ዋልያዎቹ በመጀመሪያ ጨዋታቸው አስደንጋጭ ሽንፈት ደርሶባቸዋል

ETH vs Congo CHAN 2016 2

ዋልያዎቹ በመጀመሪያ ጨዋታቸው አስደንጋጭ ሽንፈት ደርሶባቸዋል

የ2016 ቻን ውድድር ባለፈው ቅዳሜ አዘጋጇ ርዋንዳ ታላቋ ኮትዲቯርን በረታችበት የመክፈቻ ጨዋታ ከተጀመረ በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምድቡ የመክፈቻ ጨዋታውን ከዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ አድርጓል፡፡ ቀጣዩ ዘገባ በስታድ ሁዬ የተደረገውን ፍልሚያ ይዳስሳል፡፡

የምድብ ሁለት ተፎካካሪዎቹ የምድቡ ጨዋታቸውን የጀመሩት በሚከተሉት አሰላለፎች ነበር፡-

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን  (4-2-3-1)

ግብ ጠባቂ፡- አቤል ማሞ

ተከላካዮች፡- ስዩም ተስፋዬ ፣ አስቻለው ታመነ፣ አንተነህ ተስፋዬ እና ተካልኝ ደጀኔ

አማካዮች፡- ጋቶች ፓኖም፣ ተስፋዬ አለባቸው

ኤልያስ ማሞ፣ በኃይሉ አሰፋ እና ራምኬል ሎክ

አጥቂ፡- ታፈሰ ተስፋዬ

ዋና አሰልጣኝ፡- ዮሐንስ ሳህሌ       

ዲ.ሪ ኮንጎ ብሔራዊ ቡድን  (4-4-2)

ግብ ጠባቂ፡- ማታምፒ ሌይቩሚ

ተከላካዮች፡- ባኦሜቱ ጁኒየር፣ ኪምዋኪ ጆኤል፣ ቦምፑንጋ ፓዶ እና ሎማሊሳ ጆይሴ

አማካዮች፡- ቦካዲ ቦፔ፣ ሜሻክ ኤልያ፣ ሉቩምቡ ንዚንጋ እና ሙንጋንጋ ኔልሰን

አጥቂዎች፡- ምፓንጊ ጆናታን እና ሉሳዲሱ ጋይ

ዋና አሰልጣኝ፡-  ፍሎሮ ኢምቤንጌ

በሴኔጋላዊው አርቢትር ማላንጋ ዲዬዲዮ ፊሽካ የተጀመረው ጨዋታ በዲ.ሪ.ኮንጎ የበላይነት ስር ወደቀው ገና ከመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች አንስቶ ነበር፡፡ በአራተኛው ደቂቃ ሉቩምቡ በእራሳቸው የግራ መስመር ስዩም ተስፋዬን አልፎ ሄዶ ያሻገረው ጥሩ ኳስ ለጥቂት ሲወጣ፣ በ10 እና 12ኛው ደቂቃዎች ላይ አስቻለው ታመነ በተከታታይ በምፓንጊ እና ሉቩምቡ ላይ በፍፁም ቅጣት ክልል መግቢያው ላይ ጥፋቶችን ፈፅሞ የተገኙትን የቅጣት ምት አጋጣሚዎች የመጀመሪያውን ሉቩምቡ እንዲሁም ሁለተኛውን ሉሳዲሱ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል – የሁለቱም ሙከራዎች ለጥቂት በአግዳሚው ላይ ወጥተዋል፡፡ አስቻለው ለሁለተኛው ጥፋቱ የማስጠንቀቂያ ካርድ ተመልክቷል፡፡ ዋልያዎቹ የመጀመሪያ የጎል ሙከራቸውን ያደረጉት በ24ኛው ደቂቃ ራምኬል ሎክ ከቀኝ በኩል ከጠበበ ማእዘን ወደ ጎል መትቶ በግብ ጠባቂው በቀላሉ በተያዘበት ጊዜ ነበር፡፡ ራምኬል ኳሱን ለሌሎች ተጨዋቾች ቢያሻግር የተሻለ ይመስል ነበር፡፡ በ33ኛው ደቂቃ ተስፋዬ አለባቸው በግዴለሽነት የተነጠቀውን ኳስ ኮንጎዎች ወደ ጎል ሞክረውት አቤል እንደምንም ካዳነው በኋላ የመለሰውን ኳስም ሞክረውት ወደ ውጪ ወጥቶባቸዋል፡፡ በ42ኛው ደቂቃ ሎማሊሳ ከግራ መስመር በመሬት ያሻገረውን ኳስ ጎሉ ስር የነበረው ምፓንጊ አምልጦት ተካልኝ ደጀኔ አውጥቶታል፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ የኮንጓዊያኑ ጫና ፍሬ-አልባ አልሆነም፡፡ ዋልያዎቹ ተደጋጋሚውን ጥቃት ተቋቁመው ለእረፍት ሊወጡ እንደሆነ በሚገመትበት ሰዓት – በ44ኛው ደቂቃ – በጥሩ ቅብብል ተዘጋጅቶ ሉቩምቡ ከቀኝ በኩል ያሻገረውን ኳስ ሉሳዲሱ ከኢትዮጵያ ተከላካዮች በላይ ዘልሎ በጭንቅላቱ በመግጨት ኮንጓዊያኑን መሪ ያደረገ ጎል አስቆጥሯል፡፡ በ1ለ0 ውጤትም ለእረፍት ወጥተዋል፡፡ ዋልያዎቹ ለሁለተኛው ግማሽ የተመለሱት በበኃይሉ አሰፋ ምትክ ታደለ መንገሻን ቀይረው በማስገባት ቢሆንም ቅያሬው የሚያመጣውን ለውጥ ከመመልከታችን በፊት ኮንጓዊያኑ ገና እንደተጀመረ ከርቀት ድንቅ ሙከራ አድርገው ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ በአስደናቂ ሁኔታ ሲመልሰው ወዲያውኑም ሎማሊሳ ከግራ በኩል ያሻገረውን ኳስ ሉቩምቡ በጭንቅላቱ ገጭቶ በማስቆጠር የኮንጎን መሪነት አስፍቷል፡፡ የመጀመሪያው የቻን ውድድር ሻምፒዮኖቹ ጫና ሳያበቃ በ55ኛው ደቂቃ በጥሩ ፍሰት የመጣውን ኳስ አሁንም ሎማሊሳ ከግራ በኩል በመሬት ወደ ጎል አሻግሮት ምፓንጊ ሳያኘው ቢቀርም ከኋላ የመጣው ሜሻክ በቀላሉ ጎል አድርጎት ጨዋታው በጊዜ እንዲጠናቀቅ አድርጓል፡፡ ዋልያዎቹ ከዚያ በኋላ አስራት መገርሳን እና ሳምሶን ጥላሁንን እጅግ ደካማ በነበሩት ተስፋዬ አለባቸው እና ጋቶች ፓኖም ምትክ ቢያስገቡም ኳሱን በተሻለ ከመቆጣጠር ውጪ የተለየ ነገር መፍጠር ሳይችሉ በ3ለ0 ውጤት ጨዋታው ተጠናቋል፡፡ ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ተጋጣሚያቸው በሁሉ ረገድ ከእሳቸው ቡድን የተሻለ ስለነበር ማሸነፍ እንደሚገባው አምነዋል፡፡ አሰልጣኝ ዮሐንስ ተጨዋቾቻቸው ለተጋጣሚያቸው ከተገቢው በላይ ክብር ስለሰጡ ይዘውት የገቡትን የ4-2-3-1 ሲስተም መተግበር እንዳልቻሉም ተናግረዋል፡፡

ዋልያዎቹ ሲመዘኑ

ግብ ጠባቂ

አቤል ማሞ፡- አቤል ለጎሎቹ ዋነኛ ተጠያቂ ባይሆንም በዋልያዎቹ ማልያ ፈታኙን ቀን አሳልፏል፡፡ ግብ ጠባቂው ተከላካዮችን የመምራት ብቃቱ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነበር፡፡

ተከላካዮች   

ስዩም ተስፋዬ፡- የቡድኑ አምበል ፍፁም መጥፎ ቀን አሳልፏል፡፡ ሁለተኛው እና ሶስተኛው ጎሎች የተቆጠሩት ከእሱ መስመር በተሻገሩ ኳሶች ነበር፡፡

አስቻለው ታመነ፡- አስቻለው የኮንጓዊያኑን ጉልበት እና የአየር ላይ ብቃት ለመቋቋም ተቸግሮ ነበር፡፡

አንተነህ ተስፋዬ፡- አንተነህም እንደ መሀል ተከላካይ አጣማሪው እጅግ ተቸግሮ ውሏል፡፡ ከአማካዮቹ በተለይም ከተከላካይ አማካዮቹ ምንም እርዳታ አለማግኘታቸው ግን ከግምት ሊገባ ይገባል፡፡

ተካልኝ ደጀኔ፡- ተካልኝ እንደ-ክለብ ጓደኛው ስዩም በኮንጎ የመስመር አማካዮች እና ተከላካዮች ሲሰቃይ ውሏል፡፡

አማካዮች

ጋቶች ፓኖም፡- ግዙፉ አማካይ፣ ተከላካዮቹን ከጥቃት በመጋረድም ሆነ ኳስ በማሰራጨቱ ረገዶች ደካማ ነበር፡፡

ተስፋዬ አለባቸው፡- ከዓመታት በኋላ ወደብሔራዊ ቡድኑ የተመለሰው ተስፋዬም ሊያስታውሰው የማይፈልግ በጣም መጥፎ ቀን አሳልፏል፤ እሱም እንደ ጋቶች በምንም ረገድ ጥሩ አልነበረም ፡፡

ኤልያስ ማሞ፡- ከአማካይ አጋሮቹ እርዳታ ያላገኘው ኤልያስ የሚታወቅበትን ፈጠራ ማበርከት አልቻለም፡፡

በኃይሉ አሰፋ፡- ከእረፍት መልስ ወደ ሜዳ ያልተመለሰው በኃይሉ ሜዳ ውስጥ ስለመኖሩም ማወቅ ያስቸግር ነበር፡፡

ራምኬል ሎክ፡- ራምኬል ብዙ ከመሮጡ በቀር በማጥቃቱም ሆነ የመስመር ተከላካዮቹን በመርዳት ረገድ ጥሩ አልነበረም፡፡

አጥቂ

ታፈሰ ተስፋዬ፡- ከአማካዮቹ ምንም እገዛ ያላገኘው አንጋፋው አጥቂ ከተቀረው ቡድን ተነጥሎ እና ተመልካች ሆኖ ውሏል፡፡

ተቀይረው የገቡ

ታደለ መንገሻ፡- ሜዳውን ከመርገጡ ሁለተኛው ጎል የተቆጠረበት ታደለ ቡድኑ ኳሱን እንዲይዝ ለመርዳት ቢጥርም እምብዛም ስኬታማ አልነበረም፡፡

አስራት መገርሳ፡- የቀድሞው የዋልያዎቹ ቁልፍ አማካይ ቡድኑ በተሻለ ኳሱን መቆጣጠር እና ወደፊት መሄድ እንዲችል ቢያደርግም ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ በመግባቱ ተፅዕኖው ሊታይ አልቻለም፡፡

ሳምሶን ጥላሁን፡- ለመመዘን የሚያበቃ የጨዋታ ጊዜ አልነበረውም፡፡

ዋና አሰልጣኝ፡- ዮሐንስ ሳህሌ፡- በዲ.ሪ ኮንጎ የተረታው ቡድን በሁሉ ረገድ ደካማ ነበር፡፡ አሰልጣኙ በሰጡት አስተያየት የቀረፁትን ስትርቴጂ ተጨዋቾቻቸው እንዳልተገበሩ ቢገልፁም የቡድኑ ችግሮች ከዚህም ያለፉ፣ በልምምድ ሜዳ መቀረፍ የነበረባቸው፣ መሰረታዊ እና በቅርቡም ሊስተካከሉ የሚችሉ የማይመስሉ ነበሩ፡፡

ተጨማሪ ነጥቦች

  • ዋልያዎቹ ከሚገኙበት ምድብ ካሜሩን አንጎላን 1ለ0 ረትታለች፡፡ በዚህ መሰረት ዲ.ሪ.ኮንጎ እና ካሜሩን በሶስት ነጥቦች በጎል ክፍያ ተበላልጠው ሲመሩ፣ አንጎላ እና ኢትዮጵያ በዜሮ ነጥብ በጎል እዳ ተቀዳድመው ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡
  • የምድቡ ቀጣይ ጨዋታዎች በቀጣይ ሐሙስ ይደረጋሉ፡፡ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ዲ.ሪ.ኮንጎ ከአንጎላ ሲጫወቱ ምሽት አንድ ሰዓት ላይ ዋልያዎቹ ከካሜሩን ጋር ይፋለማሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.