‹‹ከሪኮርድ ይልቅ ለወርቅ ለሜዳልያው ትኩረት እሰጣለሁ›› ገንዘቤ ዲባባ

Genzebe Dibaba

በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ዛሬ ምሳ ሰዓት ላይ የሚጀመረው 15ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከመጀመሩ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በተዘጋጀው የቅድመ ውድድር ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከተጋበዙት ምርጥ አትሌቶች አንዷ የሆነችው ገንዘቤ ዲባባ በፖላንድ ሶፖት በምትካፈልበት የ3000ሜ. ውድድር ከሪኮርድ ይልቅ ለወርቅ ሜዳልያው ትኩረት እንደምትሰጥ ገልፃለች፡፡ ወደሶፖት ከማቅናቷ በፊት በ15 ቀን ውስጥ ሶስት የዓለም የቤት ውስጥ ምርጥ ሰዓቶችን ማስመዝገብ የቻለችው ገንዘቤ የ2014 የውድድር ዓመት ከተጀመረ ወዲህ በቤት ውስጥ ውድድሮች ያሳየችው ድንቅ አቋም ዋጋዋ በሚሊዮን ዶላሮች የምትገመት አትሌት እንድትሆን ሳያድጋት እንዳልቀረ ይታሰባል፡፡
በርሚንግሀም ውስጥ በተከናወነው የሁለት ማይል ሩጫ ለረጅም ግዜ በመሰረት ደፋር ተይዞ የቆየውን የዓለም የቤት ውስጥ ምርጥ ሰዓት 9:00.48 በሆነ ግዜ ማሻሻሏን ከተመለከተች በኋላ እንግሊዛዊቷ ፓውላ ራድክሊፍ ‹‹ክስተት የሆነችን አትሌት እያየን እንደሆነ አስባለሁ›› የሚል አስተያየትን የሰጠችላት ገንዘቤ አሁን ደግሞ የዲባባ ቤተሰቦች አዲሷ ክስተትነቷን ለማረጋገጥ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማሕበር በፖላንድ ሶፖት ያሰናዳውን የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የ3000ሜ. ውድድር በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች፡፡ ገንዘቤ በዚህ ውድድር ላይ ልታሳካው የምታልመው ነገር – ምንም እንኳ በዚህ ውድድር ላይ ሪኮርድ መስበር የ50 ሺህ ዶላር ተጨማሪ ጉርሻ ቢያስገኝም – በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ ደጋግማ እንዳሳየችን የዓለም ሪኮርድ የሆነ ሰዓትን ማስመዝገብ ሳይሆን የወርቅ ሜዳልያውን መውሰድ ላይ ብቻ ያነጣጠረ ነው፡፡ ባለፈው ወር ስቶክሆልም ውስጥ ባደረገችው ውድድር የ3000ሜ. የቤት ውስጥ ሪኮርዱን ከ8:23.72 ወደ 8:16.60 ዝቅ ማድረጓ አሁን ላይ ጠቀም ያለ ጉርሻ ሊያስገኝ በሚችለው ውድድር ሪኮርድ የመስበሩን ዕድል እንዳጠበባት አስባ ትፀፀት እንደሁ የተጠየቀችው ገንዘቤ ‹‹ከቀደመው የዓለም ሪኮርድ ላይ ወደሰባት ያህል ሰከንዶችን መቀነሴ አያበሳጨኝም፡፡ በስቶክሆልሙ ውድድር ላይ ማወቅ እፈልግ የነበረው ዋነኛ ነገር የብቃቴ ልክ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? በምን ያህል ፍጥነትስ መሮጥ እችላለሁ? የሚለው ነበር፡፡ በዓለም ሻምፒዮናው ላይ ውድድሩን ስለማሸነፍ እንጂ ስለሪኮርድ አላስብም፡፡ ስለፍፃሜው ውድድር ማሰብ የምፈልገውም የማጣሪያ ውድድሩን ካከናወንኩ በኋላ ነው›› ብላለች፡፡
ገንዘቤ በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከሁለት ዓመት በፊት ኢስታንቡል ላይ በ1500 ሜ. የወርቅ ሜዳልያን አሸንፋለች፡፡ ዘንድሮ በ3000ሜ. ለመወዳደር የመረጠችው ለምን ይሆን?
‹‹በዘንድሮው የውድድር ዓመት ከመጀመሪያው አንስቼ ስዘጋጅ የነበረው ለ3000ሜ. ነው›› በማለት ምላሻን የምትጀምረው የቀድሞዋ የ5000ሜ. የዓለም ወጣቶች የ5000ሜ. ሻምፒዮን ‹‹ከሁለት ዓመት በፊት በ1500ሜ. የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮን መሆን ችያለሁ፡፡ እናም ዘንድሮ ሁለቱንም ርቀቶች ስለመወዳደር ተስፋ አድርጌ የነበረ ቢሆንም የማጣሪያ ውድድሮቹ በአንድ አይነት ቀን የሚከናወኑ መሆኑ አንዱን እንድመርጥ አስገድዶኛል፡፡ ስለዚህ ለሀገሬ ጥሩ ውጤት ላስመዘግብ የምችልበትን የ3000ሜ. ውድድር መርጫለሁ›› በማለት አክላለች፡፡
ገንዘቤ በማርች 2008 ስኮትላንድ ኤድንብራ ውስጥ በተከናወነው የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ በወጣቶቹ ምድብ የወርቅ ሜዳልያን ካሸነፈችበት ግዜ አንስቶ ለሀገሯ ጥሩ ነገሮችን ስትሰራ ቆይታለች፡፡ በስኮትላንድ በተካሄደው የአገር አቋራጭ ውድድር የሴቶቹ ምድብ የወርቅ ሜዳልያዎች በሙሉ በዲባባ ቤተሰቦች ቁጥጥር ስር ለመዋል የተገደዱ ሲሆን በወቅቱ የአዋቂዎቹን ውድድር በበላይነት የፈፀመችውም ከገንዘቤ ታላቅ እህቶች አንዷ የሆነችው እና በስሟ ሶስት የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳልያዎችን ያስመዘገበችው ጥሩነሽ ዲባባ ነበረች፡፡ ‹‹ከልጅነቴ ጀምሮ ሕልሜ እንደጥሩነሽ መሆን ነበር›› ያለችው ገንዘቤ ‹‹ምንም እንኳ እርሷ የደረሰችበት ደረጃ ላይ መድረስ ባልችልም አሁን ወደስኬታማነቱ መምጣት ጀምሬያለሁ›› በማለትም ተናግራለች፡፡
በትክክልም ወደስኬታማነቱ እየመጣች የምትገኘው ወጣቷ የዲባባ ቤተሰብ ፍሬ በሶፖቱ ኤርጎ አሬና በምታደርገው የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ውድድር ላይ የትኛውም አይነት ፈተና ቢገጥማትም በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ ሶስት የዓለም ሪኮርዶችን በማሻሻል ያሳየችውን ድንቅ ብቃት መድገም እንደማይሳናት ይታመናል፡፡
ገንዘቤ በሶፖት ከውድድሩ መጀመር በፊት የሰጠችውን ጋዜጣዊ መግለጫ ያጠቃለለችው ‹‹ዘንድሮ ለቤት ውስጥ ውድድሮቹ በከፍተኛ እና በጥሩ ሁኔታ ተዘጋጅቻለሁ፡፡ ሆኖም በ1500ሜ. ጠብቄ የነበረው የዓለም ሪኮርድን መስበር ሳይሆን ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብን ነበር፡፡ ከዛ በኋላ ግን ሌሎቹንም ሪኮርዶች መስበር እንደምችል የእርግጠኝነት ስሜቱ ነበረኝ፡፡ ነገሮች እስካሁን እየሄዱ ባሉበት ሁኔታ በጣም ደስተኛ ስሆን በዚሁ መልኩ እንደሚቀጥሉም ተስፋ አደርጋለሁ›› በማለት ነበር፡፡

3 thoughts on “‹‹ከሪኮርድ ይልቅ ለወርቅ ለሜዳልያው ትኩረት እሰጣለሁ›› ገንዘቤ ዲባባ

  1. genzebe malet ethiopiawiyan jeganu kemibalu 1 yehonech jegina nat edime ena tena yisitat yaegna kurat

Leave a Reply

Your email address will not be published.