ኦፌኮ ስለ ምርጫው ያወጣው መግለጫ ተቀባይነት የለውም ተባለ

2021-06-21T080146Z_897151423_RC2V4O9BE5V4_RTRMADP_3_ETHIOPIA-ELECTION-e1624270501300

የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)፤ 6ኛውን አገር አቀፍ ምርጫ፣ ህዝቡን ያላካተተና ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የማይፈጥር በመሆኑ ለምርጫው ዕውቅና እንደማይሰጥና ጠቁሞ፤ ብሔራዊ መግባባትና እርቅ ተፈጥሮ በአንድ ዓመት  ውስጥ አጠቃላይ አገራዊ ምርጫ ሊደረግ ይገባል  ብሏል፡፡ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ፣ “ኦፌኮ ለምርጫው ዕውቅና መስጠትም ሆነ መንፈግ አይችልም” ብሏል፡፡
ፓርቲው በመግለጫው ላይ እንዳሰፈረው፤ ላለፉት ሶስት ዓመታት በአገሪቱ ስኬታማ የዴሞክራሲ ሽግግር እንዲደረግ ከፍተኛ ጥረት ሲደርግ መቆየቱን አመልክቶ ከ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ተገፍቼ ነው የወጣሁት ብሏል፡፡
ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም  በተደረገው አገር አቀፍ ምርጫ ውስጥ ያልተሳተፈው ኦፌኮ፤ ሁሉን አካታች የጋራ መንግስት እንዲቋቋምና ብሔራዊ የመግባባት ድርድር እንዲጀመር እንዲሁም በአንድ ዓመት ግዜ ውስጥ ሁሉን አቀፍ ነፃ ፍትሃዊና  ተቀባይነት ያለው ምርጫ እንዲካሄድ ጠይቋል፡፡
የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ከትናንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ ላይ አንደተናገሩት፤ ፓርቲው በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ውስጥ ያልተሳተፈ በመሆኑና በምርጫው ሂደት ውስጥ አብሮን ስላልተጓዘ ሂደቱ እንዴት እንደነበር ሙሉ ዕውቀቱ ይኖረዋል ብዬ አላስብም፤ ነገር ግን የግሉን አስተያየት የመስጠት መብት አለው ብለዋል፡፡ ለምርጫው ዕውቅና የመሰጠትም ሆነ የመንፈግ መብት ግን የለውም፤ ይህ አባባል ብዙም ዋጋ የሚሰጠው ሊሆን አይችልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ሃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ፤ ኦፌኮ ቀድሞውንም በምርጫ የሚያምን ፓርቲ አይደለም ብለዋል፡፡
ፓርቲው ከአመት በፊት ምርጫው መደረግ አለበት ሲል መቆየቱን ያስታወሱት አቶ ታዬ ደንዳአ፤ ምርጫው በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ሲራዘም በፅኑ ተቃውሟል፤ ከዚያ በኋላ ደግሞ ምርጫው ይደረግ ተብሎ ሲወሰን አመራሮቼ ካልተፈቱ አልሳተፍም ብሎ ራሱን አግልሏል ብለዋል፡፡
ኦፌኮ በምርጫው እንዲሣተፍ ብዙ ጥረት መደረጉን ያወሱት ሃላፊው፤ ፓርቲው ግን ሽምግልናውን ሁሉ አልቀበልም በማለት አሻፈረኝ ማለቱንም ገልጸዋል፡፡ የዘንድሮ ምርጫ ኦፌኮ ቀደም ባሉት ዓመታት ሲሳተፍበት ከቆየው ምርጫ አንጻር ሲታይ በእጅጉ የተሻለ ነው ያሉት አቶ ታዬ፤ የምርጫ ቦርድ ከቀደመው የተሻለ ተቋማዊ ብቃት ያለው፣ ፍርድ ቤቶች ከመንግስት ፍላጎት በተቃራኒው በነጻነት የሚወስኑበት፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን መንግስትን የሚተቹ ሪፖርቶችን የሚያወጣበትና በአጠቃላይ የፖለቲካ ምህዳሩ በእጅጉ በሰፋበት ሁኔታ የተካሄደ ምርጫ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ምርጫውን አንቀበልም ማለት በጨዋነት እነዛን ረዣዥም ሰልፎች ጠብቆ፣ ዝናብና ፀሐይ ሣይበግረው የሚፈልገውን የመረጠውን ህዝብም መናቅ ነው ያሉት አቶ ታዬ፤ ኦፌኮ በምርጫው ሣይወዳደር መቅረቱ ካስቆጨው፣  ከ5 ዓመት በኋላ ለሚካሄደው ቀጣዩ ምርጫ ራሱን አዘጋጅቶ ሊቀርብ ይችላልብለዋል።
የህግ ጠበቃውና ፖለቲከኛው አቶ ወንድሙ ኢብሳ ከአዲስ አድማስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ ኦፌኮ ከምርጫው ለመውጣት ሲወሰን ታላቅ ታሪካዊ ስህተት መፈፀሙን ገልፀው፤ አሁንም ደግሞ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የመረጡትን ምርጫ አልቀበልም ብሎ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም መጠየቁ ከድጡ ወደ ማጡ መሄዱን የሚያመለክት ነው ብሏል፡፡ ፓርቲው በዚሁ መንገድ ከቀጠለ በጣም መጥፎ የታሪክ ሞት የሚሞት ፓርቲ ይሆናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ከ37 ሚሊዮን በላይ መራጭበ 47 ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን ባቀረቡበት በዚህ ምርጫ ውስጥ ያልተሳተፈው ኦፌኮ፤ ምርጫው የአገሪቱን ፍላጎት የማያሟላና ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ሊያመጣ የማይችል ነው ሲል ዕውቅና ነፍጎታል፡፡ 

አዲስ አድማስ