ከፈርጉሰን እስከ አምቦ

liq

liq

ሲ ኤን ኤን እያየሁ ነዉ፡፡ ሚዙሪ በተባለች ግዛት ፈርጉሰን በተሰኘች አነስተኛ ከተማ ስለተፈፀመ ግድያ እና የነዋሪዉን ምላሽ እየዘገበ ነዉ፡፡ ለሳምንት ያህል የክስተቱን አካሄድ አየተከታተልኩ የሀገሬ ፖሊሶች እና አስተዳዳሪዎች ምን አይነት አፀፋዊ ምላሽ ይኖራቸዉ ይሆን ስል ከአእምሮዬ ማህደር የተወሰኑ ትዝታዎችን/ትዉስታዎችን ስቤ ላካፍላችሁ ወደድሁ፡፡ የፈርጉሰን ታሪክ የጽሁፌ መነሻ ሀሳብ እና ክስተቶችን በሩቁ ማነፃፀሪያ እንጂ ዋና ታሪኬ እንዳልሆነ ላሳስብ እወዳለሁ፡፡

ከፈርጉሰን

በቅርብ ጊዜ በአሜሪካ ዉስጥ ፈርጉሰን በተባለች አነስተኛ ከተማ ስለተነሳዉ ብጥብጥ መቼም ሳትሰሙ አትቀሩም፡፡ ወሬዉ በተለያየ ምክንያት ላመለጣችሁ ጉዳዩ እንዲህ ነዉ፡፡ አንድ ጥቁር ወጣት በነጭ ፖሊስ ይገደላል፡፡ የፈርጉሰን ነዋሪዎችም (በተለይ ጥቁሮቹ) ለዘመናት እየተፈፀመብን ያለዉ ዘርን መሰረት ያደረገ ጥቃት ዛሬም አላቆመም ሲሉ ተቃዉሞአቸዉን ይገልፃሉ፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ፤ ከፖሊስ ተጋጩ፤ ላንዱ ሲጨልም ለሌላዉ ይነጋል ነዉና አንዳንድ የእጅ አመለኞችም ሱቃችሁ ከምን ብለዉ ነጋዴዎች ጋር ጎራ ብለዉ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን እንግዲህ ፖሊሶቹም ሆነ አስተዳዳሪዎቹ አንዱን ቀን ጠንከር ሌላ ቀን ደግሞ ላላ እያሉ ህዝቡ እንዲረጋጋ በተማፅኖም በቁጣም እሰጣገባዉ እንዲረግብ እየሞከሩ ነዉ፡፡ ጋሽ ኦባማም ካንድም ሁለቴ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለዉ መደረግ ያለበትን ለማድረግ ቃል ገብተዉ፤ የሟችንም ቤተሰብ ነፍስ የማር ብለዋል፡፡

አካሄዱን በተመለከተ የተለያዩ የድጋፍም የነቀፋም አስተያየቶች እየተሰጡ ቢሆንም ከሞላ ጎደል ይህ አንድ ለህዝቡ ግድ የሚለዉ መንግስት የሚፈመዉ ተግባር ነዉ ብዬ አምናለሁ፡፡ እስቲ ደግሞ ወደዋናዉ ጉዳዬ ልግባና እኛ ሀገር በተላያዩ ጊዜያት የተፈጠሩ ክስተቶችንና ምላሻቸዉን ባጭሩ ላስቃኛችሁ፡፡

በትምህርት ተቋማት በኩል…

ለመጀመሪያ ጊዜ ሰልፍ የወጣሁት ኮሌጅ ሳለሁ ምግብና መኝታ አልተስማማንም በሚል ነበር፡፡ እኛ ተቃዉሞአችንን ሰልፍ በመዉጣት፤ ክፍል ባለመግባት የቅሬታ ደብዳቤ ለኮሌጁ ሀላፊ በማቅረብ ገለፅን፡፡ የተወሰኑ መስታወቶችንም ሰብረናል፡፡ ታዲያ የኮሌጁ አስተዳዳሪዎችና የፖሊስ አፀፋ ምን ሆነ መሰላቸሁ; በወታደር መኪና የታጨቁ ፈጥኖዎች (ወታደሮች) ጊቢዉን ወረሩ፡፡ እጅግ ብዙ ተማሪ እስር ቤት ተወረወረ፡፡ በቀን አንድ ዳቦ እየተወረወረልን ለቀናት መኝት ክፍላች ዉስጥ ለቁም እስር ተዳረግን፡፡ እኔም ‹የምሴን› ‹እንደ እባብ ተራምድ› መሬት ላይ ተብዬ ተንፏቀቅሁ፡፡ ማን ከክፍሌ ዉጣ አለኝ፡፡ ይህ ሳያንስ ምንም ያላደረጉ፤ ተቃዉሞዉ ላይ ያልተሳተፉ ተማሪዎችን ጨምሮ በርካታ የገበሬ ልጆች ወዳጆቼ ከኮሌጁ ተባረሩ፡፡በሬያቸዉን ሸጠዉ የላኩዋቸዉ ወላጆቻቸዉ ጋር ዲግሪ ሳይሆን ቢክ ብዕርና የኮሌጅ ትዝታ ይዘዉ ተመለሱ፡፡ ሰሞኑንም ምንግስት ለ‹ስልጠና› ያስገባቸዉን የከፍተኛ ተቋም ተማሪዎች በተመሳሳይ መልኩ እየተንካበከባቸዉ እንደሆነ ያልተረጋገጠ ወሬ እየሰማን ነዉ፡፡

ወደ አምቦ

አዲስ አበባ አለአግባብ ተነቦራቀቀች፤ መሬታችንን ቀማችን ሲሉ(በሌላም መክንያት ሊሆን ይችላል) ተቃዉሞአቸዉን አሰሙ፡፡ የመልስ ምት…ብዙ ወጣትና አዋቂዎች ተገደሉ (መንግስት 17 አምኗል) ሌሎች ታሰሩ፡፡ አንድ የአይን እማኝ አነዲት ሱቅ ዉስጥ ቸርቻሪ እናትን ‹ምን ተፈጠረ› ቢላቸዉ Hara’aa….sirrii miti (ዛሬ ልክ አይደለም) አሉት፡፡

ያደለዉ አንድ ሰዉ ሲሞትበት ድምፁን አሰምቶ ፍረዱኝ ይላል፡፡ መሪዉ ጆሮ ይሰጠዋል፡፡ እኛ ደግሞ አንድ ሞተ ብለን ወጥተን መቶ ሬሳ ተሸክመን ወደቤታችን እንመለሳለን፡፡ ሌላ መቶ እንዳይሞት ሰግተን ጉዳችን የእናቶች የቡና ጊዜ እና የወጣቶች የድራፍት ወሬ ማድመቂያ ሆኖ ይቋጫል፡፡

ይሄን አሰብኩና ለኛም ቆርጦልን እምቢ የምንልበትን፤ መሪዎቻችን እና ፖሊሱም የሚያስብ አእምሮና የሚራራ ልብ እንዲሰጣቸዉ ፀለይሁ፡፡ እስቲ ከነዚህ አሳዛኝ ወቅቶች በአንዱ ተነሳስቼ ለጠባቂዎቻችን; ለወታደሮቻችን፤ ለመሪዎቻችን የፃፍኳትን ግጥም ልጋብዛችሁ፡፡

የአንገት ቆብ

ማሳዉን ለማረም ደቦ ወጥቶ ወገን

እርሻዉን ለማፅዳት ላይ ታች ሲማስን

ከትጉሃን ጎራ አሻግሬ ስቃኝ

በየጥጋጥጉ መስመር የጠበቁ ብዙ ቆቦች ታዩኝ

ከተኩላዉ ትንኮሳ ሊታደሙን ፈቅደዉ

ዘብ ወጥተዉ ለቆሙት

ከጅቦቹ መንጋ ሊጠብቁን ብለዉ

ከኛዉ ለታደሙት

ትጉህ ወገኖቼ

ምስጋናዬን ልቸር ወዳንዱ ተጠጋሁ

ማንነቱን ልለይ ቆቡን ካረፈበት በድንገት ባነሳዉ

አንገቱን አገኘሁ

Hara’aa….sirrii miti

Leave a Reply

Your email address will not be published.