ዋልያዎቹ በሌሎች ላይ የተመሰረተ የመጨረሻ እድላቸውን ይሞክራሉ

Ethiopia-celebrate-300

በ2017 በጋቦን ለሚካሄደው 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሲደረገ የቆየው የማጣሪያ ጉዞ በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ይጠናቀቃል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫው ላይ የሚሳተፉት ሀገራትም በጠቅላላ ተለይተው ይታወቃሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሌሎች ምድቦች ጨዋታዎች ውጤቶች ላይ የተመሰረተ የማለፍ እና ያለማለፍ እጣፈንታም ይወሰናል፡፡ ዋልያዎቹ የሌሎችን ውጤት ከመጠበቃቸው በፊት ግን የራሳቸውን ጨዋታ በድል ማጠናቀቅ ግድ ይላቸዋል፡፡ ቀጣዩ ፅሁፍም የኢትዮጵያ ቡድን በሜዳው ሲሼልስን የሚገጥምበትን የምድብ የመጨረሻ ጨዋታ ይዳስሳል፡፡

የዋሊያዎቹ የሰሞኑ ጉዳዮች

የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን በመጨረሻ ጨዋታው በአዲስ አሰልጣኙ ገብረመድህን ኀይሌ እየተመራ ከሜዳው ውጪ ሌሶቶን መርታቱ ይታወሳል፡፡ በማሴሩ የተደረገው ጨዋታ በተለይም የመጀመሪያው አጋማሽ የዋልያዎቹ የእንቅስቃሴ የበላይነት የታየበት ብቻ ሳይሆን የጌታነህ ከበደ ጎሎች የቡድኑን የማለፍ እድል በትንሹም ቢሆን ነፍስ ሲዘሩበት የታየበት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በመጠናቀቁ እና ተጨዋቾች ወደቤታቸው በመላካቸው የተነሳ አሰልጣኙ ለሚፈልጓቸው ተጨዋቾች ጥሪ በማድረግ ከውጪ ከተጠሩት ጥቂት ተጨዋቾች በቀር ላለፈው አንድ ወር ቡድኑ በሀዋሳ ሴንትራል ሆቴል በማረፍ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ባለፉት ቀናት ደግሞ ከውጪ የተጠሩት ሽመልስ በቀለ፣ ጌታነህ ከበደ እና ዋሊድ አታ ተቀላቅለውት ቡድኑ በተሟላ ሁኔታ ዝግጅቱን አድርጓል፡፡ ምናልባት እንደ ችግር መነሳት ያለበት አሁንም ቡድኑ የወዳጅነት የአቋም መለኪያ ጨዋታ ማግኘት አለመቻሉ ነው፡፡ አሰልጣኝ ገብረመድህን የማለፍ እድላቸው ጠባብ እና በሌሎች ላይ የተመሰረተ ቢሆንም ጥሩ ለመጫወት እና ለማሸነፍ ወደሜዳ እንደሚገቡ ገልፀዋል፡፡

የማይኖሩ ተጨዋቾች

ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ በእጁ ላይ በደረሰበት ጉዳት ከጨዋታው ውጪ ሲሆን የመስመር ተከላካዩ አህመድ ረሺድም በደረሰበት ጉዳት ለጨዋታው መድረሱ ያጠራጥራል፡፡

ለሲሼልስ ጨዋታ የተያዙ የዋልያዎቹ ተጨዋቾች፡-

ግብ ጠባቂዎች

ጀማል ጣሰው (መከላከያ)፣ ሳምሶን አሰፋ (ድሬዳዋ ከተማ)፣ ተክለማሪያም ሻንቆ (አዲስ አበባ ከተማ)

ተከላካዮች

አንተነህ ተስፋዬ (ሲዳማ ቡና)፣ አብዱልከሪም መሀመድ እና አህመድ ረሺድ (ኢትዮጵያ ቡና)፣

ስዩም ተስፋዬ (ደደቢት)፣ ሙጂብ ቃሲም (አዳማ ከተማ)፣ ዋሊድ አታ (ኦስተርሰንድ/ ስዊድን)

መሐሪ መና (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ አዲሱ ተስፋዬ (መከላከያ) እና ቴዎድሮስ በቀለ (መከላከያ)

 

አማካዮች

ተስፋዬ አለባቸው እና በኃይሉ አሰፋ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ጋቶች ፓኖም እና ኤልያስ ማሞ (ኢትዮጵያ ቡና)

ሽመክት ጉግሳ እና ኤፍሬም አሻሞ (ደደቢት)፣ አስራት መገርሳ (ዳሸን ቢራ)፣

ሽመልስ በቀለ (ፔትሮ ጄት/ ግብፅ)፣ ታደለ መንገሻ እና እንዳለ ከበደ (አርባምንጭ ከተማ)

አጥቂዎች

ሰልሀዲን ሰዒድ፡- (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ጌታነህ ከበደ (ቢድ-ቬትስ ዊትስ / ደቡብ አፍሪካ)

ታፈሰ ተስፋዬ (አዳማ ከተማ)፣ ዳዊት ፍቃዱ፡- (ደደቢት) እና አዲስ ግደይ (ሲዳማ ቡና)

ዋና አሰልጣኝ፡- ገብረ መድህን ኃይሌ

ግምታዊ አሰላለፍ (4-4-2)

ግብ ጠባቂ፡- ጀማል ጣሰው

ተከላካዮች፡- ስዩም ተስፋዬ፣ ዋሊድ አታ፣ ሙጂብ ቃሲም እና አብዱልከሪም መሀመድ

አማካዮች፡- ጋቶች ፓኖም፣ ተስፋዬ አለባቸው፣ ሽመክት ጉግሳ እና ሽመልስ በቀለ

አጥቂዎች፡- ጌታነህ ከበደ እና ሰልሀዲን ሰዒድ

ትንሽ ስለ ሲሼልስ

ሲሼልስ በደቡብ ምስራቅ አፍሪካ በኩል በህንድ ውቅያኖስ ላይ የሚገኙ 115 ጥቃቅን ደሴቶች የመሰረቷት ሚጢጢዬ ሀገር ናት፡፡ በህዝብ ብዛትም የ90.000 ህዝብ ብቻ ነዋሪ በመሆን በአፍሪካ በህዝብ ብዛት የመጨረሻዋ ሀገር ናት፡፡ የውቧ ሲሼልስ ዋና ከተማ ቪክቶሪያ ስትሆን እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ እና ሴሼሎስ ክሪኦል ዋነኛ መግባቢያ ቋንቋዎች ናቸው፡፡

የዋልያዎቹ የቅዳሜ ተጋጣሚ የሲሼልስ ብሔራዊ ቡድን በየትኛውም ዓይነት ትልልቅ ውድድር ተሳትፎ የማያውቅ ከአህጉሪቱ እጅግ ደካማ የእግር ኳስ ሀገራት አንዱ ነው፡፡ ሽፍቶቹ በሚል ቅፅል መጠሪያ የሚታወቀው ቡድን በቅርቡ ባደረጋቸው የወዳጅነት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች በዚምቧቡዌ 5ለ0 እና በስዋዚላንድ 4ለ0 መረታቱ ያለበትን ደረጃ በገሀድ የሚያሳይ ነው፡፡ የዚህ ወር የፊፋ ወርሀዊ ደረጃውም 183ኛ ነው፡፡

የጨዋታው አርቢትሮች

በአዲሱ የሀዋሳ ስታዲየም የሚካሄደውን ጨዋታ የሚመሩት አርቢትሮች ከዩጋንዳ ይሆናሉ፡፡ ብራየን ንሱቡጋ ሚሮ በዋና አርቢትርነት ሲመሩ፣ ሁሴን ቡጋምቤ እና ማርክ ሶንኮ ረዳቶቻቸው ናቸው፡፡

የማለፍ ሁኔታ

አልጄሪያ 13 ነጥቦችን ይዛ አንድ ጨዋታ እየቀራት ከምድቡ በአንደኛነት ማለፏን አረጋግጣለች፡፡ በስምንት ነጥቦች ሁለተኛ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡደን እድል በየምድቦቻቸው ሁለተኛ ሆነው ከሚጨርሱት ቡድኖች መካከል የተሻለ ነጥብ እና ጎል ከሚኖራቸው ሁለት ምርጦች አንዱ መሆን ብቻ ነው፡፡ ዋልያዎቹ በየምድቦቻቸው ሁለተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ቡድኖች ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ ቤኒን (11 ነጥቦች እና 5 ጎሎች)፣ ቱኒዚያ (10 ነጥቦች እና 10 ጎሎች)፣ ዩጋንድ (10 ነጥቦች እና 3 ጎሎች)፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ (10 ነጥቦች እና 1 ጎል)፣ ኬፕ ቬርዴ (9 ነጥቦች እና 5 ጎሎች) እንዲሁም ስዋዚላንድ (8 ነጥቦች እና 2 የጎል እዳ) በመያዝ ከዋልያዎቹ ቀድመው ተቀምጠዋል፡፡ ኢትዮጵያ 8 ነጥቦች እና 4 የጎል እዳ አላት፡፡ ስለዚህ ዋልያዎቹ ወደጋቦኑ የአፍሪካ ዋንጫ ለመጓዝ ከራሳቸው ድል በተጨማሪ የተጠቀሱት ቡድኖች ነጥብ መጣል ያስፈልጋቸዋል፡፡ የነዚህን ሀገራት ጨዋታዎች ካስፈለጉም የሚከተሉት ናቸው፡፡ ቀዳሚዋ ቤኒን ከሜዳዋ ውጪ ከማሊ ትጫወታለች፡፡ ቱኒዚያ ላይቤሪያን እንዲሁም ዩጋንዳ ኮሞሮስን በሜዳዎቻቸው ያስተናግዳሉ፡፡ ኬፕቬርዴም በሜዳዋ ሊቢያን ስትገጥም፣ ስዋዚላንድ ከሜዳዋ ውጪ ከማላዊ ትጫወታለች፡፡

  • የኢትዮጵያ እና ሲሼልስ ጨዋታ ቅዳሜ በ10 ሰዓት በሀዋሳ ስታዲየም ይካሄዳል፡፡

የትጥቅ ስፖንሰር ጉዳይ

ዋልያዎቹ ከሜዳ ውጪ በታሪካቸው አዲስ ክስተት ገጥሟቸዋል፡፡ ይህም ኦፊሴላዊ የትጥቅ ስፖንሰር ማግኘታቸው ነው፡፡ ስፖንሰሩ Errea የተሰኘው የጣልያን የትጥቅ አምራች ድርጅት ነው፡፡ በስምምነቱ መሰረት ኩባንው ለቀጣዩ አራት ዓመታት ለዋልያዎቹ ብቻ ሳይሆን ለሉሲዎቹ እንዲሁም ለ20 ዓመት እና ለ17 ዓመት ቡድኖቹም ትጥቅ ያቀርባል፡፡ ኩባንያው በየዓመቱ 90 ሺ ዩሮ ዋጋ ያለው ቁሳቁስ ለብሔራዊ ቡድኖቹ ሲያቀርብ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቅናሽ ተደርጎለት 50 ሺ ዩሮ ዋጋ የሚያወጡ ቁሶችን እንዲገዛ ይጠበቃል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.