ዋልያዎቹ ሽንፈታቸውን በመቀልበስ የቻን ተሳታፊነታቸውን አረጋግጠዋል

ETH vs Bur

ETH vs Burየማለፍ የጠበበ እድል ይዞ ወደሜዳ የገባው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተጋጣሚው ላይ አስደናቂ ድል በማስመዝገብ እና የደርሶ መልስ ፍልሚያውን በድል በመወጣት በሀገር ውስጥ ሊጎች የሚጫወቱ ተጨዋቾችን ለሚያሳትፈው አህጉራዊው የቻን ውድድር ማለፉን አረጋግጧል፡፡ ቀጣዩ ዘገባ ዋልያዎቹ በቡሩንዲ አቻቸው ላይ ድል ያስመዘገቡበትን ጨዋታ ይቃኛል፡፡

ሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ለዚህ የ2016 ቻን የመጨረሻ ማጣሪያ የደረሱት በቀጠናቸው የመጀመሪያ ማጣሪያ ዋልያዎቹ ኬኒያን እና ቡሩንዲዎች ጂቡቲን በደርሶ መልስ ጨዋታዎች ከረቱ በኋላ ነበር፡፡ ሁለቱ ቡድኖች ለተከታታይ ጊዜ በቻን ውድድር ላይ ለመገኘት የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ባለፈው ሳምንት በቡጁምቡራ ባደረጉ ጊዜ ቡሩንዲዎቹ በመጀመሪያው እና በመጨረሻው ደቂቃ ባስቆጠሯቸው ጎሎች 2ለ0 አሸንፈው ነበር፡፡ በጨዋታው ወቅት በስታዲየሙ ዙሪያ ጦር መሳሪያዎቹን ያነገቡ ወታደሮች መታየታቸው እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላት ላይ የተፈጠረው ያለመረጋጋት ስሜት፣ የኤፍሬም አሻሞ አወዛጋቢ የቀይ ካርድ፣ የአሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ እና የቡሩንዲው አሰልጣኝ አህቼን ኤት-አብደልማሌክ ግጭት እና የአልጄሪያዊው የቡሩንዲ አሰልጣኝ ከመቀመጫቸው መሰናበት እንዲሁም በድህረ-ጨዋታ ፕሬስ ኮንፈረንስ ላይ አብደልማሌክ ዮሐንስ ተጨዋቻቸውን እንዳስፈራሩባቸው መክሰሳቸው አነጋጋሪ ጉዳዮች ነበሩ፡፡ የዳዊት ፍቃዱን መጎዳት፣ የኤፍሬምን መቀጣት፣ የግራ ተከላካይ ስፍራውን መሳሳት እና የፈጣሪ አማካይ እጥረትን ከግምት ያስገቡት አሰልጣኝ ዮሐንስ በእነዚህ ስፍራዎች የመከላከያዎቹን መሀመድ ናስር፣ ፍሬው ሰሎሞን እና ነጂብ ሳኒ እንዲሁም የኢትዮጵያ ቡናውን ኤልያስ ማሞን መርጠው ሲዘጋጁ ሰንብተዋል፡፡

ለእሁዱ የመልስ ጨዋታ ቡድኖቹ ወደ ሜዳ ሲገቡ የመጀመሪያ ተሰላፊዎቻቸው የሚከተሉት ነበሩ፡-

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን  (4-1-3-2)

ግብ ጠባቂ፡- ታሪክ ጌትነት

ተከላካዮች፡- ስዩም ተስፋዬ ፣ ሰልሀዲን ባርጊቾ፣ አስቻለው ታመነ እና ነጂብ ሳኒ

አማካዮች፡- ጋቶች ፓኖም፣

ኤልያስ ማሞ፣ አስቻለው ግርማ እና በረከት ይስሀቅ

አጥቂዎች፡- ራምኬል ሎክ እና መሀመድ ናስር

ተጠባባቂዎች፡- አቤል ማሞ፣ አንተነህ ተስፋዬ፣ ብሩክ ቃልቦሬ፣ ሙሉዓለም መስፍን፣ ፍሬው ሰሎሞን፣ ቢኒያም በላይ እና ምንይሉ ወንድሙ

ዋና አሰልጣኝ፡- ዮሐንስ ሳህሌ       

 

ቡሩንዲ ብሔራዊ ቡድን  (4-4-2)

ግብ ጠባቂ፡- ማክ አርተር

ተከላካዮች፡- ረሺድ፣ ኢሳ፣ ዴቪድ እና ኪዛ

አማካዮች፡- ፒስተስ፣ ጋኤል፣ ዦን ክሎድ እና ሃኪዚማን ቪያኒ

አጥቂዎች፡- መህዲ እና ነሂማና ሻሲሪ

ዋና አሰልጣኝ፡-  አህቼን ኤት-አብደልማሌክ

በግብፃዊያን አርቢትሮች እየተመራ የተጀመረው ጨዋታ በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ቡድኖች እንደተለመደው ፍጥነት በተሞላበት እንቅስቃሴ ቢጀመርም የመጀመሪያው የማጥቃት ስጋት የተፈጠረው በዘጠነኛው ደቂቃ ራምኬል ሎክ ከቀኝ በኩል ተከላካዮቹን ጥሶ ከገባ በኋላ ለአስቻለው ግርማ ያቀበለውን የቡሩንዲ ተከላካዮች ተረባርበው ሲያወጡት ነበር፡፡ አስቻለው ግን ጥፋት እንደተሰራበት በመግለፅ የፍፁም ቅጣት ምት ባለመሰጠቱ ቅሬታ ሲያሰማ ነበር፡፡ ከዚያም በ11ኛው ደቂቃ ኤልያስ ማሞ ያሻገረው የቅጣት ምት ለሰልሀዲን ባርጊቾ ቢደርስም የመሀል ተከላካዩ ኳሱን አጠንክሮ ባለመግጨቱ ለግብ ጠባቂው አስረክቦታል፡፡ በ15ኛው ደቂቃ ቡሩንዲዎች በመልሶ ማጥቃት ሄደው ነሂማና ሻሲሪ በርካታ አማራጮች የነበሩት ቢሆንም በራስ ወዳድነት ራሱ ሞክሮ በታሪክ ጌትነት ተይዞበታል፡፡ የዋልያዎቹ ፈጣን ማጥቃት በመጠኑ ከቀዘቀዘ በኋላ በ29ኛው ደቂቃ በግራ በኩል ኤልያስ እና በረከት ይስሀቅ ማራኪ ቅንጅት ፈጥረው ኤልያስ ለራሱ የመምቻ ክፍተት ፈጥሮ የሞከረው ኳስ በግብ ጠባቂው ማክ አርተር ተመልሶበታል፡፡ ቡሩንዲዎቹ ይህን ኳስ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ወስደውት ዦን ክሎድ የመታውን ኳስ ታሪክ በቀላሉ ይዞታል፡፡ በ34ኛው ደቂቃ ለራምኬል የተላከን ረዥም ኳስ አጥቂው ደርሶበት ጎል ከማድረጉ በፊት የቡሩንዲ ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተውታል፡፡ በ37ኛው ደቂቃ ጋቶች ፓኖም ከሩቅ ወደ ጎል መትቶ በተከላካዮች የተመለሰውን ኳስ ራምኬል አግኝቶ ጎል ሳያደርገው ቀርቷል፡፡ 38ኛው ደቂቃ የጨዋታውን መንፈስ የቀየረ ክስተት የተፈፀመበት ነበር፡፡ ኤልያስ ያሻገረው የቅጣት ምት በስዩም ተስፋዬ በጭንቅላት ተገጭቶ አስደናቂ ጎል ሆኗል፡፡ የቅጣት ምቱም ሆነ የስዩም ጎል ጥራት የላቀ ነበር፡፡ በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች መሀል ሜዳ ላይ እጅግ እንደተበለጡ የተረዱት ቡሩንዲዎችም ከጎሉ በኋላ አንዱን አጥቂ መህዲን በማስወጣት በተከላካይ አማካይ ተክተውታል፡፡ በ42ኛው ደቂቃ የአስቻለው ግርማ ጠንካራ ምት በግብ ጠባቂው ተመልሷል፡፡ በጭማሪ ደቂቃው ሻሲሪ የመታውን የቅጣት ምት ታሪክ አውጥቶታል፡፡

ቡድኖቹ ለሁለተኛው ግማሽ ሲመለሱ ተጨዋቾች ቀይረው ነበር፡፡ ዋልያዎቹ መሀመድ ናስርን በክለብ አጋሩ ምንይሉ ወንድሙ ሲተኩ ቡሩንዲዎች ሀኪዚማ ቪያኒን አስወጥተው ሙስጠፋ ፍራንሲስን አስገብተዋል፤ ፎርሜሽናቸውንም 4-1-4-1 ወደሚመስል ቅርፅ ቀይረዋል፡፡ የሁለተኛው ግማሽ የመጀመሪያው የማጥቃት ስጋት የተፈጠረው በቡሩንዲ ነበር፡፡ ከ25 ሜትሮች ገደማ የተገኘውን የቅጣት ምት ተቀይሮ የገባው ሙስጠፋ ፍራንሲስ በቀጥታ መትቶ ታሪክ በድንቅ መንገድ ጎል ከመሆን ታድጎታል፡፡ በ53ኛው ደቂቃ ኤልያስ ያሻገረውን የቅጣት ምት ምንይሉ ወንድሙ በጭንቅላቱ ገጭቶ ለጥቂት ወጥቶበታል፡፡ በዚሁ ደቂቃ ላይ የዋልያዎቹ ደጋፊዎችን ልብ በድንጋጤ ቀጥ ሊያደረግ የደረሰ ሁነት ተፈጥሮ ነበር፡፡ የግራ ተከላካዩ ነጂብ ሳኒ ወደ ኋላ ያቀበለው ኳስ ግብ ጠባቂው ታሪክ አምልጦት ጎል ከመሆኑ በፊት ለጥቂት ደርሶበታል፡፡ በ63ኛው ደቂቃ የቡሩንዲው ግብ ጠባቂ ተጎድቶ ሲታከም ከቆየ በኋላ ሲነሳ ግብፃዊው አርቢትር ጊዜ ከማባከን ጋር በተያያዘ የማስጠንቀቂያ ካርድ አሳይተውታል፡፡ ማክ አርተር ከዚያ በኋላ ሲያነክስ ቆይቶ መቀጠል ስላልቻለ በ70ኛው ደቂቃ በቢሀ ኦማር ተተክቷል፡፡ በ73ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ምንይሉ በመሬት ያሻገረው ጥሩ ኳስ ያገኘው ሰው ሳይኖር ባክኗል፡፡ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ዋልያዎቹን በአጠቃላይ ውጤት አቻ ያደረገ ጎል ተገኘ፡፡ ጎሉ በብዙ መንገዶች ከመጀመሪያው ጎል ጋር የተመሳሰለ ነበር፡፡ አቅራቢው ኤልያስ ማሞ፤ ከቅጣት ምት የተሻገረ ኳስ፤ በጭንቅላት ተገጭቶ የተቆጠረ፡፡ ከመጀመሪያው የሚለየው አግቢው ጋቶች ፓኖም በመሆኑ ብቻ ነበር፡፡ በ77ኛው ደቂቃ ፍሬው ሰሎሞን በረከት ይስሀቅን ተክቶ ወደሜዳ ገብቷል፡፡ በ79ኛው ደቂቃ ኤልያስ ከረዥም ርቀት የመታው ኳስ በአዲሱ ግብ ጠባቂ ተመልሷል፡፡ ኤልያስ ከዚህ ሙከራው ሴኮንዶች ብቻ በኋላ በቡሩንዲ ተከላካዮች መሀል ያሾለከው ድንቅ ኳስ አስቻለው ግርማ እግር ደርሶ አስቻለው ግብ ጠባቂውን ለማለፍ ሲሞክር ስለተጠለፈ ግብፃዊው አርቢትር ምንም ሳያመነቱ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተዋል፡፡ ጋቶች ፍፁም ቅጣት ምቱን አስቆጥሮ ቡድኑን የደርሶ መልሱ ፍልሚያ መሪ አድርጓል፡፡ በአጠቃላይ ውጤት ለመጀመሪያ ጊዜ የተመሩት ቡሩንዲዎች በቀሩት ደቂቃዎች ጎል አስቆጥረው ውጤቱን ለመለወጥ መጠነኛ ጥረት ቢያደርጉም ያን ያህል አስደንጋጭ ስጋቶች መፍጠር ሳይችሉ ጨዋታው በዋልያዎቹ 3ለ0 በአጠቃላይ 3ለ2 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

 

ዋልያዎቹ ሲመዘኑ

ግብ ጠባቂ

ታሪክ ጌትነት፡-  የደደቢቱ ግብ ጠባቂ ያን ያህል ፈታኝ ሙከራዎች ባይደረጉበትም ከጊዜ ወደ ጊዜ መረጋጋቱ እየጨመረ እንደመጣ መገንዘብ ይቻላል፡፡

ተከላካዮች   

ስዩም ተስፋዬ፡- ብቸኛው የሰውነት ቢሻው ታሪካዊ ቡድን አባል የቡድኑን አይን መግለጫ ወሳኝ ጎል አስቆጥሯል፤ የቀኝ ተከላካዩ የዋልያዎቹ ዋነኛ የጎል ምንጭ መሆኑ አስገርሟል፡፡

አስቻለው ታመነ፡- ኳስ እየያዘ ወደ ፊት በመሄድ በቦታው ክፍተት እንዲፈጠር ካደረገባቸው ጥቂት አጋጣሚዎች ውጪ አስቻለው በጣም ጥሩ ጨዋታ አሳልፏል፡፡

ሰልሀዲን ባርጊቾ፡- ዳግም ወደብሔራዊ ቡድኑ የተመለሰው የመሀል ተከላካይ ከክለብ አጋሩ አስቻለው ታመነ ጋር ተስፋ ሰጪ ጥምረት ፈጥሯል፡፡

ነጂብ ሳኒ፡- ወጣቱ የግራ ተከላካይ በመጀመሪያ የብሔራዊ ቡድን ጨዋታው በመከላከሉ ረገድ እምብዛም አልተቸገረም፡፡ የመከላከያው ተጨዋች በማጥቃቱ በኩል ግን የተሻለ የነበረው በሁለተኛው ግማሽ ነበር፡፡

አማካዮች

ጋቶች ፓኖም፡- የኢትዮጵያ ቡናው የተከላካይ አማካይ የለመደውን የፍፁም ቅጣት ምት ጨምሮ ሁለት ወሳኝ ጎሎች በማስቆጠር ወሳኝ ተግባር ፈፅሟል፤ የአደራጅነት ሚናው ግን አሁንም ጥያቄ ይነሳበታል፡፡

ኤልያስ ማሞ፡- ለዚህ ጨዋታ ተመርጦ በቀጥታ የመጀመሪያ ተሰላፊ የሆነው ኤልያስ እጅግ ድንቅ ቀን አሳልፏል፡፡ የኢትዮጵያ ቡናው አማካይ ለሶስቱም ጎሎች መገኘት ምክንያት ነበር፡፡ የጨዋታው ኮከብ መሆኑ አያከራክርም፡፡

አስቻለው ግርማ፡- በቀኝ በኩል የተሰለፈው የመስመር አማካይ ሶስተኛው ጎል ለተገኘበት የፍፁም ቅጣት ምት መነሻ ቢሆንም ከዚያ በፊት በርካታ ኳሶች ይበላሹበት ነበር፡፡ የሚያቀብላቸው ኳሶችም ሆኑ ውሳኔዎቹ እንደሌላው ጊዜ ጥሩ አልነበሩም፡፡

በረከት ይስሀቅ፡- ዋልያዎቹ ሳኦ ቶሜን በረቱበት ጨዋታ ጨዋታው እንደተጀመረ በደረሰበት የጭንቅላት ግጭት ለበርካታ ደቂቃዎች በደመ-ነፍስ ሲጫወት የነበረው እና በአቋሙ የተተቸው የሀዋሳ ከነማው አጥቂ በግራ መስመር አማካይነት ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡

አጥቂዎች

ራምኬል ሎክ፡- አዲሱ የቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂ እንደ ሁልጊዜው በታታሪነት ተጋጣሚዎቹን ሲያስጨንቅ ውሏል፡፡

መሀመድ ናስር፡- በክለቡ መከላከያ ማልያ ድንቅ አቋም ላይ ይገኝ የነበረው መሀመድ በብሔራዊ ቡድኑ ማልያ ይህን መድገም ተቸግሮ ከእረፍት መልስ ወደሜዳ አልተመለሰም፡፡

ተቀይረው የገቡ

ምንይሉ ወንድሙ፡- የክለበ ጓደኛው መሀመድን ተክቶ የተጫወተው ወጣቱ አጥቂ ወደኋላ እየተመለሰ ግንባታው ላይ መሳተፉ ወደ መስመርም መውጣቱ ለተጋጣሚ ተከላካዮች የማይተነበይ አድርጎት ነበር፡፡

ፍሬው ሰሎሞን፡- ለመመዘን የሚያበቃ የጨዋታ ጊዜ አልነበረውም፡፡

ሙሉዓለም መስፍን፡- ለመመዘን የሚያበቃ የጨዋታ ጊዜ አልነበረውም፡፡

ዋና አሰልጣኝ፡- ዮሐንስ ሳህሌ       

ቡድኑ በተለይ በሁለተኛው ግማሽ የተረጋጋ እና የሚፈልገውን የሚያውቅ መስሎ ነበር፡፡ የተጨዋቾች ቅያሬዎቹ በተለይ የምንይሉ ወንድሙ መግባት ለቡድኑ ውጤት ማማር ሚና ነበራቸው፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.