ወሬውን ትተን ከሰራን ስኬታማ መሆን እንደሚቻል አሳይተናል – አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ

Yohaness Sahle ETH vs Burundi
ከተሰራ እና ተስፋ ከተደረገ ምንም ማድረግ እንደሚቻል ከዚህ ውጤት መማር ይቻላል፡፡ ወሬውን ትተን ከሰራን ስኬታማ መሆን እንችላለን የሚል መልእክት አስተላልፈናል፡፡ እኔ ደስ ብሎኛል ግን የበለጠ የተደሰትኩት ለተጨዋቾቹ ነው

የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን በቻን የመጨረሻ ማጣሪያ የቡሩንዲ ብሔራዊ ቡድንን በደርሶ መልስ 3ለ2 ውጤት ከረታ እና ለሩዋንዳው የቻን ውድድር ማለፉን ካረጋገጠ በኋላ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ አሰልጣኝ ዮሐንስ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ በአዲስ አበባው ጨዋታ ላይ እና በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሾችን ሰጥተዋል፡፡ እኛም በርዕስ በርዕስ ከፋፍለን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

ስለደጋፊዎች ቀዝቀዝ ያለ ስሜት

የቡድኑ መረጋጋት

ዋልያዎቹ ከሌሎቹ ጨዋታዎች በተለየ ሜዳ ላይ እንቅስቃሴያቸው ከጥድፈት እና መንቀዥቀዥ የራቀ እና የተረጋጋ ነበር፡፡ ተጨዋቾቹ ገፅ ላይም ሆነ በእንቅስቃሴያቸው ላይ ስክነት ይስተዋል ነበር፡፡ አሰልጣኝ ዮሐንስ ምክንያቱን ሲያስረዱ ‹‹ቡድኑ የተረጋጋ የሆነው ልምድ እያካበተ ስለሆነ ነው፡፡ ለሳኦ ቶሜው ጨዋታ ለ27 ሰዓታት ተጉዘናል፡፡ በአውሮፕላን ጉዞዎች፣ በአመጋገብ እና በመሳሰሉት ተቸግረዋል፡፡ ግን እየለመዱት ነው፡፡ እናም እየበሰሉ መጡ፡፡ አሰልጣኞቹም ሁላችንም ለብሔራዊ ቡድን የመጫወት ጫናን እናውቀዋለን፡፡ ተጫወቱ፤ እኛ የመጣውን እንቀበላለን ብለናቸዋል፡፡ ይህ ያረጋጋቸው ይመስለኛል›› ብለዋል፡፡

ድሉ ምን ትርጉም አለው?

‹‹በማሸነፋችን ተደስቻለሁ ግን የተለየ ስሜት አይኖረኝም፡፡ በእግር ኳስ ማሸነፍም፣ መሸነፍም፣ እኩል መውጣትም እንዳለ አውቃለሁ፡፡ እግር ኳስ ተጨዋች ሆኜ በደንብ አውቀዋለሁ፡፡ ጠቃሚነቱ ለተጨዋቾች፣ ለወጣቶች እና ለክለቦችም ይሆናል፡፡ ከተሰራ እና ተስፋ ከተደረገ ምንም ማድረግ እንደሚቻል ከዚህ ውጤት መማር ይቻላል፡፡ ወሬውን ትተን ከሰራን ስኬታማ መሆን እንችላለን የሚል መልእክት አስተላልፈናል፡፡ እኔ ደስ ብሎኛል ግን የበለጠ የተደሰትኩት ለተጨዋቾቹ ነው››፡፡

ያለመነሳታቸው ምክንያት

አሰልጣኝ ዮሐንስ ከዚህ ቀደም ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ ሜዳው ዳር ላይ ቆመው ትእዛዞች ሲያስተላልፉ አልታዩም፡፡ እሳቸው ቁጭ ብለው ምክትሉ ፋሲል ተካልኝ ብቻ ሲነሳ ይታይ ነበር፡፡ አሰልጣኙ ምክንያታቸውን ሲገልፁ ‹‹ተጨዋቾቹ የሚሰሩትን ያውቃሉ፡፡ ኃላፊነቱ ከተሰጣቸው የተነገራቸውን እንደሚሰሩ ተጨዋች ሆኜ እንደማሳለፌ አውቀዋለሁ፡፡ ተጨዋቾቹ ያላቸውን ሁሉ ስለሚሰጡ እና በሚገባ ስለተነጋገርን መነሳት አላስፈለገኝም፡፡ ዝምብዬ ብነሳ እና ብጮህ እነሱንም ላስደነግጣቸው እችል ነበር››፡፡

የመሀመድ ናስር ቅያሬ

የዳዊት ፍቃዱን በቡጁምቡራው ጨዋታ መጎዳት እና መሀመድ ናስር በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ አራት ጎሎች በማስቆጠር ያሳየውን ድንቅ አቋም ተከትሎ የመከላከያው አጥቂ ለዚህ ጨዋታ የመጠራት እና የመሰለፍ እድል ቢያገኝም ከ45 ደቂቃዎች የበለጠ እንዲጫወት አልተፈቀደለትም፤ በክለቡ ልጅ ምንይሉ ወንድሙ እንዲተካም ተደርጓል፡፡ አሰልጣኝ ዮሐንስ የቅያሬውን ምክንያት ሲያስረዱ ‹‹መሐመድ ለቡድኑ አዲስ እንደመሆኑ በተለይም ከአማካዮቹ ጋር ብዙም ሊግባባ አልቻለም፡፡ እምብዛም በእንቅስቃሴ ውስጥ እየተሳተፈ አልነበረም፡፡ ራምኬልም ረዳት እያጣ ነበር›› ብለዋል፡፡

የጋቶች ፓኖም አደራጅነት

ጋቶች ፓኖም ከእሱ በማይጠበቅ መንገድ ሁለት ወሳኝ ጎሎችን ቢያገባም ከእሱ የሚጠበቀውን የቡድኑን እንቅስቃሴ የማደራጀት ሚና በሚገባ ተወጥቷል ማለት ያስቸግራል፡፡ በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ ተከላካዮቹ ኳስ የሚቀበላቸው ሰው እያጡ ራሳቸው ኳሱን ይዘው ሲወጡ እንመለከት ነበር፡፡ አሰልጣኙ ግን ጋቶች በተነገረው መሰረት እንደተንቀሳቀሰ እና ከመሀል ሜዳው ክበብ እንዳይርቅ ታዝዞ እንደነበር በመግለፅ የተሰጠበትን አስተያየት ተከላክለዋል፡፡

 

የኤልያስ ማሞ ብቃት

ኤልያስ ማሞ የጨዋታው ምርጡ ተጨዋች እንደነበር የብዙዎች እምነት ነው፡፡ ኳሶች በድፍረት ይቀበል እና ያሰራጭ ነበር፤ የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ አስጀማሪ ነበር፤ ለሶስቱም ጎሎችም መነሻ ነበር፡፡ አሰልጣኝ ዮሐንስ የኤልያስ ጥሩ የመንቀሳቀስ ዋነኛ ምክንያት ‹‹በነፃ ሚና የመጫወቱ›› እና ‹‹ወደፊት ብቻ እንዲጫወት መታዘዙ›› እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የአስቻለው ግርማ መቆየት

ፈጣኑ የመስመር አማካይ አስቻለው ግርማ ለሶስተኛው ጎል (ለፍፁም ቅጣት ምቱ) መገኘት ምክንያት ቢሆንም ባልተለመደ መልኩ ብዙ ስህተቶችን ሲሰራ ይታይ ነበር – ብዙ ኳሶችን ይቀማ ነበር፤ ጥቂት የማይባሉ ውሳኔዎቹም የተሳሳቱ ነበሩ፡፡ ብዙዎችም ተቀይሮ እንደሚወጣ አስበው ነበር፡፡ አሰልጣኙ ግን አስቻለው የተባለውን የሚሰማ እና የታዘዘውን የሚፈፅም ተጨዋች እንደሆነ አና በዚህም ጨዋታ ኳስ ያዝ ሲባል እንደያዘ ሩጥ በተባለባቸው ጊዜያትም እንደሮጠ አስረድተዋል፡፡ በእንቅስቃሴውም ደስተኛ እንደነበሩ አስረግጠዋል፡፡

የአጥቂ ችግር

ዋልያዎቹ ሶስት ጎሎች ቢያስቆጥሩም አንዱም ጎል በአጥቂዎች የተገኘ አልነበረም፡፡ አሰልጣኙም የጎል አግቢ አጥቂ ችግር እንዳለባቸው አምነዋል፡፡ ‹‹በአጥቂ ጉዳይ ችግር ላይ ነን፡፡ ወሳኝ ጎል አግቢ የለንም፡፡ ጎል ማግባት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ በተለያዩ ምክንያቶችም እየቀያየርናቸው ነው፡፡ ግን ያሉን አጥቂዎችም ያላቸውን ሁሉ ይሰጡናል፡፡ ለቅጣት ምቶች እና ፍፁም ቅጣት ምቶችም ምክንያት ይሆናሉ›› በማለት ዮሐንሰ ችግሩ ቢኖርም ያሉትም ግን የሚችሉትን እያደረጉ እና በተለየ መንገድ እየጠቀሙ እንደሆነ ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡

የዲሲፕሊን ጉዳይ

በዓለም ዋንጫ ቅድመ-ማጣሪያ ሳኦ ቶሜ አና ፕሪንሲፔን ከረቱበት ጨዋታ በኋላ አሰልጣኝ ዮሐንስ ቡድኑ በእሳቸው ስር ቀይ ካርድ እና ብዙ ቢጫዎችን አለመመልከቱን በማስታወስ ከቡድኑ ጠንካራ ጎኖች መካከል ዲሲፕሊን አንዱ እንደሆነ ተናግረው ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ኤፍሬም አሻሞ በቡሩንዲው የመጀመሪያ ጨዋታ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወጣ፣ ከመልሱ ጨዋታ በፊት ልምምድ ላይ አምበሉ ስዩም ተስፋዬ እና ራምኬል ሎክ መጋጨታቸው ተሰምቶ ነበር፡፡ በዚህ ዙሪያ ጥያቄ የቀረበላቸው አሰልጣኙ ኤፍሬም ምንም ጥፋት እንዳልሰራና በቀይ የወጣበትን መንገድ ፍፁም እንደማይቀበሉት ገልፀው አምስት ወራት አብሮ በቆየ ቡድን ውስጥ አንድ ግጭት መከሰቱ እንደትልቅ ነገር መነገር እንደሌለበትም ተናግረዋል፡፡ ዮሐንስ ‹‹የምናወራው ስለ ቮሊ ቦል፣ ቴኒስ ወይም ውሀ ዋና አይደለም፡፡ ልምምድ ላይ ብዙ ንክኪ አለ፡፡ አንዱ ተጨዋች በአንዱ ላይ ጥፋት ሲሰራ ጥፋት የተሰራበት ተጨዋች ደሙ የሞቀ ስለሆነ ምላሽ ሊሰጥ ይችላል፡፡ አምስት ወራት አብሮ የቆየ ቡድን ውስጥ አንድ ግጭት አይስገርምም፡፡ ጉዳዩ ወደእኔ እንኳ አልመጣም፡፡ ምክትሎቼ ገላግለዋቸው ጉዳዩን ፈትተውታል›› በማለት ምላሽ ከሰጡ በኋላ በዚህም ጨዋታ ስዩም ጎሉን ካገባ በኋላ ሁሉም ሲያቅፉት ራምኬል ግን ብቻውን ይህን እንዳላደረገ ለተጠየቁት ጥያቄ ‹‹እኔ እንደዚህ አይነት ነገሮችን ከኳስ ጋር አላያይዝም›› በማለት መልሰዋል፡፡

በተጨዋቾቻቸው ላይ ያላቸው እምነት

በተወሰኑ ተጨዋቾች የጠለቀ እምነት ከነበራቸው የቀድሞው የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በተለየ ዮሐንስ እጅግ በርካታ ተጨዋቾችን ሲጠቀሙ ታይተዋል፡፡ ይህን ሲያብራሩም ‹‹በተጨዋቾች ማመን እንደሀይማኖታዊ እምነት አይደለም፡፡ ሊቀያየር ይችላል፡፡ እኔ የማምነው በወቅታዊ አቋም ነው፡፡ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ቋሚ የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ ስዩም እየተጫወተ የሚገኘው እያሳየ ባለው አቅም ነው፡፡ አሁን አዳዲስ ተጨዋቾች ያመጣነው በጉዳት እና በቅጣት ተጨዋቾቻችንን ስላጣን ነው፡፡ ፕሪምየር ሊጉ ሲጀምር ደግሞ ብዙ አዳዲስ ተጨዋቾችን የመመልከት እድል ይሰጠናል›› ብለዋል፡፡

 

በቻን ምን ይጠብቃሉ?

አሰልጣኙ ለቻን ማለፋቸውን ምን ግምት እንደሚሰጡት እና በውድድሩ ላይ ምን እንደሚጠብቁ ሲጠየቁም ‹‹ወደ ውድድሩ መግባታችን አንድ ስኬት ነው፡፡ ልጆቹ የለፉበትን አሳክተዋል፡፡ ለዚህም ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ ስለቀጣዩ ነገር አላውቅም፡፡ ሁሉም ቡድኖች እንደእኛ አሸንፈው አልፈው እንደእኛ ውድድሩን በጉጉት የሚጠብቁ ናቸው፡፡ ከእነማን ጋር እንደምንጫወትም አናውቅም፡፡ ስለዚህ ምንም ልል አልችልም፡፡››

የተሻጋሪ ኳሶች ጉዳይ

ብሔራዊ ቡድኑ ሁለት ጎሎችን ከቅጣት ምት በተሻገሩ ኳሶች የማግባቱ እውነታ ኢትዮጵያዊያን በዚህ መንገድ መጫወት አይችሉም ከሚለው ተደጋጋሚ አስተያየት ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት የተጠየቁት አሰልጣኙ ለየሚገጥሟቸው ቡድኖች አጨዋወታቸውን ሊቀይሩ እንደሚችሉ ገልፀው የሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔን እና የቡሩንዲን ቡድኖች በምሳሌነት በማንሳት ትንሽ ግራ የሚያጋባ እና የሚጋጭ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ዮሀንስ ‹‹የቡሩንዲ ቡድን በአየር ላይ ኳሶች የተሻለ ነው›› ብለው እንደገና ደግሞ ‹‹በቀጥተኛ ተሻጋሪ ኳሶች ልናጠቃቸው ሞክረናል›› በማለት የሚጋጩ ሀሳቦችን ተናግረዋል፡፡

(ከላይ የሰፈሩት የአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ምላሾች ለፅሁፉ አመቺነት ሲባል ቃል በቃል የተወሰዱ አይደሉም)

3 thoughts on “ወሬውን ትተን ከሰራን ስኬታማ መሆን እንደሚቻል አሳይተናል – አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ

  1. Really it is wonderful to see such scholared Ethiopian coach in our life time. I know some Ethiopian journalists love to critisize than giving constructive comments ALL THE TIME. I suggest to be positive some times. Congratulations coach, I wish you all bests and belive in you to register new hisory.
    I am very much comfotable in your responses/justifications, and etc.

  2. It is really a very good response but i don’t understand why you (the writer of this report) finalize the interview’s summery with a negative conclusion of the coach’s positive reaction.

Leave a Reply

Your email address will not be published.