ዋሊያዎቹ ለሞት-ሽረቱ ፍልሚያ አልጄሪያ ደርሰዋል

Photo credit: soka25east.com

Walias first 11 against CBE

ዋሊያዎቹ ለሞት-ሽረቱ ፍልሚያ አልጄሪያ ደርሰዋል

በ2015ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመገኘት የማጣሪያ ጨዋታዎቹን በማድረግ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አነስተኛ የማለፍ እድልን ይዞ የወቅቱን የአህጉራችንን ኃያል አልጄሪያ ለመግጠም በጣሊያን ሮም አቆራርጦ አልጄርስ ደርሷል፡፡ የማሪያኖ ባሬቶ ቡድን የአልጄርያ ጉዞውን የጀመረው ትናንት በእኩለ-ሌሊት ሲሆን በሮም ትራንዚት አድርጎ ዛሬ እኩለ-ቀን ላይ የተጋጣሚያችን ዋና ከተማ አልጄርስ ደርሷል፡፡ ዋሊያዎቹ አልጄርስ እንደደረሱ ከአልጄሪያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለስልጣናት ሞቅ ያለ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ የአልጄሪያ ዋና ዋና ሚዲያዎች ተወካዮችም በአቀባበሉ ላይ የተገኙ ሲሆን የቡድኑን ከዋክብት ተጨዋቾች እና ሌሎች አባላትም ኢንተርቪው አድርገዋቸዋል፡፡ ቡድኑ በአልጄርስ ሼራተን ሆቴል አርፎ የመጨረሻ ዝግጅቱን ያደርግና ነገ በእኛ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ በ4፡30 ከአልጄርስ 45 ኪሎ ሜትሮች ገደማ ርቃ በምትገኘው ብሊዳ ከተማ 35.000 ተመልካቾችን አስቀምጦ በሚያስተናግደው ሙስታፋ ታከር ስታዲየም ከባለሜዳዎቹ ጋር የሞት-ሽረት ፍልሚያውን ያደርጋል፡፡

የዋሊያዎቹ የሰሞኑ ጉዳዮች

በትውልደ-ህንዱ እና በዜግነተ-ፖርቹጋላዊው ጄሬኒሞ ማሪያኖ ባሬቶ እየሰለጠነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባልተለመደ መልኩ በርካታ አዳዲስ እና ወጣት ተጨዋቾችን አሰባሰቦ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ልምምዱን ሲያደርግ የሰነበተ ሲሆን በመካከልም ወደ ካምፓላ ተጉዞ በዑጋንዳ 3ለ0 የተሸነፈበትን የአቋም መለኪያ ጨዋታ አድርጓል፡፡ ከዚህ ጨዋታ በኋላም ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ ባለፉት አራት ቀናት ምሽት፣ ምሽት ላይ (ጨዋታው የሚደረገው በምሽት ከመሆኑ አንፃር) ዝግጅቶቹን አድርጓል፡፡ ቡድኑ የወረቀት ጉዳዮቹ እስካሁን መፍትሄ ያላገኙት አሚን አስካር እና በዑጋንዳው ጨዋታ መለስተኛ ጉዳት ያስተናገዱትን የመሀል ተከላካዮቹን ሳልሀዲን ባርጊቾ እና ዋሊድ አታን ጨምሮ በዚህ ሳምንት በ24 ተጨዋቾች ልምምዱን ሲሰራ የቆየ ሲሆን ትናንት ምሽት የአልጄሪያ ጉዞውን ከማድረጉ በፊት ሶስት ተጨዋቾችን (የቅዱስ ጊዮርጊሱ አማካይ ምንተስኖት አዳነ፣ የኢትዮጵይ ንግድ ባንኩ አማካይ/አጥቂ ኤፍሬም አሻሞ እና የሲዳማ ቡናው አማካይ እንዳለ ከበደ) ቀንሷል፤ አሚንም ጉዳዩ ባለማለቁ አብሮ መጓዝ አልቻለም፡፡ በጉዳት ላይ የነበሩት ሁለቱ የመጀመሪያ ተሰላፊ ተከላካዮች ሳልሀዲን እና ዋሊድ በመጀመሪዎቹ ቀናት ለብቻቸው ቀለል ያሉ ስራዎችን ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ የተሻለ በማገገማቸው ትናንት ከሌሎቹ ጋር ተቀላቅለው ሰርተዋል፡፡ ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰውም ከጥርስ ህመሙ ጋር እየታገለ ሲሰራ ሰንብቷል፡፡ ባሬቶ በሰሞኑ ልምምዶቻቸው ላይ ተጨዋቾቻቸውን እርስ በእርስ ሲያጫውቷቸው እንደተመለከትነው በነገው ጨዋታም የሚወዱትን 4-3-3 ፎርሜሽን እንደሚጠቀሙ መጠበቅ እንችላለን፡፡ በቀሪዎቹ ልምምዶቻቸው ተጨዋቾቻቸው ካልተጎዱባቸው በቀር ጀማልን በግብ ጠባቂነት፣ አንዳርጋቸው ይላቅ ወይም አብዱልከሪም መሀመድን በቀኝ ተከላካይነት፣ ዋሊድ እና ሳልሀዲንን በመሀል ተከላካይነት፣ አበባው ቡታቆን በግራ ተከላካይነት፣ መሀል ላይ ናትናኤል ዘለቀን፣ ፋሲካ አስፋው እና ታደለ መንገሻን ወይም ሽመልስ በቀለን፤ ፊት ላይ ዩሱፍ ሳሌህ፣ ኡሞድ ኦኮሪ እና ዳዋ ሆቴሳን አልያም ራምኬል ሎክን ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ግራ የተጋቡት ለብዙ ችግሮቻችን ምክንያት በነበረው የቀኝ ተከላካይ ስፍራ ከሁለገቡ ወጣት አንዳርጋቸው፣ ከአዲሱ ተመራጭ አብዱልከሪም እና ከቢያድግልኝ ኤልያስ ማንን እንደሚያሰልፉ እና እንዲሁም በጉዳት እና በቅጣት ያጧቸውን ሁለቱን የፊት አጥቂዎቻቸውን (ሳልሀዲን ሰዒድ እና ጌታነህ ከበደ) በማን እንደሚተኩ ነው፡፡ ለአጥቂ ስፍራው አማራጮች ቢኖሩም ሁሉም አማራጮች (ኦሞድ፣ ዳዋ፣ ራምኬል፣ ዳዊት ፍቃዱ እና ዩሱፍ) ከፊት ለፊት አጥቂነት ይልቅ ከመስመር ተነስተው ማጥቃትን የሚመርጡ እና በእዚህም ሚና በንፅፅር የተሻለ መሆናቸው ባሬቶን ለውሳኔ ያስቸገረ ሆኗል፡፡

 • ዋሊያዎቹ አምበላቸውን ጨምሮ ቢያንስ አራት ወሳኝ ቋሚ ተሰላፊ ተጨዋቾቻቸውን በጉዳት እና በቅጣት ምክንያት ወደ አልጄሪያ ለመውሰድም ሆነ ለማጫወት አልቻሉም፡፡ ምናልባትም በብዙዎች አመለካከት የቡድኑ ኮከብ የሆነው አምበሉ ሳልሀዲን ሰዒድ ከወር በፊት በክለቡ አል-አህሊ እና ዛማሊክ የግብፅ ሱፐር ካፕ ጨዋታ ላይ ጉዳት አስተናግዶ ከሜዳ ከወጣ በኋላ እስካሁን ወደ ጨዋታም ሆነ ልምምድ መመለስ አልቻለም፡፡ ሌላው የቡድኑ የመጀመሪያ ተሰላፊ የመሀል ተከላካይ የኢትዮጵያ ቡናው ቶክ ጄምስም በጉዳት ምክንያት ከቡድኑ የራቀ ሲሆን በባማኮው የማሊ ጨዋታ ላይ ተጎድቶ የወጣው የደደቢቱ ግብ ጠባቂ ሲሳይ ባንጫም ድኖ አልተመለሰም፡፡ በሌላ በኩል ማሊ ላይ ወሳኝ ጎል ካስቆጠረ እና ለሌላ ጎል ካቀበለ በኋላ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣው የቢድ ቬትሱ አጥቂ ጌታነህ ከበደ ከነገውም ሆነ ከረቡዑ የማላዊ ጨዋታ ውጪ ሆኗል፡፡

‹‹የሚጠብቀንን ፈተና ለማለፍ ተዘጋጅተናል›› ማሪያኖ ባሬቶ

ሁልጊዜም ሀሳባቸውን በግልፅነት ከመናገር የማይቆጠቡት የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ በዚህ ሳምንት በሰጧቸው ቃለ-መጠይቆች እንደተለመደው የክለቦቻችን አሰልጣኞች ለወጣቶች እድል እንደማይሰጡ እና በተለይ ትልልቆቹ ክለቦች ለውጪ ዜጋ ተጨዋቾች ትኩረት በመስጠት ብሔራዊ ቡድኑን እየጎዱ መሆናቸውን በመግለፅ ተችተዋል፡፡ በእግር ኳሱ ማደግ ከፈለግንም ከምንም በላይ ለህፃናት እና ለታዳጊዎች ትኩረት መስጠት እንደሚኖርብን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ የአሁኖቹ ተጨዋቾቻቸው በልጅነታቸው መማር የነበሩባቸውን መሰረታዊ ነገሮች በዚህ ደረጃ መማር እንዳልነበረባቸውም ገልፀዋል፡፡ ባሬቶ ከተለመዱ አወዛጋቢ ንግግሮቻቸው ባሻገር ግን ስለነገው ጨዋታም ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡ ‹‹በአቋም መለኪያ ጨዋታ በዑጋንዳ 3ለ0 መሸነፋችን ያልጠበቅነው ነበር፡፡ ግን በመጫወታችን አልተከፋንም፤ ችግሮቻችንን በበለጠ ተመረንበታል፡፡ በማሊ እንዳገኘነው አይነት ሌላ የሜዳ ውጪ ድል ማግኘት የሚችል ቡድን እንዳለንም እናውቃለን›› ያሉት ባሬቶ ወሳኝ ተጨዋቾቻቸውን በተለያዩ ምክንቶች ቢያጡም ባሏቸው ተጨዋቾች ላይ ብቻ አተኩረው በአልጄሪያ ሜዳ ውጤት ይዘው ለመመለስ አና የማለፍ እድላቸውን ለማለምለም እንደሚፋለሙ ገልፀዋል፡፡ ‹‹ከሜዳችን ውጪ አልጄሪያን መግጠም ከባድ ፈተና ይሆናል፡፡ ነገር ግን ልንወጣው የምንችለው ፈተና ነው፡፡ አልጄሪያዊያኑ ማለፋቸውን ቢያረጋግጡም ወደሜዳ የምንወጣው በቆራጥነት ነጥቦችን ለማግኘት ነው፡፡ በአልጄሪያ ምን እንደሚጠብቀን እናውቃለን፡፡ በብራዚሉ ዓለም ዋንጫም ጥሩ የተጫወተ ቡድን አላቸው፡፡ ግን ፈተናውን ማለፍ እንችላለን›› ሲሉ ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ጨምረዋል፡፡

ተጨዋቾቻችንን በአጭሩ፡-

ግብ ጠባቂዎች

 • ጀማል ጣሰው፡- ክለብ – መከላከያ፤ እድሜ – 27፤ የትውልድ ቦታ – አዲስ አበባ
 • ታሪክ ጌትነት፡- ክለብ – ደደቢት፤ እድሜ – 20፤ የትውልድ ቦታ – ቢሾፍቱ

ተከላካዮች   

 • ብርሀኑ ቦጋለ፡- ክለብ – ደደቢት፤ እድሜ – 28፤ የትውልድ ቦታ – አዲስ አበባ
 • አበባው ቡታቆ፡- ክለብ – አል-ሂላል (ሱዳን)፤ እድሜ – 22 ፤ የትውልድ ቦታ – አርባ ምንጭ
 • ሳልሀዲን ባርጊቾ፡- ክለብ – ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ እድሜ – 20፤ የትውልድ ቦታ – አሶሳ
 • ዋሊድ አታ፡- ክለብ – ቢ.ኬ ሀከን (ስዊድን)፤ እድሜ – 28፤ የትውልድ ቦታ – ሪያድ (ሳዑዲ አሬቢያ)
 • ቢያድግልኝ ኤልያስ፡- ክለብ – ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ እድሜ – 26፤ የትውልድ ቦታ – አርባ ምንጭ
 • ግርማ በቀለ፡- ክለብ – ሀዋሳ ከነማ፤ እድሜ – 27፤ የትውልድ ቦታ – ሀዋሳ
 • አብዱልከሪም መሀመድ፡- ክለብ – ሲዳማ ቡና፤ እድሜ – 17፤ የትውልድ ቦታ – ወንዶ ገነት
 • አንዳርጋቸው ይላቅ፡- ክለብ – ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ እድሜ – 17፤ የትውልድ ቦታ – አዲስ አበባ

አማካዮች

 • ናትናኤል ዘለቀ፡- ክለብ – ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ እድሜ – 19፤ የትውልድ ቦታ – አዲስ አበባ
 • ፋሲካ አስፋው፡- ክለብ – ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ እድሜ – 28፤ የትውልድ ቦታ – አዲስ አበባ
 • ጋቶች ፓኖም፡- ክለብ – ኢትዮጵያ ቡና፤ እድሜ – 20፤ የትውልድ ቦታ – ጋምቤላ
 • ታደለ መንገሻ፡- ክለብ – ደደቢት፤ እድሜ – 27፤ የትውልድ ቦታ – አርባ ምንጭ
 • ሽመልስ በቀለ፡- ክለብ – ፔትሮጄት (ግብፅ) ፤ እድሜ – 24፤ የትውልድ ቦታ – ሀዋሳ

አጥቂዎች

 • ዩሱፍ ሳሌህ፡- ክለብ – አይ.ኬ ሳይሪየስ (ስዊድን)፤ እድሜ – 30፤ የትውልድ ቦታ – ስዊድን
 • ዳዊት ፍቃዱ፡- ክለብ – ደደቢት፤ እድሜ – 28፤ የትውልድ ቦታ – ቢሾፍቱ
 • ኦሞድ ኦኮሪ፡- ክለብ – አልኢትሀድ ኤል ሳካንዳሪ(ግብፅ)፤ እድሜ – 24፤ የትውልድ ቦታ – ጋምቤላ
 • ዳዋ ሆቴሳ፡- ክለብ – ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ እድሜ – 18፤ የትውልድ ቦታ – ቀርቻ
 • ራምኬል ሎክ፡- ክለብ – መብራት ኃይል፤ እድሜ – 20፤ የትውልድ ቦታ – ጋምቤላ

ዋና አሰልጣኝ፡- ጄሮኒሞ ማሪያኖ ባሬቶ

 • እድሜ – 57 ፤ የትውልድ ቦታ – ህንድ፤ ዜግነት – ፓርቹጋል

እድሜ እና የትውልድ ቦታ ምንጭ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን የልዑካን ዝርዝር

 

ማስታወሻ፡-
∙       ከዑጋንዳ ብሄራዊ ቡድን ጋር ከተካሄደው የወዳጅነት ጨዋታ በኋላ በአሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ የተቀነሱት ተጨዋቾች ሄኖክ ካሳሁን፣ዴቪድ በሻህ፣እንዲሁም ፉዓድ ኢብራሂም ብቻ ናቸው፡፡
∙       እንዳለ ከበደና አብዱል ከሪም የጉዞ ፎርማሊቲ  በሟሟላት ሂደት ላይ ናቸው፡፡
∙       የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወደ አልጄሪያ የሚያመራው ሃሙስ ህዳር 4ቀን2007 ዓ.ም ከሌሊቱ 6፡05 ላይ ነው፡፡
∙       ቡድኑ ሃሙስ ረፋዱ ላይ በ5፡25 አልጀርስ ይደርሳል፡፡
∙       ብሄራዊ ቡድኑ ከአልጀርስ ወደ አዲስ አበባ የሚመለሰው እሁድ ህዳር  7 ቀን 2007 ዓ.ም ሲሆን፤ከቀኑ 11፡40 ከአልጀርስ ይነሳና በሮም አድርጎ ህዳር 8ቀን 2007 ዓ.ም ሰኞ ጠዋት 1፡00 አዲስ አበባ ይገባል፡፡

2 thoughts on “ዋሊያዎቹ ለሞት-ሽረቱ ፍልሚያ አልጄሪያ ደርሰዋል

Leave a Reply

Your email address will not be published.