አዳማ መሪነቱን አጠናክሮ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ በድል ጉዞው ቀጥሎ ሊጉ ተቋርጧል

St. George best 11 against Dedebit - May 31-2015

St. George best 11 against Dedebit - May 31-2015

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በስድስተኛው ሳምንት በበርካታ ውዝግቦች የተሞሉ ጨዋታዎችን ካሳየን እና ከጨዋታዎቹም በኋላ የኢትዮጵያ ቡናን ጋዜጣዊ መግለጫ ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ አነጋጋሪ ጉዳዮችን ካስተናገደ በኋላ በውጥረት መንፈስ የሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎቹንም አድርጓል፡፡ የሳምንቱ ትልቁ እና በጉጉት የተጠበቀ ጨዋታው ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኙ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት የሚያደርጉት ነበር፡፡ ደደቢቶች በኢትዮጵያ ቡና ላይ ካገኙት ድል እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሀዲያ ሆሳዕናን በዳካማ የቡድን እንቅስቃሴ ከረቱ በኋላ ወደዚህ ጨዋታ መጥተዋል፡፡

ሰማያዊዎቹ በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ከጀመሩበት አሰላለፋቸው በጉዳት ምክንያት ከቡድኑ የራቀውን አጥቂው ዳዊት ፍቃዱን ብቻ በሄኖክ መኮንን ተክተው ሲጀምሩ፣ ፈረሰኞቹ በሀዲያ ሆሳዕናው ጨዋታ በቋሚነት ያልጀመሩት አሉላ ግርማ እና ተስፋዬ አለባቸውን አስጀምረዋል፡፡

ደደቢት (4-4-2 የሚመስል)

ግብ ጠባቂ፡- ታሪክ ጌትነት

ተከላካዮች፡- ስዩም ተስፋዬ፣ አክሊሉ አየነው፣ ምኞት ደበበ እና ተካልኝ ደጀኔ

አማካዮች፡- ሽመክት ጉግሳ፣ ያሬድ ዝናቡ፣ ሳምሶን ጥላሁን እና ብርሀኑ ቦጋለ

አጥቂዎች፡- ሄኖክ መኮንን እና ሳሙኤል ሳኑሚ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1 የሚመስል)

ግብ ጠባቂ፡- ሮበርት ኦዳንካራ

ተከላካዮች፡- አሉላ ግርማ፣ አስቻለው ታመነ፣ አይዛክ ኢዜንዴ እና ዘካሪያስ ቱጂ

አማካዮች፡- ተስፋዬ አለባቸው፣ ምንተስኖት አዳነ

በኃይሉ አሰፋ፣ ምንያህል ተሾመ እና ራምኬል ሎክ

አጥቂ፡- አዳነ ግርማ

ከሰሞኑ የመነጋገሪያ ርእስ ከነበሩ ዳኞች በአንዱ በኢንተርናሽናል አርቢትር በአምላክ ተሰማ ዋና ዳኝነት የተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ብዙ ሙከራዎችን ባያሳየንም በጥሩ የፉክክር መንፈስ የተሞላ ነበር፡፡ በተለይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በቅርብ ሳምንታት ርቋቸው የነበረ ታጋይነት፣ ታታሪነት እና የላቀ ፍላጎትን ሲያሳዩ ነበር፡፡ የአሰልጣኝ ማርት ኖይ ልጆች በተለይ ኳሱን ሲቀሙ መልሰው ለመንጠቅ ያሳዩት የነበረው ጥረት ለደደቢት ፈተና ሆኖ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ሰማያዊዎቹ ምርጡ ተጨዋቻቸው ሳሙኤል ሳኑሚን ወደ ጨዋታው ለማስገባት ተቸግረው ነበር፡፡ ፈረሰኞቹ ወደ ደደቢት ጎል ለመቅረብ ካደረጓቸው ጥረቶች በኋላ በ27ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ተሻግሮ በራምኬል ሎክ የተጨረፈውን ኳስ አዳነ ግርማ አስቆጥሮላቸው መሪ መሆን ችለዋል፡፡ ከጎሉ በኋላ አግቢው አዳነን ጨምሮ ጥቂት የጊዮርጊስ ተጨዋቾች አሉላ ግርማ ለወለደው ልጅ መታሰቢያ የሆነ የእሹሩሩ ፈንጠዝያ አሳይተዋል፡፡ ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም አዳነ ሌላ እድል አግኝቶ በቮሊ የሞከረው ኳስ ለጥቂት የመረብ ጎን መትቶ ወጥቶበታል፡፡ በ43ኛው ደቂቃ ምንተስኖት አዳነ ያሾለከለትን ኳስ ምንያህል ከማግኘቱ በፊት ግብ-ጠባቂው ታሪክ ጌትነት ወጥቶ አውጥቶበታል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ የባከኑ ደቂቃዎች በኃይሉ አሰፋ ለአዳነ ያቀበለውን ግዙፉ አጥቂ ወደ ጎል ቢመታውም አሁንም ታሪክ በድንቅ ሁኔታ ጎል ከመሆን ታድጎታል፡፡ በጊዮርጊሶች የ1ለ0 መሪነትም ለእረፈት ወጥተዋል፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ የተጀመረው መሀል ሜዳ ላይ ግልፅ ብልጫ እንደተወሰደባቸው የተገነዘቡት የደደቢቱ አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት የተጨዋች ለውጥ አድርገው ነበር፡፡ አሰልጣኙ አንጋፋው ያሬድ ዝናቡን አስወጥተው በወጣቱ ወግደረስ ታዬ ተክተውታል፡፡ ለውጡ ኳስ ቁጥጥር ላይ በተወሰነ መጠን የጠቀማቸው ቢመስልም የጊዮርጊስን ግብ ክልል መዳፈር ግን እምብዛም አልቻሉም፡፡ ጨዋታውም የበለጠ ኃይል የበዛበት እና በተጨዋቾች እና ተጨዋቾች እንዲሁም በተጨዋቾች እና በዳኛው መካከል አለመግባባቶች የሚታዩበት ሆኗል፡፡ በ49ኛው ደቂቃ ስዩም ተስፋዬ በአሉላ ግርማ ላይ ሰርቷል ላሉት ጥፋት አርቢትር በአምላክ የማስጠንቀቂያ ካርድ ማውጣታቸው ክርክር ፈጥሮ የነበረ ሲሆን፣ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በመጀመሪያው አጋማሽ የማስጠንቀቂያ ካርድ የተመለከተው ተስፋዬ አለባቸው እና ብርሀኑ ቦጋለ ተጎነታትለው አጠገባቸው የነበሩት አርቢትሩ በዝምታ አልፈዋቸዋል፡፡ በ56ኛው ደቂቃ ብርሀኑ ከ35 ሜትሮች ገደማ የመታው ኳስ በሮበርት ኦዳንካራ ተይዞበታል፡፡ ከአንድ ደቂቃ በኋላ አዳነ መሀል ሜዳ አካባቢ አንድ ተጨዋችን በማራኪ መንገድ አልፎ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ የሞከረው ኳስ ለጥቂት ወጥቶበታል፡፡ ወዲያውኑ ደግሞ በኃይሉ አሰፋ በግራ በኩል ወደ ደደቢት ጎል ሲያመራ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ‹ጥፋት ተሰርቶብኛል› ብሎ ቢወድቅም አርቢትሩ ‹ለማታለል ሞክረሀል› ብለው የማስጠንቀቂያ ካርድ አሳይተውታል፡፡ በ65ኛው ደቂቃ ደደቢቶች ፀጥ ያለ ቀን ያሳለፈው አጥቂው ሄኖክ ብርሀኑን በጋናዊው አጥቂ ጆሴፍ አምዮኪ ተክተውታል፡፡ በ66ኛው ደቂቃ ሌላው ተቀይሮ ገቢ ወግደረስ በጊዮርጊስ የጎል ክልል ውስጥ ጥሩ ኳስ አግኝቶ ሳይጠቀምበት ወደ ውጪ ሰዶታል፡፡ በደደቢት በኩል የታየ ምርጡ አጋጣሚ ነበር፡፡ በ68ኛው ደቂቃ ራምኬል ሎክ እንዲሁም በ70ኛው ደቂቃ ብርሀኑ ከሩቅ የመታቸው ኳሶች ኢላማቸውን አላገኙም፡፡ በ77ኛው ደቂቃ ራምኬል ሎክ ተቀይሮ በመውጣት ለብሪያን ኦሞኒ ስፍራውን ሲለቅ፣ ብርሀኑ ያልተገባ ባህሪይ በማሳየት የአርቢትሩ የማስጠንቀቂያ ካርድ መዝገብ ሰለባ ሆኗል፡፡ በ80ኛ ደቂቃ ከሰሞኑ አቋሙ የወረደው በኃይሉ በናትናኤል ዘለቀ ተተክቷል፡፡ በ83ኛው ደቂቃ ጥሩ ረዥም ኳስ የተላከለት ጆሴፍ አምዮኪ ከግብ-ጠባቂው ኦዳንካራ ጋር ቢገናኝም ኳሱን በሚገባ መቆጣጠር ሳይችል ቀርቷል፡፡ ጨዋታው በዚሁ ውጤት ተጠናቀቀ ተብሎ ሲጠበቅ ተቀይሮ የገባው ብሪያን ኦሞኒ በባከኑ ደቂቃዎች ላይ በደደቢት ተከላካዮች ስህተት ያገኘውን ኳስ ግብ ጠባቂው ታሪክን አንጠልጥሎ በማግባት የቡድኑን መሪነት አስፍቷል፡፡ ጨዋታውም በቅዱስ ጊዮርጊስ የ2ለ0 ድል ተጠናቋል፡፡

በሌሎች ጨዋታዎች፡-

  • መሪው አዳማ ከተማ እና አጥቂያቸው ታፈሰ ተስፋዬ በአስደናቂ አቋማቸው ቀጥለዋል፡፡ የሊጉ መሪዎች ወደ ሀዋሳ አምርተው ባለሜዳው ሀዋሳ ከተማን በታፈሰ ሁለት ጎሎች 2ለ1 አሸንፈዋል፡፡ ደስታ ዮሐንስ ለሃዋሳ ብቸኛዋን ጎል አስቆጥሯል፡፡
  • ከሰሞኑ በውዝግቦች ውስጥ የከረመው ኢትዮጵያ ቡና በመጀመሪያ የሜዳ ውጪ ጨዋታው ሽንፈት አስተናግዷል፡፡ ወደ አርባምንጭ የተጓዙት የአሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲች ልጆች በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩባቸው ጎሎች 2ለ0 ተረትተዋል፡፡ ለአርባምንጭ ከተማ ተሾመ ታደሰ እና በረከት ወልደፃዲቅ ጎሎቹን አስቆጥረዋል፡፡
  • ሌሎቹም ከከተማቸው ውጪ የተጫወቱት የአዲስ አበባ ክለቦችም ሽንፈት ደርሶባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በድሬዳዋ ከተማ 1ለ0 ሲሸነፍ፣ መከላከያ በሲዳማ ቡና እና ኤሌክትሪክም በዳሸን ቢራ በተመሳሳይ 1ለ0 ውጤቶች ሽንፈቶችን አስተናግደዋል፡፡ ሱራፌል ዳንኤል ለድሬዳዋ ከተማ፣ ቴዎድሮስ በቀለ ለሲዳማ ቡና በራሱ ላይ እንዲሁም ሸሪፍ ዲን ለዳሸን ቢራ የማሸነፊዎቹን ጎሎች አስቆጥረዋል፡፡
  • ሆሳዕና ላይ ፍፁም ያልተጠበቀ ውጤት ተመዝግቧል፡፡ የሊጉ ወለል እና እስካሁን አሸንፎ የማያውቀው ሀዲያ ሆሳዕና ወላይታ ድቻን 5ለ1 ደቁሷል፡፡ እንዳለ ደባልቄ፣ አበባየሁ ዮሐንስ፣ አምረላ ዴልታታ፣ አበው ታምሩ እና ዱላ ሙላቱ ለሃዲያ ሆሳዕና ጎሎቹን አስመዝግበዋል፡፡
  • ከሰባተኛው ሳምንት ጨዋታዎች በኋላ አዳማ ከተማ በ19 ነጥቦች መሪነቱን ሲያጠናክር፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ16 እና ጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው ሲዳማ ቡና በ12 ነጥቦች ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡ ደደቢት በ11 ነጥቦች፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ዳሸን ቢራ በእኩል 10 ነጥቦች፣ ወላይታ ድቻ በዘጠኝ፣ መከላከያ፣ አርባምንጭ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና በእኩል ስምንት ነጥቦች እስከ 10ኛ ደረጃ ተቀምጠዋል፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በእኩል ሰባት ነጥቦች 11ኛ እና 12ኛ ደረጃን ሲይዙ ባለስድስት ነጥቡ ሀዋሳ ከተማ እና አራት ነጥቦች የያዘው ሀዲያ ሆሳዕና የመጨረሻዎቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡ የአዳማ ከተማው ታፈሰ ተስፋዬ በስድስት ጎሎች ከፍተኛ ጎል አግቢነቱን ሲመራ፣ የደደቢቱ ሳሙኤል ሳኑሚ በአምስት ጎሎች ይከተላል፡፡
  • ፕሪምየር ሊጉ በቻን ዝግጅት እና ውድድር ምክንያት ከስድስት ሳምንታት ለሚበልጥ ጊዜ ይቋረጣል፡፡ የስምንተኛው ሳምንት ጨዋታዎች ምናልባትም የካቲት 5 እንደሚቀጥሉ ይጠበቃል፡፡

1 thought on “አዳማ መሪነቱን አጠናክሮ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ በድል ጉዞው ቀጥሎ ሊጉ ተቋርጧል

Leave a Reply

Your email address will not be published.