አምበር ዋንጫ ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስን አገናኝቷል

St.-George vs Eth Coffee Amber Champ

St.-George vs Eth Coffee Amber Champ

የአምበር የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ሲቃረብ የሁለቱም ምድቦች ጨዋታዎች ተጠናቀው አራቱ አላፊ ቡድኖች ተለይተዋል፡፡ ቀጣዩ ዘገባ ባለፉት ቀናት የተደረጉትን የሁለቱንም ምድቦች ጨዋታዎች ይቃኛል፡፡

ሰኞ የተደረጉት የሁለተኛው ምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ነበሩ፡፡ በቅድሚያ የተገናኙት በመጀመሪያው ጨዋታው በርካታ ቋሚ ተሰላፊ ቁልፍ ተጨዋቾቹን ሳይጠቀም ተጋባዡን አዳማ ከነማን በመሀመድ ናስር ሀት-ትሪክ ታግዞ 4ለ0 የደቆሰው መከላከያ እና በመጀመሪያ ጨዋታው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለ ጎል አቻ የተለያየው የዓምናው የዚህ ውድድር አሸናፊ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነበሩ፡፡ በገብረ መድህን ኃይሌ የሚመሩት መከላከያዎች በዚህም ጨዋታ በርካታ ወጣት ተጨዋቾችን የተጠቀሙ ሲሆን ከነዚህ ተስፈኛ ተጨዋቾቻቸው በአንዱ ሳሙኤል ሳሊሶ አማካይነት ባስቆጠሩት ጎል መሪ ሆነዋል፡፡ ዋና አሰልጣኛቸው ፀጋዬ ኪዳነማሪያምን በህመም ምክንያት ሳይዙ የተገኙት ንግድ ባንኮች በፊሊፕ ዳውዝ ጎል አቻ መሆን ችለው የነበረ ቢሆንም ተቀይሮ የገባው ሌላው ወጣት ማራኪ ወርቁ መከላከያን ባለድል ያደረገ ጎል አስቆጥሯል፡፡ ማራኪ ጎሉን ካስቆጠረ በኋላ ማልያውን አውልቆ ባሳየው ፈንጠዝያ የማስጠንቀቂያ ካርድ ከተመለከተ በኋላ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሆን ብለህ ኳስ በእጅ ነክተሀል ተብሎ በሁለት ቢጫ ካርዶች ከሜዳ ተሰናብቷል፡፡ በቀጣዩ ጨዋታ የተገናኙት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ ከነማ ነበሩ፡፡ ብዙ የጎል ሙከራዎች ያልታዩበት ጨዋታ ጎል ሳያስተናግድ በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ በርካታ ከዋክብት የያዙት ሁለቱ ቡድኖች በ180 ደቂቃዎች አንድም ጎል አለማስቆጠራቸውም አስገራሚ ሆኗል፡፡ ከነዚህ ጨዋታዎች በኋላ መከላከያ በስድስት ነጥቦች ሲመራ አንድ ጨዋታ እየቀረው በአንደኛነት ከምድቡ ማለፉን አረጋግጧል፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለት፣ ንግድ ባንክ እና አዳማ ከነማ በአንድ ነጥቦች ቀጣዮቹን ደረጃዎች ይዘው የምድቡን የመጨረሻ ጨዋታዎች ሊጠብቁ ተገድደዋል፡፡

የመጀመሪያው ምድብ የመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ማክሰኞ ሲደረጉ በቅድሚያ የተገናኙት ደደቢት እና ተጋባዡ ዳሸን ቢራ ነበሩ፡፡ ይህ ጨዋታ ከመደረጉ በፊት ደደቢት አራት ነጥቦች እንዲሁም ዳሸን ቢራ ሁለት ነጥቦች ነበራቸው፡፡ ደደቢቶች ይህን ጨዋታ የጀመሩት ከምድባቸው ለማለፍ ጨዋታውን አቻ መለያየት በቂያቸው ሆኖ ነበር፡፡ በብሔራዊ ቡድን ግዴታ ምክንያት ወሳኝ ተጨዋቾቻቸውን ያልተጠቀሙት ሰማያዊዎቹ ከእረፍት መልስ ሳሙኤል ሳኑሚ ባስቆጠረው ጎል መምራት እና ከምድባቸው ማለፋቸውን ያስተማመኑ ቢመስልም በዳሸኖቹ ኤዶም ሆሶሮቪ እና አማኑኤል ጥላሁን በተቆጠሩባቸው ጎሎች ለመሸነፍ እና የማለፍ እድላቸውንም በቀጣዩ ጨዋታ ላይ ለመጣል ተገድደዋል፡፡ ዳሸኖች ግን በዚህ ድል ለግማሽ ፍፃሜው መብቃታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና ከኤሌክትሪክ

የደደቢትንም ሆነ የተጋጣሚዎቹን የራሳቸውን የማለፍ እና ያለማለፍ እድል የሚወስነው የኢትዮጵያ ቡና እና ኤሌክትሪክ ጨዋታ የተጀመረው በሚከተሉት የቡድኖቹ አሰላለፎች ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ቡና (4-4-2 ዳይመንድ የሚመስል)

ግብ ጠባቂ፡- ሀሪሰን ኩሲ

ተከላካዮች፡- አብዱልከሪም መሀመድ፣ ወንድይፍራው ጌታሁን፣ ተስፋዬ ሀዲስ እና አህመድ ረሺድ

አማካዮች፡- መስኡድ መሀመድ፣ ኤልያስ ማሞ፣ ኢያሱ ታምሩ እና ዮሴፍ ደሙዬ

አጥቂዎች፡- ጥላሁን ወልዴ እና ዊልያም ያቢያን

ኤሌክትሪክ (4-4-2 የሚመስል)

ግብ ጠባቂ፡- አሰግድ አክሊሉ

ተከላካዮች፡- በረከት ተሰማ፣ ሲሴ ሀሰን፣ ተስፋዬ መላኩ እና ዓለምነህ ግርማ

አማካዮች፡- አሸናፊ ሽብሩ፣ አዲስ ነጋሽ፣ አሳልፈው መኮንን እና በኃይሉ ተሻገር

አጥቂዎች፡- አብዱልሀኪም ሱልጣን እና ብሩክ አየለ

በተለይም በኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ዝማሬዎች በሞቀ ድባብ የጀመረው ጨዋታ ሜዳ ላይም ፈጠን ባለ እና ስሜት በሚይዝ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ቡናዎች በሶስተኛው ደቂቃ በግራ መስመር አህመድ ረሺድ ሴንተር አድርጎት ጥላሁን ወልዴ ሳያገኘው በፊት የኤሌክትሪክ ተከላካዮች ተረባርበው ባወጡት ኳስ እና በ12ኛው ደቂቃ ኢያሱ ታምሩ ከቀኝ በኩል በተመሳሳይ ጥሩ ኳስ ወደ ጎል አሻግሮ ዊሊያም ያቢያን በሳተው ኳስ በቅድሚያ የማጥቃት ተነሳሽነቱን ወስደው ነበር፡፡ ከዚያም በ18ኛው ደቂቃ በዮሴፍ ደሙዬ፣ ኢያሱ እና ኤልያስ ማሞ ማራኪ ቅብብል ያገኘውን ኳስ ዊሊያም ወደ ጎል መትቶ ወጥቶበታል፡፡ በ25ኛው ደቂቃ ግን የቡናማዎቹ ተደጋጋሚ ጥረቶች ፍሬ አፍርተው ኢያሱ ለጥላሁን አቀብሎት ጥላሁን ከመስመር ሴንተር ያደረገውን ኳስ ኤልያስ በጥሩ አጨራረስ ጎል አድርጎት ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ በ34ኛው ደቂቃ ራሱ ኤልያስ የመታው የቅጣት ምት በኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ አሰግድ አክሊሉ ተመልሶበታል፡፡ በ37ኛው ደቂቃ የኤልያስ የማእዘን ምት በመስኡድ ኳሱን ሳነይካ የማሳለፍ ጥበብ ለወንድይፍራው ጌታሁን ደርሶ የመሀል ተከላካዩ የመታው ኳስ ለጥቂት ወጥቶበታል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ኤሌክትሪኮች የተጋጣሚያቸውን የበላይነት ተቋቁመው ወደ ፊት የሄዱባቸው ጊዜያት በጣም ጥቂት ሲሆኑ የቡናው ግብ ጠባቂ ሀሪሰን ኩሲ ትንሽ ገደብ ባለፈ ጀብደኝነት ከክልሉ ወጥቶ የመለሳቸው በረዥም የተላኩ ኳሶች እና በመጨረሻው ደቂቃ አብዱልሀኪም ሱልጣን ያመከነው ኳስ ብቻ ይጠቀሳሉ፡፡ ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረም አብዱልሀኪም ከቡናው ግብ ጠባቂ ጋር ቢገናኝም ተገፍቼያለሁ ብሎ ወድቋል አርቢትሩ ግን አልፈውታል፡፡ በ52ኛው ደቂቃ አብዱልከሪም መሀመድ ሴንተር ያደረገውን ዊልያም ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ በ60ኛው ደቂቃ ኤልያስ መሀል ለመሀል ያቀበለውን ኳስ ዮሴፍ እየገፋ ሄዶ በቀላሉ በማስቆጠር የቡናን መሪነት አስፍቷል፡፡ አዲሱ የቡና ተስፋ ጎሉን ካስቆጠረ በኋላ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ጎል ሲያስቆጥር እንዳደረገው ወደቀኝ ጥላ ፎቅ አካባቢ በመሄድ ከአብሮ-አደግ ጓደኛው ጋር ደስታውን ተጋርቷል፤ ወዲያውም ተቀይሮ ወጥቷል፡፡ ቡናማዎቹ በመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች ለአምበሉ መስኡድ የተረሳውን የጠራጊነት (sweeper) ሚና በመስጠት በአምስት ተከላካዮች መጫወታቸው ትንሽ አነጋጋሪ ነበር፡፡ ጨዋታውም በኢትዮጵያ ቡና 2ለ0 ድል ሲጠናቀቅ የአሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲች ቡድን ከምድቡ አንደኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡ ከጨዋታው በኋላ ለጋዜጠኞች ሀሳባቸውን የሰጡት ሰርቢያዊው የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ በመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች በአምስት ተከላካዮች የተጫወቱት የኤሌክትሪክን ረዣዥም ኳሶች ለመከላከል እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ አሰልጣኙ በቡድናቸው እንቅስቃሴ በመጠኑ ደስተኛ እንደሆኑ ነገር ግን ጎል አግቢ አጥቂ፣ የመሀል ተከላካይ፣ የግራ ተከላካይ እና እንደ ኤልያስ አይነት አልያም የተሻለ አማካይ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡

ከነዚህ ጨዋታዎች በኋላ ከምድብ አንድ ኢትዮጵያ ቡና እና ዳሸን ቢራ አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው አልፈዋል፡፡

መከላከያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ

ሐሙስ የምድብ ሁለት የመጨረሻ ጨዋታዎች ሲደረጉ በመጀመሪያ የተገናኙት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አዳማ ከነማ ነበሩ፡፡ ተጋባዦቹ አዳማዎች በተመስገን ወልደፃዲቅ፣ ወንድሜነህ ዘሪሁን እና ቶክ ጄምስ በራሱ ላይ ባስቆጠሯቸው ጎሎች የአምናውን የውድድሩን ባለድል መርታት እና ገና ከምድብ ማጣሪያ ማሰናበት ችለዋል፡፡ የእነሱ የማለፍ እና ያለማለፍ ተስፋ ግን በቀጣዩ ጨዋታ ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎቹን በማሸነፉ ከምድቡ አንደኛ ሆኖ ማለፉን ያረጋገጠው መከላከያ እና ተከታይ ሆኖ ለማለፍ ጨዋታውን የግድ ማሸነፍ የነበረበት ቅዱስ ጊዮርጊስ ለወሳኙ ፍልሚያ ወደ ሜዳ ሲገቡ አሰላለፋቸው የሚከተለው ነበር፡-

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-4-1-1 የሚመስል)

ግብ ጠባቂ፡- ሮበርት ኦዳንካራ

ተከላካዮች፡- አሉላ ግርማ፣ አይዛክ ኢዜንዴ፣ ደጉ ደበበ እና አበባው ቡታቆ

አማካዮች፡- ተስፋዬ አለባቸው፣ ምንተስኖት አዳነ፣ ምንያህል ተሾመ እና በኃይሉ አሰፋ

አጥቂዎች፡- አዳነ ግርማ እና ብሪያን ኦሞኒ

 

መከላከያ (4-4-2 የሚመስል)

ግብ ጠባቂ፡- ሙሉጌታ አሰፋ

ተከላካዮች፡- ታፈሰ ሰርካ፣ አዲሱ ተስፋዬ፣ ቴዎድሮስ በቀለ እና ነጂብ ሳኒ

አማካዮች፡- ቴዎድሮስ ተስፋዬ፣ ሚካኤል ደስታ፣ ሳሙኤል ታዬ እና  ሳሙኤል ሳሊሶ

አጥቂዎች፡- ባዬ ገዛኸኝ፣ መሀመድ ናስር

በጨዋታው የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊሶች የኳስ ቁጥጥሩን የበላይነት የያዙ ሲሆን የጎል መሪነቱንም ለመያዝ የወሰደባቸው ዘጠኝ ደቂቃ ብቻ ነበር፡፡ የበኃይሉ አሰፋን የማእዘን ምት አይዛክ ኢዜንዴ በጭንቅላቱ ገጭቶ በማስቆጠር ፈረሰኞቹን መሪ አድርጓል፡፡ በ14ኛው ደቂቃ ባዬ ገዛኸኝ ከሩቅ የመታው አስደናቂ ኳስ በሮበርት ኦዳንካራ በድንቅ ሁኔታ ጎል ከመሆን ተርፏል፡፡ በ20ኛው ደቂቃ ተስፋዬ አለባቸው ከሩቅ የመታውን ኳስ ሙሉጌታ አሰፋ እንዲሁ አውጥቶበታል፡፡ በ30ኛው ደቂቃ ከ20 ሜትሮች ገደማ አበባው ቡታቆ የመታውን የቅጣት ምት ሙሉጌታ ቢመልሰውም ማራቅ ባለመቻሉ አጠገቡ የነበረው ብርያን ኦሞኒ በቀላሉ ለጊዮርጊስ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል፡፡ በ34ኛ ደቂቃ ምንተስኖት ያሻገረውን ኳስ በኃይሉ ሳይደርስበት ቀርቶ ከኋላ የመጣው አዳነ ግርማ መቶት በአግዳሚው ላይ ወጥቶበታል፡፡ በ36ኛው ደቂቃ በኃይሉ ከተስፋዬ የተቀበለውን ኳስ በመሬት ወደ ግብ መትቶ ግብ ጠባቂው ቢመልሰውም ኳሱ በጭንቅላቱ ላይ አልፎ ጎል ሊሆን ሲል የመሀል ተከላካዩ ቴዎድሮስ በቀለ ደርሶ ከመስመር ላይ አውጥቶታል፡፡ የ40ኛው እና 45ኛው ደቂቃዎች የአሉላ ግርማ ሙከራዎችም ይጠቀሳሉ፡፡

የሁለተኛው አጋማሽ አጀማመርም ከመጀመሪያው ብዙም የተለየ አልነበረም – ጊዮርጊሶች በጨዋታ የበላይነታቸው ቀጠሉበት፤ በ53ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ሶስተኛ ጎል አስቆጠሩ፡፡ በጊዮርጊስ ቀኝ መስመር በመሀመድ ናስር እና ሳሙኤል ሳሊሶ አለመግባባት ያገኘውን ኳስ አሉላ ወደ ጎል አሻግሮት ምንተስኖት አዳነ በጭንቅላቱ በመግጨት ድንቅ ጎል አስቆጥሯል፡፡ 65ኛው ደቂቃ የጨዋታው አወዛጋቢ ክስተት የታየበት ነበር፡፡ የጨዋታው አርቢትር ዘካሪያስ ግርማ በተስፋዬ ላይ አደገኛ የሚመስል ጥፋት የፈፀመውን በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የገባው ሽመልስ ተገኝን በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ አስወጥተውታል፡፡ በሙሉ ቡድን ተጋጣሚያቸውን መቋቋም ላልቻሉት መከላከያዎች ይህ ውሳኔ አስደንጋጭ ነበር፤ ወደ ጨዋታው የመመለስ ተስፋቸውም ጨልሟል፡፡ የገብረመድህን ኃይሌ ልጆች በ74ኛው ደቂቃ ልዩነት የማጥበቢያ እና የማስተዛዘኛ ጎል በመሀመድ ናስር አማካይነት ቢያስቆጥሩም በ80ኛው ደቂቃ ፈረሰኞቹ በኦሞኒ አማካይነት አራተኛ ጎላቸውን ማስቆጠር ችለዋል፤ ጊዮርጊሶች ሁሉንም ጎሎች ያስቆጠሩት በጭንቅላት መሆኑ አስገራሚ ሲሆን ጨዋታውም በ4ለ1 ውጤት ተጠናቋል፡፡ ሁለቱ ቡድኖችም ተያይዘው ወደ ግማሽ ፍፃሜው አልፈዋል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ማርቲን ኩፕማን ከጨዋታው በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል ፍልስፍናቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ጊዜ አንደሚስፈልጋቸው ገልፀዋል፡፡ ከኋላ ጀምሮ ኳስ መስርቶ የሚጫወት እንደ ባርሴሎና አይነት ቡድን መገንባት እንደሚፈልጉ ያስረዱት ሆላንዳዊው አሰልጣኝ በቡድኑ ውስጥ የተመለከቱት ጨዋታውን የማሸነፍ ከፍተኛ ፍላጎት ‹‹የቀድሞ ወታደሮች›› ሲሉ የገለፅዋቸውን የቡድኑን አንጋፋ ተጨዋቾች እንዲጠቀሙ እንዳስገደዳቸው ተናግረዋል፡፡

  • ከምድብ አንድ ኢትዮጵያ ቡና በአምስት ነጥብ እና ሁለት የጎል ክፍያ እንዲሁም ዳሸን ቢራ በተመሳሳይ አምስት ነጥብ እና አንድ የጎል ክፍያ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ሲያልፉ፣ ከምድብ ሁለት ስድስት ነጥብ እና ሁለት የጎል ክፍያ ያለው መከላከያ እና አምስት ነጥብ እና ሶስት የጎል ክፍያ የሰበሰበው ቅዱስ ጊዮርጊስ ተቀላቅለዋቸዋል፡፡ በዚህ መሰረት የግማሽ ፍፃሜ ፍልሚያዎቹ ለሰኞ ፕሮግራም የተያዘላቸው ሲሆን በዘጠኝ ሰዓት መከላከያ ከዳሸን ቢራ እና በ11 ሰዓት ኢትዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ይጫወታሉ፡፡
  • የመከላከያው መሀመድ ናስር በአራት ጎሎች ጎል አግቢነቱን ሲመራ የኢትዮጵያ ቡናው ዮሴፍ ደሙዬ በሶስት ጎሎች ይከተለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.