አዲሱ የግብፅ ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀበሉ

 

JUNE 11, 2014 | በ ተጻፈ

በቅርቡ የግብፅ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት አብዱልፈታህ አል ሲሲ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀበሉ፡፡

የፕሬዚዳንት አል ሲሲ በዓለ ሲመት ለመታደም የኢትዮጵያን ልዑካን ቡድን ይዘው ወደ ካይሮ ያመሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ  ፕሬዚዳንቱን ጋብዘዋቸዋል፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ ግብዣውን ያቀረቡት በካይሮ በሚገኘው ቤተ መንግሥት ከአዲሱ ፕሬዚዳንት አል ሲሲና ከግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነቢል ፉህሚ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ከመከሩ በኋላ ነው፡፡ በውይይቱ ወቅት በግብፅ የኢትዮጵያ አምባሳደር መሐመድ ድሪር ተገኝተዋል፡፡

የግብፅ ትልቁ ጋዜጣ አል አህራም እንደዘገበው፣ ፕሬዚዳንት አል ሲሲ የኢትዮጵያና የግብፅን ታሪካዊ ግንኙነት አስምረውበታል፡፡ ታላቁ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በውይይት መፍታት እንደሚፈልጉ ለዶ/ር ቴድሮስ አረጋግጠውላቸዋል፡፡ እንዲሁም ኢትዮጵያ ራሷን ለማልማት ያላትን ፍላጎት እንደሚረዱ ገልጸው፣ ግብፅም በዓባይ ላይ ያላትን የውኃ ድርሻ ኢትዮጵያም እንድትረዳ ጠይቀዋል፡፡ ሁለቱ እህትማማች አገሮች በዓባይ ውኃ መተባበር እንጂ መጠላት የለባቸውም ማለታቸው ተዘግቧል፡፡

አል አህራም የፕሬዚዳንቱን ቃል አቀባይ ዋቢ በማድረግ ባስነበበው ዘገባ፣ ዶ/ር ቴድሮስ ኢትዮጵያ የግብፅን የውኃ ፍላጎት የመቀነስ ምንም ፍላጎት እንደሌላትና ግድቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ብቻ የታሰበ መሆኑን እንዳስረዱዋቸው አትቷል፡፡ በተመሳሳይ ዶ/ር ቴድሮስ ለመካከለኛው ምሥራቅ ዜና አገልግሎት (MENA) እንደገለጹት፣ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ባደረጉት ውይይት ሁለቱም አገሮች ግንኙነታቸውን በአዲስ ምዕራፍ ለማስኬድ ተስማምተዋል፡፡ ‹‹ግንኙነታችንን በአዲስ ምዕራፍ ለማስኬድና መተማመንን ለመፍጠር እየሠራን ነን፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ትብብር ለመፍጠር አዲስ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያስፈልገናል፤›› ማለታቸውንም ሚዲያው ዘግቧል፡፡ ‹‹ፍላጎት ካለ ተስፋ አለ›› ማለታቸውንም አክሏል፡፡ የተቋረጠውን የሦስትዮሽ ውይይት እንደገና ለመጀመር መስማማታቸውንም አስረድቷል፡፡

በዚህ ወር መጨረሻ በኢኳቶሪያል ጊኒ በሚካሄደው የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ፕሬዚዳንት አል ሲሲን ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ለማገናኘት ማሰባቸውንም ጋዜጣው አክሎ ዘግቧል፡፡ በበዓል ሲመቱ፣ ‹‹ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት እንዲያበላሸው አልፈቅድም›› ያሉት ፕሬዚዳንት አል ሲሲ፣ ሁለቱም አገሮች ችግራቸውን በውይይት ለመፍታት ያላቸውን አቋም ግልጽ አድርገዋል፡፡

ዘወርልድ ኒውስ ቡለቲንና አል ዓረቢያ ኒውስ የመንግሥት ቃል አቀባዩን ዋቢ በማድረግ እንደዘገቡት፣ ፕሬዚዳንት አል ሲሲ በኢትዮጵያ መንግሥት የቀረበላቸውን ግብዣ በአዎንታ ተቀብለዋል፡፡ አል አህራም ኦንላይን እንደዘገበው፣ በግብፅ የኢትዮጵያ አምባሳደር መሐመድ ድሪር በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ከግብፅ ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና በበኩላቸው፣ አዲሱ የግብፅ ፕሬዚዳንት ያሳዩት የመነጋገር ፍላጎት በኢትዮጵያ መንግሥት ተቀባይነት ያለው እንደሆነ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የተቋረጠው ውይይት እንደገና እንዲጀመርና በአገሮቹ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በውይይት ለመፍታት የኢትዮጵያ መንግሥት የምንጊዜም አቋም መሆኑን በመግለጽ፣ ‹‹መንግሥት መቼም ቢሆን ከግብፅ መንግሥት ጋር ለመወያየትና ለመነጋገር ዝግጁ ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ያሳዩት ፍላጎት በበጎ የሚታይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን የተቋቋመው የህዳሴው ግድብ የዓለም አቀፍ የውኃ ባለሙያዎች ቡድን የግድቡን ማኅበራዊና አካባቢያዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ ያቀረበው ምክረ ሐሳብ ተግባራዊ በሚደረግበት ላይ የተጀመረው ውይይት በግብፅ እንቢተኝነት መቋረጡ ይታወሳል፡፡ ያንን ተከትሎ አንዳንድ የግብፅ ባለሥልጣናት ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት፣ እንዲሁም ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ለመውሰድ እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በተጨማሪም የግብፅ መንግሥት ግድቡን የሚሰልል ሳተላይት ማምጠቁን መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡

ምንጭ፦ ሪፖርተር

2 thoughts on “አዲሱ የግብፅ ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀበሉ

  1. We are happy in the willing of this army chief visiting Ethiopia;many threatens Ethiopia in vain saying ‘the coup built satellite controlling Ethiopia & its recent Dam’ . We got this coup-chief humble,not as many speak of fearing him.We wish God’s love agreeing them on this Ethiopia recent Dam.If they aren’t agree,we are ready to write our letter to WORLD-POWER NATIONS to interfere the matter.We are happy if world countries,nations agree,love,share what they have to one another in this TEMPORAL WORLD.God bless you.

Leave a Reply

Your email address will not be published.