ኢትዮጵያዊቷ ነፃነት ጉደታ በቫሌንሺያ የዓለም ሪኮርድ በመስበር የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮን ሆነች

Netsanet win

ኬንያዊው ጂኦፍሬይ ካምዎሮር በወንዶቹ ፉክክር በተከታታይ ለ3ኛ ግዜ ሻምፒዮን ሆኗል

ኢትዮጵያ ለውድድሩ ከተዘጋጁት 4 የወርቅ ሜዳልያዎች 3ቱን በማሸነፍ የአጠቃላይ የበላይነቱን ወስዳለች

በስፔን ቫሌንሺያ በተከናወነው 23ኛው የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ/ትሪኒዳድ አልፎንሶ የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና ኢትዮጵያዊቷ ነፃነት ጉደታ 1፡06፡11 በሆነ ሰዓት የሴቶች ብቻ ውድድር የዓለም ሪኮርድን በመስበር ጭምር ሻምፒዮን ለመሆን በቅታለች፡፡

ነፃነት ጉደታ ውድድሩን በአሸናፊነት ለመጨረስ በመገስገስ ላይ

የስፔን ምስራቃዊ የባሕር ዳርቻ ከተማ በሆነችው ቫሌንሲያ አስተናጋጅነት በተካሄደው የሴቶቹ ፉክክር የተለመደው የኬንያ እና ኢትዮጵያ አትሌቶች ፉክክር የታየበት ሲሆን የቅድመ ውድድር የሜዳልያ አሸናፊነት ግምት የተሰጣቸው አትሌቶችም ብርቱ ተፎካካሪ ሆነው በመዋል የሜዳልያ ደረጃው ውስጥ መግባት ችለዋል፡፡ ከ10ኛው ኪሎ ሜትር በኋላ አራት አትሌቶች ተነጥለው በመሪነቱ ስፍራ ላይ በተቀመጡበት የሴቶቹ ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ ነፃነት ጉደታ፣ ኬንያውያኑ ጄፕኮስጋይ እና ፓውሊኔ ካሙሉ እንዲሁም ባሕሬይንን ወክላ የተወዳደረችው ትውልደ ኬንያዊቷ ኢዩንስ ቼቢቺ አብረው ሲሮጡ ቆይተዋል፡፡ አራቱ አትሌቶች ወደ15ኛው ኪሎ ሜትር ሲቃረቡ ወደፊት ተነጥላ መውጣት የጀመረችው ነፃነት ከዛ በኋላ በነበሩት አምስት ኪሎ ሜትሮች ውስጥ ከተፎካካሪዎቿ ጋር ያላትን ልዩነት በማስፋት 20ኛው ኪሎ ሜትር ላይ የደረሰችው በሁለተኛነት ትከተላት ከነበረችው ኬንያዊቷ ፓውሊኔ ካሙሉ በ40 ሰከንድ ቀድማ ነበር፡፡ ነፃነት ውድድሩን በድንቅ ሁኔታ በአሸናፊነት ስታጠናቅቅ የገባችበት 1፡06፡11 የሆነ ሰዓትም ሴቶች ብቻ በተፎካከሩበት ውድድር ኔዘርላንዳዊቷ ሎርናህ ኪፕላጋት በ2007 ዓ.ም በቀድሞ አጠራሩ የዓለም የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና ዩዲኔ ጣልያን ላይ አስመዝግባው የነበረውን 1፡06፡25 የሆነ የዓለም ሪኮርድ መስበር ያስቻላት ሆኗል፡፡ በወንድ አሯሯጭ በመታገዝ በሚካሄደው ውድድር የርቀቱ የዓለም ሪኮርድ ባለቤት የሆነችው እና ለአሸናፊነቱ ቀዳሚ ግምት ተሰጥቷት የነበረችው ኬንያዊቷ ጆሴሊኔ ጄፕኮስጋይ ከነፃነት በኋላ 43 ሰከንድ ዘግይታ በመግባት የብር ሜዳልያ ስታገኝ የሀገሯ ልጅ ፓውሊኔ ካሙሉ በ1፡06፡56 በሆነ የራሷ ምርጥ ሰዓት የነሐስ ሜዳልያ ወስዳለች፡፡ ኢትዮጵያን የወከሉት ቀሪዎቹ አራት አትሌቶች በሙሉ የራሳቸውን ምርጥ ሰዓት በማሻሻል መጨረስ የቻሉ ሲሆን በ1፡08፡07 አምስተኛ የወጣችው ዘይነባ ይመር እና በ1፡08፡09 ስድስተኛ ሆና ያጠናቀቀችው መሰረት በለጠ በቡድን ለተመዘገበው የወርቅ ሜዳልያ ድል የበኩላቸውን ድንቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ በቀለች ጉደታ በ1፡08፡12 ስምንተኛ ዝናሽ መኮንን በ1፡08፡30 አስራ አንደኛ ሆነው በማጠናቀቅ የቡድን የወርቅ ሜዳልያ አግኝተዋል፡፡

ነፃነት ጉደታ ሪኮርድ ያሻሻለችበትን ሽልማት ከሰባስቲያን ኮ ስትቀበል

በሴቶቹ የተናጠል ፉክክር በ2002 ዓ.ም. ብርሀኔ አደሬ እንዲሁም በ2012 መሰረት ሀይሉ ካስገኙት ስኬት ቀጥሎ ሶስተኛውን የወርቅ ሜዳልያ ድል ለኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ነፃነት ከድሏ በኋላ በሰጠችው አጭር አስተያየት ‹‹ግቤ ውድሩን በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ነበር፡፡ ያንን ማሳካት ችያለሁ እናም በጣም ደስ ብሎኛል›› ብላለች፡፡ ከዚህ በፊት በተካሄዱት ሁለት የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮናዎች ላይም ኢትዮጵያን መወከል ችላ የነበረችው ነፃነት በ2014 ኮፐንሀገን ዴንማርክ ላይ ስድስተኛ እንዲሁም ከሁለት ዓመት በፊት በዌልስ ካርዲፍ አራተኛ ሆና ማጠናቀቅ እንደቻለች ይታወሳል፡፡ ዘንድሮ በቫሌንሺያ የውድድሩ አሸናፊ በመሆኗ ካገኘችው የ30 ሺህ ዶላር ሽልማት በተጨማሪም የዓለም ሪኮርድ ለሰበረችበት የ50 ሺህ ዶላር ሽልማት በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ፕሬዝደንት ሰባስቲያን ኮ እጅ ተበርክቶላታል፡፡

የሴቶች የቡድን ሽልማት ስነስርዓት

በወንዶቹ ፉክክር የቅድመ ውድድሩ ተጠባቂ አትሌት ኬንያዊው ጂኦፍሬይ ካምዎሮር የራሱ የዓመቱ ምርጥ በሆነ 1፡00፡02 ሰዓት በቀዳሚነት በማጠናቀቅ በተከታታይ ለ3ኛ ግዜ የውድድሩ ሻምፒዮን ሆኗል፡፡ ከ15ኛው ኪሎ ሜትር በኋላ ብዛት ካላቸው የቅርብ ተፎካካሪዎቹ ተነጥሎ ከወጣ በኋላ ሁነኛ ተገዳዳሪ ያልነበረው ካምዎሮር ውድድሩን ያሸነፈው በቀላሉ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ አብራሀም ቼብሮን ከባህሬይን የራሱ የዓመቱ ምርጥ በሆነ 1፡00፡22 ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ በመጨረሻዎቹ ጥቂት መቶ ሜትሮች ውስጥ ከኢትዮጵያዊው ጀማል ይመር ጋር ያደረገውን ትንቅነቅ በበላይነት መጨረስ የቻለው ኤርትራዊው አሮን ክፍሌ የራሱ የምንግዜም ምርጥ በሆነ 1፡00፡31 የነሐስ ሜዳልያ ደረጃውን ወስዷል፡፡ ጀማል ይመር በ1፡00፡33 አራተኛ፣ ጌታነህ ሞላ የራሱ የዓመቱ ምርጥ በሆነ 1፡00፡47 አምስተኛ አንዲሁም በተስፋ ጌታሁን የራሱ የምንግዜም ምርጥ በሆነ 1፡00፡54 ስድስተኛ በመውጣት ኢትዮጵያ የቡድን የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ ለመሆን አብቅተዋታል፡፡ ልዑል ገብረስላሴ የራሱ የዓመቱ ምርጥ በሆነ 1፡01፡07 አስረኛ ጂክሳ ቶሎሳ የራሱ የምንግዜም ምርጥ በሆነ 1፡01፡50 ሀያ ሶስተኛ ሆነው በማጠናቀቅ የወርቅ ሜዳልያው ድል ተጋሪ ሆነዋል፡፡

ለውድድሩ ከተዘጋጁት 4 የወርቅ ሜዳልያዎች መካከል ኢትዮጵያ በቡድን ሁለቱንም በተናጠል የሴቶቹን በማሸነፍ የአጠቃላይ የበላይነቱን ወስዳለች፡፡

የወንዶች የቡድን ሽልማት ስነስርዓት

የሜዳልያ ሰኝጠረዥ

Leave a Reply

Your email address will not be published.