“ከ12ኛ ክፍል በላይ የተማሩ አሰልጣኞች በሌሉበት ሀገር ዮሐንስን ማግኘት ታላቅ ዕድል ነው”

Ethiopian Football Federation President“ከ12ኛ ክፍል በላይ የተማሩ አሰልጣኞች በሌሉበት ሀገር ዮሐንስን ማግኘት ታላቅ ዕድል ነው”  

  • “የአራት አህጉራት ሰርቲፊኬቶች አሉኝ፤ 20 ዓመት አሰልጥኛለሁ፤ አብረውኝ የተማሩ አሰልጣኞች አሁን ትልቅ ደረጃ ላይ ናቸው”
  • “ቢያንስ ዲፕሎማ የሌለውን ሰው በፍፁም አንቀጥርም”
  • “ለ2017 አፍሪካ ዋንጫ መብቃት ዋናው መስፈርት ነው”

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የወንዶች እግር ኳስ ቡድን በቅርቡ ማሪያኖ ባሬቶን ከዋና አሰልጣኝነት አሰናብቶ በዮሐንስ ሳህሌ መተካቱ ይታወሳል፡፡ ይህንንም በማስመልከት (ምንም እንኳን ቢዘገይም) አርብ በ11 ሰዓት በኢንተር-ኮንቲኔንታል ሆቴል መግለጫ ተሰጥቷል፡፡ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ፣ አዲሱ ተሿሚ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ፣ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላቱ አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ፣ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ እንዲሁም ከስር ከጋዜጠኞች ጋር ተቀምጠው የነበሩት አቶ ቾል ቤል ከጋዜጠኞች ለተጠየቋቸው በርካታ ጥያቄዎች ምላሾቻቸውን ሰጥተዋል፤ ምንም እንኳ ሳይመለሱ የታለፉ እና ተድበስብሰው የተመለሱ ጥያቄዎች ቢኖሩም፡፡ መግለጫው ከተጠራበት ርዕስ ውጪ ብዙ አላስፈላጊ ጥያቄዎች ከተጠየቁበት ከዚህ ፕሬስ ኮንፈረንስ ላይ የተሻሉ ወሳኝ ናቸው ያልናቸው ምላሾች ከዚህ በታች ቀርበዋል፡፡

በሹመቱ ዙሪያ

በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ሹመት ዙሪያ ከተነሱ በርካታ ጥያቄዎች መካከል መስፈርቶቻችሁ ምን ነበሩ? የዮሐንስ የአሰልጣኝነት ልምድ በቂ ነው ወይ? እጩዎቹስ ስንት ነበሩ? ፍላጎታቸውን ሳታውቁ ያወዳደራችኋቸውስ ነበሩ ይባላል? በሹመቱ ላይ የቴክኒክ ኮሚቴው ምን ያህል ሚና ነበረው? የሚሉ ይገኙበት ነበር፡፡ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ መስፈርቶቻቸው የትምህርት ደረጃ (ቢያንስ ዲፕሎማ)፣ የአሰልጣኝነት ፍቃድ፣ ከ3-5 ዓመት የማሰልጠን ልምድ፣ ውጤታማነት… የእነዚህ ሁሉ ድምር እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ ዮሐንስም በነዚህ ረገድ የተሻለ ታሪክ እንዳለው አረጋግጠዋል፡፡ የአካዳሚክ ትምህርት ደረጃ በመስፈርትነት መግባቱ ተገቢ ነው ወይ ተብሎ ለተጠየቀው ጥያቄ አቶ ጁነይዲ የላቀ ውጤት እና ልምድ ያለው አሰልጣኝ ቢገኝ የትምህርቱ ጉዳይ ከግምት ላይገባ እንደሚችል ሲገልፁ አቶ ቾል ቤል ግን በዮሐንስ ሹመት ሁሉም ሊደሰት እንደሚገባው፣ የእኛ ሀገር አሰልጣኞች ከ12ኛ ክፍል በላይ እንዳልተማሩ እና ቢያንስ ዲፕሎማ የሌለውን ሰው በአሰልጣኝነት እንዲያጩ የሚደረገው ጫና ተገቢ ያልሆነ እና መቼም የማያደርጉት እንደሆነም አስረግጠዋል፡፡ ብዙ ሲባልበት በሰነበተው የአሰልጣኙ ልምድ ዙሪያ አቶ ጁነይዲ ሲናገሩ አዲሱ አሰልጣኝ በ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኑ፣ በደደቢት እና በአሜሪካን ሀገር የማሰልጠን ልምዶች እንዳሉት ገልፀዋል፡፡ እራሱ አሰልጣኝ ዮሐንስ በበኩሉ ታላቁ አሰልጣኝ ጆሴፕ ጋርዲዮላ ያለ ምንም ልምድ ከወጣት ቡድኑ በአንድ ጊዜ ዋናውን የባርሴሎና ቡድን እንዳሰለጠነ በማስታወስ ለእግር ኳስ ስኬት ልምድ የግድ እንዳልሆነ ገልፆ ነገር ግን እርሱ የ20 ዓመታት የአሰልጣኝነት ልምድ እንዳለው ተናግሯል፡፡ የአራት አህጉራት የአሰልጣኝነት ሰርቲፊኬቶች እንዳሉት፣ ከእርሱ ጋር ስልጠናን የጀመሩ ሰዎችም (በሶስት የዓለም ዋንጫዎች የቀረበውን የቀድሞውን የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ቦብ ብራድሌን ለአብነት አንስቶ) አሁን በትልቅ ደረጃ እየሰሩ መሆናቸውን አስታውሷል፡፡ በሊጉ የመስራት ልምድ ከተነሳ ከዚህ ቀደም የሰሩት የውጪ አሰልጣኞች ላይ ይሄ ጥያቄ ለምን እንዳልተነሳ ጠይቋል፡፡ “በአሜሪካን ሀገር የሰራ ዶክተር ኢትዮጵያ ውስጥ መጥቶ ማከም አይችልም?” ሲልም የአሜሪካን ሀገር የማሰልጠን ልምዱ በሚዲያ አስተያየቶች ላይ ለምን እንደሚዘነጋ ጠይቋል፡፡ ሚዲያዎች ከውጪ ሀገር የሚመጡ አሰልጣኞችን ስራ ሲናገሩ ለምን ስለሀገራቸው ሰው በእኩል ደረጃ እንደማያወሩም ቅሬታውን ገልጿል፡፡ በአሜሪካ ሀገር መፀዳጃ ቤት እያጠበ በራሱ ገንዘብ ለተማረው ትምህርትም ተገቢው ክብር ሊሰጥ እንደሚገባ በአንክሮ ገልጿል (ይህን ሲል በአዳራሹ ውስጥ የአድናቆት ጭብጨባ ተሰምቷል)፡፡ አቶ ጁነይዲ እጩዎቹ እንደሚባለው አራት ብቻ ሳይሆኑ (የፌዴሬሽኑ ህዝብ ግንኙነት ባለሙያ በላከው መግለጫ ላይ አራት መሆናቸው ከእነ ስማቸው እና ካገኙት ደረጃ ጋር በግልፅ ተቀምጦ ነበር) በስራ ላይ የሚገኙት አስራ አራቱም የፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች እንደነበሩ እና ለፍጥነት ሲባል ያለ ብዙዎቹ እውቅና ቀድሞውንም በፌዴሬሽኑ እጅ ይገኙ የነበሩት መረጃዎቻቸው እንደተጠኑ ተናግረዋል፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ብዙ ያነጋገረው የቴክኒክ ኮሚቴው ለሹመቱ ዋነኛውን ሚና እንደተጫወተም ገልፀዋል፡፡ በረዳት አሰልጣኞች ጉዳይ እስካሁን ምንም ውሳኔ እንዳልተወሰነ ግን የመምረጥ መብቱ ለአሰልጣኙ እንደተሰጠም አቶ ጁነይዲ ጨምረዋል፡፡

ክፍያ፣ ዝግጅት እና መዋቅር

አሰልጣኙ በብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝነቱ ሊከፈለው በተስማማው ወርሀዊ ደመወዝ ዙሪያም ጥያቄዎች ቀርበው ነበር፡፡ ዮሐንስ በዜግነት አሜሪካዊ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ እንዴት በዶላር ሳይሆን በብር እንደተደራደረ ሲጠየቅ አሜሪካዊ መሆኑ በአንዳንድ ወሳኝ ነገሮች ውስጥ (ደህንነት፣ ውጪ ጉዳይ እና የምርጫ ተሳትፎ) እንዳይሰራ ያደርገው ይሆናል እንጂ ከሌላ ነገር እንደማይከለክለው፣ በዶላር ቢደራደርም እንኳን (በደደቢት ያደርገው እንደነበረው) ከባንክ ሄዶ የሚወስደው በብር እንደሆነ እንዲሁም በገንዘብ ዙሪያ ተደራድሮ እንደማያውቅ እና ወደፊትም እንደማደራደር በመግለፅ ትንሽ ደበስበስ ያለ ምላሽ ሲሰጥ አቶ ጁነይዲ በበኩላቸው ደደቢት ሲገባ፣ ከ17 ዓመት በታች ቡድንን ሲይዝ አሜሪካዊነቱ ሳይነሳ አሁን እንዴት ይነሳል? ብለው ከጠየቁ በኋላ “ዮሐንስ ኢትዮጵያዊ ነው፤ ኢትዮጵያዊ ነው” በማለት አስረግጠዋል፡፡ የደመወዝ መስፈርታችሁ ምንድን ነው? ለሰውነት ቢሻው 50.000 ብር ከዚያ ለማሪያኖ ባሬቶ 18.000 ዶላር አሁን ደግሞ ለዮሐንስ 75.000 ብር… ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ጁነይዲ “እንዴ… ሁለት ለመጋባት የተስማሙን ሰዎች ለምን ተስማማችሁ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው?” ሲሉ ፈገግ የሚያሰኝ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ዮሐንስ ግን ክፍያው ከኃላፊነቱ አንፃር አያንስህም ወይ ተብሎ የቀረበለትን ጥያቄ ሳይመልሰው አልፏል፡፡ ለአፍሪካ ዋንጫ እና ለቻን ማጣሪያዎች እየተደረገ ስላለው ዝግጅት ሲጠየቁ ፕሬዚዳንቱ በሁሉ ረገድ (ትጥቅ፣ የወዳጅነት ጨዋታዎች፣ ሆቴል፣ ሜዳ…) እየተዘጋጁ እንደሆነ እና ምንም አይነት ውዝግቦች እና ሰበቦች እንዳይኖሩ ጠንክረው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በዋልያዎቹ መዋቅር ዙሪያ ዮሐንስ ከሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በሚጓዝ መንገድ ብቻ ሀሳብ እንደሚያቀርብ እና ፌዴሬሽኑ ከተስማማበት ተግባር ላይ እንደሚውል ገልጿል፡፡

ከዮሐንስ ምን ይጠበቃል?

በኮንትራቱ ላይ ስለተቀመጠ መስፈርት ለቀረበው ጥያቄ አቶ ጁነይዲ ከባሬቶ ውዝግብ በተማሩት መሰረት በዮሐንስ ኮንትራት ላይ ዋልያዎቹን ለ2017 አፍሪካ ዋንጫ ማሳለፍ በዋነኛ መስፈርትነት እንደተቀመጠ እና የቻን ውድድር እንደመዘጋጃነት እንደሚታይ ገልፀዋል፡፡ አሰልጣኙ በበኩሉ በሊጉ የውጪ ተጨዋቾች መብዛታቸው ኃላፊነቱን ከባድ ቢያደርግበትም የማይቻል እንዳልሆነ እና ዓላማው ዋልያዎቹን ሁለት፣ ሶስት እርምጃ ወደፊት መውሰድ እንደሆነ ይህንንም ለማሳካት የሚችለውን ሁሉ እንደሚያርግ እና ይህን ማድረግ ካልቻለ ማንንም ሳይጠብቅ በራሱ ፍቃድ እንደሚለቅ አረጋግጧል፡፡ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ እና ለቻን ማጣሪያዎች ሁለት ቡድኖች የመገንባት እቅድ እንዳለው እና የቻኑን ውድድር ወጣቶችን ለመመልከት እና ልምዳቸውን ለማሳደግ ሊጠቀምበት እንዳሰበም አሰልጣኙ ገልጿል፡፡

አወዛጋቢው ቴክኒክ ኮሚቴ

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ከአሰልጣኙ ጉዳዮች ባሻገር የቴክኒክ ኮሚቴው ነገር አነጋጋሪ ርዕስ ሆኖ ነበር፡፡ የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ የቴክኒክ ዴፓርትመንትን እና የቴክኒክ ኮሚቴን ስራዎች የማቀላቀል ሁኔታ እንደሚታይ በመግለፅ ስለሁለቱ አካላት ምንነት ለማብራርት የሞከሩ ቢሆንም ማብራሪያቸው ነገሩን በበለጠ ከማወሳሰብ ያለፈ ተግባር አልተወጣም፡፡ በብሔራዊ ቡድኑ ዙሪያ የሚሰራው የቴክኒክ ኮሚቴው በዮሐንስ ሹመት ላይ ትልቁን ሚና እንደተጫወተ እና ሰሞኑን በተለያዩ ሚዲያዎች ቀርበው እጃቸው እንደሌለበት የሚገልፁ የቴክኒክ ኮሚቴው አባላትም በውሳኔው ተሳትፎ እንደነበራቸው አቶ ዘሪሁንም ሆኑ አቶ ቾል ገልፀዋል፡፡ ከኮሚቴው በፈቃዱ እንደለቀቀ የተናገረው አሰልጣኝ አብረሀም ተክለ ሀይማኖትም ለስራ አስፈፃሚው ያቀረበው የመልቀቂያ ደብዳቤ እንደሌለ እና ይህ ሳይኖር ሊለቅ እንደማይችል በሁለቱ ሰዎች ሲገለፅ በተለይ አቶ ቾል አብረሀም በሚዲያው ሊኮነን እንደሚገባው ምክር ሰጥተዋል፡፡ በቴክኒክ ኮሚቴው ብቃት እና አቅም ላይ ለቀረቡት ጥያቄዎች ደግሞ አቶ ጁነይዲ በጥንቃቄ እየሰሩበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የሰርቲፊኬቶች ጉዳይ

አሰልጣኝ ዮሐንስ በተለያዩ አህጉራት በሰበሰባቸው ሰርቲፊኬቶቹ እውነተኛነት ዙሪያ የማጣራት ስራ ተሰርቶ እንደሆነ የተጠየቁት ፕሬዚዳንቱ አስፈላጊ ሲሆን ለማጣራት እንደማያስቸግር ገልፀው መመልከት የሚፈልግ ሰው ካለ ግን (የሰርቲፊኬቶቹ ዝርዝር ይነገረን የሚል ጥያቄ ቀርቦ ነበር) ወደቢሮ ጎራ እንዲል ጋብዘዋል፡፡

ሌሎች የጎን ጉዳዮች

ማሪያኖ ባሬቶ ሲሰናበቱ ለሚዲያዎች በተላከው ፕሬስ ሪሊዝ መሰረት የሶስት ወር ደሞዛቸው በካሳ መልክ ተከፍሏቸዋል ወይስ ለፖርቹጋላዊው በደረሰው ደብዳቤ መሰረት ምንም አልተከፈላቸውም? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ፕሬዚዳንቱ ለባሬቶ ክፍያው መፈፀሙን አረጋግጠዋል፡፡ በመግለጫው መዘግየት እና የመረጃ እጥረት ዙሪያም አቶ ጁነይዲ መዘግየቱ የተከሰተው የተሟላ መረጃ ይዞ ለመቅረብ ከነበረ ፍላጎት መነሻ መሆኑን አስረድተው የመረጃ እጥረት ለተባለው ግን የየዕለት ስራዎቹን ለሚዲያ ይፋ ለማድረግ የሚገደድ መስሪያ ቤት እንደሌለ አስረግጠዋል፡፡ በመግለጫው ወቅት ያልተገኙት የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተክለወይኒ አሰፋ እየደወሉ ያስፈራሩናል በሚል ከጋዜጠኛ ለቀረበላቸው አስተያየትም አቶ ጁነይዲ ይህን እንደማያውቁ እና ምናልባት በስሜታዊነት የተፈፀመ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

1 thought on ““ከ12ኛ ክፍል በላይ የተማሩ አሰልጣኞች በሌሉበት ሀገር ዮሐንስን ማግኘት ታላቅ ዕድል ነው”

Leave a Reply

Your email address will not be published.