ መነሻ የበለጠ ብልጫ እና ጎል ተስፋ አድርገው ሁለተኛው አጋማሽ ቢቀጥልም እንደተመኙት አልሆነላቸውም፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽ የተረጋጋ እና ዓላማ የነበረው የኳስ ቁጥጥር ሲመናመን፣ የጎል ሙከራዎቹም በጣሙን አንሰው ታይተዋል፡፡ የማይበገሩት አናብስትም የጨዋታውን ቅኝት ከተጋጣሚያቸው የበላይነት ስር ማውጣት ችለዋል፡፡ በ56ኛው ደቂቃ ያዚድ አቱባ የመታው ኳስ ወደውጪ ሲወጣበት፣ በ60ኛው ደቂቃ ከግራ የተሻገረውን ኳስ ሳሙኤል ንሌንድ በጭንቅላቱ ሞክሮት ቋሚውን ታክኮ ወጥቶበታል፡፡ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ማንጃንግ ኮምቢ ከርቀት የመታው ኳስም ወጥቶበታል፡፡ በ68ኛው ደቂቃ አስቻለው በግዴለሽነት ያበላሸው ኳስ ሳሙኤል ንሌንድ እግር ደርሶ አጥቂው ወደጎል ያደረገው ሙከራ በሌላ ተከላካይ ተደርቦ ወጥቷል፡፡ ካሜሩናዊያኑ ማእዘን ምቱን በአጭሩ በመቀባበል ጀምረውት ሶሌይማን ሙሳ ያሻገረው ኳስ ንጋማሌ ሞሚ ጋ ደርሶ ከቅርብ ርቀት ያገኘውን ኳስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፤ ለአሰልጣኝ ንቶንጎ ምፒሌ ማርቲን ቡድን የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር፡፡ በ74ኛው ደቂቃ ያሬድ ባዬ በሰራው ጥፋት ምክንያት ከ25 ሜትሮች ገደማ የተሰጠውን የቅጣት ምት አንጎላ ላይ ከተመሳሳይ ስፍራ ጎል ያስቆጠረው ያዚድ አቱባ ወደጎል ቢሞክረውም ኢላማውን ማግኘት ሳይችል በአግዳሚው ላይ ሰዶታል፡፡ በ77ኛው ደቂቃ ዋልያዎቹ የመጀመሪያ የተጨዋች ቅያሬያቸውን በማድረግ ኤልያስ ማሞን አስወጥተው በታደለ መንገሻ ተክተውታል፡፡ ከዚህ በኋላ ብዙ ሙከራዎች እና የተለዩ ክስተቶች ያልታዩ ሲሆን አቻ ውጤቱን በመፈለግ እና ጊዜ ለማባከን በመፈለግ በሚመስል ሁኔታ አሰልጣኝ ዮሐንስ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ታፈሰ ተስፋዬ እና ቢኒያም በላይን በሙሉዓለም እና ራምኬል ሎክ ተክተው አስገብተዋል፡፡ ጨዋታውም ምንም ጎል ሳያሳየን በ0ለ0 ውጤት ተጠናቋል፡፡

 

የዋልያዎቹ አለቃ ዮሐንስ ሳህሌ ከጨዋታው በኋላ በሰጡት አስተያየት ተጨዋቾቻቸው በተለይም አስራት መገርሳ ጥሩ እንደተጫወቱ ገልፀዋል፡፡ የአፍሪካ ሻምፒዮኑ ቲፒ ማዜምቤ ተጨዋቾችን በመያዙ ምክንያት ተጨዋቻቸው የዲ.ሪ.ኮንጎ ቡድንን ፈርተው እንደነበር እንደተረዱ እና እግር ኳስ የ11ለ11 ጨዋታ በመሆኑ ከዚህ በኋላ እንዳይፈሩ ነግረዋቸው ለካሜሩኑ ጨዋታ እንደገቡም አሰልጣኙ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ዋልያዎቹ ሲመዘኑ

ግብ ጠባቂ

አቤል ማሞ፡- ከርቀት ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች ብቻ የተደረጉበት አቤል ዝም ያለ ምሽት አሳልፏል፡፡ ከእሁዱ ጨዋታ በተለየ ግን ቡድኑን ለመምራት እና ለማነቃቃት ሲሞክር ታይቷል፡፡

ተከላካዮች   

ስዩም ተስፋዬ፡- አምበሉ ከካሜሩን የመስመር አማካዮች እምብዛም ችግር አልገጠመውም፡፡ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ወደፊት ለመሄድ ሲሞክርም ነበር፡፡

አስቻለው ታመነ፡- አስቻለው ከአንዳንድ ጥቃቅን ስህተቶች ውጪ ከአዲሱ ተጣማሪው ያሬድ ጋር የካሜሩንን አጥቂዎች በሚገባ ተቆጣጥሮ ውሏል፡፡

ያሬድ ባዬ፡- የዳሸን ቢራው ተከላካይ ያሬድ የማስጠንቀቂያ ካርድ ቢመለከትም ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡

ተካልኝ ደጀኔ፡- ወጣቱ የግራ ተከላካይ አንዳንድ አደገኛ የተሻገሩ ኳሶችን ማውጣት ችሏል፡፡

አማካዮች

አስራት መገርሳ፡- ከበርካታ ወራት በኋላ ለብሔራዊ ቡድኑ በመጀመሪያ ተሰላፊነት የጀመረው አስራት በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ ድንቅ እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡ ቁመተ-ረዥሙ አማካይ ቡድኑን በመምራት፣ ኳሶችን በትክክል በማሰራጨት እና ተከላካይ ክፍሉን በማገዝ ለቡድኑ መልካም እንቅስቃሴ ትልቁን ሚና ተጫውቷል፡፡

ጋቶች ፓኖም፡- ከአስራት ፊት የተጫወተው ጋቶች ካለፉት ጥቂት ጨዋታዎች በአንፃራዊነት የተሻለ ተንቀሳቅሷል፡፡ ኢላማቸውን ባያገኙለትም በርካታ የጎል ሙከራዎችንም አድርጓል፡፡

ኤልያስ ማሞ፡- ፈጣሪው አማካይ አንዳንድ አስደናቂ እንቅስቃሴዎችን ቢያሳይም ባጠቃላይ ግን ተሳትፎው አመርቂ አልነበረም፡፡

በኃይሉ አሰፋ፡- በኃይሉ በተጫወተበት መስመር የነበረውን ተከላካይ ተካልኝን በማገዝም ሆነ በታታሪነት ጥሩ ሲሰራ ውሏል፡፡ ማጥቃቱ ላይ ግን እምብዛም ጥሩ አልነበረም፡፡

ራምኬል ሎክ፡- ራምኬልም እንደ ክለብ አጋሩ በኃይሉ መከላከሉን በማገዙ ጥሩ ቢሆንም በማጥቃቱ ረገድ ተሳትፎው በጣም ደካማ ነበር፡፡

አጥቂ

ሙሉዓለም ጥላሁን፡- ታታሪው አጥቂ እንደብቸኛ አጥቂ ኳሱን ታግሎ ለመቆጣጠር እና የቡድን ጓደኞቹን ወደእንቅስቃሴ ለማስገባት ያደረገው ጥረት በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ መልካም የሚባል ነበር፡፡

ተቀይረው የገቡ

ታደለ መንገሻ፡- ለተከታታይ ጨዋታ ተቀይሮ የገባው ታደለ ቀስ በቀስ በተዳከመው ቡድን ውስጥ ተፅዕኖውን ለማሳረፍ አልቻለም፡፡

ታፈሰ ተስፋዬ፡- ለመመዘን የሚያበቃ የጨዋታ ጊዜ አልነበረውም፡፡

ቢኒያም በላይ፡- ለመመዘን የሚያበቃ የጨዋታ ጊዜ አልነበረውም፡፡

ዋና አሰልጣኝ፡- ዮሐንስ ሳህሌ፡- አሰልጣኙ ከዲ.ሪ.ኮንጎው ጨዋታ በኋላ ለዚህ ጨዋታ ያደረጓቸው የተጨዋቾች ቅያሬዎች በአንፃራዊነት ስኬታማ ነበሩ፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽ አቀራረባቸውም መልካም ነበር፡፡ የሁለተኛው አጋማሽ አቀራረባቸው እና የተጨዋች ቅያሬዎቻቸው ግን ጥያቄ የሚያስነሱ ነበሩ፡፡

ተጨማሪ ነጥቦች

  • ዋልያዎቹ ከሚገኙበት ምድብ ዲ.ሪ.ኮንጎ አንጎላን 4ለ2 በመርታቷ አንድ ጨዋታ እየቀረ ከምድቡ ማለፏን አረጋግጣለች፡፡ ከሁለቱ ጨዋታዎች በኋላ የዲ.ሪ.ኮንጎ ቡድን በስድስት ነጥቦች የምድቡ አናት ላይ ሲቀመጥ፣ ካሜሩን በሶስት ነጥቦች ሁለተኛ፣ ኢትዮጵያ በአንድ ነጥብ ሶስተኛ እና ምንም ነጥብ የሌላት አንጎላ መጨረሻ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
  • የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታዎች በቀጣይ ሰኞ ይደረጋሉ፡፡ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከቀኑ 11 ሰዓት በተመሳሳይ ሰዓት ኢትዮጵያ ከአንጎላ በኪጋሊው አማሆሮ ስታዲየም እንዲሁም ዲ.ሪ.ኮንጎ ከካሜሩን በስታድ ሁዬ ይፋለማሉ፡፡ ዋልያዎቹ ከምድባቸው ለማለፍ አንጎላን ማሸነፍ እና የካሜሩን በዲ.ሪ.ኮንጎ መሸነፍ (የጎል እዳንም መቀነስ እንዳለ ሆኖ) ያስፈልጋቸዋል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.