ኢትዮጵያ ቡና ወደ ድል ቢመለስም አነጋጋሪ ክስተቶችን ማስተናገዱን ቀጥሏል

አሰልጣኝ ፖፓዲች

  • የኢትዮጵያ ቡና አመራሮች ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶባቸዋል
  • አሰልጣኝ ፖፓዲች ‹‹ውጡልን›› ተብለዋል
  • ዳኝነቱ ለውዝግብ ምክንያት ሆኗል
  • ሀዲያ ሆሳዕና የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል

የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሜዳ ላይ ፉክክሩ እምብዛም ባይማርክም ሜዳ ላይ እና ከሜዳ ውጪ እየተከሰቱ ባሉ አነጋጋሪ ጉዳዮች ከፍ ያለ ትኩረት ስቧል፡፡ የዳኝነት ውዝግቦች፣ የተቃውሞ መግለጫዎች፣ የደጋፊ ስርአት-አልበኝነት… የሳምንት ከሳምንት የተለመዱ ክስተቶች ሆነዋል፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ ቡና ከውዝግብ እና ከድራማዊ ክስተቶች ጋር የተዛመደ እስኪመስል በየጨዋታው የተለያዩ ትኩረት የሚስቡ ጉዳዮችን ማስተናገድን ተያይዞታል፡፡ ቡናማዎቹ በደደቢት በተረቱበት ጨዋታ ላይ የተፈፀሙት ከዳኝነት ውሳኔዎች ጋር የተያያዙ ክስተቶች እና ከጨዋታው በኋላ የክለቡ ኃላፊዎች የሰጡት አነጋጋሪ ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ለግማሽ ሰዓት ጨዋታውን እስከማስቋረጥ የደረሰው የሀዋሳ ስታዲየሙ የደጋፊዎች ግጭት፣ በጥሎ ማለፉ ሀዲያ ሆሳዕናን በመለያ ምቶች ሲረቱ ደጋፊዎች ፖሊስን በመቃወም ከስታዲየም ጥለው የወጡበት ክስተት ብዙ ያነጋገሩ ነበሩ፡፡ በእነዚህ ደረጃ ብዙ ባያስብልም በሲዳማ ቡና በተረቱበት ጨዋታ ላይ ደግሞ ቡድኑም ሆነ አሰልጣኙ መጠነኛ ተቃውሞ ከራሳቸው ደጋፊ ገጥሟቸው ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ቡናዎች ከዚህ ሽንፈት እና በተሻለ አቋም ከድሬዳዋ ከተማ አቻ ተለያይተው ከተመለሱበት ጨዋታ በኋላ በሜዳቸው ሀዲያ ሆሳዕናን ሲያስተናግዱ እነዚህን ሁሉ ስሜቶች ይዘው ነበር፡፡ ደጋፊው በቡድኑ ተከታታይ ደካማ ውጤቶች በመከፋት ስሜት ውስጥ ሆኖ እንዲሁም አሰልጣኙ፣ ተጨዋቾቹ እና የክለቡ ቦርድ ከፍ ያለ ጫና ውስጥ ሆነው ጨዋታውን ጀምረዋል፡፡ በአሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲች የሚመሩት ቡናማዎቹ በጉዳት ላይ የሰነበተው ግብ ጠባቂያቸው ሀሪስተን ኮአሲን በቋሚዎቹ መካከል ሲያቆሙ፣ አብዱልከሪም መሀመድ (ቀኝ) እና ሳላምላክ ተገኝን (ግራ) በመስመር ተከላካይ እንዲሁም ወንድይፍራው ጌታሁን እና ኤፍሬም ወንድወሰንን በመሀል ተከላካይ ስፍራዎች አስጀምረዋል፡፡ ጋቶች ፓኖም ከእነሱ ፊት ሲሰለፍ፣ ጥላሁን ወልዴ፣ ኤልያስ ማሞ፣ መስኡድ መሀመድ እና እያሱ ታምሩ ከብቸኛ አጥቂው ዊልያም ያቡን ጀርባ ጨዋታውን ጀምረዋል፡፡ በሜዳቸው በወራጅ ቀጠና ተፎካካሪያቸው በኤሌክትሪክ ከደረሰባቸው ሽንፈት በኋላ ወደዚህ ጨዋታ የመጡት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በበኩላቸው ጃክሰን ፊጣ (ግብ ጠባቂ)፣ ታረቀኝ ጥበቡ፣ ቢኒያም ገመቹ፣ እርቅይሁን ተስፋዬ እና ሄኖክ አርፊጮ (ተከላካዮች)፣ አግላን ቃሲም፣ አበው ታምሩ፣ አበባየሁ ዮሐንስ፣ አየለ ተስፋዬ እና አምራላ ደልታታ (አማካዮች) እንዲሁም እንዳለ ደባልቄን (አጥቂ) ተሰላፊ አድርገዋል፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሁለቱ መካከል ከተደረገው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ በተለየ ይህኛው ጨዋታ አጀማመሩ ፈጣን፣ አይን-ሳቢ እና ፉክክር የተሞላበት ነበር፡፡ ይህኛው ጨዋታ በዚያ ጨዋታ ሙሉ ጊዜ ከተደረጉ የጎል ሙከራዎች የበለጡ ሙከራዎችን በመጀመሪያው ሩብ ሰዓት ውስጥ ብቻ መመልከት ችሎ ነበር፡፡ በዘጠነኛው ደቂቃ ኤልያስ ማሞ ከሩቅ የመታው ኳስ አግዳሚ  ሲመልስበት፣ በ11ኛው ደቂቃ የሀዲያ ሆሳዕናው አምራላ ደልታታ በጭንቅላቱ የሞከረው ኳስ ጎል ከመሆን የዳነው በሀሪስተን ኮአሲ አስደናቂ ጥረት ነበር፡፡ ከዚያ ግን በ19ኛው ደቂቃ ላይ ቡናማዎቹን በበለጠ ጫና ውስጥ የከተተ፣ የስታዲየሙን ድባብ የለወጠ፣ ያልተጠበቀ ክስተት ሆነ – የሀዲያ ሆሳዕናው አጥቂ እንዳለ ደባልቄ ከፍፁም ቅጣት ክልል ውጪ በመሬት የመታው ኳስ ሀሪስተንን አልፎ የቡና መረብ ውስጥ ተገኘ፡፡ ጎሉ በተለይም ከሀዲያ ሆሳዕና ጎል ኋላ ዳፍ-ትራክ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ የታደሙ የአግቢውን ቡድን ደጋፊዎችን በደስታ ሲያስፈነጥዝም በአብዛኛው የስታዲየሙ ክፍሎች የነበሩትን የባለሜዳዎቹን ደጋፊዎች በድንጋጤ ዝምታ ውስጥ ከትቷል፡፡ ደጋፊዎቹ በድንጋጤ ረጭ ይበሉ እንጂ በቀጣዮቹ ደቂቃዎች የቡና ተጨዋቾች ጎል አስቆጥረው ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት አድርገዋል፡፡ በ25ኛው ደቂቃ ጋቶች ፓኖም ከኤልያስ እና ከመስኡድ መሀመድ ጋር አንድ-ሁለት ከተጫወተ በኋላ መሬት አስታኮ የመታው ኳስ ወደ ውጪ ሲወጣበት፣ በ30ኛው ደቂቃ በድንቅ ቅብብል የመጣውን ኳስ ጥላሁን ወልዴ ወደ ጎል ሞክሮት ኢላማውን ማግኘት ሳይችል ቀርቷል፡፡ በ32ኛው ደቂቃ ኤልያስ ያሻገረው ጥሩ ቅጣት ምት ማንንም ሳያገኝ ለጥቂት ወጥቷል፡፡ በ34ኛው ደቂቃ መስኡድ ከፍፁም ቅጣት ክልል ውጪ በአየር ላይ ተገልብጦ ወደጎል የሞከረው አስደናቂ ኳስ በግብ ጠባቂው ጃክሰን ፊጣ ተጨርፎ ጎል ከመሆን ተርፏል፡፡ በ37ኛው ደቂቃ ኤልያስ በጥሩ ሁኔታ ወደውስጥ ገብቶ ለጥላሁን አቀብሎት ከቡድን ጓደኛው በማራኪ ተረከዝ በተመለሰለት ኳስ ከግብ ጠባቂ ፊት ለፊት ቢገናኝም ወደጎል የሞከረው ኳስ በአግዳሚው ላይ ወጥቶበታል፡፡ የፖፓዲች ቡድን ሜዳ ላይ የአቻነት ጎል ለማግኘት ጫናውን ቢያበዛም በ40ኛው ደቂቃ ላይ በተለይም በቀኝ ጥላ-ፎቅ እና በክቡር ትሪቢዩን ስፍራዎች የጨዋታው በጣም አነጋጋሪው ሁነት ተከሰተ፡፡ ቡድኑ የተመሰረተበትን 40ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በሚመስል ሁኔታ በዚህ ደቂቃ ላይ በተለይም ከላይ በተጠቀሱት ስፍራዎች ላይ የነበሩት የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በክለባቸው አመራር ላይ በህብረት ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ ‹‹ኮሚቴው ይልቀቅልን››፣ ‹‹ኢትዮጵያ ቡና የህዝብ ነው›› የሚሉትን ጨምሮ የአመራሮችን ስም እስካነሱ ተቃውሞዎች እና ስድቦች ድረስ ተሰምተዋል፡፡ አመራሮችን በአካል ለማጥቃት የሚመስሉ ሙከራዎችም ከጥቂት ደጋፊዎችም ቢሆን ታይተው ነበር፡፡ ይህ በአዲስ አበባ ስታዲየም በዚህ ደረጃ ተስተውሎ የማያውቅ የራስን ቡድን የመቃወም ድርጊት በእረፍቱ ሰዓትም ላይ ቀጥሎ ታይቷል፡፡ ጨዋታው በዚሁ ውጤት ከተጠናቀቀ ምን ሊከሰት እንደሚችል በርካቶች ለመገመት ይሞክሩም ነበር፡፡ ቡድኖቹ ለሁለተኛው አጋማሽ እንደተመለሱ ውጥረቱን ሊያባብስ እና ነገሮችን ሊያጦዝ የሚችል እንቅስቃሴ ከሀዲያ ሆሳዕናው አጥቂ እንዳለ ተነሳ፡፡ በክረምቱ የኢትዮጵያ ቡና ንብረት የነበረው እና በሰርቢያዊው አሰልጣኝ ባለመፈለጉ የለቀቀው ፈጣኑ አጥቂ በቡና ተከላካዮች መካከል የሰጠውን ኳስ አምራላ ደልታታ ብቻውን አግኝቶ ወደ ጎል ቢያመራም የተጋጣሚው ተከላካዮች ደርሰውበት ወድቆ አጋጣሚውን ሳይጠቀምበት ቀርቷል፤ የቡና ደጋፊዎች የሴኮንዶች ድንጋጤም ረገብ ብሏል፡፡ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ተጨዋቻቸው ተጠልፎ እንደወደቀ እና ፍፁም ቅጣት ምት እንደሚገባቸው ቅሬታ ቢያቀርቡም አርቢትሩ ጨዋታውን አስቀጥለዋል፡፡ በ52ኛው ደቂቃ ቡናማዎቹ በማራኪ ቅብብል ወደ ጎል አምርተው ዊልያም ያቡን ያዘጋጀለትን ኳስ ጥላሁን ወደ ጎል መትቶት ኢላማውን ሳያገኝ በአግዳሚው ላይ ወጥቶበታል፡፡ ኢትዮጵያ ቡናዎች ተደጋጋሚ ጫናቸው በ60ኛው ደቂቃ ፍሬ አስገኝቶላቸዋል – ኤልያስ ተከላካዮችን በጥሩ መንገድ አልፎ በጫና ውስጥ ለአብዱልከሪም መሀመድ ያቀበለውን ታታሪው የቀኝ ተከላካይ በቀጥታ በመምታት አቻ ያደረገቻቸውን ድንቅ ጎል ማስቆጠር ችሏል፡፡ ከጎሉ ጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ቡናዎች ተጨማሪ የማሸነፊያ ጎል ለማግኘት በተፈጠረባቸው ተስፋ ይመስላል አማካዮቹ ኤልያስ እና ጥላሁንን በማስወጣት በግዙፎቹ አጥቂዎች ፓትሪክ ቤናውን እና አርሲን ፊልስ ተክተዋቸዋል፡፡ ፊት መስመሩም በሶስት ካሜሩናዊያን ተይዟል፡፡ ነገር ግን አሰልጣኙ ተስፋ እንዳደረጉት ወዲያው ጎል ሊገኝ አልቻለም፤ እንዲያውም የመጀመሪያው ጎል በተቆጠረበት ጊዜ ላይ ቡድኑ ፈጥሮት የነበረው የማጥቃት ቅኝት እና ቅርፅ የጠፋ መስሏል፡፡ ቡድኑ የጎል ሙከራዎችም ማድረግ የተሳነው ሲሆን በ87ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ዮሐንስንም በኢያሱ ታምሩ ምትክ አስገብቷል፡፡ ቡናማዎቹ የጓጉለትን የማሸነፊያ ጎል እና ርቋቸው የሰነበተውን ድል ለማግኘት የተሳናቸው በመሰለበት በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃ ላይም ‹‹ፖፓዲች out›› የሚሉ አሰልጣኙን የሚቃወሙ ድምፆች ተሰምተዋል፤ ፖፓዲችም የሚቃወሟቸው ደጋፊዎች እንዲረጋጉ በምልክት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ከጥቂት የባከኑ ደቂቃዎች በኋላ ጨዋታው በዚሁ ውጤት ሲጠናቀቅ ከፍተኛ ብስጭት ውስጥ በነበሩት የባለሜዳዎቹ ደጋፊዎች ዘንድ ምን ሊፈጠር እንደሚችል እየተገመተ ባለበት ጊዜ ላይ (በ90ኛው ደቂቃ) ግን ከቀኝ መስመር የተገኘው የኢትዮጵያ ቡና የቅጣት ምት ተሻግሮ ተቀይሮ የገባው ፓትሪክ ቤናውን በጭንቅላቱ በመግጨት ለቡናማዎቹ ያልተጠበቀ የማሸነፊያ ጎል አስቆጥሯል፡፡ ስታዲየሙ በተለይም የቡና ደጋፊዎች የታደሙባቸው ስፍራዎች በፈንጠዝያ ሲንቀጠቀጡ አስፈላጊ አንድ ነጥብ ለመውሰድ ተቃርበው የነበሩት የሀዲያ ሆሳዕና ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች ባልጠበቁት ሀዘን ተመትተዋል፡፡ ጨዋታው ሲጠናቀቅም ‹‹ለጨዋታው የማይገባ ብቃት አሳይተዋል›› ባሏቸው የጨዋታው አርቢትሮች ላይ ለመምታት እስከመጋበዝ እና የተጠባባቂ ወንበር መደገፊያን እስከ መስበር ያደረሰ ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ የቡና ተጨዋቾች፣ አሰልጣኝ እና አመራሮች በበኩላቸው በወሳኟ ጎል፣ ከተደገሰላቸው ተቃውሞ ተርፈው ከስታዲየም ለቅቀዋል፡፡

አሰልጣኝ ፖፓዲች
አሰልጣኝ ፖፓዲች

ከጨዋታው በኋላ የቡድኖቹ አሰልጣኞች በሰጧቸው አጭር ቃለ-መጠይቆች ፖፓዲች ‹‹በመጥፎ ጊዜም ከጎናችን አልተለዩም›› ያሏቸውን ደጋፊዎቻቸውን ሲያመሰግኑ፣ ሀዲያ ሆሳዕና ደካማ ውጤቶቹ የማይመጥኑት ጠንካራ ቡድን በመሆኑ ሊጠነቀቁት እንደሚገባ ለተጨዋቾቻቸው ነግረዋቸው እንደገቡ ይህም ሜዳ ላይ እንደታየ ገልፀዋል፡፡ የተሸናፊው ሀዲያ ሆሳዕና አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ በበኩላቸው ደካማ እና ለጨዋታው የማይመጥን ዳኝነት ነጥባቸውን እንዳስነጠቃቸው ተናግረዋል፡፡ ከጨዋታው በኋላም ሀዲያ ሆሳዕናዎች በሊጉ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ እንዲቀመጡ ምክንያት የሆነው ተደጋጋሚ የዳኝነት ችግር ካልተስተካከለ ራሳቸውን ከሊጉ እስከማግለል እንደሚደርሱ ለእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ባስገቡት ደብዳቤ አስጠንቅቀዋል፡፡

 

በሌሎች ጨዋታዎች፡-

  • ደደቢት በሜዳው ድሬዳዋ ከተማን 2ለ0 በመርታት ሶስተኛ ደረጃውን አስጠብቋል፤ ተስተካካይ ጨዋታ ወደሚቀራቸው መሪዎችም ተጠግቷል፡፡ ለሰማያዊዎቹ ሁለቱንም ጎሎች ያስቆጠረው ሽመክት ጉግሳ ሲሆን ከ25 ሜትር ገደማ በመምታት ያስቆጠረው ጎል አስደናቂ ነበር፡፡
  • በጥሩ የውጤት ጉዞ ላይ የነበረው ሲዳማ ቡና ከሜዳው ውጪ በአርባምንጭ ከተማ ሽንፈት ደርሶበታል፡፡ አርባምንጮች ተሾመ ታደሰ፣ በረከት ወልደፃዲቅ እና ታደለ መንገሻ (ፍ.ቅ.ም) ባስቆጠሯቸው ጎሎች 3ለ1 አሸንፈዋል፡፡ ኤሪክ ሙራንዳ ለሲዳማ ቡና አስቆጥሯል፡፡
  • ባለፈው ውድድር ዘመን ላለመውረድ ተፋልመው በመጨረሻ የተረፉት ዳሸን ቢራ እና ሀዋሳ ከተማ በባህርዳር ስታዲየም ባደረጉት ጨዋታ ያለጎል አቻ ተለያይተዋል፡፡
  • በ11ኛው ሳምንት ጨዋታው ወደ ቦዲቲ ተጉዞ በወላይታ ድቻ የውድድር ዘመኑ ሁለተኛ ሽንፈቱን የቀምሰው ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አዳማ ከተማ ሀሙስ በሜዳው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ሲያስተናግድ፣ ከድል የተመለሱት ኤሌክትሪክ እና ወላይታ ድቻ አዲስ አበባ ላይ ይፋለማሉ፡፡ ለአህጉራዊ ጨዋታዎች ከሀገር ወጥተው የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ የሚያደርጉት ጨዋታ ተራዝሟል፡፡
  • ካልተጠናቀቁት የ12ኛው ሳምንት ጨዋታዎች በኋላ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት ቅዱስ ጊዮርጊስ በ23 ነጥቦች በመሪነቱ ሲቀጥል አንድ ጨዋታ የሚቀረው አዳማ ከተማ በተመሳሳይ 23 ነጥቦች በግብ ክፍያ ተበልጦ ይከተላል፡፡ ደደቢት በ22፣ ሲዳማ ቡና በ17፣ አንድ ጨዋታ የሚቀራቸው ድሬዳዋ ከተማ በ17 እና ወላይታ ድቻ በ16 ነጥቦች እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና በ15 ነጥቦች እስከ ደረጃ ሰንጠረዡ አጋማሽ ያሉትን ስፍራዎች ይዘዋል፡፡ ዳሸን ቢራ እና ሀዲያ ሆሳዕና በ12 እና አምስት ነጥቦች በቅደም ተከተል የሊጉ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ ይገኛሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.