አቶ አብዲ መሐመድ ዑመርን ጨምሮ ለአራት ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት የ11 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

Abdi Ille

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ዑመርን ጨምሮ በአራት ተጠርጣሪዎች ላይ የ11 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቀደ፡፡

የፌደራል መርማሪ ፖሊስ በግለሰቦቹ ላይ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ጠይቆ ነበር፡፡

የወንጀል ምርመራ ቡድኑ ባለፉት 11 ቀናት ከ9 በላይ ምስክሮችን ቃል የተቀበለ ሲሆን በሁከትና ብጥብጡ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸዉ ግለሰቦች የጉዳት መጠን የሚያሳይ መረጃም ከሆስፒታል ስለመጠየቁም ተናግሯል፡፡

ከዉጭ ሃገራት የገቡ 14 ሞባይልና 10 ሲም ካርዶች በመረጃ መረብ ደህንነት ኤጄንሲ በኩል ማጣራት እንዲደረግባቸዉ ስለመላኩም የወንጀል ምርመራ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

በግብረ አበርነት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ለማዋልና የተጨማሪ ምስክሮችን ቃል ለመቀበል እንዲሁም የተጎጅዎችን የህክምና ማስረጃ ለማግኘት ማሰባሰብ እንደሚቀረዉ ፖሊስ ተናግሯል፡፡

የጅምላ ግድያ የተፈጸመባቸዉን ግለሰቦች አስክሬን ለማዉጣትም ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ፖሊስ አስታዉቋል፡፡

ተጠርጣሪዎች በበኩላቸዉ በመርማሪ ፖሊስ የተጠየቀዉን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተቃዉመዋል፡፡
አንደኛ ተጠርጣሪ አቶ አብዲ መሃመድ ዑመር ከጠያቂ ቤተሰብ ጋር በሶማሊኛ እንዳልግባባ ተከልክያለሁ ያሉ ሲሆን የዋስትና መብታቸዉም እንዲከበር ጠይቀዋል፡፡

ሌላኛዋ ተጠርጣሪና የቀድሞዉ የክልሉ ሴቶችና ህጻት ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ረሂማ መሃመድ ከደም ግፊት ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ህክምና ለማግኘት እንደሚፈልጉ ቢጠይቁም እንዳተፈቀደላቸዉ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ተጠርጣዎቹ ከምግብ ከህክምናና ከመኝታ ቤት ጋር በተያያዘ አሉብን ያሏቸውን ችግሮች እንዲፈቱላቸዉም ጠይቀዋል፡፡

የወንጀል ምርመራ ቡድኑ አቶ አብዲ መሃመድ ያነሱት ጥያቄ በመጀመሪያዉ ቀን የተከሰተ መሆኑን ተናግሮው አሁን ላይ ከሚመለከታዉ ጋር በመነጋገር ተስተካክሏል ብሏል፡፡

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተረኛ የወንጄል ችሎት አቶ አብዲ መሃመድ ዑመርና ሌሎች ተጠርጣዎች ያነሱትን ጥያቄ በሚመለከት ህገመንግስታዊ መብታዉ እንዲከበርላዉ ሲል አዟል፡፡

ግራ ቀኙን የተመለከተዉ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ከተጠየቀዉ የምርመራ ጊዜ ዉስጥ 11 ቀናት የፈቀደ ሲሆን ዉጤቱን ለመጠበቅ ለጥቅምት 9 ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል፡፡