ዋልያዎቹ በመከራ የሴካፋ ሩብ ፍፃሜን ተቀላቅለዋል

Waliya vs Congo

የዋልያዎቹ አቋም ደጋፊዎችን አስከፍቷል

  • የደቡብ ሱዳን ብቃት አነጋጋሪ ሆኗል
  • አስገራሚ ውጤቶች እየተመዘገቡ ናቸው
  • የሀዋሳ ድባብ አዘጋጆቹን እና ስፖንሰሮችን አስደስቷል

በደቡብ አፍሪካው ግዙፍ የቴሌቪዥን ኔትዎርክ ዲኤስቲቪ የስያሜ ስፖንሰርነት ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በአዲስ አበባ፣ ባህርዳር እና ሀዋሳ ስታዲየሞች እየተካሄደ የሚገኘው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሀገራት ዓመታዊ የእግር ኳስ ውድድር (ሴካፋ ቻሌንጅ ካፕ) የምድብ ማጣሪያውን አገባዶ ለሩብ ፍፃሜው ደርሷል፡፡ ቀጣዩ ፅሁፍ የምድብ ማጣያውን ጉዞ ለመዳሰስ ይሞክራል፡፡

 

  • የዋልያዎቹ ደካማ አቋም እና የማለፍ ትግል

 

ከትንሽዋ ርዋንዳ፣ በቅርብ ጊዜያት አቋሟ እያሽቆለቆለ ከምትገኘው ታንዛኒያ እና ለአስርተ ዓመታት መረጋጋት ከራቃት ሶማሊያ ጋር ከተደለደለች በኋላ በቀላሉ ከምድቧ እንደምታልፍ ግምት ተሰጥቷት የነበረችው አዘጋጇ ኢትዮጵያ በምድብ ማጣሪያው እጅጉን ተቸግራ በምርጥ ሶስተኛነት ለማለፍ እንኳን በባከነ ሰዓት በራስ ላይ የተቆጠረ ጎል አስፈልጓት በመጨረሻ ሩብ ፍፃሜውን ተቀላቅላለች፡፡ በመክፈቻው እለት በአዲስ አበባ ስታዲየም በርዋንዳ የ1ለ0 ሽንፈት ያስተናገደው የአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ቡድን፣ በሁለተኛ ጨዋታው አሰልጣኙ ‹‹የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ አስመስሎት ነበር›› ያሉትን የሶማሊያ ቡድንን እጅግ ታግሎ በመሐመድ ናስር እና በኃይሉ ግርማ የጭንቅላት ጎሎች ከረታ በኋላ በመጨረሻ ጨዋታው ከታንዛኒያ ጋር 1ለ1 ተለያይቶ በምርጥ ሶስተኛነት ሩብ ፍፃሜውን ከተቀላቀሉ ሁለት ቡድኖች አንዱ መሆን ችሏል፡፡ ቡድኑ ይህንንም አጋጣሚ ያገኘው በታንዛኒያ አቻው ሲ’መራ ከቆየ በኋላ በ92ኛው ደቂቃ አስቻለው ግርማ አሻግሮ የታንዛኒያው የመሀል ተከላካይ ሳሊም ምቦንዴ ራሱ ጎል ላይ በማስቆጠሩ ነበር፡፡ ይህቺ የዋልያዎቹን የሴካፋ ቆይታ ያራዘመች ጎል በሀዋሳ ስታዲየም የታደሙትንም ሆነ በቴሌቪዥን ሲመለከቱ የነበሩ የቡድኑ ደጋፊዎችን ብታስደስትም እና እፎይታ ብትሰጥም ብሔራዊ ቡድኑ በውድድሩ ላይ እያሳየ ባለው አቋም በርካቶች ደስተኛ አይደሉም፡፡ ቡድኑ ጎሎች ለማስቆጠርም ሆነ የጎል እድሎች ለመፍጠር እጅጉን እንደሚቸገር፣ የተዋሀደ እና የተቀናጀ እንቅስቃሴ ማሳየት እንደተሳነው እና በደጋፊው ፊት እንደሚጫወት ቡድንም ፍላጎት እና ተነሳሽነት እንደማይታይበት ብዙዎች ይተቻሉ፡፡ አሰልጣኙ ግን ከየጨዋታዎቹ በኋላ በሰጧቸው ቃለ-መጠይቆች ላይ ለአዳዲስ ወጣቶች እድል ለመስጠት እየጣሩ እንደሚገኙ፣ ቡድናቸው ከፍተኛ የጨዋታ መደራረብ ስለገጠመው ድካም እንዳለበት እና የቡድኑ ደካማ እንቅስቃሴ የፕሪምየር ሊጉ ነፀብራቅ እንደሆነ ለደካማ የቡድኑ አቋም ምክንያቶችን ሰጥተዋል፡፡ ከዚህ ምድብ ርዋንዳን እና ሶማሊያን ረትቶ ከኢትዮጵያ ጋር አቻ የተለያየው የታንዛኒያ ብሔራዊ ቡድን በአንደኛነት እንዲሁም የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ብሔራዊ ቡድኖችን አሸንፎ በታንዛኒያ የተረታው እና ውድድሩን ለቻን መዘጋጃነት እንደሚጠቀምበት አስቀድሞ የገለፀው የርዋንዳ ብሔራዊ ቡድን በሁለተኛነት ለሩብ ፍፃሜው በቅተዋል፡፡

 

  • ኃያላኑን ያፋለመው ምድብ

 

የምስራቅ አፍሪካ ኃያላኑ ኡጋንዳ እና ኬኒያ በምድብ ማጣሪያው ያገናኘው ምድብ ከፍተኛ የማለፍ ፉክክር ተደርጎበታል፡፡ ሁለቱ የውድድሩ ነገስታት እና ባላንጦች በአዲስ አበባ ስታዲየም ባደረጉት የምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታ ኬኒያዊያኑ 2ለ0 በማሸነፍ ያለፈውን ውድድር የፍፃሜ ድላቸውን ደግመውታል፡፡ ነገር ግን ሀራምቤዎቹ በዚህ ብቃታቸው ለመቀጠል ተቸግረው ከቡሩንዲ ጋር አቻ በመለያየት እና ፍፁም ባልተጠበቀ መንገድ በዛንዚባር 3ለ1 በመረታት የማለፍ ተስፋቸው ትልቅ ስጋት ውስጥ ገብቶ ነበር – የቡሩንዲ በኡጋንዳ መረታት በመጨረሻ አተረፋቸው እንጂ፡፡ በሴሬዲዬቪች ሚሉቲን ሚቾ የሚሰለጥኑት ኡጋንዳዊያኑ በበኩላቸው ከመጀመሪያ ሽንፈታቸው አገግመው ዛንዚባር እና ቡሩንዲን በመርታት በአንደኛነት ኬኒያን አስከትለው ወደሩብ ፍፃሜው አልፈዋል፡፡

 

  • የደቡብ ሱዳን አስደናቂ አቋም

 

የዚህ ውድድር አስደናቂ ክስተት ያለምንም ጥርጥር የደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ቡድን ነው፡፡ ነፃ ሀገር ከሆኑ በኋላ እግር ኳስን በመጫወት አምስት ዓመታት እንኳን ያልሞላቸው ‹ብሩህ ከዋክብቱ› በሶስተኛ የሴካፋ ውድድራቸው (በ2012 እና 2013 ተሳትፈዋል) የመጀመሪያ ድላቸውን በጂቡቲ ላይ አስመዝግበዋል፤ ይህም አልበቃ ብሏቸው የደቡብ አፍሪካዋን ተጋባዥ ማላዊንም ፍፁም ባልተጠበቀ ሁኔታ ረትተዋል፤ ከቀድሞ እናታቸው ሱዳን ጋርም አቻ ተለያይተዋል፡፡ ያለፉትን ዓመታት በጦርነት እና ባለመረጋጋት ውስጥ ያሳለፉት እና በእግር ኳስ ሜዳ ላይ ግን አስደናቂ መሻሻል እያሳዩ የሚገኙት ደቡብ ሱዳናዊያኑ ከምድባቸው በቀዳሚነት ከማለፋቸው ባሻገር በድንገት የውድድሩ ተጠባቂ ቡድን መሆንም ጀምረዋል፡፡ በዚህ ምድብ የሱዳን እና የጂቡቲ አቻዎቹን የረታው እና በደቡብ ሱዳን የተሸነፈው የማላዊ ቡድን በሁለተኛነት ሲያልፍ፣ ጂቡቲን ረትቶ ከደቡብ ሱዳን አቻ የተለያየው የሱዳን ብሔራዊ ቡድን ከአዘጋጇ ኢትዮጵያ ጋር በምርጥ ሶስተኛነት ሩብ ፍፃሜውን መቀላቀል ችሏል፡፡

የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች

የዲኤስቲቪ ሴካፋ ቻሌንጅ ዋንጫ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ወደ አዲስ አበባ የተመለሱ ሲሆን ሰኞ እና ማክሰኞ በአዲስ አበባ ስታዲየም የሩብ ፍፃሜ ፍልሚያዎቹ እንደሚካሄዱ አዘጋጁ ፕሮግራም አውጥቷል፡፡ በዚህ መሰረት ሰኞ የምድብ ሁለት አሸናፊዋ ኡጋንዳ ከምድብ ሶስት ሁለተኛ ማላዊ ስትጫወት በአንድ ምድብ የነበሩት ታንዛኒያ እና አዘጋጇ ኢትዮጵያ በሚያስገርም አኳኋን ከ48 ሰዓታት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ይፋለማሉ፡፡ ማክሰኞ እንዲሁ በተመሳሳይ በአንድ ምድብ ውስጥ የነበሩት ሁለቱ ሱዳኖች ዳግመኛ ሲገናኙ ከየምድባቸው ሁለተኛ ሆነው ያጠናቀቁት ርዋንዳ እና ኬኒያም ይጫወታሉ፡፡

2 thoughts on “ዋልያዎቹ በመከራ የሴካፋ ሩብ ፍፃሜን ተቀላቅለዋል

Leave a Reply

Your email address will not be published.