ኢትዮጵያ ቡና በአስደናቂ አቋም ደደቢትን ረትቷል

13147829_1006620506074258_7861940163003704721_o

ሁሌም በከፍተኛ ጉጉት የሚጠበቀው የደደቢት እና ኢትዮጵያ ቡና ፍልሚያ እንደተለመደው በድማቅ ድባብ እና በማራኪ እንቅስቃሴ ታጅቦ ተካሂዷል፡፡ የአዲስ አበባ ስታዲየም በቅርብ ሳምንታት ዝናብ ምክንያት ጭቃ መሆን የተለመደውን የሁለቱን ቡድኖች እግር ኳሳዊ ፍልሚያ ላያዩ እንደሚችሉ ብዙዎችን ስጋት ውስጥ ከትቶ የነበረ ቢሆንም ሜዳ ላይ የታየው ግን በተቃራኒው ነበር፡፡ ከጨዋታው በፊት በአንድ ደረጃ እና አንድ ነጥብ ብቻ ይራራቁ የነበሩት ሁለቱ ቡድኖች (ደደቢት በ29 ነጥቦች ሶስተኛ እና ኢትዮጵያ ቡና በ28 አራተኛ ደረጃ ላይ ነበሩ) በሚከተሉት አሰላለፎች ወደሜዳ ገብተዋል፡፡

ደደቢት (4-4-2 የሚመስል)

ግብ ጠባቂ፡- ታሪክ ጌትነት

ተከላካዮች፡- ብሩክ ተሾመ፣ አክሊሉ አየነው፣ ምኞት ደበበ እና ተካልኝ ደጀኔ

አማካዮች፡- ሽመክት ጉግሳ፣ ያሬድ ዝናቡ፣ ሳምሶን ጥላሁን እና ብርሀኑ ቦጋለ

አጥቂዎች፡- ዳዊት ፍቃዱ እና ሳሙኤል ሳኑሚ

ኢትዮጵያ ቡና (4-1-4-1 የሚመስል)

ግብ ጠባቂ፡- ሀሪስተን ኮአሲ

ተከላካዮች፡- አብዱልከሪም መሀመድ፣ ወንድይፍራው ጌታሁን፣ ኤፍሬም ወንድወሰን እና አህመድ ረሺድ

አማካዮች፡- ጋቶች ፓኖም፣ መስኡድ መሀመድ፣ ኤልያስ ማሞ፣ ኢያሱ ታምሩ እና አማኑኤል ዮሀንስ

አጥቂ፡- ሳዲቅ ሴቾ

ጨዋታው በአርቢትሩ ፊሽካ ተጀምሮ ደጋፊዎች ወደ መቀመጫዎቻቸው ሳይመለሱ ነበር ምናልባትም የጨዋታውን ሂደት የቀየረ ክስተት የተፈፀመው፡፡ ኢትዮጵያ ቡናዎች ከማእዘን ምት ያሻገሩትን ኳስ ነፃ የነበረው ሳዲቅ ሴቾ በጭንቅላቱ በመግጨት ገና በሁለተኛው ደቂቃ ቡድኑን መሪ ያደረገ ጎል ማስቆጠር ችሏል፡፡ ባለፉት ሳምንታት የደጋፊዎቹ የትችት ኢላማ የነበረው ሳዲቅ ጎሉን ካስቆጠረ በኋላ ያሳየው ፈንጠዝያ የነበረበትን ጫና የሚያሳይ ነበር፡፡ በተከታዮቹ ደቂቃዎች ቡናማዎቹ ኳሱን በሚገባ መቆጣጠር ችለዋል፡፡ በ14ኛው ደቂቃም ጋቶች ፓኖም ከርቀት መሬት ለመሬት የመታው ኳስ ወጥቶበታል፡፡ በ17ኛው ደቂቃ አብዱልከሪም መሀመድ እና ኢያሱ ታምሩ አንድ-ሁለት ተቀባብለው ገብተው አብዱልከሪም ከጠበበ ማእዘን ወደጎል የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት ቢያገኘውም በሚገባ መያዝ ባለመቻሉ አጠገቡ የነበረው ሳዲቅ ለቡድኑም ሆነ ለእራሱ ሁለተኛውን ጎል አስቆጥሯል፡፡ ይህ ጎል ቀድሞውኑም በእንቅስቃሴ የተበለጡትን ሰማያዊዎቹን ይበልጥ ተስፋ ያቆረጠ የመሰለ ነበር፡፡ በ20ኛው ደቂቃ ደደቢቶች የመጀመሪያ ሊባል የሚችል የጎል ሙከራቸውን በዳዊት ፍቃዱ አማካይነት አድርገው ወደውጪ ወጥቶባቸዋል፡፡ ከዚያ ግን በ25ኛው ደቂቃ ላይ በጣም ጥሩ የሚባል የማግባት አጋጣሚ ቢፈጥሩም ከግብ ጠባቂው ፊት ለፊት የተገናኘው ሳሙኤል ሳኑሚ እድሉን ሳይጠቀምበት ሙከራው በሀሪስተን ኮአሲ ብቃት ከሽፎበታል፡፡ በ32ኛው ደቂቃ ጋቶች በመሬት የመታው የቅጣት ምት በታሪክ ጎል ከመሆን ተመልሷል፡፡ 41ኛው ደቂቃ ላይ ቡናዎች በአስደናቂ ቅብብል ከሄዱ በኋላ አማኑኤል ዮሐንስ ከመስኡድ መሀመድ የተቀበለውን ኳስ በድንቅ መንገድ ተቆጣጥሮ እና ተጨዋቾችን አልፎ ወደጎል መትቶ ለጥቂት በአግዳሚው ላይ ወጥቶበታል፡፡ 44ኛው ደቂቃ ላይ ሳኑሚ ወደጎል የመታው ኳስ በአግዳሚው ላይ ወጥቶበት የመጀመሪያው አጋማሽ በኢትዮጵያ ቡና የ2ለ0 መሪነት ተጠናቋል፡፡

ቡድኖቹ ለሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታ ወደሜዳ ሲመለሱ፣ የደደቢቱ አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት ሁለት ቅያሬዎችን አድርገዋል፡፡ በአቋም ይሁን በጉዳት ባይታወቅም ግብ ጠባቂው ታሪክን እና አማካዩ ያሬድ ዝናቡን አስወጥተው፣ በቅደም ተከተል በብርሀነ ፍስሀዬ እና ሄኖክ ካሳሁን ተክተዋቸዋል፡፡ ገና እንደተጀመረም ወንድይፍራው ጌታሁን በሰራው ስህተት ሳኑሚ ጥሩ እድል ቢፈጠርለትም ይህንንም ኳስ በአግዳሚው ላይ ልኮ ቀኑ እንዳልሆነ አረጋግጧል፡፡ በ51ኛው ደቂቃ ከመስኡድ የተነሳን ኳስ ሳዲቅ በግብ ጠባቂው ብርሀነ ስህተት ታግዞ ሶስተኛ ጎሉን ቢያስቆጥርም ከጨዋታ ውጪ ተብሎ ተሽሮበታል፡፡ በ54ኛው ደቂቃ ደደቢቶችም ከማእዘን በተሻገረ ኳስ ጎል ቢያስቆጥሩም ሀሪስተን ላይ ጥፋት ተሰርቷል በሚል ምክንያት አርቢትሩ ሳያፀድቁት ቀርተዋል፡፡ በ56ኛው ደቂቃ ሳኑሚ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ብርሀኑ ቦጋለ በቮሊ ወደጎል ቢሞክረውም ለጥቂት ወደውጪ ወጥቶበታል፡፡ በ60ኛው ደቂቃ ቡናዎች ተከታታይ አጋጣሚዎችን አግኝተው በደደቢት ግብ ጠባቂ እና ተከላካዮች ርብርብ ጎል ሳይሆን ቀርቷል – በመጀመሪያ አህመድ ረሺድ በመሬት ወደጎል አካባቢ የላከውን ብርሀነ ሲያወጣ፣ ኢያሱ ታምሩ ደርሶ ወደጎል ቢሞክርም ብሩክ ተሾመ መልሶበታል፤ ከዚያ እንደገና መስኡድ ወደጎል አሻግሮ ኢያሱ በጭንቅላቱ ወደጎል ቢሞክርም በአግዳሚው ላይ ወጥቶበታል፡፡ በ63ኛው ደቂቃ ዳዊት ፍቃዱ በመሬት አጠንክሮ የመታው ኳስ በሀሪስተን ተይዟል፡፡ ግብ ጠባቂው ኳሱን ከያዘ በኋላ አላስፈላጊ የመገልበጥ (ሮል የማድረግ) ትርኢት አሳይቷል፡፡ ይህ የደጋፊ ‹‹ጩኸት›› ለሚወድ ለሚመስለው ሀሪስተን ሁለተኛ ተመሳሳይ ድርጊቱ ነበር፡፡ በ64ኛው ደቂቃ አህመድ ከብሩክ ኳስ ቀምቶ ለኤልያስ ካቀበለ በኋላ ኤልያስ ከፍ አድርጎ ያቀበለው ኳስ ከግብ ጠባቂው ጋር ቢያገናኘውም ሙከራው ኃይል ስላልነበረው በብርሀነ ተይዞበታል፡፡ ከዚያ በኋላ ጨዋታው የኃይል አጨዋወት አመዝኖበት የማስጠንቀቂያ ካርዶች ተመዘዋል፡፡ በ78ኛው ደቂቃ ሳኑሚ በቡና ፍፁም ቅጣት ክልል በወንድይፍራው ተገፍቶ ቢወድቅም አርቢትሩ ፍፁም ቅጣት ምት ሊሰጡ አልፈቀዱም፡፡ በዚሁ ደቂቃ ላይ ቡናማዎቹ አማኑኤልን አስወጥተው በጥላሁን ወልዴ በመተካት የመጀመሪያ ቅያሬያቸውን ፈፅመዋል፡፡ በ83ኛው ደቂቃ አህመድ ተከላካዮችን በቀላሉ ካለፈ በኋላ ከቅርብ ርቀት ወደጎል የመታው ኳስ በአግዳሚው ላይ ወጥቶበታል፡፡ በ85ኛው ደቂቃ ቡናዎች ጨዋታውን የገደሉበትን ጎል በእለቱ ልማደኛ ሳዲቅ አማካይነት አስቆጥረዋል፡፡ መስኡድ የደደቢትን የጨዋታ ውጪ ወጥመድ ጥሶ ገብቶ ከግብ ጠባቂው ፊት ለፊት ከተገናኘ በኋላ፣ ራሱ ከማግባት ይልቅ ሮጦ ለመጣው ሳዲቅ አቀብሎት የቡድን ጓደኛው ሀት-ትሪኩን እንዲሰራ አድርጎታል፡፡ ከጎሉ በኋላ ደደቢቶች የመጨረሻ ቅያሬያቸውን በማድረግ ብሩክን አስወጥተው ጆሴፍ አግዮኪን አስገብተዋል፡፡ ከዚያ በኋላ የሚጠቀሱ ክስተቶች ሳይታዩ በኢትዮጵያ ቡና የ3ለ0 ድል ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

በሌሎች ጨዋታዎች፡-

  • መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ሆሳዕና አምርቶ በሰልሀዲን ሰዒድ ሁለት ጎሎች የሊጉን ወለል ሀዲያ ሆሳዕናን 2ለ0 ረትቷል፡፡ የባለሜዳው ቡድን ደጋፊዎች በራሳቸው ቡድን አባላት እና አመራሮች ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ እንዳሰሙ ተነግሯል፡፡
  • ሁለተኛ ደረጃ ላይ የነበረው አዳማ ከተማ ወደ ጎንደር አቅንቶ በዳሸን ቢራ ሽንፈትን ተከናንቧል፡፡ 1ለ0 በተጠናቀቀው ጨዋታ ሸሪፍ ዲን ለባለሜዳዎቹ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል፡፡
  • ይርጋለም ላይ በተደረገ ጨዋታ ሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1ለ1 ሲለያዩ ኤሪክ ሙራንዳ ለሲዳማ እና ቶክ ጄምስ ለንግድ ባንክ ጎሎቹን አስቆጥረዋል፡፡
  • ሀዋሳ ከተማ ሜዳው ላይ መከላከያን 2ለ0 ረትቷል፡፡ ለሀዋሳ ሙጂብ ቃሲም እና ፍርድአወቅ ሲሳይ የማሸነፊያዎቹን ጎሎች አስቆጥረዋል፡፡
  • ድሬዳዋ ላይ በተደረገ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ያለጎል 0ለ0 ተለያይተዋል፡፡
  • ላለመውረድእርስበእርስእየተፎካከሩየሚገኙትአርባምንጭከተማእናኤሌክትሪክአርባምንጭላይባደረጉትፍልሚያባለሜዳዎቹ 3ለ0 በሆነውጤትድልአድርገዋል፡፡ ተሾመታደሰሁለትጎሎችንሲያስቆጥርቀሪዋንጎልበረከትተሰማበራሱላይአስቆጥሯል፡፡
  • በነዚህ ውጤቶች መሰረት ቅዱስ ጊዮርጊስ በ40 ነጥቦች መሪነቱን ሲያጠናክር፣ በሁለተኛው ዙር አስደናቂ የስኬት ግስጋሴ ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና በ31 ነጥቦች ሁለተኛ ደረጃን ይዟል፡፡ ሽንፈት ያስተናገዱት አዳማ ከተማ እና ደደቢት በ30 እና 29 ነጥቦች አንድ፣ አንድ ደረጃ ዝቅ ለማለት ተገደዋል፡፡ ከታች ባለ22 ነጥቦቹ መከላከያ እና ዳሸን ቢራ፣ 21 ነጥቦች የያዘው አርባምንጭ ከተማ እና ባለ19 ነጥቡ ኤሌክትሪክ ላለመውረድ ይፎካከራሉ፡፡ ሰባት ነጥቦችን ብቻ የሰበሰበው የደረጃ ሰንጠረዡ ወለል ሀዲያ ሆሳዕና ከዚህ በኋላ ላለመውረድ ያለው ተስፋ እጅግ የተመናመነ መስሏል፡፡
  • የአዳማ ከተማው ታፈሰ ተስፋዬ በ11 ጎሎች ከፍተኛ ጎል አግቢነቱን ሲመራ፣ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አዳነ ግርማ እና የኢትዮጵያ ቡናው ዊልያም ያቡን በዘጠኝ ጎሎች ይከተላሉ፡፡
  • የ20ኛው ሳምንት የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታዎች ለፊታችን ማክሰኞ እና ረቡዕ ፕሮግራም ተይዞላቸዋል፡፡ በዚህ መሰረት ማክሰኞ በ9 ሰዓት በአዳማ – አዳማ ከተማ ከሀዋሳ ከተማ ሲፋለሙ በአዲስ አበባ ስታዲየም በ9 ሰዓት መከላከያ ሲዳማ ቡናን እንዲሁምበ11፡30 ኤሌክትሪክ ዳሸን ቢራን ያስተናግዳሉ፡፡ ረቡዕ በቦዲቲ ወላይታ ድቻ ሀዲያ ሆሳዕናን ሲያተናግድ፣ አዲስ አበባ ላይ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡ በአዲስ አበባ ስታዲየም በ9 ሰዓት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድሬዳዋ ከተማን ሲያስተናግድ በ11፡30 ቅዱስ ጊዮርጊስ  ከደደቢት ይፋለማሉ፡፡ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ በ10፡00 ኢትዮጵያ ቡና አርባምንጭ ከተማን ያስተናግዳል፡፡

1 thought on “ኢትዮጵያ ቡና በአስደናቂ አቋም ደደቢትን ረትቷል

Leave a Reply

Your email address will not be published.