ዋሊያዎቹ፣ ባሬቶ እና የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ

Coach Barreto

በቅርብ ዓመታት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ የማሪያኖ ባሬቶን ያህል የግራ እና ቀኝ ፅንፍ አስይዞ ያወዛገበ፣ ያከራከረ እና ያነጋገረ ግለሰብ ስለመኖሩ ያጠራጥራል፡፡ ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ከ12 ወራት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆነው ከመሾማቸው አስቀድሞ ከሌሎች የውጪ ሀገር አሰልጣኞች ጋር ለስራው ሲወዳደሩ እና በመጨረሻም ኃላፊነቱ ሲሰጣቸው፣ ጥርጣሬዎች በሚያስነሳው የስራ ህይወት ማስረጃቸው ዙሪያ ብዙ ውዝግቦች ተነስተው ነበር፤ ከዚያ ቀደም በሌሎች ሀገራት ስራዎቻቸው ሰውዬው የገጠሟቸው ችግሮች እና አለመግባባቶች (በተለይ ከአለቆቻቸው እና ሚዲያዎች ጋር) ተነስተውም የሹመቱ ትክክለኛነት የመከራከሪያ ርዕስ ሆኖ ነበር፡፡ የሚከፈላቸው ከፍተኛ ወርሀዊ ደሞዝ (ምንም እንኳን ከሌሎች የውጪ ዜጋ የአፍሪካ ሀገራት አሰልጣኞች ያነሰ ቢሆንም) እና የሚታሰብላቸው ተጨማሪ ጥቅማ-ጥቅምም ሌላው መነጋገሪያ ነበር፡፡ ከዚያ ስራቸውን ሲጀምሩ ደግሞ የአዲስ አበባ ስታዲየም እና ሌሎች የክልል ጨዋታዎችን በቋሚነት አለመታደማቸው፣ የምክትል አሰልጣኝ ምርጫዎቻቸው እና ከሁሉም በበለጠ ሲኒየር ተጨዋቾችን ወደጎን ገፍቶ በወጣት ተጨዋቾች ላይ ትኩረቱን ያደረገው የተጨዋቾች ምርጫቸው የማያልቁ ክርክሮች መነሻ ሆኖ ነበር፡፡  ግን ከላይ የሰፈረው የፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ አከራካሪነት ከዚያ በኋላ ከታየው አንፃር ኢምንት ነበር፡፡ የባሬቶ እና ቡድናቸው የልምምድ ሜዳ፣ የብራዚል ቆይታ እና የወዳጅነት ጨዋታዎች ስራ በአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ በተግባር መታየት ሲጀምር ውዝግቡ ከፍ ያለ ደረጃ ደረሰ፡፡ በተለይ ሶስተኛ ተከታታይ የማጣሪያው ሽንፈታቸው ከነበረው በማሊ ከተረቱበት የአዲስ አበባው ጨዋታ እና ጨዋታውን ተከትሎ ከሰጡት አነጋጋሪ ፕሬስ ኮንፈረንስ በኋላ በደጋፊዎችም ሆነ በስፖርት ጋዜጠኞች ዘንድ የነበረው ክርክር ፍፁም ፅንፍ የያዘ  እና ታይቶም የማይታወቅ አይነት ነበር፡፡ አንዱ ወገን የሚሰሩትን የማያውቁ፣ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፏችንን ያሳጡ፣ የሀገሪቷን የእግር ኳስ እድገት ወደ ኋላ የጎተቱ፣ እብሪተኛ  ብሎ ሲያወግዛቸው ሌላኛው ወገን ለወጣቶች እድል የሰጡ፣ የወደፊቱ እግር ኳሳችንን ተስፋ ያሳዩን፣ የወደፊቱን ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ግንባታ የጀመሩ፣ ጀግና ብሎ ጋዜጠኛው በየሚዲያው እንዲሁም ህዝቡ በየመንገዱ እና በየቡና ቤቱ  ሲጠዛጠዝ ሰነበተ፡፡ በማሊው ድል እና በተገኘው ትንሽ ተስፋ በመሀል ትንሽ መረጋጋት ከታየ በኋላ ደግሞ ቡድኑ በአዲስ አበባ ከማላዊ ጋር አቻ ተለያይቶ የማጣሪያ ጉዞው ባለማለፍ ሲገባደድ የ58 ዓመቱ አሰልጣኝ ስራ፣ የማጣሪያ ጉዞ እና የወደፊት ቆይታ ዳግም የብዙ ውዝግቦች ምክንያት ሆነ፡፡ ያው እንደተለመደው አንዱ ወገን የአሰልጣኙን ስራ እና ራዕይ አንኳሶ ከፌዴሬሽኑ ጋር የተስማሙበትን ለአፍሪካ ዋንጫ የማሳለፍ ቃል ባለማሳካታቸው በፍጥነት መሰናበት እንዳለባቸው ሲገልፅ፣ ሌላኛው ፅንፍ ደግሞ እንደዚህ ዓይነት ስምምነት እንደሌለ እና ለወደፊቱ ብሔራዊ ቡድን ግንባታ ሲባል አሰልጣኙ መቆየት እንደሚኖርባቸው ሲከራከር ከረመ፡፡ በመሀል ክርክሩ ረገብ ቢልም የ23 ዓመት በታች ቡድኑ በሱዳን አቻው በደርሶ-መልስ ተረትቶ መውደቁን ተከትሎ የባሬቶ ጉዳይ እንደገና መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከየት የመጣ ወሬ እንደሆነ ሳይታወቅ የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በባሬቶ ቆይታ ዙሪያ ተነጋግሮ ሊወስን እንደሆነ ቢነገርም ፌዴሬሽኑ ይህ ፈፅሞ ሀሰት እንደሆነ በህዝብ ግንኙነቱ በኩል ገልፆ ነበር፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ በዋልያዎቹ አለቃ ዙሪያ ሌላ ውዝግብ ተፈጥሯል፡፡ ይህም በአንዳንድ ሚዲያዎች በተለይ በኦፊሴላዊ ድረ-ገፆች እና በማኅበራዊ ድረ-ገፆች ባሬቶ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ በፌዴሬሽኑ መወሰኑን መነገሩ እና ባሬቶ ግን ለበዓል እረፍት ከሄዱበት ፖርቱጋል ሆነው ዜናው ሀሰት መሆኑን መግለፃቸው ነው፡፡ በኋላም በአንዳንድ ሚዲያዎች ማጣራት ማረጋገጥ እንደተቻለው ፌዴሬሽኑ በባሬቶ ዙሪያ ከቴክኒክ ክፍሉ በተሰጠው አስተያየት ብቻ የአሰልጣኙን ጉዳይ መመልከት ባለመፈለጉ ከስራ አስፈፃሚ አባላቱ መካከል አራቱን (አቶ አበበ ገላጋይ፣ አቶ አሊሚራህ መሀመድ፣ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ እና አቶ ልዑል-ሰገድ በጋሻው) በንዑስ ኮሚቴነት መርጦ ጉዳዩን አጣርተው ሪፖርት እንዲያቀርቡለት አዞ ነበር፡፡ ሪፖርቱ ቢሰራም ግን ጥቂቶቹ የፌዴሬሽኑ ኃላፊዎች ለካፍ ስብሰባ ከሀገር በመውጣታቸው ሪፖርቱ ታይቶ ውሳኔ አልተሰጠበትም፤ እናም ባሬቶ ይነሱ የሚል ውሳኔ በጭራሽ ከፌዴሬሽን ቢሮ አልወጣም፡፡ ታዲያ ከየት መጣ? የሚያስገርመው ስማቸውን የማንጠራ የተለያዩ ሚዲያዎች በዚህም ዙሪያ ፍፁም የሚጋጩ ሀሳቦችን ሲያስተጋቡ መሰንበታቸው ነው፡፡ አንዳንዶቹ የባሬቶን መሰናበት በእርግጠኝነት ሲነግሩን አንዳንዶቹ ለፖርቹጋላዊው እንቀርባለን ያሉ ጋዜጠኞች ደግሞ ይህ ሀሰት መሆኑን እና ባሬቶ ራሳቸው በፍቃዳቸው ስራውን ለመልቀቅ መዘጋጀታቸውን ነግረውን ነበር፡፡ ግን ሁለቱም ወገኖች (የሚዲያዎቹ ሰዎች) የሠጡን ቀነ-ገደብ ተጠናቋል፤ የፌዴሬሽኑ ኃላፊዎች ከካይሮ ስብሰባቸው ከተመለሱ በኋላ ለቀናት የእግር ኳሱን ማህበረሰብ ባመሰው ጉዳዩ ዙሪያ ምንም ለማለት አልፈቀዱም፤ ባሬቶም ከትንሳኤ በዓል የእረፍት ቆይታቸው ተመልሰው በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታ መታደም ጀምረዋል፡፡ በፌዴሬሽኑ ቢሮ እና በባሬቶ አእምሮ ውስጥ ምን እንደተወጠነ ማወቅ ባንችልም ለአሁን ግን ማዕበሉ የሰከነ መስሏል፤ ወሬዎቹ እና ክርክሮቹም ቀስ በቀስ ድምፃቸው መቀነስ ጀምሯል፡፡ በዚህ መሀል ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ እና የቻን (በሀገር ውስጥ ተጨዋቾች የሚደረገው ውድድር) የማጣሪያ ድልድሎች ወጥተዋል፡፡ በተለይ ህዝቡ በጉጉት የሚጠብቀው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ተስፋ የሚሰጥ ሆኗል፡፡

የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ   

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ታላቁ የአፍሪካ ዋንጫ ቀጣዩ የ2017 ውድድር በመካከለኛ አፍሪካዊቷ ሀገር ጋቦን እንዲዘጋጅ በወሰነበት ያለፈው ሳምንቱ የካይሮ ጉባኤው ላይ የማጣሪያ ድልድሉንም አድርጓል፡፡ በአዲስ ፎርማት ለሚደረገው የማጣሪያ ውድድር አዘጋጇ ጋቦንን (ለአቋም መለኪያ ሲባል ብቻ ትሳተፋለች) ጨምሮ 42 ሀገራት በ13 ምድቦች የተደለደሉ ሲሆን 13ቱ የየምድቦቹ አሸናፊዎች፣ እንዲሁም አዘጋጇ ጋቦንን እና እሷ ከምትገኝበት ምድብ ዘጠኝ በስተቀር ከሌሎቹ 12 ምድቦች የተሻለ የነጥብ ድምር ያላቸው ሁለት ምርጥ ሁለተኞች ባጠቃላይ 16 ሀገራት በ31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ ዋሊያዎቹ በምድብ 10 ከአልጄሪያ፣ ሌሶቶ እና ሲሼልስ ጋር ተመድበዋል፡፡

ተፎካካሪዎቻችንን በጥቂቱ፡-

አልጄሪያ፡- በፊፋ ወርሀዊ የሀገራት ደረጃ ሰንጠረዥ ከዓለም 21ኛ እና ከአፍሪካ አንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው አልጄሪያ በቅርቡ በኤኳቶሪያል ጊኒ ተዘጋጅቶ በነበረው የአፍሪካ ዋንጫ የተገመተችውን ያህል መጓዝ ባትችልም በዓለም ዋንጫው ያሳየችው ድንቅ ብቃት ፈፅሞ ሊረሳ አይችልም፡፡ ከፍ ያለ ደረጃ ያላቸው አሰልጣኝ እና በታላላቅ የአውሮፓ ሊጎች የሚጫወቱ ከዋክብት እንዳሏትም ሊዘነጋ አይገባውም፡፡ የበረሀዎቹ ተኩላዎች በመጨረሻው አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያም ከዋሊያዎቹ ጋር ተመድበው ሁለቱንም የደርሶ መልስ ጨዋታዎች በድል መወጣታቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡

ሌሶቶ፡- በአፍሪካ ዋንጫው የመሳተፍ ታሪክ የሌላት ደቡብ አፍሪካዊቷ ሀገር በእግር ኳስ የማትጠራ፣ በወቅታዊው የፊፋ የሀገራት የደረጃ ሰንጠረዥም 122ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሀገር ናት፡፡ ሌሶቶ በደቡብ አፍሪካ ሊግ ከሚጫወቱ በጣት የሚቆጠሩ ተጨዋቾች ሌላ ከፍ ብሎ የሚጠራ ክለብም ሆኑ ተጨዋቾች የሌላት ሀገር ናት፡፡

ሲሼልስ፡- በህንድ ውቅያኖስ ላይ ከሚገኙ በርካታ ደሴቶች የተዋቀረችው የአህጉራችን ባለትንሽ ቁጥር ህዝብ ሲሼልስ እንደ ሌሶቶ ሁሉ በእግር ኳስ የሚነገር ስኬትም ሆነ ታሪክ የሌላት ሚጢጢዬ ሀገር ናት፡፡ በወቅታዊው በፊፋ የሀገራት የደረጃ ሰንጠረዥ ከ209 ሀገራት 189ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ሲሼልስ ክለቦች በተለያዩ ጊዜያት ከኢትዮጵያ ክለቦች ጋር ተገናኝተውም በሰፊ ውጤቶች የመሸነፍ ታሪክ አላቸው፡፡

ከላይ በትንሹ ለመመልከት እንደሞከርነው ከአልጄሪያ በቀር በምድባችን እምብዛም የሚያሰጋን ተፎካካሪ ባይኖረንም እግር ኳስ የማይተነበይ ነውና እያንዳንዱን ጨዋታ በትኩረት፣ በጥሩ ዝግጅት እና ፍላጎት ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ይህን ካደረግን ታላቋ አልጄሪያን ለመብለጥ ብንቸገር እንኳን ከአራቱ ጨዋታዎች ሙሉ ነጥቦች በመውሰድ በምርጥ ሁለተኛነት የማለፍ እድል ሊኖረን ይችላል፡፡ ግን ከዚያ በፊት በብሔራዊ ቡድኑ ዙሪያ ያሉ ያልጠሩ ነገሮች ሁሉ መጥራት ይኖርባቸዋል፡፡ አወዛጋቢው የዋና አሰልጣኝ ጉዳይ በተለይ ፈጣን ውሳኔ የሚፈልግ ነው – ውሳኔው ባሬቶን ማቆየት ከሆነ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች አሟልቶ እንደሚያቆያቸው በመግለፅ መረጋጋትን መፍጠር፣ አልያም ለማሰናበት ከተወሰነም ውሳኔውን አፍጥኖ የሚሾመው አዲሱ አሰልጣኝ ስራውን በጊዜ እንዲጀምር ማድረግ፡፡ ይህ ከተፈፀመ እና ሁሉም ወገኖች የሚጠበቅባቸውን ካደረጉ ከሁለት ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በሚደረገው የጋቦኑ የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ የማንሳተፍበት ምክንያት አይኖርም፡፡

የቻን ማጣሪያ

በሀገር ውስጥ ሊግ የሚጫወቱ ተጨዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት የአፍሪካ ሀገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) አራተኛው ውድድር በ2016 በሩዋንዳ እንዲደረግ ፕሮግራም የተያዘለት ሲሆን የማጣሪያ ድልድሉም ወጥቷል፡፡ ከዋናው የአፍሪካ ዋንጫ በተለየ በማጣሪያው የአንድ ዞን ሀገራትን ብቻ እርስ በእርስ በሚያገናኘው በዚህ ውድድር ማጣሪያም ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ከኬንያ ጋር እንድትጫወት የተመደበች ሲሆን በደርሶ መልስ አሸንፋ ይህን ዙር ካለፈች ከቡሩንዲ እና ጂቡቲ አሸናፊ ጋር ተጫውታ አሸናፊው በሩዋንዳው ውድድር ላይ ተሳታፊ ይሆናል፡፡

  • የሁለቱም ውድድሮች የማጣሪያ ጨዋታዎች በቀጣዩ ሰኔ ወር ይጀመራሉ፡፡

2 thoughts on “ዋሊያዎቹ፣ ባሬቶ እና የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ

  1. Still in Position?It’s really a joke to hear this person has kept his job after all these failures?Now,I’ve already concluded that the country has no system and responsible body at all!!!

  2. ፌደሬሽኑ ብቻ ሳይሆን የስፖርት ጋዜጠኞቻን ጭምር አሳፋሪዎች ናቸው ። 1, ሰውነት ቢሻውን ከማባረር ተጨማሪ ሥልጠና እንዲሁም የባህሪይ ችግሩን ለማረቅ ባለሙያ ማፈላለግ ላይ ማተኮር ነበረባቸው። 2, እንደዚህ አይነቱን ስኬታማ ሐገራዊ ሰው፣ ያውም እድሜ ልኩን ለግጦሽ እስኪሰናበት ድረስ ያፈራው ሐብት በስመ ነጭ በወራት ያውም ያለስኬት ተከፍሎት ላገለገሉ ሰው በዚያው በስታድየም ህዝብ በተሰበሰበበት ለስራው እውቅና ቢሰጥ፣ ለተተኪው አሰልጣኞች ትልቅ ተስፋ ነበር። 3, ማይክ በመጨበጡ ያሻውን በእድል ከጥሬ በመናገሩ ጋዜጠኛ መሆኑ ከሚሰማው የስፖርት ጋዜጠኛ
    ሚዛናዊ ዜና እንዲቀርብ ተግቶ ቢሰራ ስልጠና ቢያዘጋጅ 4, የውጭ አሰልጣኝ ላይ ከማተኮር ተጨማሪ ስልጠና ቢተኮር ወደፊት በታዳጊ ላይ ሰርተው ውጤታማ ስፖርተኞችን ማፍራት ያስችላል። 5, ውጤት ሲመጣ መደሰት ብቻ ሳይሆን ውጤት ሲጠፋ ጨመታገስና ከአሰልጣኙ ጊዜ መሰጠት፣ 6, ውጤቱ በሟች ፊክሲንግ ምን ያህል እየተበላሸ መሆኑን በመገንዘብ ፌደሬሽኑ በቂ ሆኖ ቢሠራ

Leave a Reply

Your email address will not be published.